ታምራት ተስፋዬ
ዓለም ወደ አንድ የመረጃ (የኢንፎርሜሽን) መረብ በመጣበት በአሁን ወቅት በተለይ በኢኮኖሚ በጣም የበለፀጉ አገሮች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነታቸውን ይበልጥ ለማቀላጠፍ የመረጃ አያያዝ ስርዓታቸውን ለማሻሻልና ስርዓት ባለው መልኩ ለማደራጀትና ለማሰራጨት ከፍተኛ መዋለ ነዋይ ፈሰስ እያደረጉ ናቸው።
አህጉራችን አፍሪካም ከቅርብ አመታት ወዲህ ለዲጂታል መሰረተ ልማት ከፍተኛ ትኩረት መስጠት ጀምራለች። ከቀናት በፊትም የአፍሪካ ግዙፉ የመረጃ አቅራቢና የቴሌኮሚኒኬሽን አገልግሎት ሰጪው ቴራኮ በሁለት ነጥብ አምስት ቢሊየን ራንድ የአፍሪካ ግዙፍ የመረጃ ማእከል ለመገንባት ቅድመ ዝግጅቶችን ማጠናቀቁን አስታውቋል። ድርጅቱ የመረጃ ማእከሉን ለመገንባት የሚያስፈልገው ገንዘብ ማግኘቱም ታውቋል።
በ38 ሜጋ ዋት ሃይፐር ስኬል ጆሀንስበርግ ውስጥ የሚገነባው የመረጃ ማእከል “ ጄቢ 4” የሚል ስያሜ የተሰጠው ሲሆን ግንባታው ሲጠናቀቅም በአይነቱ የተለየና በአፍሪካ ከፍተኛ የዳታ ማእከል ይሆናል ተብላል። ግንባታው ስድስት ሄክታር መሬት ላይ በሁለት ምእራፍ የሚገነባ ነው።
የመጀመሪያው የመረጃ ማእከል እአአ በ2022 የመጀመሪያ ሶስት ወር ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል። አብሳን ጨምሮ በርካታ ስመጥርና ግዙፍ ተቋማት የድርጅቱ ራእይ እውን እንዲሆን ብድር ከማቅረብ ጀምሮ እጃቸውን መዘርጋታቸውም ታውቋል።
የድርጅቱ ዋና የፋይናንስ ኦፊሰር ሳሙኤል ኢርሚን፣ በመረጃ ማእከል መሰረተ ልማት መጠነ ሰፊ መዋእለ ነዋይ ፈሰስ በማድረግም ከሰሀራ በታች የአፍሪካ ገበያ ማገልገል እንደሚፈልጉና ድርጅቱ በዲጂታል መሰረተ ልማት ላይ የሚደረገውን ኢንቨስትመንትም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው ያስታወቀው።
ቴራኮ ቲም ፓርሶን እና በላክስ ቫን ውክ በተባሉ ግለሰቦች እኤአ በ2008 የተመሰረተ ነው። (ምንጫችን ቢዝነስ ቴክ ነው።)
አዲስ ዘመን የካቲት 02/2013