ዘለዓለም የሳጥን ወርቅ
እኛ ለዓለም ጥበብን ያሳየን፤ የእውቀት የስልጣኔ ፈር ቀዳጆች፤ ከዓለም ሁሉ በኩረ ዘፍጥረት ቀዳማዊያን ነን። ኢትዮጵያዊነት ሲነሳ አብሮ የሚነሳ በርካታ ታሪክ እና ትውፊት አለን። ከባህል ጋር የተቆራኙ ዘመን ተሻጋሪ ገድሎች ወግ፣ ባህል፣ ልማድ፣ ስርዓት፣ ታሪክ፣ ቅርስ፣ አለባበስ፣ የሰርግ የለቅሶ ሥነሥርዓቶች እኚህ ሁሉ የእኛ መገለጫዎች ናቸው።
በየትኛውም ዓለም የሌለ የእኛ ብቻ የሆኑ ኢትዮጵያዊ ጥበብና ኢትዮጵያዊ ስርዓት አለን። ከብዙዎቹ ባህሎቻችን መካከል ለዛሬ የሁላችን ስለሆነው የባህል ልብሳችን ለማንሳት ወድጃለሁ። እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ የብዙ ጥበበኞች መፍለቂያ ሀገር ናት። እውቀትን ለተለያዩ ዓለም ሀገራት ያስተማሩ ጥንታዊ አባቶች ነበሩን።
ፋሽን ባህላዊ ይዘቱን ሳይለቅ ከፍ ያለ እድገት ላይ እንዲደርስ ብሎም በዚያ አገርና ሕዝብ ተጠቃሚ እንዲሆን ማድረግ አስፈላጊ ነው። ለዚያ ነው ባህላዊ አልባሳቶቻችን ወደ ፋሽን ኢንዱስትሪው እየገቡ በተለያየ ዲዛይን ተዘጋጅተው ለህብረተሰቡ መቅረብና ተመራጭና ተወዳዳሪ መሆን አለባቸው የሚባለው።
ባህልን ሳናዛንፍ ዓለም እየተራመደበት ያለውን የፋሽን ኢንዱስትሪ በመከተል ብሎም የራሳችን ባህል የሚመጥኑ አዳዲስ ፋሽን ዲዛይኖችን በመተግበር ባህልን በጠበቀ መልኩ ከዘመኑ ፋሽን ጋር የታረቁ አልባሳት በብዛት ማምረትና ማቅረብ ይገባል።
የዛሬዋ ዓለም የኢትዮጵያ አባቶች የተጽዕኖ ውጤት ናት ብል አጋነንክ እንደማትሉኝ ተስፋ አደርጋለሁ። ዛሬም በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍል የውጪውን ዓለም የሚያስንቁ በርካታ ሙያተኞች አሉ። በመዲናችን ያለውን የባህል ልብስ መሸጫ ብናየው እንኳን ለዚህ በቂ ማሳያ ሆኖ እናገኘዋለን።
ባህልና ስርዓታችን እንዳለ ሆኖ ራሳችንን ለተቀረው አለም ከምናስተዋውቅባቸው እሴቶቻችን መካከል አለባበሳችን አንዱ ነው:: ይህ ስርዓታችን ደግሞ የዘመኑን ፋሽን የተከተለና በሕዝቡ ተመራጭ ሊሆን ይገባል። ለዚህ ደግሞ የባህል ልብሳችን ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛል። ለዚህ ጽሑፍ እንዲሆነኝ የተለያዩ የባህል ልብስ መሸጫ ሱቆችን ተዘዋውሬ ለማየት ችዬ ነበር።
አብዛኞቹ በሚባል ሁኔታ የማህበረሰቡን ፍላጎት የሚያረኩ በአይነትና በብዛት የተመረቱ በርካታ ሀገራዊ አልባሳቶችን ሲያቀርቡ ለማየት ችያለሁ። ማንኛውም ሰው በመረጠው አልባሳት ላይ የፈለገውን አይነት ዲዛይን ማሰራት እንዲችል በራቸውን ክፍት ያደረጉ በርካታ ሱቆችም እንዳሉ አይቻለሁ። በዚህ ጉዞዬ ያስተዋልኩትና ቢቀረፍ የምለው ችግር ማህበረሰባችን አሁንም ለባህል ልብስ ያለው አመለካከት እንደነበረ መሆኑ ነው።
ወቅት እየጠበቁ የሚገዙና ወቅት እየጠበቁ የሚለብሱ ብዙዎች ናቸው። አብዛኞቹ ነጋዴም ወቅት እየጠበቀ የበዓላት ሰሞን ካልሆነ ማህበረሰቡ በማንኛውም ሰዓት የሀበሻ ልብሶችን የመግዛት ልማድ እንደሌለው ገልጸውልኛል። ኢትዮጵያዊነት ሁሌም አብሮን የሚኖር ማንነት እስከሆነ ድረስ አለባበሳችንም ከባህል እና ስርዓታችን ጋር ሁሌም መሆን አለበት። በዓመት አንድ ጊዜ በበዓላትና መሰል ዝግጅቶች ላይ እንድንለብስ መግዛት የለብንም። ሙሉ በሙሉ ባይባልም አሁን ላይ ይሄ አመለካከት በአንዳንድ ሰዎች ላይ በተወሰነ መልኩ ተወግዶ አይቻለሁ።
በራሳችን ሀብት የምንኮራበት ትክክለኛው ጊዜ ላይ ነን። እንዳውም ትምህርት ቤት ሳይቀር የተማሪ ዩኒፎርም የሚሆንበት ጊዜ ቢመጣ ባይ ነኝ። እስኪ አስቡት ትምህርት ቤት በባህል ልብስ ስንማር? ሌላው ቢስተካከል የምለው ትዝብቴ በዚህ ሙያ ለረጅም ጊዜ የቆዩ ሙያተኞች የድካማቸውን ያክል ተጠቃሚ ሆነው አለማየቴ ነው።
ከነሱ ይልቅ ነጋዴው ክፍል ይበልጥ ተጠቃሚ የሆነበት የገበያ ስርዓት ነው ያለው። ይሄ ነገር መስተካከል ቢችል እና ሁሉም የልፋቱን ያክል ተጠቃሚ ቢሆን ከዚህ የተሻለ የግብይት ስርዓት መፍጠር ይቻላል ብዬ አስባለሁ። ለሙያተኞቻችን ክብር መስጠት አለብን። በባህላዊ ልብሶቿ ኢትዮጵያን ለአለም ያስተዋወቁ እነሱ ናቸው። እነሱ ባይኖሩ፣ እነሱ ባይሰሩ ኖሮ በዚህ ልክ በአለባበሳችን ላንታወቅ እንችል ሁሉ ነበር። ክብር ለሚገባው ክብርን መስጠት ባህላችን ነውና በጠቀሙን ልክ እንጥቀማቸው ስል ማሳሰብ እወዳለሁ።
ከጉብኝቴ የተረዳሁት ሌላው መልካም ነገር ደግሞ በሁሉም የእድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ወንድና ሴቶች እንደምርጫቸው የሚፈልጉትን አይነት አልባሳት ማግኘታቸው ነው። ማንም መቼም፣ የትም የሚለብሳቸው በዘመናዊ መልክ የተሰሩ እንደዚሁም ደግሞ በፈለገው ዲዛይን ለአዘቦትና ለስራ የሚሆነውን ልብስ የሚመርጥበት ሰፊ የገበያ እድል ተፈጥሯል።
ከዚህ ቀደም ለሀገር ምርት ትኩረት ያልተሰጠበት ጊዜ ነበር አሁን ላይ ሙሉ በሙሉ ባይባልም ወደ ራሳችን እየተመለስን ይመስለኛል። ዛሬም ድረስ ግን ዘመናዊነት እየመሰለን የአውሮፓና የእስያ ምርቶችን የምንጠቀም ብዙዎች ነን። ስልጣኔ የራስ የሆነን ነገር መውደድ መቀበል ነው። ስልጣኔ ራስን መሆን.. የራስን መውደድ ነው። ብዙዎቻችን የሀገር ውስጥን ምርት እንደተራ ነገር በማየት ለውጪ ምርት ትኩረት በመስጠት በሞኝነት ኖረናል።
እኛ ለራሳችን ምርት ክብርና ፍቅር ከሌለን ማንም ከየትም መጥቶ አያከብርልንም። ሰዎች የእኛ የሆነውን ነገር እንዲወዱን በመጀመሪያ እኛ ወደን ማሳየት አለብን። ባለቤት ያቃለለውን አሞሌ እንደሚባለው እኛ ያልተቀበልንውን የእኛ የሆነ ነገር ማንም አይቀበለውም።
ዓለም ላይ ከራሳቸው ምርት ሌላ የማይጠቀሙ በርካታ ሀገራት አሉ አሁን ላይ እነኚህ አገራት በስልጣኔም በኢኮኖሚም ከፊት የተሰለፉ ናቸው። ሀገራቸውን የሚወዱ ዜጎች የሀገራቸውን ምርት በመጠቀም ፍቅራቸውን የሚገልጹ ናቸው። የራስን ምርት መጠቀም በተዘዋዋሪ መንገድ ራስን መጥቀም ነው።ለሀገር ብልጽግና አስተዋጽኦ ማድረግ ነው። የሀገር ፍቅር ከሚገለጽባቸው መንገዶች ውስጥ አንዱ የራስን ምርት መጠቀም ነው።
በጣም የሚገርመው ነገር ደግሞ ምርቶቻችን ከአውሮፓ ምርቶች የተሻሉ ሆነው እያየን እንኳን ዛሬም ድረስ ለፈረንጅ ትርኪ ምርኪ ቅድሚያ መስጠታችን ነው። ኢትዮጵያ የወጣት ሀገርና ሁሉም ወጣት የሀገሩን ምርት በመግዛት ለሀገሩ ያለውን ፍቅር መግለጽ አለበት እላለው። ነጮቹ በእኛ ሞኝነት ሀገራቸውን ሲያበለጽጉ ኖረዋል።
መንቃት አለብን.. ማህበረሰባችን ለራሱ ቅድሚያ በመስጠት የሀገር ውስጥ ምርቶችን እንዲጠቀም በመንግስትም በሚመለከተውም አካል የግንዛቤ ስራ ቢሰራ የተሻለ የኢኮኖሚ መሰረት መገንባት እንችላለን ብዬ አምናለሁ፡ በዚህ አጋጣሚ ለሀገር ምርት ልዩ ፍቅር ያላቸውንም አንዳንድ ሰዎችን መታዘብ ችያለሁ። ከእኛ አልፈው ነጮቹ የእኛን የባህል ልብስ ለብሰው ያየሁበትም አጋጣሚ ብዙ ነው። በቅርቡ በማህበራዊ ሚዲያ እንኳን የሆሊዷ ኮከብ አንጀሊና ጆሊ የኢትዮጵያ ምርት የሆነውን የባህል ጋቢ ስትገዛ የሚያሳይ ምስል ተመልክተናል። እኛ እንደሚገባ አልተቀበልነውም እንጂ ኢትዮጵያዊነት ብዙዎች የሚሹት ማንነት ነው። ጥበባችሁን ውደዱ..የራሳችሁ የሆነን እውነት ተከተሉ። የሀገር ውስጥ ምርትን በመግዛት የሀገራችንን የእድገት ግስጋሴ እናረጋግጥ።
አዲስ ዘመን የካቲት 01/2013