በዕዝ ኢኮኖሚ
ይመራ የነበረው የደርግ
መንግሥት እንደ ዘይትና
ስኳር ባሉ መሠረታዊ
የፍጆታ ምርቶችን በተለየ
መልኩ በህብረት ሱቆች
አማካኝነት ጥብቅ ቁጥጥር
እየተደረገባቸው ኅብረተሰቡ ተጠቃሚ
እንዲሆን ይደረግ ነበር፡፡
በዘመነ ኢህአዴግ ደግሞ
እከተለዋለሁ ባለው ነፃ
ኢኮኖሚ ምክንያት እነዚህ
ሸቀጦች ወደ ግል
ነጋዴዎች ቋት ገቡ፡፡
እነዚህ ሸቀጦች በነጋዴው እጅ መውደቃቸውን ተከትሎ ከዕለት ዕለት ዋጋና ፍላጎቱ እየጨመረ፤ በአንጻሩ አቅርቦቱ እየቀነሰ ሄደ፡፡ ቀደም ሲል በየአካባቢው የነበሩ የተልባና መሰል የዘይት መጭመቂያዎች በሂደት እየተዘጉ መሄድ ደግሞ ችግሩን በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሆን አደረገው፡፡ ይህም የኅብረተሰቡን ኑሮ ዕለት ተዕለት እያናረው፤ የሕዝቡን ብሶት እያባባሰው ሄዷል።
መንግሥትም የችግሩ አድማስ እየሰፋ በሄደ መጠን የመፍትሄ አማራጮችን ፍለጋ እንዲያማትር መገደዱ አልቀረም፡፡ በአንድ በኩል የዘይት ምርትን በመቶ ሚሊዮኖች በሚቆጠር የውጭ ምንዛሬ ከውጭ በማስገባት ችግሩን ለመፍታት ጥረት አድርጓል፡፡ በተለይ የፓልም ዘይትን ከድጎማ እና ከቀረጥ ነፃ እስከማስገባት የደረሰ አቅጣጫ ተከትሏል፡፡ ምርቱ በነጋዴዎች ብቻ ሳይሆን በሸማች ማህበራት በኩል በተመጣጣኝ ዋጋ ለኅብረተሰቡ እንዲደርስ ለማድረግ ሞክሯል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ችግሩን በዘላቂነት መፍታት ያስችላል የተባለለት የተቀናጀ የአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ ሂደት ውስጥ ተገብቷል፤ በዚህ ሂደት አስፈላጊው ድጎማና ድጋፍ እየተደረገላቸው የዘይት ፋብሪካዎች ዳግም እንዲያቆጠቁጡ የማስቻል እርምጃ ወስዷል፡፡ በዚህም የታሰበውን ያህል ውጤታማ መሆን ባለመቻሉ ችግሩ ሳይቃለል ይልቁንም ዛሬ ለደረሰበት የተጋነነ የምርት እጥረት እና የዋጋ ንረት ደርሷል፡፡
የዘይት ጉዳይ ሀገራዊ አጀንዳ በሆነበት በአሁኑ ወቅት የዘይትን አቅርቦት ችግር ለዘለቄታው ለመፍታት መንግሥት ያስቀመጠው ስትራቴጂ ውጤት የሆነው፣ ከፍተኛ የመንግሥትና የባለሀብቱ ቁርጠኝነት የታየበት፣ ባለፉት ሁለትና ሦስት ዓመታት በተደረገ ሰፊ ርብርብ የፊቤላ የዘይት ፋብሪካ ትናንት እውን መሆን ችሏል፡፡
በ30 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈው እና በ4 ነጥብ5 ቢሊዮን ብር ወጪ ተገንብቶ የተመረቀው የፊቤላ ኢንዱስትሪያል ኮምፕሌክስም በዋናነት የምግብ ዘይት የሚያመርት ነው፤ ፋብሪካው ቀደም ሲል ለዘይት ይወጣ የነበረውን ወጪ ከ20 እስከ 30 በመቶ (እስከ 100 ሚሊዮን ዶላር) ያስቀራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ፋብሪካው ዘርፉ የደረሰበትን ቴክኖሎጂና ዘመናዊ መሣሪያዎች የሚጠቀም፣ እንዲሁም የሚያመርተው ዘይት የኅብረተሰቡን ጤና የማይጎዳ መሆኑ የተረጋገጠ ነው፤ ሙሉ ለሙሉ ወደሥራ ሲገባ በቀን 1ሺ500 ቶን ዘይት በማምረት የሀገሪቱን 60 በመቶ የዘይት ምግብ ፍላጎት እንደሚሸፍን ይጠበቃል፡፡ ከየካቲት አንድ ጀምሮም ምርቱን በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች በተመጣጣኝ ዋጋ ያቀርባል፡፡
ፋብሪካው ወደ ምርት መግባቱ የሚስተዋለውን የዘይት እጥረት ከማቃለል፤ ዛሬ ላይ በስግብግብ ነጋዴዎች በኅብረተሰቡ ላይ እየደረሰ ያለውን የዋጋ ንረት የሚቀርፍ እንደሚሆንም ታምኖበታል፡፡ የገበያውን ዋጋ ከማረጋጋት ባለፈ ለምግብ ዘይት ግዢ የሚወጣውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ በማስቀረት አገራዊ ጠቀሜታው የጎላ ይሆናል፡፡
የሕዝብ የኑሮ ጫና፣ ለአገርም የኢኮኖሚ ሸክም የሆነ ችግር ለማቃለል የሚንቀሳቀሱ ባለሀብቶች ሊበረታቱ እና ተገቢው እውቅና ሊሰጣቸውም ይገባል፡፡ ከራስ ይልቅ ለአገር እና ሕዝብ ቅድሚያ የሰጡ ናቸው እና ሊመሰገኑና የበለጠ ሊደገፉ ያስፈልጋል። ፋብሪካውም የውጭ ምንዛሬን ከማዳን ከቴክኖሎጂ ሽግግር፤ ከሥራ ዕድል ፈጠራ፤ የአርሷደሩን ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ፤ የግብርና ኢንዱስትሪ ትስስርን ከማሳደግ፤ ያለውን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ታሳቢ በማድረግ ለቀጣይም በቂ ትኩረት ሊሰጠው ያስፈልጋል፡፡
ሌሎች መሰል ፋብሪካዎችን እውን ለማድረግ መንግሥት የጀመረውንና በፊቤላ ኢንዱስትሪያል ኮምፕሌክስ የታየውን ቁርጠኝነት በሌሎችም የሕዝብን ተጠቃሚነት ታሳቢ ለሚያደርጉ መሰል ፕሮጀክቶች በተጠናከረ መልኩ ሊያስቀጥል ይገባል፡፡ ለዚህ ደግሞ የሰሩትን እያመሰገኑና እየደገፉ ለተጨማሪ ኃላፊነት ማትጋትም መትጋትም ይገባል።
አዲስ ዘመን የካቲት 1 ቀን 2013 ዓ.ም