መልካምስራ አፈወርቅ
በወጉ ያልጠናው ትዳር ዛሬም ላለመውደቅ እየተንገዳገደ ነው። አብሮነታቸው የጸናው ጥንዶች በየቀኑ ስለኑሯቸው ያስባሉ። ሁሌም የልጆቻቸው ህይወትና ዕጣ ፈንታ ያስጨንቃቸዋል።
በኣባወራው ትከሻ የወደቀው ኑሮ ያለበቂ ገቢ ወራትን ተሻግሯል ። በብዙ ድካም የሚገኘው ጥቂት ገንዘብ ከቤት ኪራይ አልፎ አያውቅም። ከእጅ ወደ አፍ በሆነው ህይወት መላው ቤተሰብ የልቡ ሳይሞላ ጊዚያትን አስቆጥሯል ።
ልጆች ማደግ ሲጀምሩ ፍላጎታቸው መጨመር ያዘ ። ለእነሱ ከትምህርታቸው በላቀ የጓደኞቻቸው ልብስና ጫማ ከአይናቸው ይገባል። እኩዮቻቸውን ባዩ ጊዜ እንደነሱ መሆን ይሻሉ።በየቀኑ ሁኔታቸውን ያስተዋሉት ወላጆች ልጆቻቸውን ከሰው እኩል ባለማድረጋቸው ያዝናሉ፤ ይቆጫሉ ።
ውሎ ሲያድር ጥንዶቹ መምከር ጀመሩ ።ነገን በተሻለ ለመኖር የተሻለውን አሰቡ።ልጆችን ለማስተማርና በወጉ ለመኖር በቂ ገንዘብ ያስፈልጋል። ገንዘቡን ለማግኘት በርትቶ ከመስራት የተሻለ ምርጫ የለም ።
እናት ዘወትር የሚያስጨንቃትን ጉዳይ ለመፍታት አረብ አገር ሄዳ ለመስራት ወስናለች።ውሳኔዋን የተቀበለው ባለቤቷም ልጆችዋን እያሳደገ ሊቆያት ተስማምቷል።
ህይወት በአረብ አገር …
አሁን እናት ከልጆቿና ከባለቤቷ ልትለይ ግድ ብሏል፡፤ይህ ይሆን ዘንድም የነገው የተሻለ ህይወት ምክንያት ሆኗል ።በጥንዶቹ ውጥን የታሰበው ዕቅድ ከተሳካ ልጆች እንደታሰበው ያድጋሉ፡፤ጥሩ ገንዘብ ከተገኘ ቤተሰቡ ከቤት ኪራይ ይወጣል።እናት አባት የልባቸው ደርሶ ምኞታቸው ይሳካል።
ህጻናት ልጇቿን በዕንባ የተለየችው ወይዘሮ ለተሻለው ነገ ባህር አቋርጣ አረብ አገር ደረሰች።የሰው አገር ህይወት እንደራስ አይሆንም። ቋንቋው ባህሉ ይለያል።ምግብና መጠጡ እንዳሻው አይገባም። አረማመድ አዋዋሉ ያሳስባል፣ያስጨንቃል። እንዲህ በሆነ ጊዜ በየሰበቡ ይከፋል፣ ሆድ ያስብሳል።
ወይዘሮዋ ጉልበቷን ሰጥታ ገንዘብ ለማግኘት ሌት ተቀን ባዘነች።ሲጠሯት አቤት፣ ሲልኳት ወዴት ብላም ዝቅ ብላ ታዘዘች። አንዳንዴ አሰሪዎቿ ያንቋሽሿታል፣ስሟን እየጠሩም ዱላ ሊያነሱባት ይሞክሯሉ።ይህኔ ፣ከልብ ይከፋታል፡፤አንገቷን ደፍታ ትተክዛለች፣ ታነባለች።
በክፋት ቀን ፈጥና ራሷን ለማብርታት ብርቱ ነች። ሁሌም ከነገሮች በኋላ ትጽናናለች።ዛሬን በችግር ማለፏ ለበጎ መሆኑ በገባት ጊዜም ዕንባዋን ጠርጋ ነገን ታስባለች።
በልጆቿ ናፍቆት የምትፈተነው እናት ከአንዱ ቤት ወደአንዱ እያለች ነው። እያደር አገሩን መልመዷ ብዙዎችን አሳውቋታል ። ይህ አጋጣሚም አቅሟን ጨምሮ ገንዘብ እንድትይዝ እየረዳት ነው።
በወጉ ገንዘብ መያዝ የጀመረችው ወይዘሮ አሁን ቤትና ልጆችዋን እያሰበች ነው። በየጊዜው ለባለቤቷ የምትልከው ብር የትናንት ህልሟን እንደሚፈታላት እርግጠኛ ነች።ይህ ገንዘብ ከልጇቿ አልፎ ለሌላ ቁምነገር እንደሚበቃ አልጠፋትም።
አገር ቤት ያለው ባለቤቷ አደራውን ተቀብሎ ልጆች ማሳደግ ይዟል። ሁሌም የነገው በጎነት የሚተርካላቸው ታዳጊዎች ከኪራይ ቤት የሚወጡበትን ቀን ይናፍቃሉ። እናትና አባት ያቀዱት ከተሳካ ካሉበት ችግር የሚወጡት ጊዜ ሩቅ አይሆንም።
አባት ቤት እየሰራ መሆኑን ለእናታቸው ሲናገር ሰምተዋል። ይህ እውነት ለእነሱ ትልቅ ትርጉም አለው።ከውጭ አገር መልስ ከእናታቸው ጋር አብረው መኖራቸውን እያሰቡ ተደስተዋል።
ወይዘሮዋ አመታትን በቆጠረችበት ቆይታ ክፉ ከደግ አልፋለች። ያም ሆኖ ስለነገ እያሰበች መጽናናት ልምዷ ነው ። በድካሟ ወዝ ያገኘችው ገንዘብ ለአገርቤት ህይወቷ መልካም መሆኑ አስደስቷታል።
ከስደት መልስ…
አሁን ወይዘሮዋ የአረብ አገር ውሏን አጠናቃለች።ከቀናት በኋላ ወደአገርቤት ተመልሳ ልጆቿን ትስማለች።ባለቤቷን ወዳጅ ዘመዶቿን ታገኛለች።ስፍራው ስትደርስ ብዙ ዕቅዶች አሏት፡ ልጆቿን ከቤት ኪራይ አውጥታ ፣ኑሮዋን ለመቀየር እረፍት የላትም።
እንዳሰበችው ሆኖ ስደተኛዋ ሴት ከአገሯ ተመለሰች ። የተራቧት ልጆቿ ከዕቅፏ ገብተው ናፍቆታቸውን ሲወጡ ከረሙ። ባለቤቷ ጠያቂ እንግዶችን ሲቀበልና ሲሽኝ ቆየ።ቤተሰቡ በስጦታ ተንበሸበሽ ።ይህ አጋጣሚ ደስታ ፈጥሮም ሳቅ ጨዋታው ሰነበተ።
ቀናት ተቆጠሩ ። የናፍቆቱ ጊዜ ተጠናቆ ባልና ሚስት ዳግም ለምክር ተቀመጡ።ሚስት እስካሁን የላከችውን ብር እያሰበች ነው።ባሏ እየሰራ ያለውን መኖሪያ ቤት ለመጎበኘት ቸኩላለች። አባወራው ከሚስቱ አጠገብ ተቀምጦ ጥያቄዋን ሊመልስ ተዘጋጅቷል።
ያልታሰበ …
ጥንዶቹ ጭቅጭቅ ይዘዋል፡፤ ሚስት ባሏ የሚነራትን እውነት አምና መቀበል ቸግሯታል። እስከዛሬ የላከቸው ገንዘብ መባከኑን በሰማች ጊዜም ከልብ አዝናለች ። ተሰርቷል የተባለው ቤት ውሸት መሆኑን ስታውቅ ደግሞ ሀዘኗ ጨምሯል ።
ወይዘሮዋ አባወራው በእሷና በልጆቿ የፈጸመው በደል ከአቅሟ በላይ ሆነባት።በሰው አገር ተንከራታ ያፈራቸው ገንዘብ በግፍ መነጠቋ ሲያሲያዝናት ቆየ፡፤ ዕንባ የሞሉ አይኖቿ በለቅሶ ከረሙ። ጠዋት ማታ ተብሰለሰለች፡፤ ምንም ማድርግ አልቻለችም። አንገቷን ደፍታ እውነቱን ከመቀበል ሌላ ምርጫ አልነበራትም፡፤
ህይወት እንደገና…
የትናንቱ ትዳር እንደነበረው ቀጥሏል፡፤ አሁንም ከቤት ኪራይ ያልወጣው ቤተሰብ እየተቸገረ ነው። የአመታት ልፋቷ ያልሰመረው ወይዘሮ ዛሬም ልጆቿን ለማሳደግ ደፋ ቀና ትላለች።ጎጆዋን ለማቅናት ፣ ቤቷን ላለማጉደል የምትሮጠው ሴት የባሏ ክፉ ድርጊት ያበሳጫት ይዟል።
ዛሬም ሰላም ያጣው ቤት በጭቅጭቅ ውሎ ያድራል።አባወራው በየሰበቡ ጠብ ያነሳል፡፤ሰክሮ በመጣ ቁጥር ይሳደባል‹፣ጭቅጭቁ ከቤቱ አልፎ ሌሎችን እየረበሸ ነው ። የግቢው ነዋሪዎች የጎረቤታቸውን ጩኸትና ስድብ ችለዋል፡፤አንዳንዶቹ ድርጊቱ ሲበዛ ለምን ሲሉ ይጠይቃሉ። ይህኔ ጠጪው አባወራ ይብስበታል፡፤ያሻውን እየተሳደበ የፈለገውን ይናገራል።በ‹‹አያገባችሁም›› ቁጣም አመናጭቆ ይመልሳል።
የቤቱ ባለቤትና አካራይ ትልቅ ሴት ናቸው። በግቢው ካሉ ነዋሪዎች በወጉ ይግባባሉ።እሳቸው የጥንዶቹን ሰላም ማጣት አሳምረው ያውቁታል ፡፤ የወይዘሮዋ ብስጭትና ትካዜ ባሳሰባቸው ጊዜም ሊመክሯት፣ሊያጽናኗት ይሞክራሉ።
የኣባወራው ሚስት የአከራይዋን ቅርበት ፈልጋዋለች።ሁሌም የልቧን ባዋየች ጊዜ ቀለል ይላታል።ለሴትዬዋ የአሁን ህይወቷን ፣ችግሯንና ያሳለፈችውን ስቃይ ትነግራቸዋለች ። ይሰሟታል ። ሰምተውም ይሆናል ያሉትን ይመክሯታል።ለእሳቸው ሲሆን ያለችበትን ኑሮና ህይወት አትደብቅም ።
የአባወራው ዓይኖች…
አባወራው ሚስቱን ዘወትር ከቤት አከራይዋ ጋር ያያታል፡፤ስትወጣ ስትገባ ሳታገኛቸው አታልፍም ፡፤ ሲመጡ ሲሄዱ ሳያይዋት አይውሉም፡፤ይህ ግንኙነት ደግሞ ለእሱ ተመችቶት አያውቅም፡፤ወይዘሮዋ ሚስቱን ባገኝዋት ቁጥር ብዙ ችግር እንደምታወራላቸው ያውቃል።
የሚባለውን ሰምተው ዝም እንደማይሉ ሲገባው በየቀኑ የሚሆነውን እያሰበ መበሳጨት ጀምሯል፡፤ቂም የያዘው አባወራ ሁለቱን በአንድ ባያቸው ጊዜ ጥርሱን እየነከሰ፣ እጁን እየፈተገ ጥላቻውን ያሳያል።ባህሪውን የምታውቀው ሚስቱ ለድርጊቱ ቦታ አትሰጥም።የሚያደርገውን እያየች በትዕግስቷ ቀጥላለች።
ባል የሁለቱን ቅርበት በበጎ ለማየት አልፈቀደም። አካራይዋ ሚስቱን የሚመክሯት ከክፋት እንደማያልፍ ገምቷል፡፤እሷ እሳቸውን ባገነች ቁጥር የምትነግራቸውን ሲያስብ የራሱ ታሪክ ውል ይለዋል።ይህኔ ውስጡ ይረበሻል። በእሱ ስህተትና ስካር የተፈጠረውን ቢያውቅም።አምኖ መቀበል ይቸገራል።
አሁን አባወራው አካራይዋን ከመገላመጥ አልፎ ክፉ መናገር ጀምሯል።‹‹በትዳሬ ገብተሻል›› በሚል ሰበብም ያሻውን ይሳደባል ። ሴትዬዋ በሚሰሙት ክፉ ቃል ተቀይመው ፊት ነስተውታል ፡፤ከአንገት በላይ የቆየው ሰላምታ ቀርቶም ንግግር አልባ ግንኙነት ቀጥሏል።
በባልና ሚስቱ መሀል የዘለቀው አለመግባባት ብሶበታል።ያለሰላም ውሎ የሚያድርው ጎጆ ለአፍታ በልጆች ጨዋታ ደምቆ መልሶ በዝምታ ይዋጣል።ዝምታው በጠብና ጭቅጭቅ ለመደፍረስ ጊዜ አይወስድም።ጥንዶቹ የቆየውን ችግር ከአሁኑ እያዛመዱ ይጣላሉ። ጠቡ ቂም አስቋጥሮም ቀናት በኩርፊያ ያልፋሉ።
አዲስ ወሬ ..
ሰሞኑን የአባወራው ገጽታ ከወትሮው ተለይቷል፡፤አከራይዋን ባየ ጊዜ ለመማታት ይቃጣዋል።ግልምጫው አሽሙሩና ንዴቱ ከእሳቸው አልፎ ሌሎችን እያስገረመ ነው ። ሁኔታውን ያዩ አንዳንዶች ከመምከር አልፈው ለመጠየቅ ሞከሩ።ተከራዩ ለሚጠይቁት ምላሽ ሰጠ።አካራይዋ ሚስቱን ከትዳሯ እንድትፋታ እየመከሯት መሆኑን ተናገረ።
‹‹ከሚስቴ ሊያፋቱኝ ነው›› ያለው አባወራ ከሚኖርበት አልራቀም፡፤ጥርጣሬው አስግቶትም ቤቱን መልቀቅ አልፈለገም።ቤተሰቡን ከነችግሩ እንደያዘ፣ ከሚስቱ እየተጣለ ኑሮውን ቀጠለ ።አንዳንዴ ሴትዬዋን ባገኘ ጊዜ ‹‹በትዳሬ አትግቢ›› ሲል ይጮሀል፣ በጨኸቱ መሀል ጥላቻውን በዛቻ አዋዝቶም ለሚሰሙት ያደርሳል።
በግቢው የደፈረሰው ሰላም አልጠራም። አሁንም ሰውዬው ሴትዬዋን እንደገላመጠ፣ሚስት ባሏን እንዳኮረፈች፣ልጆች ዕንቅልፍና እፎይታ እንዳጡ ነው። ጉዳዩን ከልምድ የቆጠሩ ብዘዎች ለሁኔታው የተጨነቁ አይመስልም።የተለመደውን ሁኔታው ለአፍታ እንዳዩ ፈጥነው ይረሱታል።
ታህሳስ 18 ቀን 2011 ዓም…
ጨልሟል ። አሁን ከምሽቱ አራት ሰአት እየሆነ ነው ። ወይዘሮዋ በተለመደው ሰአት ልጆችዋን ይዛ ከመኝታዋ አረፍ ብላለች፡፤የግቢው ነዋሪዎች በሮቻቸውን እየዘጉ ነው ። ቀስ በቀስ ዝምታ የዋጠው መንደር በውሾች ድምጽ መተካት ጀምሯል።በዚያ ምሽት ግን አንድ ሰው ወደቤቱ አልደረሰም፡፤በሚራመድበት ጎዳና ለአፍታ ቆም እያለ ማሰብ ጀምሯል።ይህ ሰው የቤቱ ተከራይ በቀለ ሁንዴሳ ነው።
በቀለ በመንገዳገድ ጨለማውን እየጣሰ ከሰፈሩ ተቃርቧል።ከተያያዘው አንደበቱ የሁልጊዜው ስድብ እየወጣ ነው።የግቢውን በር አልፎ ወደ መኖሪያ ቤቱ ሲዘልቅ ሚስቱ ሁለቱን ልጆች ታቅፋ ተኝታለች ።ይህ እውነት ለእሱ አዲስ ሆኖ አያውቅም። ሰክሮና አምሽቶ በመጣ ቁጥር የሚያጋጥመው ነው ።
ከቤት እንደገባ የተኙትን ተመለከታቸው።ሁሉም በዕንቅልፍ ተዳክመዋል።አተኩሮ እያያቸው አንደኛውን ልጅ ተጣራ ። የሰማው የለም ።እየተናደደ ማልጎምጎም ያዘ ። ጥቂት ቆይቶ ወደውጭ መውጣት ፈለገ። ከዛ በፊት ወደጓዳ ተንደርድሮ አንዳች ነገር ፈለገ።ወዲያው ዓይኖቹ የፈለገውን አሳዩት።ጥቁር እጀታ ያለውን ቢላዋ ጨብጦ ወደውጭ ሮጠ ።
በአጥሩ ስር …
በቀለ የጨበጠውን እንዳጠበቀ ግቢውን ፈጥኖ አቋረጠ።ሽንቱን ለመሽናት ፈልጓል።ዓይኖቹ አሁንም እየቃበዙ ነው።ጭር ያለው ግቢ የሚፈልገውን እሰኪያሳየው መቃኘቱን አልተወም።
ጥቂት ቆይቶ ለሽንቱ ከአጥሩ ስር ተጠጋ።በዚህ አፍታ የቤቱ ባለቤት ከውጭ ወደውስጥ እየገቡ መናገር ጀመሩ። በዚህ ሰአት አጥራቸውን ለሽንት የተጠጋው ሰው አናዷቸዋል።ወይዘሮዋ ብሽቀት እንደያዛቸው ሁኔታው ነውር መሆኑን ለመናገር ሞከሩ።የጀመሩትን ተናግረው ሳይጨርሱ ከበቀለ ጋር ተፋጠጡ።
እሱ መሆኑን እንዳወቁ ክፉኛ ደንግጠው ወደኋላ አፈገፈጉ።በቀለ የሴትዬዋ ድንጋጤ አንዳች ትርጉም ሰጠው። መፍራታቸው ያለምክንያት እንዳልሆነ ገባው። ወዲያው እየተጣደፈ ቀረባቸው።ግቢውን አልፈው ወደቤት ሳይገቡ ከፊታቸው ቀድሞ ቆመ።ጨለማ ቢሆንም በእጁ ያለውን አወቁት ። ይህኔ በድንጋጤ ተደናቅፈው ወደቁ።
ከወደቁበት ሳይነሱ አጠገባቸው ደርሶ ልብሳቸውን ይዞ አነቃቸው።ለመነሳት አልሞከሩም። አቅም አጡ። አጠገባቸው ደርሶ አፈጠጠባቸው ።ዓይምሮው ክፉ ታሪኮች እያመላለሰ ያሰበውን እንዲፈጽም ገፋው። ፈጥኖ ቢላዋውን አወጣ፡፤ለመጮህ አፋቸውን ከመክፈታቸው ጆሯቸው፣ትከሻና ጀርባቸውን ደጋግሞ ወጋቸው።እየጮሁ በጀርባቸው ተዘረሩ።
የፖሊስ ምርመራ ..
ፖሊስ ወንጀሉ ከተፈጸመበት ሰፈር ደረሰ። መንደርተኛው ተጎጂዋን ከሀኪም አድርሶ ከቦ ያወራል፡፤ጉዳዩን ለማጣራት ምርመራ የጀመረው ምክትል ሳጂን ቢኒያም በሪሁን የተጠርጣሪውን ባለቤትና ሌሎችን ለጥያቄ አቅርቦ ምርመራውን ጀመረ ።ይህ በሆነ አፍታ ጊዜ የተጎጂዋ ህይወት ማለፉ ተሰማ።የፖሊስ ቡድኑ ወንጀሉን ፈጽሞ ከስፍራው የተሰወረውን ግለሰብ ማሰስ ጀመረ። አላጣውም።በቁጥጥር ስር አውሎ ቃሉን ተቀበለ።
ውሳኔ
ሀምሊ 22 ቀን 2011 ዓም በችሎቱ የተሰየመው የልደታው ከፍተኛ ፍርድቤት በተከሳሽ በቀለ ሁንዴሳ ላይ የመጨረሻውን ውሳኔ ለማሳለፍ በቀጠሮው ተገኝቷል፡፤ግለሰቡ በፖሊስ ምርመራና በዓቃቤህግ መረጃዎች በተጠናክረበት ክስ ጥፋተኝነቱ ተረጋግጧል፡፡ ፍርድቤቱ ጥፋተኝነቱን አይቶ በሰጠው ውሳኔም እጁ ከተያዘበት ጊዜ አንስቶ በሚታሰብ የአስራስምንት ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ ሲል በይኗል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 29/2013