የሰላም አየር በአማራ ክልል ፍቃዱ ከተማ

ለሀገር ሉዓላዊነት በጋራ ደማቸውን ያፈሰሱ ሕዝቦች ልዩነትን በውይይት መፍታት ተስኗቸው መሣሪያ ሲማዘዙ ከማየት በላይ የሚያሳዝን ነገር አይኖርም፡፡ ሉዓላዊነትን በጋራ አንድነት የጠበቁ ኢትዮጵያውያን የውስጥ ችግርን በንግግርና በውይይት መፍታት ተስኗቸው በተፈጠሩ ግጭቶች እጅግ ውድ ዋጋ ተከፍሏል፡፡ ኅብረ ብሔራዊነትና ብዝሃነት በሚስተዋልበት ምድር የሃሳብ ልዩነቶች መኖራቸው ኃጢያት ሊሆን አይችልም። ኃጢያት ሊሆን የሚችለው ልዩነቱን በጋራ መክሮ መፍታት ሲሳንና ወንድም በወንድሙ ላይ የመሣሪያ አፈሙዝ መደገን ሲጀምር ነው፡፡ ወንድምና እህትን ገድሎና እርስ በርስ ተጨራርሶ የሚመዘገብ ድልም ሆነ የሚጻፍ አዎንታዊ ታሪክ የለም፡፡

አርቆ ማሰብ በተሳናቸው ስመ ነፃ አውጪዎች ፊትአውራሪነት እና በኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች አይዞህ ባይነትና ድጋፍ በሀገራችን በተለይም በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች ውስጥ የተከሰቱ ግጭቶች የብዙዎችን ሕይወት ቀጥፈዋል፤ ሀብት ንብረት አውድመዋል፡፡ አርሶ አደሩ እንዳያርስ፣ ነጋዴው እንዳይነግድ፣ ተማሪው እንዳይማር እና ልማት እንዳይከናወን አደናቅፈዋል፡፡

ይኼ አካሄድ እንደማያዋጣ እና ማንኛውም ልዩነት አለኝ የሚል ኃይል ልዩነቱን በንግግርና በውይይት ብቻ እንዲፈታ በሚል መንግሥት ችግሮቹን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ተደጋጋሚ ጥሪ ከማድረጉም በላይ በተግባራዊነት ብዙ ርምጃ ተራምዶ ቁርጠኝነቱን አሳይቷል፡፡

ይኼ የሰላም ጥሪ ከጠንካራ የሕግ ማስከበር ሥራ ጋር ተያይዞ አሁን ላይ በአማራ ክልል እጅግ ተስፋ ሰጪ ውጤት መታየት ጀምሯል፡፡ ከሰሞኑ በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ሚዳ ወረሞ ወረዳ እጃቸውን የሰጡ ከ467 በላይ ጽንፈኞች የሰላሙ አየር በአማራ ክልል እጅግ እየጸና መምጣቱን ይመሰክራሉ፡፡

የአማራ ክልል ኮሙኒኬሽን ቢሮ የትናንትና ዘገባም ይህንኑ እውነት የሚመሰክር ነው፡፡ ቢሮው በመግለጫው “በተከታታይ ቀናት መንግሥት ያደረገላቸውን የሰላም ጥሪ ተቀብለው ለገቡ ከ467 በላይ ለሚሆኑ የጽንፈኛ ቡድኑ አባላት ለነበሩ ታጣቂዎች አቀባበል ተደረገላቸው።

በሰሜን ሸዋ ዞን ሚዳ ወረሞ ወረዳ ወረሞ ዋጂቱ ንዑስ ወረዳ ባሉ ሁሉም ቀበሌዎች በተከታታይ ቀናት የመንግሥት የሰላም ጥሪ ለተቀበሉ ከ467 በላይ ለሚሆኑ የጽንፈኛ ቡድኑ አባላት ሐምሌ 06 ቀን 2017 ዓ.ም አቀባበል ተደርጓል።

የ101ኛ አየር ወለድ ክፍለ ጦር አዛዥ ኮሎኔል ማቲዎስ ማደቦ እንደተናገሩት፤ የትም፣ መቼም ቢሆን ሰላም አሸናፊ ነው፡፡ ለሰላም ቅድሚያ በመስጠት መንግሥት ያቀረበውን የሰላም ጥሪ በመቀበል ወደ ቀደመ ሰላማዊ ሕይወት መመለስ መቻላችሁ ብልህነት ነው ብለዋል።

የሰሜን ሸዋ ዞን ብልፅግና ፓርቲ ቅርጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኤሊያስ አበበ እንደተናገሩት፤ ትናንት በጥፋት እና በተሳሳተ መንገድ ላይ የነበሩ ዛሬ ላይ የሰላም ጥሪ የተቀበሉ እና ወደ ቀደመ ሰላማዊ ሕይወታቸው የተመለሱ ወንድሞቻችን የተገኘውን አንጻራዊ ሰላም ለማስቀጠል በየደረጃው ከሚገኘው የአካባቢው ማህበረሰብ ጋር በጥምረት በመሥራት የሰላም ባለቤት መሆን ይገባል ሲሉ ገልጸዋል።

የሰሜን ሸዋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ መካሻ አለማየሁ ካሳለፍናቸው አስከፊ የሰላም እጦት ችግሮች ትምህርት በመውሰድ ለሰላም ቅድሚያ በመስጠት የአካባቢው ማህበረሰብ ያጣውን ሰላም መልሶ እንዲያገኝ ላስቻለን እና ጫካ የነበሩ ወንድሞቻችንን በፍቅር ለተቀበሉ ጥምር ጦር ምስጋና አቅርበዋል፡፡ በተደረገው የሰላም ጥሪ ከ467 በላይ የሚሆኑ የጽንፈኛ ቡድኑ አባላት ከነሙሉ ትጥቃቸው አቀባበል የተደረገላቸው መሆኑን አስረድተዋል። አክለውም

በቀጣይ ተከታታይ ቀናቶች አጫጭር የአስተሳሰብ እና አቅም ግንባታ ሥልጠናዎች እንደሚሰጡ ገልጸዋል።

በመርሃ ግብሩ የሰሜን ሸዋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ መካሻ አለማየሁ፤ የብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኤሊያስ አበበ፤ የ101ኛ አየር ወለድ ክፍለ ጦር አዛዥ ኮሎኔል ማቲዎስ ማደቦ፣ የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሰይድ ኢብራሂምን ጨምሮ ሌሎች የዞን፣ የወረዳ እና የሀገር መከላከያ ሠራዊት አመራሮች ተገኝተዋል” ብሏል፡፡

ይህ ኢትዮጵያውያንን ሞቅ የሚያደርግ ጠላትን ደግሞ ክው የሚያደርግ ዜና ነው፡፡ የሚያዋጣው መንገድ ሰላም ብቻ ነውና በማወቅም ሆነ ባለማወቅ በተሳሳተ ዓላማ በጽንፈኝነት እኩይ ተግባር ላይ የተሠማሩ ቀሪ ኃይሎችም ይህንን ፈለግ ሊከተሉ ይገባል፡፡

ፍቃዱ ከተማ

አዲስ ዘመን ረቡዕ ሐምሌ 9 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You