ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የትራምፕን ርምጃ የሚደግፍ ውሳኔ አሳለፈ

የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር የሀገሪቱን የትምህርት ሚኒስቴር ኃላፊነቶች ለመቀነስና መሥሪያ ቤቱንም ለመዝጋት የጀመረውን እንቅስቃሴ የሚደግፍ ውሳኔ ማሳለፉ ተገልጿል፡፡ በውሳኔው መሠረት የትራምፕ አስተዳደር ለትምህርት ሚኒስቴር የሚያደርገውን የገንዘብና ሌሎች ድጋፎችን ማቋረጥ ይችላል፡፡ ውሳኔው የትራምፕ አስተዳደር የትምህርት ሚኒስቴርን ለማፍረስ የሚያደርገው እንቅስቃሴ እንዲቀጥልና ይህን የትራምፕ ጥረት የሚያደናቅፉ መሰናክሎችን ገለል ለማድረግ የሚያስችል እንደሆነ ተገልጿል፡፡

ፕሬዚዳንት ትራምፕ የፍርድ ቤቱን ውሳኔ አወድሰዋል። ፕሬዚዳንቱ ባወጡት መግለጫ፤ ‹‹ለተማሪዎችና ወላጆች ትልቅ ድል ነው፡፡ ብዙዎቹን የተቋሙን ኃላፊነቶች ወደ ግዛቶች ለመመለስ ለሚሠራው ሥራ ወሳኝ ርምጃ ነው›› ብለዋል፡፡ የትምህርት ሚኒስትሯ ሊንዳ ማክማሆን በበኩላቸው፤ ውሳኔው ተገቢና የሚጠበቅ ቢሆንም፤ የፕሬዚዳንቱ ውሳኔ ተፈጻሚ እንዲሆን የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ጣልቃ ገብነት አስፈላጊ እንዳልነበር ተናግረዋል፡፡

‹‹ፕሬዚዳንቱ የአስፈጻሚው አካል መሪ እንደመሆናቸው ስለፌዴራል ተቋማት አደረጃጀት፣ የሠራተኞች ብዛትና የዕለት ከዕለት የሥራ ሁኔታ የመወሰን ሥልጣን አላቸው። ውሳኔያቸው ተፈጻሚ እንዲሆን የጠቅላይ ፍርድ ቤት ጣልቃ ገብነት ማስፈለጉ አሳፋሪ ነው›› በማለት ተናግረዋል።

በአሜሪካ የሚገኙ መንግሥታዊ ያልሆኑ የትምህርት ዘርፍ ማህበራት እና አክቲቪስቶች የጠቅላይ ፍርድ ቤቱን ውሳኔ በጥብቅ ኮንነውታል፡፡ የፍርድ ቤቱ ውሳኔ አሜሪካውያን ፍትሐዊ የትምህርት ተደራሽነት እድል እንዳያገኙ የሚያደርግ በመሆኑ ሁሉንም ሕጋዊ አማራጮች እንደሚጠቀሙ ገልጸዋል፡፡

ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ባለፈው መጋቢት ወር የሀገሪቱን የትምህርት ሚኒስቴር ለመዝጋት የሚያስችል የማስፈጸሚያ ትዕዛዝ መፈረማቸው ይታወሳል፡፡ ትራምፕ በምርጫ ቅስቀሳቸው ወቅት ምርጫውን ካሸነፉ ሚኒስቴሩን እንደሚያፈርሱት ቃል ገብተው ነበር፡፡

ፕሬዚዳንቱ የመሥሪያ ቤቱ አንዳንድ ተግባራት አሜሪካውያንን የማይጠቅሙ እንደሆኑ በተደጋጋሚ ተናግረዋል፡፡ ፕሬዚዳንቱ የትምህርት ሚኒስትር አድርገው ሾመዋቸው የነበሩት ሊንዳ ማክማሆንም ውሳኔውን እንዲያስፈጽሙ ኃላፊነት ተሰጥቷቸዋል፡፡ ከአንድ ሺ 400 በላይ የመሥሪያ ቤቱ ሠራተኞች ከሥራቸው ተሰናብተዋል፡፡

ትራምፕ የውሳኔውን ማስፈጸሚያ ከመፈረማቸው ቀደም ብለው ‹‹የፌዴራሉን የትምህርት ሚኒስቴር ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማፍረስ ወስኛለሁ፡፡ ያልተለመደ ይመስላል፡፡ ውሳኔው ትክክል እንደሆነ ግን ሁሉም ሰው ያውቃል፤ ዲሞክራቶችም ያውቃሉ›› ብለው ነበር፡፡

የፕሬዚዳንቱ ውሳኔ የሚኒስቴሩን ሥልጣንና ኃላፊነቶች ለግዛቶች (States) የሚሰጥ ነው፡፡ ፕሬዚዳንቱ እንዳሉት፤ ለተማሪዎች የሚቀርቡ ብድሮችና ርዳታዎች ይቀጥላሉ፡፡

‹‹የቤተሰቦችን፣ የግዛቶችንና የማህበረሰቦችን አቅም በማሳደግ የትምህርት ዘርፍን ማሻሻል›› የሚል ስያሜ የተሰጠው የፕሬዚዳንቱ ትዕዛዝ፤ ወላጆችና ልጆቻቸው ‹‹ከከሸፈው የአሜሪካ የትምህርት ሥርዓት›› ነፃ እንዲወጡ እድል እንደሚሰጥ በትዕዛዙ ማብራሪያ ላይ ተገልጿል፡፡

ትዕዛዙ የሀገሪቱን ብሔራዊ የትምህርት እድገት ምዘና ጥናት መረጃዎችን ዋቢ በማድረግ የትምህርት ሚኒስቴሩን ድክመት ዘርዝሯል፡፡ የምዘና ጥናቱ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ 70 በመቶ የሚሆኑት የስምንተኛ ክፍል ተማሪዎች ከደረጃ በታች የሆነ የንባብ ችሎታ ያላቸው ሲሆኑ፤

72 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ የሂሳብ ትምህርት ውጤታቸው ከደረጃ በታች ነው፡፡ እኤአ ከ2022 ጀምሮ ተማሪዎቹ በንባብም ሆነ በሂሳብ ጥሩ የሚባል ለውጥ አላስመዘገቡም፡፡

በምጣኔ ሀብት ትብብርና ልማት ድርጅት (Organization For Economic Co-operation and Development – OECD) እና በፔው የጥናት ማዕከል (Pew Research Center) የተሠሩ ጥናቶች የሚያመለክቱትም አሜሪካውያን ተማሪዎች በንባብና በሂሳብ የሚጠበቀውን ያህል ውጤት እንዳላስመዘገቡ ነው፡፡

መሥሪያ ቤቱ ከእዚህ ቀደምም የትምህርት ጉዳይ በግዛቶች ቁጥጥር ስር ሊሆን እንደሚገባና መሥሪያ ቤቱ አላስፈላጊ በሆኑ አስተሳሰቦች እንደተበከለ በፅኑ ከሚያምኑ ወግ አጥባቂ የአሜሪካ ፖለቲከኞች ተቃውሞ ሲቀርብበት ቆይቷል፡፡

ዲሞክራቶች በእዚህ የፕሬዚዳንቱ ውሳኔ ላይ ከፍተኛ ተቃውሞ አሰምተዋል፡፡ ለአብነት ያህልም አንጋፋው ዴሞክራት ሴናተር ቼክ ሹመር ‹‹የትምህርት ሚኒስቴርን ለማፍረስ የተፈረመው ትዕዛዝ ፕሬዚዳንቱ እስካሁን ከወሰኗቸው እጅግ አደገኛና አውዳሚ ውሳኔዎች መካከል አንዱ ነው፡፡ ይህ ውሳኔ ሕጻናትን ይጎዳል›› ብለው ነበር፡፡

የሚቺጋኗ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ራሺዳ ታሊብ በበኩላቸው፤ ፍትሐዊ የትምህርት አቅርቦት እንዲኖር የሚያስችሉ ብሔራዊ ደረጃዎችን ማስፈጸም የሚችል ሌላ ተቋም ባለመኖሩ ሚኒስቴሩ መዘጋት እንደሌለበት ሞግተዋል፡፡ ‹‹ሚኒስቴሩ ከሌለ ልጆቻችን አስታዋሽ አይኖራቸውም፤ የሚፈልጉትንና የሚገባቸውን ትምህርት ማግኘትም አይችሉም›› ብለዋል፡፡

ውሳኔው ኢ-ሕገመንግሥታዊ መሆኑን ጠቅሰው፤ ወደ ፍርድ ቤት እንደሚያመራ ጠቁመው ነበር፡፡ ‹‹All4Ed›› የተሰኘ ተቋም ባለፈው ዓመት ባደረገው የዳሰሳ ጥናት፣ በጥናቱ ከተሳተፉ ሰዎች መካከል 58 በመቶ የሚሆኑት መሥሪያ ቤቱ እንዲፈርስ አይፈልጉም፡፡

ይሁን እንጂ የፕሬዚዳንቱ ውሳኔ ተፈጻሚ የሚሆነው የኮንግረሱን ይሁንታ ካገኘ ነው፡፡ አንዳንድ የኮንግረሱ አባላት ለፕሬዚዳንቱ ውሳኔ ድጋፋቸውን የሰጡት ወዲያውኑ ነበር፡፡

የሉዉዚያና ሴናተር ቢል ካሲዲ፣ ሚኒስቴሩ ተልዕኮውን ሊያሳካ ባለመቻሉ የፕሬዚዳንት ትራምፕን ውሳኔ እንደሚደግፉ እና መሥሪያ ቤቱ ሊዘጋ የሚችለው በኮንግረሱ ይሁንታ ብቻ በመሆኑ ይህን ለማሳካት የሚያስችሉ ርምጃዎችን እንደሚወስዱ ገልጸው ነበር፡፡

የፕሬዚዳንቱ ትዕዛዝ ተፈጻሚ እንዲሆን ከ100ዎቹ ሴናተሮች መካከል የ60ዎቹን ድጋፍ ማግኘት አለበት፡፡ የፕሬዚዳንቱ ፓርቲ አባላት በሴኔቱ ያላቸው ውክልና ደግሞ 53 ብቻ ነው፡፡

ከኮንግረሱ ይሁንታ በተጨማሪም የፕሬዚዳንቱ ውሳኔ የፍርድ ቤት እግድ ሊገጥመው እንደሚችል ተገምቶ ነበር። እንደተገመተውም ባለፈው ግንቦት ወር አንድ የፌዴራል ዳኛ ትዕዛዙ እንዳይተገበር የእግድ ውሳኔ አስተላልፈው ነበር፡፡ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የሻረው ይህን የእግድ ውሳኔ ነው፡፡

የአልጀዚራው ሺሃብ ራታንሲ ከዋሽንግተን ዲሲ ባሰራጨው ዘገባ፤ የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ ለትራምፕ አስተዳደር ትልቅ ድል እንደሆነ አመልክቷል፡፡ ‹‹የትምህርት ሚኒስቴር እ.አ.አ በ1979 የተቋቋመው በኮንግረሱ ውሳኔ ነው፡፡ ተቋሙ ሊዘጋ የሚችለው በኮንግረስ ውሳኔ ብቻ ነው። የትራምፕ አስተዳደር ከአንድ ሺህ 400 በላይ የመሥሪያ ቤቱን ሠራተኞች ማሰናበቱ ተቋሙን እንደመዝጋት የሚቆጠር ርምጃ ነው›› ብሏል፡፡

የአሜሪካ የትምህርት ሚኒስቴር የሀገሪቱን የትምህርት ሥርዓት እንዲቆጣጠር በፕሬዚዳንት ጂሚ ካርተር የአስተዳደር ዘመን በ1971 ዓ.ም የተቋቋመ የካቢኔ ደረጃ ያለው መሥሪያ ቤት ነው፡፡ መሥሪያ ቤቱ ተቃውሞ የገጠመው ገና ሲቋቋም ነው፡፡ በወቅቱ የመሥሪያ ቤቱ መቋቋም የግዛቶችን ሥልጣን ይጋፋል ያሉ ሪፐብሊካኖች የፕሬዚዳንት ካርተርን ውሳኔ ተቃውመው ነበር፡፡ ይሁን እንጂ የአሜሪካ የትምህርት ሚኒስቴር ሥልጣኖች ውሱን ናቸው፡፡ ሚኒስቴሩ ሥርዓተ ትምህርቶችንም ሆነ የትምህርት ቤት መርሃ ግብሮችን የመቅረፅ ሥልጣን የለውም፤የፌዴራል ብድሮችንና ርዳታዎችን ከማከፋፈል እና የትምህርት መረጃዎችን ከመሰብሰብ የዘለለ ብዙም ኃላፊነት የለውም፡፡

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ረቡዕ ሐምሌ 9 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You