
አዲስ አበባ፡– ለኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ፈረንሳይ እውቅናና ድጋፍ እንደምትሰጥ በኢትዮጵያ የፈረንሳይ አምባሳደርና በአፍሪካ ኅብረት የሀገሪቱ ተወካይ አምባሳደር አሌክሲስ ላሜክ ገለጹ፡፡
በኢትዮጵያ የፈረንሳይ አምባሳደርና በአፍሪካ ኅብረት የሀገሪቱ ተወካይ አምባሳደር አሌክሲስ ላሜክ ከኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ ኢትዮጵያ የባሕር በር ተጠቃሚነት አማራጮቿን ለማስፋት ያላት ፍላጎት ተገቢና ሕጋዊ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
‹‹አንዲት ሀገር፣ በተለይም ትልቅ የሆነች ሀገር፣ የባሕር በር ተጠቃሚነት አማራጮቿን ማስፋቷ ሕጋዊ ነው፡፡ እጅግ ተገቢ የሆነ ጥያቄ ነው›› ብለዋል፡፡
ዓለም አቀፍ ሕግን ተከትሎና ከጎረቤት ሀገራት ጋር በሚደረግ ምክክር እስከተከናወነ ድረስ ጥያቄው ተገቢና ሕጋዊ እንደሆነ አምባሳደሩ ተናግረዋል፡፡
ይህ ጉዳይ ፈተና የሆነው ለኢትዮጵያ ብቻ እንዳልሆነ የተናገሩት አምባሳደሩ፤ በአውሮፓም ብዙ የባሕር በር የሌላቸው ሀገራት እንዳሉ ጠቁመዋል፡፡
ሀገራቱ በድርድርና ከጎረቤቶቻቸው ጋር ባደረጓቸው ምክክሮች የባሕር በር ተጠቃሚ መሆን እንደቻሉ ገልጸዋል፡
አምባሳደር ላሜክ፤ ‹‹የጥያቄውን ተገቢነት እንረዳለን። ጉዳዩ ከኢትዮጵያ ጋር የምናደርገው ውይይት አካል ነው፡፡ ይህ የኢትዮጵያ ፍላጎት በጥሩ የትብብር መንፈስ ከጎረቤት ሀገራት ጋር በሚደረግ ምክክርና በሰላማዊ መንገድ ምላሽ እንደሚያገኝ አምናለሁ›› በማለት ተናግረዋል፡፡
ፈረንሳይና ኢትዮጵያ በባሕር ኃይል ልማት ዘርፍ የሚያደርጉትን ትብብር በተመለከተ ደግሞ፤ ከኢትዮጵያ መንግሥት በቀረበ ጥያቄ መሠረት ፈረንሳይ ድጋፍ እያደረገች እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
‹‹የባሕር ኃይል የፈረንሳይ ታሪክና ማንነት ወሳኝ አካል ነው፡፡ የባሕር ኃይል አቅምን ለማሳደግ እገዛ እንድናደርግ ከኢትዮጵያ የቀረበ ጥያቄ አለ፡፡ ለባሕር ኃይሉ ድጋፍ ለማድረግ ደስተኞች ነን፤ ድጋፎችን እያደረግን ነው›› ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ የባሕር ኃይል ማደራጀቷ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሰላምና ጸጥታን ለማስፈን የራሷን አስተዋጽኦ እንድታበረክት እንደሚያስችላት ጠቁመው፤ ፈረንሳይ ለኢትዮጵያ ባሕር ኃይል የሥልጠና ድጋፎችን እያደረገች እንደምትገኝ ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያና ፈረንሳይ የ125 ዓመታት የዲፕሎማሲ ግንኙነት ታሪክ እንዳላቸው ያስታወሱት አምባሳደር ላሜክ፤ የሀገራቱ ግንኙነት ታሪክ ብቻ ሳይሆን ጥልቅና ተጨባጭ የወዳጅነት ትስስር እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በኢትዮጵያ እና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በፈረንሳይ ያደረጓቸው ጉብኝቶች እና ያካሄዷቸው ጥልቅና የመተማመን ውይይቶች የእዚህ ሁነኛ ማሳያዎች እንደሆኑ ጠቅሰዋል። አምባሳደር ላሜክ ‹‹ከኢትዮጵያ ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የመሠረቱ ቀዳሚ ሀገራት መካከልም ፈረንሳይ ሁለተኛዋ ሀገር ናት፡፡ ረጅም ታሪክ እንጋራለን፤ በእዚህም ኩራት ይሰማናል›› ብለዋል፡፡
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሐምሌ 9 ቀን 2017 ዓ.ም