አዲስ አበባ፦ /ኢቢሲ/ በ10 ሺህ የሚቆጠሩ የደቡብ እና ኦሮሚያ ክልሎች አርሶአደሮችን እና ወጣቶችን ተጠቃሚ የሚያደርገው የጊዳቦ መስኖ ፕሮጀክት ተመረቀ፡፡ ለግንባታው ከ1.2 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ተደርጓል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ግድቡን ከትናንት በስቲያ በመረቁበት ወቅት እንዳሉት፤የመስኖ ፕሮጀክቱ ከልማቱ ባሻገር የሲዳማና የጉጂ ህዝብን አቀራርቦ የሚያስተሳስር ሲሆን፣ በቀጣይም መንግሥት በሌሎች ክልሎችም ለእንደዚህ ዓይነት ፕሮጀክቶች በቅድሚያ ትኩረት ይሰጣል፡፡
ፕሮጀክቱን ሙሉ በሙሉ ከዲዛይን እስከ ግንባታ በኢትዮጵያዊያን መሠራቱም ታላቅ ኩራት እንደሆነ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አመልክተዋል፡፡ ዘመናዊ መስኖን በማስፋት አገሪቱ ያላትን የውሃና የመሬት ሀብት በመጠቀም ከመቀየር የበለጠ አመራጭ እንደሌላት በመረዳት ለዕድገትና ለመለወጥ ተባብሮ መሥራት እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል፡፡
የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ለማ መገርሳ እና የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሚሊዮን ማቲዮስ የመስኖ ፕሮጀክቱ የሁለቱን ህዝቦች የጋራ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ በተለይም ወጣቶችን በዘመናዊ መስኖ ሰፋፊ የመስኖ እርሻዎችን ለማልማት ዓይነተኛ ሚና ይጫወታል ብለዋል፡፡
አቶ ለማ ፕሮጀክቱ በአሁኑ ጊዜ የሚታየውን አላስፈላጊ ክርክርና ንትርክ በመተው ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ባላቸው እንደ ጊዳቦ ባሉ የልማት ፕሮጀክቶች ላይ ትኩረት እንዲደረግ ጠይቀዋል፡፡
ከግድቡ ግንባታ መጠናቀቅ ባሻገር ቀጣይ ሥራ የሆነው የመስኖ ካናል ዝርጋታና ቀሪ የልማት አውታሮች ግንባታ በአጭር ጊዜ ተጠናቆ በሺዎች የሚቆጠሩት የሁለቱ ክልል ወጣቶችና አርሶ አደሮች ወደ ሥራ እንዲገቡ አስፈላጊው ርብርብ እንዲደረግም በወቅቱ ተጠይቋል፡፡
ይህ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ጉጂና በደቡብ ክልል ሲዳማ ዞንን በማስተሳሰር ጊዳቦ ወንዝ ላይ የተገነባ ዘመናዊ የመስኖ ግድብ ፕሮጀክት በ2002 በ910 ሚሊዮን ብር ወጪ ተጀምሮ በሁለት ዓመታት ይጠናቀቃል ቢባልም ሲጓተት ቆይቷል፡፡ ለመመረቅም 8 ዓመት ፈጅቶበታል፡፡ የግንባታው መጓተት፣ የዲዛይን ለውጥና ሌሎች ጉዳዮች የግድቡን የግንባታ ወጪ ከፍ አድርጎታል ተብሏል፡፡
ከ1.2 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገበት ይህ ግድበ በ4.3 ኪሎ ሜትር ስፋት መሬት ላይ ውሃ እንዲይዝ ተደርጎ ነው የተገነባው፡፡ 1ሺህ 2 መቶ ሄክታር መሬት የሚሸፍን ሰው ሠራሽ ሀይቅ ይኖረዋል፡፡
ከ13ሺህ ሄክታር በላይ መሬት እንደሚያለማ የሚጠበቀው ፕሮጀክቱ 8 ሺህ ሄክታሩን ወጣቶች በሰፋፊ የንግድ እርሻዎ የጊዳቦ መስኖ ግድብ በዓሣ እርባታ፣ በቱሪዝማና በእርሻ ሥራ ከፍተኛ ጠቀሜታ ያበረክታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
የሁለቱ ክልል ህዝቦች ተወካዮች፣ አባገዳዎችና የአገር ሽማግሌዎች በምረቃ ስነ ስርዓት ላይ ታድመዋል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 28/2011