ኢትዮጵያ ከፍተኛ መጠን ያለው የዘይት ምርት በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ወደ ሀገር ውስጥ ታስገባለች ። ያም ሆኖ የዘይት ፍላጎትና አቅርቦቱ የተመጣጠነ ባለመሆኑ የዘይት እጥረት፣ የዋጋ ግሽበት እና የጥራት ጉዳይ በየጊዜው ህብረተሰቡን ሲያማርር ቆይቷል። በየወቅቱም ህገወጥ እንቅስቃሴ እንዲበረታ ምክንያት ሆኗል።
እንዲሁም ከዘይት ጥራት ጋር በተያያዘም አንዳንድ የዘይት ምርት የጤና ችግር እያስከተለ ነው በሚል ቅሬታ አስከትሏል። ይህም በንግድ ሥርዓቱ ላይ አለመተማመን እያሳደረ ይገኛል።
የሀገር ውስጥ ዓመታዊ የዘይት ፍጆታ ከፍተኛ በመሆኑ በሀገር ውስጥ የሚመረተው ፍላጎቱን ሊሸፍን አልቻለም። ይሄንኑ ክፍተት ለመሸፈን መንግስት ከፍተኛ ድጎማ በማድረግ ከውጭ ዘይት ማስገባት ከጀመረ ዓመታት አልፈዋ ።
በአስመጪነት የተሰማሩ ነጋዴዎችም በተመሳሳይ ሁኔታ ዘይት ወደ ሀገር ውስጥ ያስገባሉ። ይሄም ሆኖ በሀገር ውስጥ የዘይት ዋጋ እና የጥራት ጉዳይ አነጋገሪ ሆኖ ዛሬ ድረስ ቀጥሏል።
መንግስትም ችግሩን ለመፍታት በተለያየ ጊዜ የመፍትሄ እርምጃ ሲወስድ ቆይቷል። የፓልም ዘይት ላይ ድጎማ በማድረግ እንዲሁም በሌሎች የዘይት ምርቶች ላይ ታክስ በማንሳትና በመቀነስ ጭምር በተመጣጣኝ ዋጋ ህብረተሰቡ የዘይት ተጠቃሚ እንዲሆን ጥረት አድርጓል። ይህም ሆኖ አሁንም ችግሩ ከመባባስ ይልቅ መሻሻል አላሳየም ።
በሀገር ውስጥ ያለውን አቅርቦትና ፍላጎት ለማጣጣም ሌላው የተቀመጠው አቅጣጫ በሀገር ውስጥ ምርቱ በብዛት እንዲመረት ባለሀብቶችን ማበረታታትና ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር ነው።
ይሄንኑ የመንግስትን ጥሪ ተቀብለውና ለሀገርና ለወገን አለሁ ብለው ከፍተኛ መጠን ያለውን ሀብታቸውን በኢንቨስትመንቱ ዘርፍ እያፈሰሱ ካሉት ባለሀብቶች መካከል የበላይነህ ክንዴ ኮርፖሬት በዋነኛነት ተጠቃሽ ነው።
ባለሀብቱ በ4 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ወጪ በአማራ ክልል ቡሬ አካባቢ ዘይት እና ተጓዳኝ ምርቶችን ለማምረት የሚያስችላቸውን ግንባታ አጠናቀው ለማስመረቅ ተዘጋጅተዋል። ፕሮጀክቱ ላለፉት ስድስት ዓመታት ግንባታ ላይ የቆየ ሲሆን ከአጠቃላይ ወጪው መካከል 3ነጥብ 5 ቢሊዮኑ በባለሀብቱ ቀሪው ከባንክ የተሸፈነ ነው።
የህዝብን ችግር ተረድተው የመንግስትንም ጥሪ በመቀበል እራሳቸው ተጠቅመው ሀገራቸውን ለማገዝ በኢንቨስትመንቱ እያደረጉ ያለው እንቅስቃሴ ከአንድ ለሀገሩና ለህዝቡ አሳቢ ከሆነ ባለሀብት የሚጠበቅ ነው። ከፍ ያለ እውቅናም ሊቸረው የሚገባም ነው።
ከሀገር ሀብት ማሸሽ በበዛበት ፣ ስለሀገርና ስለህዝብ ማሰብ ትልቅ ዳገት እየሆነ በመጣበት ፣ በአየር ባየር ንግድ መክበር የወቅቱ ትልቁ የንግድ ፈሊጥ በሆነበት በዚህ ወቅት እንዲህ አይነቱን ሀገራዊና ህዝባዊ ፋይዳ የላቀ ኢንቨስትመንትን በከፍተኛ መዋለ ነዋይ ገንብቶ እውን ማድረግ ዋጋው ከምስጋና በላይ ነው።
ሌሎች ባለሀብቶች ሀገርና ህዝብን እየፈተኑ ላሉ ችግሮች መፍትሄ ሆነው እንዲሰለፉ መነቃቃትን ከመፍጠር ባለፈ በሀገሪቱ እየተገነባ ያለው የይቻላል መንፈስ ሌላ አንድ እርምጃ እንዲራመድ የሚያስችል ተጨባጭ ተሞክሮ ጭምር ነው።
ባለሀብቱ ከትንሽ ነገር ተነስተው ከፍ ባለ ቁርጠኝነትና የዓላማ ጽናት የመጡበት መንገድና ያስመዘገቡት ስኬት በራሱ ብዙ ባለሀብቶችን ለማፍራት የሚያስችል፣ የተነሳሽነት የስሜት መነቃቃት መፍጠር የሚያስችል ከፍ ያለ አቅም የተሸከመ ነው።
ለሀገር መስራት ያኮራል ፤ ያስከብራል ። የዚህ ሀገራዊ ኩራቴ ምንጭ ለመሆን ባለሀብቶች በትጋት፣ በታማኝነትና በአገር ተቆርቋሪነት ስሜት ሊሰሩ ይገባል። ይሄ ሲሆን ሀገር ያድጋል፤ ወገን ይጠቀማል። ትሩፋቱም ለትውልድ የሚሻገር ታሪክ ይሆናል።
አዲስ ዘመን ጥር 22/2013