ተገኝ ብሩ
በጠዋት ሥራና ጉዳያቸውን ጥለው የእኔና የሚስቴ ጉዳይ ለማየት የተሰበሰቡት ሽማግሌዎች ጠባብ የሆነውን ቤቴን ሞሉት፡፡ለአሥር ዓመታት የቆየሁበት ሰፈር ላይ የተግባባኋቸውና የምወዳቸው 6 ሰዎችን ሰበሰብኩ ።እኔ አንድ ጥግ ቆሜ የሚስቴና የእኔን ጉዳይ አስረድቼ ተቀመጥኩ ።
“እኔ የምትፈልገውን እየሰጠሁ! የጎደላትን እየሞላሁ ሳልሰስት ለእስዋ ምቾት እና ድሎት እለፋለሁ ።በእጄ አንዲት ጥሪት ሳልቋጥር አምጣ ያለችኝን እንቺ ፤ ወዲ በል ስትለኝ ውሰጂ እያልኩ ዛሬ ድረስ ቆይቻለሁ ።እወዳታለሁ ፈፅሞ ልለያት አልፈልግም ።የምወደውና የምሳሳለት ልጅ ከእርስዋ አግኝቻለሁ፤ልሂድ ማለትዋን አስቁሙልኝ፡፡” ብዬ ቁጭ አልኩ ።
ድሮ እወዳት የነበረችውና ዛሬ ሙሉ በሙሉ የተቀየረችብኝ ሚስቴ የተሰበሰቡት ሽማግሌዎች ክብር በማይመጥን መልኩ ያልተቆጠቡ ቃላት ትወረውራለች፡፡እኔን እየዘለፈች፤ የተከበሩ ወዳጆቻችን ከምንም ሳትቆጥር በጩኸትና ቁጣ በተቀላቀለበት ስሜት የፈጠረችውና ሆነ የምትለውን ትዘረዝራለች ።“እንደ ሴት ማጌጥ መዘነጥ እፈልጋለሁ፣ እንደ ሰው መለወጥ ያምረኛል ።
በቃኝ! በቃኝ! እንዴ ሰው ነኝ ከዚህ በላይ መሸከም አልችልም ።በቅተኸኛል፡፡”ስትል ከሽማግሌዎቹ መሀል ሁኜ በትዝብት እመለከታታለሁ ።እውነት ይህን የምትናገረው የኔ ሚስት የምወደው ልጄ ታዕምር እናት ናት ።ይሄን ያህል በድያታለሁ? የምታወራውን ሰምቼ ግራ ተጋባሁ፡፡
ጉዳያችንን ለማየት የተሰበሰቡት ሽማግሌዎች አሁን የምትገልፀው ምሬት ብቻ በማየት እኔ ላይ ቢፈርዱ ሁላ አልታዘባቸውም ።“ቤቱን ማስተዳደር አቅቶታል ።ደህነት መሮኛል ።እኔ እራሴን መለወጥ ስለምፈልግ ከእርሱ ጋር መሆን እና መቀጠል አልፈልግም፡፡”
አለች ፈርጠም ብላ ።ከምትናገረው ቃል ቆርጣ ከኔ ለመለየት እንደፈለገች ገባኝ ።የሽማግሌዎቹ መሰብሰብ ዋጋ እንደሌለው ተረዳሁ። ሽማግሌዎቹን የሰበሰብኩት የመጨረሻ ሙከራ ልሞክር ብዬ እንጂ ልቧ ከሸፈተ ቆይቷል ።
በግል እንዳትለየኝ ብዙ ጥረት አድርጊያለሁ ።“ሰብልዬ ተይ አብሮነት ይሻለናል ብዬ ደጋግሜ ልምኛት ነበር ።መጀመሪያ የነበረንን ፍቅር እይ! የምንወደው ልጃችን ተመልከቺ! አብሮነታችን አይቋረጥ፤ ውሎ አድሮ የምትፈልጊው ደረጃ ላይ እንደርሳለን፣ታገሽኝ …” ብያት ነበር፤ አልሰማችኝም ።
ስንጋባ ካንተ ሌላ ዓለም የለኝም ያለችኝ ፍቅሬ ሚስቴ ዛሬ አንተ ጋር ያለው ዓለም ስለጨለመ ሌላ ዓለም ልመልከት ማለት አበዛች ።
ከሰብለ ጋር በቆየንባቸው ሁለት ዓመታት አንድም ቀን ትለየኛለች ብዬ አስቤ አላውቅም ።ባህሪዋ ሲቀየር በአንዴ ስትለዋወጥ ግራ የተጋባሁት ለዚያ ነው ።ባተሌ ነኝ ያ እረፍት እራሴን ለመለወጥ የምተጋ ።እራሴን ለመለወጥ የምሮጥ ።
ጠዋት መርካቶ የሚቀድመኝ የለም ።በተለይ ዓርብና እሮብ ከክልል ከተሞች የሚመጡ ነጋዴዎች የሸቀጥ እቃ ገዝተው የሚያስጭኑበት ዕለት በመሆኑ ጫንቃዬ እስኪዝል እየተሸከምኩ እውላለሁ ።
ሲመሽ ከሁለት ዓመት በፊት ያገባኋት ሚስቴ ጋር እሮጣለሁ ።ቤት እንደገባሁ ተጣጥቤ ልብሴን ከመቀየሬ በፊት ቀን ስሰራበት የዋልኩትን ገንዘብ በንጋታው ለትራንስፖርት የሚሆነኝን ቀንሼ ለእስዋ አስረክባለሁ ።
ቤታችን ያስፈልገዋል የምትለውና የሚያስፈልገውን የምታደርገው እስዋው ናት ።መጀመሪያ ላይ ጎበዝና የተሰጣትን አብቃቅታ ቤታችንም ድምቅ ብላ እንድትታይ አድርጋት ነበር ።
የሰራሁትን ሁሉ ለእስዋው ስለምሰጣት በአቅማችን በቂ የሆነ ነገር ሁሉ አሟልታ በፍቅር ውለን ማደር በደስታ ጊዜ ማሳለፍም አዘውትረን ነበር ።ምን ዋጋ አለው ዛሬ ሰብሊ መለያየትን መርጣ ሰዎች በተሰበሰቡበት የመጨረሻ ቃልዋን “በቃኝ ከእርሱ ጋር መኖር አልፈልግም” ሆነ፡፡
አቤት ሰው ለካስ መክሊቱን ተረድቶ እዚያ ላይ አልተገኘምእንጂ በአንድ ጉዳይ ላይ የተዋጣለት ባለሙያ ነው ። ሰብሊ ምርጥ ተዋናይ ናት ።ሽማግሌዎቹ ፊት የተወጣላት የተበዳይ ገፀባህሪ ተላብሳ መስላ ሳይሆን ሆና ነው የተወነችው ።
የዚያ ቀን አንድ የተውኔት ወይም የፊልም አዘጋጅ ከሽማግሌዎቹ ውስጥ ቢኖር መርጦ በተውኔቱ አልያም በፊልሙ ዋና ገፀ ባህሪ ይሰጣት ነበር ። አቤት ያዙኝ ልቀቁኝ በሚል ቡራ ከረዩ ተውረገረገች ።
ደሞ የለበሰችው ልብስ ከዚያን ቀን በፊት ያለበሰችውና ድሮ ከኔ ጋር እንደተዋወቅን ታዘወትረው የነበረና ሶስት አራት ቦታው የተነደለ ቀሚስ ነው ።አሁን ላይ ይሄ ቀሚስ ለመልበስ አይደለም ለማየትም ትጠላዋለች ።ተለውጣለቻ ።ዛሬ ግን ሽማግሌዎቹ ፊት ይሄን ለብሳ ሳይ ተገረምኩ ።
ሚስቴ ናትና እንዲያምርባት እጅጉን እፈልግ ነበር ። ከቤታችን ወጪ በላይ የእርስዋ መዋቢያና አልባሳት በልጦ እንኳን እያየሁ በእስዋ እያማረችና እየፈካች መሄድ ከመደሰት እና ያምርብሻል ከማለት ውጪ አንድም ቀን ይሄ ነገር በዛ ብዬ አላውቅም ።መጀመሪያ ከምሰጣት ብር ላይ እንደምትቆጥብ ትነግረኝ ነበር ።
ኋላ ላይ “የምትሰጠኝ ብር እንኳን ለቁጠባ ለቤታችንም አይበቃም” ማለት ጀመረች ።የምሰጣት ብር ከወጪያችን ተርፎ ቢጠራቀም ሊለውጠን የሚችል መሆኑን ባውቅም መናገርን ተውኩ፡፡
ተሸክሜ ከባለሱቆችና ከነጋዴዎች በየቀኑ የሚሰጠኝ 300 እስከ 500 ብር ድረስ አንድም ሳላጎል የምሰጣት ከቤትዋ ወዴት ትወስደዋለች ።ቢተርፍ ለራስዋ ነው እያልኩ ነበር ።ሰብሊ አንድ ልጅ ወልዳ ካበረከተችልኝ በኋላ ተለወጠች ።በፊት የማውቃት ሚስቴ ሰውነትዋ መለስ ካለና መልሳ ማማር ከጀመረች በኋላ ተቀየረች ።
ከቤት ዘንጣ ወጥታ ምሽት እኔ ከመርካቶ ስመለስ አንዳንዴም እኔ ገብቼ ከቆይታ በኋላ መድረስ አዘወተረች የህፃናት መዋያ በሌለን ገንዘብ ከፍለን እንድናውለው የተደረገው ልጃችን መጎዳቱና የእስዋ ሁኔታ መቀየር አሳስቦኝ አወራኋት ልትሰማኝ ግን አልፈቀደችም፡፡
የድሮዋ የምወዳትና የማፈቅራት ሚስቴ ሰብለ አዲስ ሆነችብኝ ።ልጄን ተወችው፤ እስዋ ስትፈካ ልጄ ጠወለገ ። የማደርገው ግራ ገባኝ ።ጓደኞችዋ በዙ፣መዋያዋ በረከተ፣ አዳዲስ ሰዎችን ተላምዳ እኔና ቤቴ አስጠላናት ።ውጪ ውጪ ማለት አበዛች ።አስታራቂ ይሆናሉ ያልኳቸው ሽማግሌዎች አሰፍራ ከቤት አባረረችብኝ፡፡ተከትላቸው እንደማትመለስ ነግራኝ ከቤት ወጣች ።
የሁለት ዓመት ልጅዋ እንኳን ላትመለስ መሄድዋን አንዳች ነገር የነገረው ይመስል ስቅስቅ ብሎ ሲያለቅስ እየሰማች ቆይቶ ወደስዋ የመጡት ልብሶችዋና ማጌጫዎችዋን ይዛ ከቤታችን ራቀች፡፡እኔም በእንባ ሸኘኋት፡፡ተመልሼ ልጄን አቅፌ ማባበል ጀመርኩ፡፡
ይህ ከሆነ አምስት ዓመት አለፈው ።ልጄን ብቻዬን እየተጣጣርኩ አሳደኩት ብቸኛ መፅናኛዬ ሆነ ።በፍቅር እወደዋለሁ ።የዘወትር ድካሜና ልፋት ፍሬ አፍርቶ በፊት ለሰብለ ሳልቆጥብ እሰጣት የነበረው መቆጠብ ጀምሬ ባጠራቀምኩት ገንዘብ ከሸክም ተላቅቄ የራሴ መለስተኛ ሱቅ ከፍቼ በመስራት ትርፋማ ሆንኩ ።
የተሻለና ለኑሮ ምቹ የሆነ ቤት ተከራይቼ ሰራተኛ ቀጥሬ መኖር ጀመርኩ ። አንድ ቀን ጠዋት ላይ የቤት ሰራተኛዬ ቁርስ እያሰናዳች እኔ መታጠቢያ ክፍል ሆኜ የምወደው ልጄ በር ሲንኳኳ ከፍቶ ሲያወራ ወጣሁ።
አንዲት ልጅ ተንበርክካ “ልጄ! አታወቀኝም እኔ ሰብለ እናትህ ነኝ አታውቀኝም!”ብላ ልታቅፈው ስትል ወደ ኋላ እየሄደ እኔ አባት እንጂ እናት የለኝም ሲላት ደረስኩ ።ያየሁትን ማመን አቃተኝ ።ሰብለ ከስታና ጥቁርቁር ብላ ሌላ ሰው ሆና አየኋት ።ድሮ ልንጋባ ስንል ባላውቃት እስዋ መሆንዋን ማወቅ እቸገር ነበር ።
ቆሜ ተመለከትኳት ከአይኗ እንባ ታወርዳለች ከንፈርዋ ይንቀጠቀጣል፡፡አዘንኩላት፤ ወዲያው ስትሄድ ያደረገችው ትውስ ብሎኝ ሀዘኔታዬ ወደ ንዴት ተቀየረ ።በሩን ዘግቼባት ወደ ቤት ገባ ።ቁርስ በልቼ በኋላ በር ወጣሁ ። ተፈፀመ ።
አዲስ ዘመን ጥር 21/2013