መርድ ክፍሉ
በወጣትነት እድሜ ብዙ ሥራዎች ለመስራት እቅድ የሚያዝበትና ዝግጅት የሚደረግበት እድሜ ነው። በወጣትነት ጥሩም ይሁን መጥፎ ነገሮች ቢደርሱ ትምህርት ተወስዶ ለቀጣይ እምርታ ከማምጣት ረገድ መሰረት የሚጣልበት ወቅትም ነው ።
ዛሬ በወጣትነት እድሜያቸው የተለያዩ ነገሮች በመፍጠርና ወደ ሥራ እድል በመለወጥ ስኬታማ የሆኑትን የሁለት ወጣቶች ተሞክሮ እናቀርባን ።ስለ ወጣቶቹ ታሪክ ከፋና ቴሌቪዥንና ከሥራ እድል ፈጠራ ኮሚሽን ድረ-ገፅ ያገኘነውን መረጃ እንደሚከተለው አቅርበነዋል ።
ወጣት ብሩክ በቀለ ከልጅነት ዕድሜው ጀምሮ ሲያልመው የነበረውን ህልም አጠናቆ እራሱ በሰራው አውሮፕላን ሊጓዝ ዝግጅቱን አጠናቋል ።ከልጅነቱ ጀምሮ በጣም ይገርመው የነበረውን አንድ ግዑዝ አካል ወደላይ ተነስቶ የሚጓዝበትን መንገድ ማወቅ በጣም ይፈልግ ነበር።
ለዚህም እንዲረዳው የሜካኒካል ኢንጅነሪግ ትምህርት አጥንቷል።በውስጡ የነበረውን ፍላጎት በትምህርት በመደገፍ የራሱ ፈጠራ የሆነ አውሮፕላን ለመስራት ቻለ፡፡
በቀጣይ የሰራውን አውሮፕላን ለማብረር ፍላጎት ያለው ሲሆን በቅርቡም እንደሚያሳካው በልበ ሙሉነት ይናገራል ።ለሰራው አውሮፕላን ቀላል የሆኑ የአልሙኒየም ቁሶችን ተጠቅሟል። አውሮፕላኑ በቀላሉ እንዲነሳና ክብደት ለመቀነስ በማሰቡ አልሙኒየም ለመጠቀም መፈለጉን ይገልፃል ።
በራሱ አቅም የሚችላቸውን ቁሳቁሶች እየገዛ መስራቱንም ይናገራል ።አውሮፕላን የሚያስፈልገው አምስት መሰረታዊ ነገሮችን እሱ በሰራው አውሮፕላን ውስጥ መካተታቸውን ይጠቁማል ።በቅርቡ ለሙከራ እንደሚያበርም ያመለክታል ።
በቴክኖሎጂው ዘርፍ አገሪቱ ብዙ እየተጓዘች አለመሆኑን ይናገራል። አስፈላጊ ትብብሮች ቢደረጉ ከውጭ የሚገቡ ምርቶች በራስ አቅም መስራት ይቻላል ።ወጣት ብሩክ የሚፈልገው የተሰሩ ፈጠራዎች የሚሞከሩባቸው ቦታዎች እንዲዘጋጁለት ነው ።
ግብዓቶች ከተገኙ አውሮፕላን መስራት ቀላል እንደሆነም ይጠቅሳል ።እንደ ልዩ ነገር የሚታዩ ቴክኖሎጂዎችን በራስ ሰርቶ መጠቀም እንደሚቻልም ያስረዳል ።
የሰራው አውሮፕላን የመጀመሪያ ሥራ እንደመሆኑ የተለያዩ ችግሮች ቢኖሩበትም አውሮፕላኑን ከማብረር ምንም ነገር እንደማያግደው ይጠቁማል ።የገንዘብ ድጋፍ የሚያገኝበት ሁኔታ ከተመቻቸ ብዙ ሊሰራ እንደሚችል ያመለክታል ።የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና የኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ትብብር ሊያደርጉለት ሁኔታዎች እያመቻቹ መሆኑን ይጠቅሳል ።
በግለሰብ የተሰሩ አውሮፕላኖች ስም ሲሰጣቸው በምዕፃረ ቃል እንዲጠሩ ተደርጎ መሆኑን የሚናገረው ወጣት ብሩክ፣ አገርን፣ አውሮፕላኑ የተሰራበትን ስፍራ እና ዓመተ ምህረትን እንደሚያካተቱ ይገልፃል ።
የጥበብን ፀጋ የሚጎናፀፉት ብዙዎች ቢሆንም ከሁሉም አይነት ግን የሚካኑት ጥቂቶች ናቸው ።ከሙዚቃውም፣ ከስዕሉም፣ ከተውኔቱም፣ ከሞዴሊንጉም እንዲሁም ከዲዛይኑም ጥበብ የተቸራት ሁለገቧ ሥራ ፈጣሪ ማህሌት አፈወርቅ ከልጅነቷ ጀምሮ እያንዳንዱን ተሰጥኦዋን ሞክራ ስትጨርስ ልቧ አብዝቶ በወደደው የፋሽን ዲዛይኑ ላይ አረፈ፡፡
‹‹በህልም ብቻ የሚሆን ነገር የለም ህልም ወደ ድርጊት መቀየር አለበት ።የሚያልሙትን ነገር ካልሞከሩ መሳካት አለመሳካቱ አይታወቅም። ለኔ ትልቁ የጠቀመኝ ነገር ብዙ ነገር ሞክሬ የምወደውን መምረጥ መቻሌ ነው። የሚቆጨኝ ነገር የለም›› ትላለች ‹‹የማፊ ማፊ›› መስራች እና ዋና ሥራ አስኪያጅ ማህሌት፡፡
የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ እያለች ጀምሮ የማትሳተፍበት የጥበብ መድረክ አልነበረም። በተለይ ከ7ኛ ክፍል ጀምሮ ትምህርት ቤቴ ውስጥ በሚዘጋጁ የተለያዩ መድረኮች ላይ በዳንስ እና በሙዚቃ ትሳተፍ እንደነበር ትናገራለች ።የቀሚስ ዲዛይኖች እየሳለች ለጓደኞቿ ትሰጣቸውም ነበር ።
በተጨማሪም ከጓደኞቿ ጋር የፋሽን መድረኮች ታዘጋጅም ነበር ።ለመጀመሪያ ጊዜ ዲዛይን ያደረገችው ልብስ የድሮ ዩኒፎርሟን ቀዳዳ እንደነበር ታስታውሳለች፡፡
ዘጠነኛ ክፍል ስትደርስ ቅዳሜና እሁድ የሞዴሊንግ ትምህርት መማር ጀመረች ።ጎን ለጎንም ከጓደኞቿ ጋር ከቤተሰብ ይሰጣት የነበረውን የኪስ ገንዘብ አጠራቅማ ሙዚቃ ሰርታለች ።ሙዚቃው በተለያዩ የሬድዮ ጣቢያዎች ተቀባይነትን አግኝቶ ተደምጦላታል።
ድምፃዊ ዮሴፍ ገብሬ (ጆሲ) ሙዚቃውን ሰምቶ አፈላልጎ አገኛትና ከእሱ ጋር ‹‹ጆሲ ኢን ዘ ሀውስ›› የተሰኘውን ሙዚቃ መስራቷን ትናገራለች ።በጊዜው በጣም እውቅናን ያገኘ ዘፈን ስለነበር እሷን ወደ ሙዚቃው ሥራ በቀጥታ እንዳስገባት ትጠቅሳለች፡፡
ሙዚቃው ከተለቀቀ ከሁለት ዓመት በኋላ ቪድዮ ሊሰራ ሲታሰብ የልብስ ዲዛይን እንደምትሞክር ለድምፃዊ ዮሴፍ ገብሬ ስለነገረችው በቪድዮ ላይ ለሚሳተፉ ሰዎች በሙሉ ዲዛይን እንድታደርግ እድሉ ተሰጣት ።እንደ ሥራ ደግሞ መጀመሪያ የሰራችው ዲዛይን እንደነበረም ትናገራለች ።
የዲዛይን ሥራዋ በተለይ በአርቲስቶች ዘንድ ጥሩ ትውውቅ እና ገበያ ፈጠረላት ።ጎን ለጎንም የተለያዩ የሞዴሊንግ እና የፊልም ሥራዎች ትሰራ ነበር ።እንዲሁም የሙዚቃ ሥራዎችን አብራቸው እንድትሰራ ከብዙ ሰዎች ጥያቄ ይቀርቡላት እንደነበር ታመለክታለች፡፡
ምንም እንኳን በጊዜው የምትወደውን ሥራ ሁሉ የመሞከር እድሉ ቢቀናትም ልጅ ስለነበረች ከሁሉም አቅጣጫ ድንገት የመጣው እውቅና ገዝፎ ከብዷት እንደነበር ታስታውሳለች ።አድናቆቱ እና እውቅናው መልካም ቢሆንም ውስጧ ግን ደስተኛ አልነበረም ።እንደዛ መፍጠኑን አልወደደችውም ነበርና የተለያዩ የሙዚቃ ሥራዎች ሲመጡ እየመለሰች ለራሷ ጊዜ ሰጥታ ምንድነው የምፈልገው? የቱ ነው የሚያስደስተኝ? ብላ ራሷን መጠየቅ መጀመሯን ትጠቅሳለች ።
ከሁሉም ሥራዎች ነፃነት የሰጣትን የዲዛይን ሥራ አጥብቃ ያዘች ።ሁሉንም መሆን ቢቻልም ግን አብልጣ የምትወደው ላይ ትኩረት ስታደርግ ስኬታማ መሆን እንደምትችል ገባት ።ይሄንን ለመወሰን ሁለት ዓመት ቢፈጅባትም መጨረሻ ላይ “በቃ ማፊ ዲዛይነር ነች!” ብላ መወሰንዋን ታስረዳለች፡፡
ይህን ሥራም ስትጀምር 21 ዓመቷ ነበር ።እናቷ በሰጠቻት 40 ሺህ ብር መነሻ ካፒታል አንድ ማሽን ገዛች ።በ2009 ዓ.ም መሸጫ ሱቅም ከፈተች ።ብቻዋን እየሰራች ብትጀምርም ቀስ በቀስ አንድ ሰፊ ቀጠረች ።
ምንም እንኳን ደንበኞች ለማፍራት ባትቸገርም ዲዛይን ለማድረግ ያቀደቻቸው ቀለል ያሉ የባህል ልብሶችን ሳይሆን ሰዎች እንዲህ ይሁንልን ብለው በሚያዙት የተለመደው አይነት የባህል ልብስ ሥራ ውስጥ እራሷን በማግኘቷ በድጋሚ ቆም ብላ እንድታስብ እንዳደረጋት ትጠቁማለች፡፡
የእሷ ህልም የነበረው ያሰበቻቸውን ልብሶች ‹‹ማፊ›› በሚባል ብራንድ ተመርተው ሰው እንደየአቅሙ እንዲገዛ ነበር ።ነገር ግን ያንን ለማድረግ የሚያስፈልገው የሂሳብ አያያዝና የቢዝነስ አስተዳደር እውቀት አልነበራትም። ቢዝነሱን የሚያስተምራት ሰው ስላልነበር ወደምትፈልገው አቅጣጫ መሄድ እንዳልቻለች ትናገራለች ።
በዚህ ምክንያትም የተሻለ ለመረዳት ሁለት ዓመት ከሰራች በኋላ ሱቋን ዘግታ ‹‹አፍሪካን ውመን ኢንተርፕረነርሺፕ›› ፕሮግራምን መቀላቀሏን ትጠቅሳለች፡፡
‹‹እዚህ ቦታ ደርሻለሁ ተብሎ እውቀት በቃኝ አይባልም! በተቻለ መጠን ሁሉ ከምናገኛቸው ሰዎች መማር ጥሩ ነው ።የቢዝነስን ፅንሰ ሀሳብን ከማህበራቱ በመማር እና ከብዙ ሥራ ፈጣሪ ሴቶች ልምድን በመቅሰም በ2011 እ.ኤ.አ እንደህልሜ “ማፊ ማፊ” የተሰኘውን ብራንዴን በመፍጠር ሌላ ሱቅ ለመክፈት በቃሁ ።
ዛሬ በድርጅቴ ውስጥ 55 ሰራተኞች ያሉ ሲሆን ከእነዚህ 90 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ሴቶች ናቸው፡፡›› ትላለች ።
በዓለም አቀፍ ደረጃም ሆነ በኢትዮጵያ የፋሽን ኢንዱስትሪው በይበልጥ ሴቶች የሚሳተፉበት ቢሆንም የሴት ሰራተኞችን ቁጥር እንድታበዛ ያደረጋት ምክንያት ሥራውን እንደጀመረች አካባቢ የሽመና ሥራ የሚሰሩ ባለሙያዎች ዲዛይነር እና ነጋዴ ሳይጠብቁ እንዴት ገበያ ላይ መወዳደር እንደሚችሉ ስልጠና ትሰጥ እንደነበር ታስረዳለች፡፡
ህልሟ እና ትግሏ ትልቅ ቢሆንም ዘርፉ ላይ በርካታ ችግሮች እንዳስተዋለች የምትናገረው ማህሌት፤ ኢትዮጵያ በጥጥ ምርት ከአፍሪካ ብትታወቅም የምርት ጥራቱ ግን በዛው ልክ እንዳላደገ ትጠቅሳለች ።ያለማዳበሪያ ያደገ ወይንም ኦርጋኒክ የሆነ የጥጥ ምርት እንደልብ አለመገኘቱ ትልቅ ፈተና እንደሆነም ታስረዳለች ።
እውቅና ያላቸው ያለ ማዳበሪያ የሚያመርቱ ጥቂት ጥጥ አምራቾች ሀገር ውስጥ ቢኖሩም ጥጡ ፋብሪካ ከገባ በኋላ ግን በማዳበሪያ ከተመረተው ጋር ይደባለቃል ።ዓለም አቀፍ ገበያ ላይ ሲቀርብ ደግሞ መጀመሪያ የሚጠየቀው “ያለማዳበሪያ በተመረተ ጥጥ ስለመሰራቱ እውቅና አለው ወይ?” የሚለው ነው ።የውጭ ገበያ ላይ ሥራዋን ስታቀርብ የሚጠብቃት ይህ መሆኑን ታብራራለች ።
ሌላ አገር ባሉ ዲዛይነሮች የተለመደው ነገር አምራቾችን በመምረጥ አንዱን ጥሬ እቃ ከአንድ አገር ሌላውን ከሌላ ቦታ አስመጥቶ መስራት ነው ።ይሄን ችግር ለማስተካከል የፈጀውን ጊዜ ይፍጅ እንጂ ሙሉ ለሙሉ ኢትዮጵያ ውስጥ ተመርቶ ከኢትዮጵያ የሚወጣ ልብስ እንዲሆን ፍላጎት እንዳላት ትጠቅሳለች ።
ሌላው ፈተና ደግሞ የመስሪያ ገንዘብ እጥረት ነው ።ባለሀብቶች እንደሌላው ሀገር ልምድ በፋሽን ኢንዱስትሪው ላይ መዋዕለ-ነዋያቸውን የማፍሰስ ተሞክሮ አልተለመደም ።ወጣት ሥራ ፈጣሪ ተሁኖ ከባንክ ብድር ማግኘትም እጅግ ከባድ ነው ።እሷ ከጥቃቅን እና አነስተኛ ትንንሽ ብድሮችን በመበደር እንደዚህ አይነት ፈተናዎችን እንደተወጣች ትገልፃለች ።
ከዚህም አለፍ ሲል በ10 ዓመት ቆይታዋ የመስሪያ ቦታ ችግር እጅግ እንደፈተናት የምትገልፀው ማህሌት፤ በመንግሥት የሚሰጡ መስሪያ ቦታዎችን ለማግኘትም ያለው ሂደት ጊዜ የሚፈጅ ሆኖ ስላገኘችው በኪራይ ቤት ለመስራት መገደዷን ትገልፃለች ።እንዲህ ያሉ ፈተናዎች ከዘርፉ ሳይቀረፉ የዓለምን ኢኮኖሚ ያናጋው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ወደ ኢትዮጵያም ገብቶ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ መሆኑ እጅግ የሚያስጨንቅ ሁኔታን ፈጥሮባቸው እንደነበር ትናገራለች፡፡
የኮቪድ 19 ወረርሽን በተከሰተበት ወቅት ‹‹ሙሉ ለሙሉ ነበር ሥራችን የቆመው ።የሰራተኞቼ ነገር በተለይ ደግሞ የሽመና ሥራው ላይ ያሉት እጣ ፈንታ እጅግ ያሳስበኝ ነበር ።ትልቅ ኃላፊነት እንዳለብኝ ስለተሰማኝ መተኛት አልቻልኩም ነበር ።ኢትዮጵያ ውስጥ ገና የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል አድርጉ ከመባሉ በፊት ኢንተርኔት ላይ ገብቼ እንዴት እንደሚሰራ እና ምን ምን እንደሚያስፈልገው ካየሁ በኋላ ቀጥታ ወደ ማምረት ገባን፡፡›› ትላለች ።
መጀመሪያ የተመረቱትን ጭምብሎች በጠቅላላ ለድጋፍ ዋለ ።ቀስ በቀስ መንግሥትም ጭምብል መልበስን አስገዳጅ ሲያደርግ ወደ መድኃኒት እና ቁጥጥር ባለስልጣን በመሄድ የማምረቻ ፍቃድ መጠየቋን ትናገራለች ።ባለስልጣኑ ፍቃድ የሚሰጠውም ሆነ የፅዳት አስገዳጅነትን የሚተገብረው በቀዶ ጥገና ወቅት የሚደረጉ ጭምብሎችን ለሚያመርቱ እንጂ የጨርቅ ጭምብል ለሚያመርቱ የተዘጋጀ መመሪያ እንደሌለ ቢገልፅም ለማምረት የተዘጋጀው ጭምብል እጅግ አደገኛ የሆነውን ወረርሽኝ ለመከላከል የሚውል እና ጥንቃቄ የሚያስፈልገው ሥራ በመሆኑ የምትሰራበትን ቦታ በማጽዳት ምርት ማምረት እንደጀመረች ትጠቁማለች ።
እንዲህም ሆኖ ስድስት ሰራተኞቿን ለማሰናበት መገደዷን ታመለክታለች ። ከዋናው ምርት ገቢ በመቋረጡ ግማሽ ሰራተኞቿ ደግሞ ለተወሰኑ ሰዓታት ብቻ እንዲሰሩ ማድረግ ግድ እንደሆነባት ትናገራለች ።
ይሄን ጊዜ በሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን ትብብር ከማስተር ካርድ ፋውንዴሽን የመጣው ድጋፍም በከባድ ጊዜ እንደደረሰላቸው ትገልፃለች ።በተደረገው ድጋፍ ያሏትን ሰራተኞች ከቅነሳ ከማዳን በተጨማሪ ቀድማ ማምረት የጀመረችውን ጭምብል በተጨማሪ የሰው ሀይል እና ማሽን እንድታመርት አስችሏታል ።
ጊዜው እና ሁኔታው ጭምብሎችን እንድታመርት ግድ ቢላትም ዓላማዋ የሆነውን የተቋቋመችበት አላማ የፋሽን ዲዛይን ሥራዋን ለማስቀጠል ጊዜውን እንደመዘጋጃ እየተጠቀመችበት እንደሆነ ትገልፃለች ።ህልሟ ትልቅ እንደሆነ የምትናገረው ማህሌት፤ ገበያው በድጋሚ በስፋት ሲከፈትም ከነበረችበት አድጋ እና ተሻሽላ ለመቅረብ ዝግጅት መጀመሯን ትናገራለች፡፡
‹‹እስካሁን የመጣሁት መንገድ አብስሎኛል ።ሰው የትኛውንም ያህል ተሰጥኦ ቢኖረው ካለፋ እና ጠንካራ ሰራተኛ ካልሆነ እንዲሁም ወደሚፈልገው ህልም የሚወስደውን መንገድ ተነስቶ ካልጀመረ መቼም ስኬታማ አይሆንም ።ስኬት ደግሞ ግዴታ ትልቅ ገንዘብ ማግኘት አልያም ትልቅ ቦታ ላይ መቀመጥ ብቻ አይደለም መንገድ ተነስተን ጀመርን ማለት ስኬታማ ነን ማለት ነው ።
ህልሜ አሁን ከያዝኩት በላይ ትልቅ ነው ።ወደ እዛ የሚወስደኝን መንገድ እየተጓዝኩ ነው ያለሁት ።የሚወዱት ነገር ላይ ትኩረት አድርጎ እስከመጨረሻው ይዞ መሄዱ ዋጋ አለው።›› ብላለች።
አዲስ ዘመን ጥር 21/2013