የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ዘርፍ የአገሪቱ ኢኮኖሚ በዝቅተኛና በመካከለኛ ደረጃ የሚያስፈልገውን የሠለጠነ ሙያተኛ በማፍራትና ቴክኖሎጂ በማቅረብ በኩል ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት ዕሙን ነው፡፡ በመሆኑም ዘርፉ አገሪቱ ከግብርና መር ወደ ኢንደስትሪ በምታደርገው ኢኮኖሚያዊ ሽግግር ለኢንደስትሪው አቅምና መሠረት ይጥላል፡፡ ለዚህም የትምህርትና ሥልጠና ፖሊሲው ከወጣ በኋላ ላለፉት ዓመታት በዘርፉ በተለያዩ የሙያ ዓይነቶች ሰፊ አቅም ግንባታ ሥራ ሲሰራ መቆየቱ ይታወቃል፡፡ ይሁን እንጂ በዘርፉ የሚፈለገውን ለውጥ ማምጣት እንዳልተቻለ ይነሳል፡፡ እኛም በዚህ ዙሪያ ችግሮቹን ለማቃለል ምን እየተሰራ ነው? ለቀጣይስ ምን ታቀደ? በሚል ከፌደራል ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ተሻለ በሬቻ ጋር ቆይታ አድርገናል፡፡ በቅድሚያም የትምህርት ፍኖተ ካርታ ለማዘጋጀት በተደረገ ጥናት ዘርፉን አስመልክቶ የተገኙ ግኝቶች ምን እንደሚመስሉ በማሳየት እንጀምር፡፡
ጥናት
ወጣቶች 10ኛ ክፍል ካጠናቀቁ በኋላ 80 በመቶ የሚሆኑት ወደ ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና በመሳተፍ ሥራ እንዲፈጥሩና ኢኮኖሚውን እንዲደግፉ ከማድረግ አንፃር ሰፊ ክፍተት እንዳለ ጥናቱ ያመላክታል፡፡ በ2008 ዓ.ም ለ10ኛ ክፍል የአጠቃይ ሁለተኛ ደረጃ ፈተና የተቀመጡት 1 ሚሊየን 30 ሺህ 97 ሲሆኑ በ2009 ዓ.ም ወደ መሰናዶ ትምህርት/11ኛ ክፍል/ የገቡት 265 ሺህ 339 ብቻ ናቸው፡፡ በዚህም 824 ሺ ሠልጣኞች መሳተፍ ሲገባቸው በመደበኛ ቴክኒክና ሙያ የሰለጠኑት ግን 302 ሺህ 83 ናቸው፡፡ የተሳትፎው ዝቅተኛ መሆን የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ተቋማት የማስፋፋት ሥራ ጋር የተያያዘ ነው፡፡
በአገር አቀፍ ደረጃ ካሉት 1 ሺህ 27 ወረዳዎች ውስጥ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ተቋማት ያላቸው 367 ወረዳዎች ናቸው፡፡ በዚህም ኢትዮ ሶማሌ፣ አፋር፣ ጋምቤላ፣ ድሬዳዋ፣ አዲስ አበባና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ እንደ ቅደም ተከተላቸው በከፋ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ጥናቱ ያሳያል፡፡ በተያያዘ ተቋማቱ ደረጃውን በጠበቀ ግብዓት ያልተሟሉና አብዛኞቹ በትልልቅ ከተሞች የተቋቋሙ መሆናቸውንም ያስቀምጣል፡፡ ባሉትም ተቋማት ደግሞ ተሳትፎው አጥጋቢ የሚባል አይደለም፡፡ ለዚህም እንደ ችግር ሆኖ የሚነሳው በሕብረተሰቡ ዘንድ ስለተቋማቱ ያለው ግንዛቤ አናሳነት ነው፡፡
በተቋማቱና በሕብረተሰቡ ላይ ከሚስተዋሉ ክፍተቶች በተጨማሪም የሙያ ደረጃዎችን የሚሸከም የኢንደስትሪ አቅም አለመፈጠርና አደረጃጀቱ አለመኖሩ ቅንጅቱም የላላ መሆኑ በችግርነት ተቀምጧል፡፡ ኢንደስትሪውን በዕምነት ያልተቀበለው የትብብር ሥልጠና በጥናቱ ተነስቷል፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ ፈጠራን የማያበረታታና ከሥራ ጋር ያልተቀናጀ ሥርዓተ ትምህርት መኖሩን ሌላው ችግር ሆኖ ተለይቷል፡፡ አገሪቱ ለምታካሂደው ሁለንተናዊ ዕድገት የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና በተለያዩ ዘርፎች የሚያስፈልገው ብቁ የሰው ኃይል፣ ቴክኖሎጂና የኢንደስትሪ አሰራር ዕውቀት ወሳኝ ነው፡፡ ሆኖም ከቅድመ መደበኛ ትምህርት ደረጃ ጀምሮ ለዕድሜ ደረጃቸው የሚመጥን የሙያ ትምህርት እንዲያውቁና የሥራ ፍቅርን፣ ፈጠራንና ሙያን እንዲለማመዱ አያደርግም፡፡
ወደ ሥልጠና የገቡት ሠልጣኞችም ፈጠራን በሚያበረታታ መልኩ እየሰለጠኑ አለመሆናቸውን ጥናቱ ያረጋግጣል፡፡ በየተቋማቱ በተለይም በገጠር አካባቢ የሚዘጋጁት ፕሮግራሞችም ለሥራ ዓለም ዝግጁ የሚያደርጉ አይደሉም፡፡ በችግሮቹ ተያያዥነትም ወደ ዘርፉ ለመደበኛ ስልጠና ገብተው ከሚሰለጥኑት ወጣቶች አብዛኞቹ ለመመዘን ፍላጎት የላቸውም፡፡ የሚመዘኑትም የብቃት ፈተናውን ያማያልፉት 31 ነጥብ 3 በመቶ ናቸው፡፡ በተመሳሳይ ከኪራይ ሰብሳቢነት ያልፀዳ ኢንደስትሪው ባለቤት ያልሆነበት የሙያ ብቃት ምዘናም ተጠቃሽ ክፍተት ነው፡፡ ከሥልጠናው ብቃት ችግርም በራሳቸው ሥራ ከመፍጠር ይልቅ ሥራ ጠባቂ ሆነው ይታያሉ፡፡
የሥልጠና ብቃት ችግር ሲነሳ በቀዳሚነት የሚታየው የአሰልጣኞች ጉዳይ ነው፡፡ በጥናቱ እንደተረጋገጠውም፤ የሥልጠና ጥራትን ማረጋገጥ ያልቻለ የአሰልጣኝ ምልመላና ዝግጅት ስርዓት መኖሩ ነው፡፡ ኢንደስትሪዎችና ተቋማቱ በዘርፉ በከፍተኛ ደረጃ የሰለጠነ ባለሙያ ያስፈልጋቸዋል፡፡ ነገር ግን አሰልጣኞቹ የኢንደስትሪ ልምድ እንደሌላቸው ጥናቱ ያሳያል፡፡
ቅንጅት
የኢትዮጵያ ቴክኒክና ሙያ ስርዓት የተቀዳው ከጀርመን ሲሆን፤ እ.አ.አ 1964 ጀምሮ በዘለቀው የልማት አጋርነትም ዘርፉን ለመደገፍ በርካታ ተግባራት ተከናውነዋል፡፡ በነበረው ቆይታም 1 ነጥብ 2 ቢሊየን ዩሮ ለሁለትዮሽ ግንኙነቱ ጀርመን ለኢትዮጵያ ማበርከቷን መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡ ባለፈው ዓመትም የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ዘርፉን በመደገፍ በኢኮኖሚው ዘርፍ ውጤት ለማምጣት ተጨማሪ የ210 ሚሊየን ዩሮ ድጋፍ እንደሚደረግ ተገልፆ ነበር፡፡ በወቅቱም በአገሪቱ በየዓመቱ ገበያውን የሚቀላቀሉ ሁለት ሚሊየን ብቁ ያልሆኑ ዜጎች መሆናቸው በኢትዮጵያ የተለያዩ አገራት አምባሳደሮች በተገኙበት መድረክ ተገልፆ ነበር፡፡
ዘርፉ ከግብርና ወደ ኢንደስትሪ የሚደረገው ሽግግር በቴክኖሎጂ በመደገፍ ትልቅ ድርሻ የሚወጣ ቢሆንም በአንድ በኩል የሰልጣኞች ብቁ አለመሆን በሌላ በኩል ደግሞ በአመለካከት የሚስተዋሉ ክፍተቶች ጎታች ማነቆ ሆኖ ቆይቷል፡፡ አገሪቱም ይህን ችግር ለማቃለል በምታደርገው ጥረት የጀርመን መንግስት የተለመደ ድጋፉን እንደሚያጠናክር ይገልፃል፡፡ በቅርቡም በኢትዮጵያ መዲና አዲስ አበባ ለይፋዊ የስራ ጉብኝት የገቡት የጀርመኑ ፕሬዚዳንት ፍራንክ ቫልተር ሽታይንማየር ኢንስቲትዩቱን በተመለከቱበት ወቅት መናገራቸው ይታወሳል፡፡
በሁለቱ አገራት ግንኙነት በተደረጉ የዕውቀት ሽግግርና የገንዘብ ድጋፎች በኢንስቲትዩቱ ለውጥ አምጥቶ መመልከታቸው ድጋፉ ትክክለኛ ቦታ ላይ መዋሉን እንደሚያረጋግጡትም ተናግረው ነበር፡፡ በመሆኑም ለጀርመን የኢኮኖሚ ጥንካሬ ትልቅ መሠረት ሆኖ የሚነሳው ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ዘርፍ ያካበተውን ልምድ ለአገሪቱ ለማካፈል መንግስታቸው እንደሚሰራም ያረጋግጣሉ፡፡
ኢንስቲትዩቱ
የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ኢንስቲትዩት ከተመሰረተበት ዓመት ጀምሮ በየጊዜው የቅበላ አቅሙን እያሳደገ መምጣት ችሏል፡፡ በአሁኑ ወቅት ዋናው ጊቢን ጨምሮ በክልሎች በሚገኙ ሳተላይት ካምፓሶች ከ9 ሺህ 200 በላይ ተማሪዎችን በተለያዩ የትምህርት ክፍሎች ያስተምራል፡፡ በዋናነት ትኩረቱ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና መምህራንና አመራሮችን ማፍራት የሆነው ይህ ብቸኛ ተቋም፤ ለሁሉም ክልሎችና ለሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና መምህራኖችን በመጀመሪያና በሁለተኛ ዲግሪ ያሰለጥናል፡፡
በአሁኑ ወቅት በመጀመሪያ ዲግሪ በ22 የትምህርት ክፍሎችና በሁለተኛ ዲግሪ ደግሞ በስምንት የትምህርት ክፍሎች ስልጠና የሚሰጥ ሲሆን፤ ኢንስቲትዩቱ የቴክኒክና ሙያ አመራርን በሁለተኛ ዲግሪ እንዲሁም አጫጭር ሥልጠናዎችንም በመስጠት አቅም መገንባት ላይ ትኩረቱን አድርጎ ይሰራል፡፡ በየጊዜው አቅሙን በማሳደግ የተለያዩ ፕሮግራሞችን እየከፈተ እየሰራም ነው፡፡ በዚህም አገሪቱ እያደገች በመሆኗ በሁሉም ኢንደስትሪ ዘርፎች፣ የግንባታ፣ የግብርናና የአግሮ ፕሮሰሲንግ ዘርፎች ዜጎችን በማሰልጠን ለገበያው ያቀርባል፡፡
ዋና ዳይሬክተሩ፤ የጀርመን መንግስት ኢንስቲቲዩቱን ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ዘርፍ ሲደግፍ ረዘም ያለ ጊዜን ማስቆጠሩ ይታወሳል፡፡ ኢንስቲትዩቱም ከተቋቋመበት 2003 ዓ.ም ጀምሮ በርካታ ድጋፎቹን አግኝቷል፡፡ በዚህም በገንዘብ ቢተመን ከ60 ሚሊየን ዩሮ በላይ ድጋፍ ያገኘ ሲሆን፤ ይህም በስልጠና ጥራቱ ላይ ውጤት እንዳስገኘ በዕለት ተዕለት ተግባር ላይ ይታያል፡፡
ዋነኛ ትኩረቱ አቅም ግንባታ የሆነው ድጋፉ ከሚያደርገው አስፈላጊ ግብዓቶች ድጋፍ ጎን ለጎን ሌላኛው የትኩረት አቅጣጫው የሰው ኃይል ማብቃት ነው፡፡ በዚህም የአመራርና የመምህራን አቅም ግንባታ ትኩረቱን አድርጎ ይሰራል፡፡ በዚህም የመምህራኑን ዕውቀትና ክህሎት ለማዳበር የተለያዩ ስልጠናዎችን የመስጠት፣ ዓለም አቀፍ ተሞክሮን የመቀመር እንዲሁም ስርዓት መዘርጋት አቅም ግንባታውን ለማሳካት የሚያከናውናቸው ዋና ዋና ተግባራት ናቸው፡፡
የአቅም ግንባታ ሥራው የሚመራው በጀርመኑ ድርጅት ጂአይዜድ ሲሆን፤ የግብዓት ድጋፉ ደግሞ ኬኤፍደብሊው በሚባለው የጀርመን ኢንቨስትመንት ባንክ የሚደረግ ነው፡፡ ባንኩ በርካታ ሚሊየን ዩሮ የሚገመት መሳሪያዎችን፣ አስፈላጊ ግብዓቶችንና ተሽከርካሪዎችን ላለፉት ዓመታት ዘርፉን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሳደግ ሲደግፍ ቆይቷል፡፡ በዚህም ተቋሙ በአውሮፓ ደረጃ መሳሪያዎች የተሟላለት ተቋም እንዲሆን አስችሎታል፡፡ ባለፈው ሳምንት የጀርመኑ ፕሬዚደንት በአገሪቱ በነበራቸው ቆይታም ከጠቅላይ ሚኒስትርና ፕሬዚዳንት ጋር መምከራቸውም ቀድሞ የነበረውን ትስስር የበለጠ የሚያጠናክር ይሆናል፡፡
ምን ይስተካከል?
ዘርፉ ከ10 ዓመት በፊት በጣም ጥቂት በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ብቻ የሚሰለጥኑበት ጥቂት ኮሌጆች የነበሩበት ቢሆንም በአሁኑ ወቅት ግን በመንግስት ደረጃ ብቻ ከ600 በላይ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ተቋማት ይገኛሉ፡፡ በተቋማቱም ከ400 ሺህ በላይ መደበኛ ሰልጣኞችና 800 ሺህ የሚጠጉ በዓመት ውስጥ አጫጭር ስልጠና የሚወስዱ ሰልጣኞች አሉ፡፡ ይህም ስርዓቱ ኪዜ ወደ ጊዜ ገጽታው እየተሻሻለ ዜጎችም ተጠቃሚ እየሆኑ መምጣቸውን ማሳያ ይሆናል፡፡ ይሁን እንጂ አሁንም ቢሆን ችግሩ በሚፈለገው ደረጃ ተቃሏል ማለት አይቻልም፡፡
ዘርፉ የወደቁ ተማሪዎችን መሰብሰቢያ እንደሆነ ተደርጎ መታሰቡ የሚጠበቅበትን ውጤት እንዳያስመዘግብ ጎታች ከሆኑ ምክንያቶች ውስጥ አንዱና ዋነኛው ተደርጎ ይነሳል፡፡ ሁለተኛ ደረጃ ከሚጨርሱ ተማሪዎች በፖሊሲ ደረጃ በተቀመጠው መሠረት 80 በመቶ የሚሆኑት ወደ ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ስርዓት የሚገቡ ሲሆን፤ ቀሪዎቹ 20 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ወደ ዩኒቨርሲቲ ይገባሉ፡፡ በዚህም አብዛኞቹ በዚህ ስርዓት የሚያልፉ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ብዙ ሥራን እንደሚጠይቅ ያመላክታል፡፡
ለችግሮች ቀጣይ የቤት ሥራ
አመለካከት ተከታታይ ሥራን የሚጠይቅ በመሆኑ በአሁኑ ወቅትም ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና እንደ ሁለተኛ አማራጭ መታየቱ እየተቀረፈ አይደለም፡፡ ምንም እንኳ እያደገና እየተሻሻለ የመጣ ምቹ ሁኔታ እንዳለ ባይካድም የብዙ ጊዜ ሥራ የሚጠይቁ ያልተቀረፉ የቤት ሥራዎች እንዳሉ ግን መገንዘብ ግን ይገባል፡፡
ዘርፉ ገጽታውን ለመገንባት የሚሰጠው ስልጠና ጥራቱ የተጠበቀ መሆን ይኖርበታል፡፡ ሰልጣኞቹም ቆይታቸውን ጨርሰው ወደ ገበያ ሲወጡ ተፈላጊና ሥራ ላይ የሚሰማሩ መሆን አለባቸው፡፡ ለዚህም የምሩቃኑን በጭንቅላት ብቻ ሳይሆን ዝቅ ብለው ብረት ቆርጠውና እጃቸውን አቆሽሸው የመሥራት ጅማሮ አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል፡፡ ኢንስቲትዩቱም በዚህ ላይ በትኩረት እየሰራ ይገኛል፡፡ በዚህም እንደ ትልቅ ክፍተት የሚነሳው ከኢንደስትሪዎች ጋር ያለ ግንኙነት መላላትና ተቀናጅቶ አለመሥራት ችግር ለማቃለል ይሰራል፡፡
በአገር በሚፈለገው ደረጃ ያልጠነከረው ይህን ወሳኝ ግንኙነት አጠናክሮ ለማስኬድ ኢንስቲትዩቱ በየዓመቱ የኢንደስትሪ ፎረሞችን በማዘጋጀት ውይይት ያደርጋል፡፡ በአሁኑ ወቅትም 43 በላይ ኢንደስትሪዎች ጋር መግባባት በመፍጠር በቅንጅት ይሰራል፡፡ በዚህም ተማሪዎች በኢንደስትሪዎች እንዲሰለጥኑና በኢንስቲትዩቱ ውስጥ የሚሰሩ የተለያዩ ቴክኖሎጂዎች ሽግግርም ይደረጋል፡፡ መምህራኖቹንም ወደ ኢንደስትሪዎች በመውሰድ ተግባራዊ ስልጠና እንዲያገኙ ይሰራል፡፡ ሥራው በሚፈለገው ደረጃ ባለመድረሱም ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመሆን የኢንደስትሪ ንቅናቄ ይደረጋል፡፡ በተያያዘም በቀጣይ ኢንደስትሪዎች በሙሉ እንዲመጡና ዘርፉን እንዲደግፉ ለማድረግ የሚሰራው ሥራ ይቀጥላል፡፡
ቴክኒክና ሙያ በጀርመን አገር የመጀመሪያ ምርጫ መሆኑን በማንሳት ይህንን በአገሪቱ ለማምጣት እየተሰራ ነው፡፡ ለዚህም ከዕውቀትና ክህሎቱ በላይ ትልቁን ድርሻ የሚወስደውና ለችግሮች ምንጭ የሆነው የአመለካከት ክፍተቱን ለመሙላት በትኩረት ይሰራበታል፡፡ ኢንስቲትዩቱ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና መምህራንና አመራሮችን የሚያፈራ በመሆኑም በዘርፉ የሚስተዋሉ የአመለካከት ክፍተቶችን ለማቃለል በዋናነት ገጽታውን ለመገንባት የሚያስችሉ ሥራዎችን ለመተግበር አቅዷል፡፡
ዘርፉ የተቀዳበት የጀርመንን ስርዓት ባለሙያ የሚከበርበት ብሎም እያንዳንዱ ሰው በሙያው የሚኮራበት ነው፡፡ ስለሆነም ኢንስቲትዩቱ በዋናነት መምህራንና አመራሮችን የሚያሰለጥን ከመሆኑ ጋር ተያይዞ አመለካከት ቀረፃው በሰፊው በመሥራት ሥራን የማይንቁና በሙያቸው የሚኮሩ ዜጎች እንዲኖሩ ይሰራል፡፡ ሥራውም የተለያዩ አካላት ርብርብ የሚጠይቅ በመሆኑም እያንዳንዱ ዜጋ፣ የትምህርት ተቋማትና ድርጅቶች እንዲሁም መገናኛ ብዙሃን ሁሉ የራሳቸውን ድርሻ ሊወጡ ይገባል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 27/2011
በፍዮሪ ተወልደ