I. መግቢያ
አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከለውጡ በኋላ በአዲስ አመራር መመራት ከጀመረች እነሆ አራት ወራት ተቆጥረዋል ። እነዚህ ወራት በነባሩ አመራር የተጀመሩ የልማት ስራዎች እንዲቀጥሉ የተደረገበት፤ በከተማዋ ህግና ስርዓት እንዲከበር የሚያደርጉ የስራ መመሪያዎች የተላለፉበት፤ ለረጅም ዓመታት ሲጓተቱና ሲደራረቡ ከመጡ የነዋሪው ጥያቄዎች መካከል አንዳንዶቹ ፈጣን ውሳኔ እንዲያገኙ የተደረጉበት ወራት ነበሩ፡፡
በተለይ በአዲስ ዓመት «አዲስ አበባን በአዲስ ተስፋ ብርሃን!!!» የሚል መረሃ ግብር በየደረጃው ከነዋሪው ጋር ያደረግናቸው ውይይቶች ህብረተሰቡ በሰፊው የሚያነሳቸውን ጥያቄዎች መነሻ በማድረግ ለምላሻቸው የአጭር ግዜ ልዩ እቅድ በማውጣት ወደ ስራ እንድንገባ አድርጎናል ።ከነዚህም መካከል በአጭር ግዜ ልንፈታቸው የቻልናቸው እና ያከናወናቸው፡-
- በከተማ ነዋሪውን የትራንስፖርት ችግር ለመቅረፍ 560 የግል ማህበራት አውቶብሶች በኪራይ ወደ ስምሪት እንደሚገቡ መደረጉ፤
- ከጋራ የመኖሪያ ቤት እጣ አወጣጥና አረካከብ ጋር ተያይዞ የነበሩ ችግሮችን በመለየት 74,144 የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ቁልፍ፣ ውልና ካርታ ለእድለኞችና የልማት ተነሺ አርሶ አደሮች አስረክበናል ። ይኸውም ለ13ኛ ዙር 51 ሺህ 229 የጋራ መኖሪያ ቤት እድለኞች እና 22 ሺህ 915 የልማት ተነሺ አርሶ አደሮች ካርታ፣ ቁልፍ እና ውል ርክክብ ዘግይቶ የቆየ በመሆኑ አፋጣኝ መፍትሄ በመስጠት የተፈታ መሆኑ፤
- በስራ እድል ፈጠራ በኩል የከተማ አስተዳደሩ 200 ሚሊየን ብር በጀት በመመደብ 28ሺህ ወጣቶችና ሴቶች የአረንጓዴ ልማት እና የአካባቢ ጥበቃ ፤ የመንገድ ዳር አካፋዮችንና ፓርኮችን የማስዋብ ስራ ላይ እንዲሰማሩ አሰልጥኖ ወደ ስራ ማስገባት፤
- በአዲስ አበባ ከተማ በሶስት አካባቢዎች የተገነቡ ዘመናዊ እና ሁለገብ የአትክልት፣ የፍራፍሬ እና የሰብል ምርቶች መገበያያ ማዕከላት የላፍቶ አትክልትና ፍሬፍሬ የገበያ ማዕከል በአንድ ቢሊዮን ብር ወጪ በአንድ ወር ግዜ ተገንብቶና ፣ ጀሞ ሁለገብ የገበያ ማዕከል እና ፉሪ ሁለገብ የሴቶች የገበያ ማዕከል መለስተኛ እድሳት ተደርጎላቸው ስራ እንዲጀምሩ መደረጉ።
- በተያዘው በጀት ዓመትም ከ280 ኪሎ ሜትር በላይ አዳዲሰ የመንገድ ግንባታዎች ከ6.8 ቢሊዮን ብር በጀት መጀመሩ፤
- የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለሥልጣን በተያዘው በጀት ዓመት በ2 ቢሊዮን ብር ወጪ 55 ጥልቅ የውሃ ጉድጓድ በማልማት አንድ መቶ ሺህ ሜ.ኪዩብ ውሃ ለማምረት እየሰራ መሆኑ፤
- በመንግስት ሆስፒታሎች የኩላሊት እጥበት እያደረጉ ላሉ ሕመምተኞች ዓመቱን ሙሉ ነጻ የዲያሌሲስ ወጪ በከተማ አስተዳደሩ እንደሚሸፈን መደረጉ፤
- ኢትዮጵያ የልብ ህሙማን ህፃናት መርጃ ማዕከል ለታካሚ ህፃናት እና ቤተሰቦች ስቃይን ለመቀነስ በነፃ አገልግሎት እየሰጠ ያለውን የበጎ አድራጎት ስራ በዘላቂነት ለመደገፍ ያስችል ዘንድ የታክስ የዕዳ ምህረትና ከኪራይ ገቢ ግብር ነፃ እንዲደረግ መሆኑ።
- በከተማዋ ለሚገኙ ዝቅተኛ የተማሪዎች የምገባ ስራ ላይ ለተሰማሩ እናቶች የአንድ ዓመት የገቢ ግብር ወጪን የዕዳ ምህረት እንዲደረግም ውሳኔ ማስተላለፉ፤ ለአብነት ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡
በተጨማሪም በጥቅምት 10 ቀን 2013 ዓ.ም የአዲስ አበባ ምክር ቤት ባካሄደው 8ተኛ ዓመት 1ኛ መደበኛ ጉባኤ እና በፓርቲው በጥቅምት 23 ባካሄደው የአመራር ኮንፍረንስ ሃገራዊ ለውጡን አጠናክሮ ለማስቀጠል በየደረጃው ያሉ አመራሮች ከኔትዎርክ፤ ከሌብነትና ከብልሹ አሰራር የፀዳ ለማድረግ ቁርጠኛ ውሳኔ የወሰነ መሆኑንና ጠንካራ ፓርቲና የመንግስት መዋቅር በመዘርጋት መጣራትና መስተካከል ያለባቸውን ጉዳዮች ቅድሚያ ሰቶ እንደሚያጣራ ለዚህም ነዋሪው በግንባር ቀደምትነት እንዲያግዝ ጥሪ ማቅረባችን ይታወሳል፡፡
በዚሁ መሰረት በመንግስት አገልግሎት አሠጣጥ ችግሮች መካከል የመሬት አስተዳደር እና ቤትና መሬት ነክ ጉዳዮች የከተማችን ዋነኛ የህዝብ ቅሬታ ምንጭ ሆነው በመገኘታቸው ቅድሚያ ሰጥቶ መጣራት አስፈላጊ በመሆኑ እቅድ በማውጣት ሊሰራ ተችሏል፡፡
በመሆኑም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከመሬት ወረራና ህገ-ወጥ ግንባታ፤ ባለቤት አልባ ህንጻዎች፤ ከኮንደሚኒየም ቤቶች እና የቀበሌ ቤቶች ጋር በተያያዘ በከተማችን ያሉ ህገ- ወጥነትን በተመለከተ ዝርዝር ጥናት እንዲጠና መደረጉንና የማጣራት ስራዎች መጠናቀቃቸው ተገልጿል ።ሆኖም ግን ከተለያዩ አካላት የሚነሱ ብዥታዎችን ለማጥራት እና አካሄዱን እና ውጤቱን አስመልክቶ ዝርዝር መረጃ ለመስጠት ይሄ ፅሁፍ ተዘጋጅቷል፡፡
የዚህ ማጣራት ዋነኛ አላማ እየተነሱ ያሉ ችግሮችን ፊት ለፊት መጋፈጥ አስፈላጊ በመሆኑ እና በማጣራት ሂደቱ ከሚገኙ ውጤቶች በመነሳት ሊስተካከሉ የሚገባቸው አሰራሮችን ለማስተካከል፤ እንዲሁም እርምጃ የሚወሰድባቸውን አስተዳደራዊ፤ ፖለቲካዊና ህጋዊ እርምጃ በቁርጠኝነት በመውሰድ የነዋሪውን ጥያቄ ለመመለስ ያለመ ነው፡፡
በአጠቃላይ በከተማችን ከመሬት ወረራና ህገወጥ ግንባታ እንዲሁም ባለቤት አልባ ህንፃዎች ጋር በተያያዘ ያሉ ችግሮች በርካታ ዓመታትን ያስቆጠሩና ምቹ የሆነ አጋጣሚን በመጠበቅ ሲፈፀም የቆየ ተግባር ነው ። ይህ ህገወጥ ተግባር በከተማችን ስርአት አልበኝነት እንዲስፋፋ ከማድረጉም ባሻገር በነዋሪው ዘንድ ከፍተኛ ቅሬታ በማሳደር በመንግስት ላይ መተማመንን እንዲያጣ ካደረጉ ምክንያቶች ዋነኛው ነው፡፡
ስለሆነም የከተማ አስተዳደሩ ለዚህ ችግር መፍትሄ በጥናት ላይ መሰረት ለማድረግ የመጀመሪያ እርምጃው ከከተማ አስተዳደር እና ከፌዴራል መንግስት መዋቅር የሚመለከታቸው አካላትና በጉዳዩ ዙርያ ድጋፍ ሊያደርጉ የሚችሉ አካላት የተውጣጣ አንድ ግብረ ሃይል ማቋቋም ሲሆን ይህ ግብረ ሃይል እቅድ በማውጣት በ10ሩም ክ/ከተሞች በእያንዳንዱ 12 አባላት በድምሩ 120 የሰው ሀይል ያለው ግብረ ሃይል ተደራጅቶ እስከ ብሎክ አደረጃጀት ግብረ ሃይሉ እንዲዘረጋ እንዲሁም ህዝቡ በሰፊው እንዲሳተፍ ተደርጓል፡፡
በዚህ ግብረ-ሃይል፡-
– ከአዲስ አበባ ከተማ፡- ከመሬት ተቋም፣ ከአቃቢ ህግ፣ ከሰላምና ፀጥታ፣ ከህዝብ ቅሬታና አቤቱታ፣ ከፖሊስና ከከንቲባ ፅ/ቤት አመራሮችና ባለሙያዎች የተካተቱ ሲሆን፡-
– ከፌደራል ተቋማት ደግሞ፡- ከፌደራል ፖሊስ፣ ከስራና ከተማ ልማት ሚኒስቴር የግብረ ሃይሉ አባላት በመሆን ስራው እንዲሰራ ተደርጓል፡፡
በየደረጃው ያለው ግብረ ሃይል ባቀደው መሰረት የተለያዩ ጥቆማዎችን በመያዝ በአንድ በኩል በየክ/ከተማው የህገ ወጥ የተባሉትን እንዲለይ የተደረገ ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ በከተማ አስተዳደሩ በህጋዊ አሰራሩ የግንባታ ፈቃድ ሳይወስዱ የተገነቡ የተለያዩ ግንባታዎችን በዝርዝር በመለየት እንዲሁም እስከ ብሎክ ድረስ ያለውን የፓርቲ መዋቅራችንን በመጠቀም ባለቤት አልባ የሆኑ ቤቶችን የመለየት ስራ በመስራትና ቤቶቹና ግንባታዎቹ በተከናወኑበት ቦታ ላይ ማስታወቂያ በመለጠፍ የግንባታው ባለቤት የሆነ አካል ማስረጃዎቹን እንዲያቀርብ በማድረግና ከዚሁ ውስጥ ባለቤት ያልቀረበባቸውን ህንፃዎች ላይ ተጨማሪ የማጥራት ስራ የመሬት አስተዳደር ፋይልንና የቤዝማፕ መረጃን በመጠቀም በዝርዝር እንዲለዩ ተደርጓል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ለከንቲባ ፅ/ቤትና ለክብርት ከንቲባ በቀጥታ በተለያየ መልኩ የቀረቡ ጥቆማዎችንም የተለያዩ ኮሚቴዎችን በማደራጀት ከቀረቡት ጥቆማዎች ውስጥ ባለቤት አልባ የሆኑ ህንፃዎችና ቤቶችን የመለየት ስራ ተሰርቷል፡፡
የኮንደሚኒየም ቤቶችን በዝርዝር የማጥራት ስራ በኮተቤ ዩኒቨርሲቲ አማካኝነት በዝርዝር እንዲጠና የተደረገ ሲሆን የጥናት ስራው በአራት መንገዶች መረጃዎቹ እንዲጣሩ የተደረገ ሲሆን፣ በዚህም በከተማችን ቤቶች ኮርፖሬሽን ላይ ያለን መረጃ፣ በዕጣ የተላለፉ ቤቶች ዝርዝር፣ ከባንክ ጋር ውለታ የተፈፀመበት መረጃና በመስክ የተገኘን መረጃ ማዕከል በማድረግ ዝርዝር መረጃውን የመተንተን ስራ ተሰርቷል፡፡
የቀበሌ መኖሪያና ንግድ ቤቶች ቆጠራና ኦዲታዊ ጥናትን አስመልክቶ ከህብረተሰቡ የደረሱ ጥቆማዎችን ለማጣራት ከየወረዳ ቤቶች ልማት ጽ/ቤቶች የተገኘ መረጃን መሰረት በማድረግ ማጣራት ተችሏል፡፡
II. አጠቃላይ ግኝቶች በዝርዝር
1. የመሬት ወረራን አስመልክቶ
በአጠቃላይ በከተማችን 13,389,955 ካሬ ወይም 1,338 ሄክታር መሬት በህገወጦች ተይዟል።
- ይኸውም በከተማችን ካሉ 121 ወረዳዎች ውስጥ በ88ቱ ወይም 73% በሚሆኑት ላይ ወረራው ተፈፅሟል፡፡
- በከተማችን የተፈፀመው የመሬት ወረራ የከረመ ታሪክ ያለውና በየጊዜው እየተደራረበ የመጣ ህገወጥ ድርጊት ነው፣ በዚህ ጥናት ላይ እንደተመላከተው ከ1997 ጀምሮ በከተማችን በተለያየ አግባብ ህገወጥ የመሬት ወረራው ሲፈፀም የነበረ ነው፡፡
- በ2010 ሀገራዊ ለውጥ ከመምጣቱ በፊት ሰፋ ባለ መልኩ የመሬት ወረራው የነበረና ከለውጡ በኋላም አጠቃላይ አመራሩ ህገ ወጥነትን በተገቢው ባለመከላከሉ ችግሩ እንዲደራረብ አድርጎታል፡፡
2. ባለቤት አልባ ቤቶችና ህንፃዎችን በተመለከተ
በአጠቃላይ ሲታይ ባለቤት አልባ በሚል የተለዩት ቤቶችና ህንፃዎች በድምሩ 322 ሲሆኑ፣ የቦታ ስፋታቸው ደግሞ 229,556 ካሬ መሆኑ ተለይቷል፡፡
- ከነዚህ ባለቤት አልባ ሆነው ከተለዩት ቤቶችና ህንፃዎች መካከል ግንባታቸው የተጠናቀቁት 58 ሲሆኑ 125፣409 ካሬ ላይ ተገንብተውና ተከራይተው ያሉ ነገር ግን ባለቤት ነኝ የሚል አካል መረጃውን እንዲያቀርብ በተደጋጋሚ ቢጠየቁም ማቅረብ ባለመቻላቸው ባለቤት አልባ ሆነው አግኝተናቸዋል፡፡
- ግንባታቸው ያልተጠናቀቀ እንዲሁም ባለቤታቸው ያልታወቁ ህንፃዎች ብዛት በድምሩ 264 ሲሆን ስፋታቸው ደግሞ 104,147 ካሬ ላይ ያረፉ ቤቶችና ህንፃዎች ናቸው፡፡
- እነዚህ ቤቶች በተለይ በየካና በላፍቶ ክ/ከተሞች ላይ በአንድ አካባቢ መሬት በመውረር ግንባታ የተገነባባቸው ናቸው፡፡
2.1. በከተማችን ህገወጥ የመሬት ወረራ ባህሪያትና በአጠቃላይ የመሬት ወረራና ህገወጥ ድርጊቶች በሶስት ዋና ዋና መንገዶች የተፈፀመ ነው፡-
- በህገወጥ መንገድ ባዶ የሆነ የመንግስትን መሬት በወረራ በመያዝ የተፈፀመ፣ ይህ ድርጊት በግለሰብ ደረጃና በሃይማኖት ተቋማትም ጭምር የተፈፀመ መሆኑ፣
- በህገወጥ መልኩ የመንግስትና የህዝብን መሬት በቡድን በመሄድና መንደር በመመስረት የሚገለፅ፣
- በህገወጥ መልኩ ይዞታን በማስፋፋት የመንግስትን መሬት በመውረር የሚገለፅ ሲሆን፣ ከዚህ አንፃር በግለሰቦችና በሪል ስቴት አልሚዎች የተፈፀመ ህገወጥ ድርጊት ነው ።
- በከተማችን ሲፈፀም የነበረው የመሬት ወረራና ህገወጥ ድርጊቶች በተለያየ ጊዜ ሲፈፀሙ የነበሩ ከመሆኑም ባሻገር ህገወጥ ድርጊቶቹ ሲፈፀሙ የነበረው፡-
- አጠቃላይ የመሬት ማኔጅመንት አሰራሮችን በመጣስ
- ጥገኛ ባለሀብቱና የመንግስት አመራሩ መሀከል በነበረ የጥቅም ትስስር
- ህገወጥ የመሬት ድርጊቱን የሚያስፈፅሙ ደላሎች ከመንግስት አመራሮች ጋር ኔትወርክ በመፍጠር የሚፈፀም የነበረ መሆኑ
- መንግስት ወደ አስተዳደራዊና ህጋዊ እርምጃ እንዳይገባ ደግሞ የህግ ማስከበር ስራውን ከብሄር ጋር በማገናኘት የተወሰነ ብሄርና ህዝብ እየተጠቃ እንደሆነ የተለያዩ የሚዲያና የመንግስት አሰራራችንን ተጠቅሞ በማስጮህ የመንግስትን እጅ ለመጠምዘዝ መሞከር
- በሌብነትና ዝርፊያ ውስጥ የነበረው ሀይል ራሱን ለመሸፈንና ለመከላከል ህዝቡንና የተወሰነ ብሄርን ለመሸፈኛነት የመጠቀም ሁኔታ ዋና ዋና ማሳያዎች ናቸው፡፡
- በከተማ አስተዳደሩ የተለያዩ ተቋማት የእርስ በርስ ቅንጅትና ትብብር ባለመኖሩ የተነሳ ችግሩ የሰፋ መሆኑ(ለማሳያ ያህል፣ የመሬት ተቋማት ከአካባቢ ጥበቃ፣ ከፀጥታ መዋቅሩ ጋር እንዲሁም ከውሀና መብራት ሀይል መስሪያ ቤቶች ጋር ያለመናበብ ችግር የመሬት ወረራ ድርጊቱ እንዲባባስ አድርጎታል)
2.2. ከመሬት ወረራው አፈፃፀም ዋና ዋና መገለጫዎች
- የሪል ስቴት አልሚዎች በህጋዊ መንገድ ከተሰጣቸው ቦታ ውጪ ሰፋ ያለ ቦታ በህገወጥ መንገድ አስፋፍተው መያዝ፣
- በሪል ስቴት ስም አነስተኛ መሬት በመውሰድ የግለሰብ ቤት በመገንባት የመጠቀም ሁኔታ፣
- መሬት ባንክ የገባ መሬት አለአግባብ በህገወጥ መንገድ ጥቅም ላይ እንዲውል ማድረግ፣
- ለአካባቢ ጥበቃ የተለዩ ቦታዎችን በህገወጥ መንገድ ወሮ በመያዝ ግንባታ ማከናወን፣
- ሰፋ ባለ መልኩ መንደር በመመስረት መልኩ በተወሰኑ ቦታዎች ላይ፣
- በግለሰብ ደረጃ መሬት መውረርና ከህጋዊ ይዞታ ውጪ ቦታ አስፋፍቶ መያዝ፣
- የማህበር ቦታዎች የሆኑትን በህገወጥ መንገድ መያዝና ለግለሰቦች መጠቀሚያ ማድረግ፣
- የሀይማኖት ተቋማት በህገወጥ መንገድ መሬት በመውረር ቤተ ዕምነት መገንባት፣
- ለጥቃቅንና አነስተኛ የተያዙ ቦታዎችን ለግለሰብ እንዲተላለፉ ማድረግ፣
- ለተለያዩ የኮንስትራክሽን ስራዎች በጊዜያዊነት የተሰጡ ቦታዎችን ህገወጥ በሆነ አግባብ ለመደበኛ ግንባታ ማዋል፣
- በከተማ ግብርና ስም መሬት በህገወጥ መንገድ መያዝ፣
- በልማትና በተለያዩ ምክኒያቶች ምትክ ቦታ ወስደው ካሳ የተከፈለበትን ቦታ ባለማስረከብ የመጠቀም ሁኔታ፣
- የመሬት ይዞታ አጠቃቀምን አለአግባብ በመቀየር መሬት እንዲተላለፍ ማድረግ፣
- በመንግስት ተቋማት የተያዙ ይዞታዎች ላይ ግለሰቦች የተለያየ ግንባታ በማካሄድ የመጠቀም ሁኔታ፣
- ለአረንጓዴ ቦታ ልማት በሚል በጊዜያዊነት ቦታ በመያዝ በህገወጥ መንገድ ቋሚ ግንባታ ማካሄድና የይዞታ ማረጋገጫ ለማውጣት ጅምር እንቅስቃሴዎች መታየታቸው፣
- በኮንደሚኒየም ቤቶች አካባቢ ለነዋሪው የተለዩ የጋራ መጠቀሚያ ቦታዎችን አለአግባብ መያዝ፡፡
3. የኮንደሚኒየም ቤቶችን በተመለከተ
በከተማችን ባለፉት ዓመታት የተገነቡ የኮንደሚኒየም ቤቶችን ያሉበትን ሁኔታና በዋናነት ደግሞ የቤቶቹ ተጠቃሚ የሆኑ ግለሰቦች ህግና ስርዓቱን በጠበቀ መንገድ ቤቶቹን እንደያዙና በዚህም ጋር በተያያዘ ያሉ ስርአት አልበኝነትና የተፈፀሙ ህገወጥ ድርጊቶችን በተገቢው መልኩ መለየት እንዲቻል በአጠቃላይ የቤት ማስተላለፍ ሂደት ችግሮችንና ተያያዥ ህገ-ወጥ ተግባራትን ለማጣራት የከተማ አስተዳደሩ በመወሰኑ በኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ አማካኝነት በሳይንሳዊ አግባብ ዝርዝር ጥናት እንዲጠና አቅጣጫ ተቀምጦ ላለፉት ሁለት ወራት ሲሰራ ቆይቷል፡፡
የቀረበውን መረጃ መነሻ በማድረግ በጥናት ስራው ላይ በአራት መንገዶች መረጃዎቹን የማጥራት ስራው ተሰርቷል ።በዚህም በከተማችን ቤቶች ኮርፖሬሽን ላይ ያለን መረጃ፣ በዕጣ የተላለፉ ቤቶች ዝርዝር፣ ከባንክ ጋር ውለታ የተፈፀመበት መረጃና በመስክ የተገኘን መረጃ ማዕከል በማድረግ ዝርዝር መረጃውን የመተንተን ስራ ተሰርቶ ተጠናቋል።
በጥናቱ ውጤት መሰረትም በህገ ወጥ መንገድ የተያዙ የጋራ መኖሪያ ቤቶች በጠቅላላው 21,695 ሲሆኑ 15,891 የጋራ መኖሪያ ቤቶች መረጃ ያልቀረበባቸው፣ 4530 ባዶ የሆኑ፤ 850 ዝግ የሆኑ፤ እና 424 በህገወጥ መልኩ በግለሰቦች ተይዘው የሚገኙ ሲሆን በዕጣ ሳይሆን በተለያዩ አግባቦች ወደ ተጠቃሚው ግለሰቦች የተላለፉ ደግሞ 51,064 ቤቶች ሆነው ተገኝተዋል፡፡
በተጨማሪም በቤቶች ኮርፖሬሽን ተመዝግቦ የሚገኘው ባለዕጣዎች የስም ዝርዝር እና በመስክ በተገኘው የተጠቃሚዎች የስም ዝርዝር መሀከል ልዩነት ያላቸው ቤቶች 132,678 እንደሆኑና 18,423 ቤቶች ደግሞ የቤት ባለቤት ስም የሌላቸው መሆኑን በጥናቱ ተለይቷል፡፡
በነዚህ ቤቶች ውስጥ የሚኖሩ ግለሰቦች መረጃቸውን እንዲያቀርቡ በተደጋጋሚ ቢጠየቁም መረጃ ማቅረብ ያልቻሉ ወይም ያልፈለጉ በመሆናቸው ቤቶቹ በህገ ወጥ መንገድ የተያዙ መሆናቸውም በጥናቱ ተለይቷል ፡፡
ያልተገነቡ የጋራ መኖሪያ ቤቶችና የጋራ መጠቀሚያ ህንፃዎች ሁኔታ በተመለከተ 28 ብሎክ ማለትም ከ782 እስከ 842 የሚሆኑ ቤቶች እና የጋራ መጠቀሚያ ህንፃዎች /ኮሚናል/ ደግሞ 83 ሳይገነቡ መቅረታቸውን ጥናቱ ማመላከቱ ተገልጿል፡፡
በፌደራልና በአዲስ አበባ ዋና ኦዲተር መ/ቤቶች በተሰራው የኦዲት ውጤት መሰረትም በአጠቃላይ ላልተገነቡ ህንፃዎች የቦርድም ሆነ የስራ አመራር የውሳኔ ቃለ ጉባኤ አልተገኘም ። ምንም እንኳን መረጃ ባይገኝም ለግንባታው ክፍያ አልተከፈለም ብሎ መደምደም እንደሚያስቸግር በኦዲት ጥናቱ ላይ ተመላክቷል፡፡
4. የቀበሌ ቤቶችን በተመለከተ
ከየወረዳ ቤቶች ልማት ጽ/ቤቶች በተገኘ መረጃ መሰረት አጠቃላይ በከተማ አስተዳደሩ ስር የሚተዳደሩ 150,737 የቀበሌ መኖሪያ እና ንግድ ቤቶች አሉ ። በዚህ ጥናት ተደራሽ መሆን የቻሉት 138,652 የመኖሪያ እና የንግድ ቤቶች ናቸው፡፡
4.1. የቀበሌ ቤቶችን በተመለከተ
በከተማችን 10,565 የቀበሌ ቤቶች በቁልፍ ግዥ፣ ሰብሮ በመግባት፣ እና በሌሎች ህጉ ከሚፈቅደው ውጪ በህገ-ወጥ መንገድ ተይዘዋል፡፡
በጥናቱ ተደራሽ ከተደረጉ የቀበሌ መኖሪያ ቤቶች ውስጥ፡-
- 7723 ቤቶች ውል በሌላቸው (ህገወጥ) በሆኑ ሰዎች ተይዘዋል፡፡
- 2207 የቀበሌ ቤቶች ወደግል የዞሩ፣
- 265 በሶስተኛ ወገን የተያዙ፣
- 164 ኮንደሚንየም በደረሳቸው/የራሳቸው ቤት ባላቸው ሰዎች የተያዙ የቀበሌ መኖሪያ ቤቶች መኖራቸው ነው፡፡
- 137 ለመኖሪያነት የሚያገለግሉ የቀበሌ ቤቶች በሽያጭ ወደ ግል የተላለፉ፤
- 1243 ታሽገው/ተዘግተው የተቀመጡ፣
- 5043 የፈረሱ፤
- 180 አድራሻቸው የማይታወቁ/የጠፉ የቀበሌ መኖሪያ ቤቶች እንዳሉ ተረጋግጧል፡፡
4.2. የቀበሌ ንግድ ቤቶችን በተመለከተ
በአጠቃላይ የንግድ ቤቶች ብዛታቸው 25,096 ሲሆን ከነዚህ ውስጥ በህገወጥ መንገድ የተያዙ የቀበሌ የንግድ ቤቶች ብዛት 4,076 ናቸው፣
- 1,070 የንግድ ቤቶች ውል የሌላቸው ነጋዴዎች እየተጠቀሙባቸው መሆኑ ተለይቷል፡፡
- 2,451 የቀበሌ የንግድ ቤቶች ከአንድ በላይ የንግድ ቤት በያዙ 1,086 ነጋዴዎች እንደተያዙ ተለይቷል፡፡
- 376 የቀበሌ ንግድ ቤቶች ደግሞ በተከራይ ተከራይ በሶስተኛ ወገን መያዛቸው ተለይቷል፣
- 179 የታሸጉ የንግድ ቤቶች እንዳሉም ለመለየት ተችሏል፡፡
III. አቅጣጫና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መልዕክት
በከተማችን አዲስ አበባ ከህገወጥ የመሬት ወረራና ባለቤት አልባ ቤቶች ጋር በተያያዘ ያሉ ችግሮችን በጥናት ላይ በተደገፈ መልኩ ለማጥራትና መፍትሄ ለመስጠት በተቀመጠው የበላይ አመራሩ አቅጣጫ መሰረት በሁሉም ክ/ከተሞች ላይ አጥሪ ኮሚቴ በማደራጀት አጠቃላይ ስራውን በዕቅድ ለመምራትና በየጊዜውም የበላይ አመራሩ የቅርብ ክትትል ተደርጎበት በጥራት የተሰራና የተጠናቀቀ ተግባር ነው፡፡
በከተማችን የተፈፀመው የመሬት ወረራ የከረመ ታሪክ ያለውና በየጊዜው እየተደራረበ የመጣ ህገወጥ ድርጊት ነው፣ በዚህ ጥናት ላይ እንደተመላከተው ከ1997 ጀምሮ በከተማችን በተለያየ አግባብ ህገወጥ የመሬት ወረራው ሲፈፀም የነበረ ሲሆን ሀገራዊ ለውጡ በ2010 ከመምጣቱ በፊት ሰፋ ባለ መልኩ የመሬት ወረራው የነበረ ሲሆን ከለውጡ በኋላም አጠቃላይ አመራሩ ህገወጥነትን በተገቢው ባለመከላከሉ ችግሩ እንዲደራረብ አድርጎታል፡፡
በከተማችን አዲስ አበባ ከህገወጥ የመሬት ወረራና ባለቤት አልባ ቤቶች ጋር በተያያዘ ያሉ ችግሮችን በጥናት ላይ በተደገፈ መልኩ ለማጥራትና መፍትሄ ለመስጠት በተቀመጠው የበላይ አመራሩ አቅጣጫ መሰረት በሁሉም ክ/ከተሞች ላይ አጥሪ ኮሚቴ በማደራጀት አጠቃላይ ስራውን በዕቅድ ለመምራትና በየጊዜውም የበላይ አመራሩ የቅርብ ክትትል ተደርጎበት በጥራት የተሰራና የተጠናቀቀ ተግባር ነው ። በድምር ውጤቱ ሲታይ አጠቃላይ ስራው በጥራትና በበላይ አመራሩ የቅርብ ክትትል መመራቱ ውጤታማ አድርጎታል፡፡
በህገወጥ መንገድ ከተወረሩት ቦታዎች ውስጥ ሰፋ ባለ መልኩ ህገወጥ መንደር የተመሰረተባቸውን አካባቢዎች ህገ ወጥ የመሬት ወረራውን የመቀልበስ ሂደት የሚያስከትለውን ማህበራዊ ቀውስ ግምት ውስጥ በማስገባት የቀጣይ ውይይትና አቅጣጫ ከፌደራል መንግስት ጋር የሚፈልግ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ በከተማችን ደረጃ ግን ዝርዝር የተመሰረቱት ህገወጥ መንደሮችን ሁኔታ ከመዋቅራችን ውጪ ባለ አካል ዝርዝር ጥናት እንዲጠና ለማድረግ የሚያስችል ዕቅድ ተዘጋጅቶ ወደ ተግባር ለመግባት በሂደት ላይ እንገኛለን፡፡
ዋናው ቀጣይ ስራችን ለከተማችን እድገት እና ለከተማ ነዋሪያችን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት እንቅፋት ሆኖ የሚጋረጥብንን ከመንግስት መዋቅር ጀምሮ በህብረተሰባችን ውስጥ ተንሰራፍቶ የሚገኘውን ስርአት አልበኝትንና በአቋራጭ መክበርን በመከላከል ፍትሀዊነትን ለማስፈን መታገል ነው፡፡
በመሆኑም፡-
1. በመሬት፤ በህገ-ወጥ ህንፃዎች፤ በቀበሌ ቤቶችና ኮንዶሚኒየም ልማት አጠቃቀም ዙሪያ የተካሄዱ ጥናቶች በየዘርፉ የለዩአቸውን ችግሮች በጥሞና እየመዘንን የህዝቡን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ በሚያስችል መንገድ የማስተካከያ ስራ እንሰራለን፡፡
2. በከተማችን የሚታዩ ብልሽቶች እንዲገቱና እንዳይስፋፉ ህዝቡ በሁሉም መስክ ውጤታማ ተሳትፎ እንዲኖረው በትጋት እንሰራለን።
3. ብልሽቶች በህዝቡ ላይ የሚፈጥሩትን ምሬትና ቅሬታ ለመቀነስ በራችንን፤ አዕምሯችንን ልባችንን ከፍተን የህዝቡን ጥቆማ፤ ብሶትና አቤቱታ እያዳመጥን ግልፅነትና ትምአኒነትን በመፍጠር እንሰራለን፡፡
4. ህገ-ወጥነትን እየተከላከልን ህጋዊነትን እናሰፍናለን፡፡
በአጠቃላይ ማንኛውም ህገ-ወጥ ተግባር የሚፈፀመው በህብረተሰቡ ውስጥ ነው ። ህዝባችን ሳያውቀው የሚከናወን አንዳችም ተግባር የለምና በመከላከሉ እንዲሁም መሰል ህገ-ወጥ ተግባራት በሚታዩበት ወቅትም በማጋለጡ በኩል የሚጠበቅባችሁን በመፈፀም ከጎናችን እንድትቆሙ ጥሪአችንን እናቀርባለን፡፡
ጥር 2013 ዓ.ም
አዲስ አበባ
አዲስ ዘመን ጥር 19/2013