ከመጋቢት ወር 2011 ዓ.ም ጀምሮ በአገራችን ስርነቀል ለውጥ ተደርጓል። ይህ ለውጥ ደግሞ ያመጣቸው በርካታ መልካም አጋጣሚዎች የመኖራቸውን ያህል ቀላል የማይባሉ ፈተናዎችንም አስተናግዷል።
በተለይ ከለውጡ በፊት በህገወጥ መንገድ ወደሃብት ከፍታ የወጡና ከነዚህ አካላት ጋር ትስስር በመፍጠር በየደረጃው የግል ኪሳቸውን ያደለቡ ህገወጦች ለውጡ የሚፈጥረውን ግልጸኝነትና ህጋዊነት ከወዲሁ በመፍራት ለውጡን መገዳደር የጀመሩት ገና በለውጡ ማግስት ነው። ለዚህ የተከተሉት ዋነኛ መንገድ ደግሞ በህገወጥ መንገድ የዘረፉትን ገንዘብ በማውጣት ግጭቶችን ስፖንሰር ማድረግና ማባዛት ነው።
በዚህ መሰረት ከለውጡ ማግስት ጀምሮ ባለፈው ጥቅምት ወር እስከተካሄደው ህግ የማስከበር ዘመቻ ድረስ በመላ አገሪቱ 114 ግጭቶች ተከስተዋል። ከነዚህም ውስጥ በኦሮሚያ 37፣ በአማራ 23፣ በቤኒሻንጉል ጉምዝ 15፣ በአዲስ አበባ 14፣ በጋምቤላ 7 እንዲሁም በደቡብ ክልል 5 ግጭቶች መከሰታቸው ይታወቃል።
ከነዚህ ግጭቶች ውስጥ በተለይ በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች ከለውጡ ዋዜማ ጀምሮ በተከሰቱ ግጭቶች በሚሊየን የሚቆጠሩ ዜጎች ከኖሩበት ቀዬ ተፈናቅለዋል፤ በርካታ ዜጎችም ህይወታቸውን አጥተዋል፤ ሃብት ንብረታቸውም ወድሟል። በጌዲኦና በጉጂ፣ በምዕራብ ወለጋ፣ በሻሸመኔ፣ በቡራዩ፣ በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች እና በአዲስ አበባ ጭምር በተከሰቱ ግጭቶችም በርካታ ውድመት ደርሷል።
እነዚህ ግጭቶች ታዲያ በርካታ ጉዳት ቢያደርሱም አብዛኞቹ መንግስት በወሰዳቸው ጠንካራ እርምጃዎችና በህብረተሰቡ ጥረት ከሞላ ጎደል ወደሰላማዊ መንገድ እየተመለሱ ይገኛሉ። በተለይ የነዚህ ግጭቶች ዋነኛ ስፖንሰር የነበረው የህወሓት ጁንታ ቡድን ከተመታ በኋላ አብዛኞቹ ግጭቶች ቀንሰዋል።
ያም ሆኖ ግን አንዳንዶቹ ግጭቶች የመንግስት መዋቅርን ጭምር በመጠቀምና በህብረተሰቡ ውስጥ ሰርጸው በመግባት ስር የሰደዱ በመሆናቸው በቀላሉ የሚቋጩ አይደሉም። በዚህም የተነሳ አንዳንዶቹ እስከአሁን ድረስ ዋጋ እያስከፈሉ ይገኛሉ። ከነዚህም ውስጥ በተለይ በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል መተከል ዞን በተደጋጋሚ እየተከሰተ የሰላማዊ ዜጎችን ህይወት እየቀጠፈ የሚያልፈው ሴራ ጭራው ያልተጨበጠ ሚስጢር እንደሆነ ዘልቋል።
በመተከል ዞን ያለው ግጭት በዚህ ደረጃ የችግሩ አስኳል ቶሎ ሊገኝ ያልቻለው በተለያዩ ምክንያቶች እንደሆነ የክልሉ አመራሮች እና ምሁራን ይገልፃሉ። ከነዚህም ውስጥ ክልሉ የተለያዩ የተፈጥሮ ሃብቶች ያሉት በመሆኑ ከዚህ ሃብት በስተጀርባ ጥቅማቸው የቀረባቸው ሃይሎች የፈጠሩት ችግር፣ ክልሉ የታላቁ ህዳሴ ግድብ እየተገነባበት ያለ ከመሆኑ ከዚህ ጋር ተያይዞ የተለያዩ የውጭ ሃይሎች ሴራ ያለበት መሆኑና በአካባቢው ለረጅም ዓመታት የቆዩ የተሳሳቱ ትርክቶች ለግጭቱ መባባስ ከሚጠቀሱ ምክንያቶች ዋናዎቹ ናቸው።
ከዚህም ባሻገር ከቀበሌ ጀምሮ የወረዳ፣ የዞን እና የክልል አመራሮችና የምክር ቤት አባላት ጭምር የተሳተፉበት መሆኑ ችግሩን ውስብስብ አድርጎታል። በተለይ የቀበሌና የወረዳ አመራሮች ከህብረተሰቡ ጋር በቅርበት ያሉና አብረው ተቀላቅለው የሚገኙ በመሆኑ ከህብረተሰቡ ነጥሎ ለማውጣት አዳጋች ነው። ለችግሩ መባባስም ይህ ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክቷል።
መንግስትም ችግሩን ለመፍታት በርካታ ጥረቶችን እያከናወነ ሲሆን ከነዚህም ውስጥ በቅርቡ ተግባራዊ የተደረገው ዞኑን በጊዜያዊ አስተዳደር መምራት ተጠቃሽ ነው። በዚህ መሰረት በዞኑ በተለይ ካለፉት ሁለት ሳምንታት ወዲህ የተሻለ ሰላም እየሰፈነ ይገኛል።
ይህንን ተከትሎም በተለይ በችግሩ የተማረረው ሰላማዊ ዜጋ እንዲህ አይነት ድርጊቶችን በአደባባይ እያወገዘ ሲሆን የመፍትሄው አካል ለመሆንም የበኩሉን አስተዋፅኦ እያደረገ ይገኛል።
በተለይ በመንግስት መዋቅር ውስጥ የተወሸቁና የህዝቡን ሰላማዊ ኑሮ የሚበጠብጡ አካላትን አጋልጦ ለመስጠትና በአካባቢው ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን የህብረተሰቡ ተሳትፎ ትልቅ አስተዋፅኦ ይኖረዋል። ይህንን መነሻ በማድረግም እስካሁን ባለው ሂደት በመንግስት መዋቅር ስር ሆነው ሰላምን የሚያናጉ በርካታ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች በህግ ጥላ ስር ውለው ተጠያቂ እየሆኑ ይገኛሉ።
ከነዚህም መካከል የክልሉ ምክትል ርእሰ መስተዳድርን ጨምሮ የምክር ቤት አባላት፣ የቀበሌ ሊቃነመናብርት፣ የወረዳና የዞን አስተዳዳሪዎች፣ የቢሮ ሃላፊዎችና ሌሎች በርካታ ባለስልጣናት በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው እየተጣራ ይገኛል።
ይህ ደግሞ በአካባቢው ተጨባጭ ለውጥ እንዲመጣ ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል። በመሆኑም መንግስት ይህንን አጠናክሮ መቀጠል አለበት። በተለይ በመንግስት ጉያ ውስጥ ሆነው እሳት የሚጭሩ ሃይሎችን በመልቀም መንግስት ራሱን ማፅዳት አለበት።
ይህ ካልሆነ ግን እሳቱን ማብረድም ሆነ ማጥፋት አዳጋች ይሆናል፤ ዜጎችንም በእሳቱ ከመቃጠል ማዳን አይቻልም። ድምር ውጤቱም ለአገር ህልውና አደጋ ነው። ስለዚህ የመንግስትን መዋቅር የማጽዳቱ ስራ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል።
አዲስ ዘመን ጥር 19/2013