ተገኝ ብሩ
ለአገር መፅናት ለእናት ምድራችን ህልውና ወሳኝ ነውና “አንድ እንሁን!” ሲባል አንድ ሆኖ የመቆም ፅንሰ ሃሳብን ባለመረዳት አሊያም የአንድ እንሁንና የአንድ አይነት እንሁን ትርጓሜን መሳት ብዙዎቻችንን አለመግባባት ውስጥ ሲከት ብሎም ለንትርክ ምክንያት ሲሆን ይታያል። ልዩነትን አምነው ከተቀበሉት በዚያ ልዩነት ውስጥ የፀና አንድነት መፍጠር አይከብድም።
ይህ እውነት ነው፤ ልንታረቀው የሚገባ ፈፅሞ ሊሸፈን የማይችል ሀቅ። መቀበል ግድ የሚል እውነታ። የተለያየ ቋንቋ፣ ልዩ ልዩ አምልኮና እምነት፤ የበዛ ባህል፣ አይነተ ብዙ አመለካከት፤ ዓይነተ ብዙ የፖለቲካ አቋም በዚህች ሀገር ገፅታ ላይ የሚንፀባረቀው እውነት ነው። ሁላችንም የዚህ አገር ፍሬዎች የታላቅዋ ኢትዮጵያ ልጆች ነን። የአንድ አገር ህዝቦች ነን። አንድ አገር ላይ የተገኘን፣ ነገር ግን አንድ አይነት ፈፅሞ አይደለንም። አንድ ሆኖ መቆም ግን ግድ ይለናል።
የተለያየ አመለካከትና የተለያየ ባህል መኖሩን አምኖ ከተቀበሉ ከዚያ ጋር ታርቆ አንድ ሊያደርግ የሚችል ነገር መብዛቱን ተገንዝቦ በስምምነትና በጋራ ለሁሉም ምቹ የሆነች አገር መገንባት ላይ ማተኮር ነው የሚገባው።
አንድ አገር ላይ የምንኖር ስለዚህች ሀገር ክብር የምንሰዋ ለህልውናዋ መፅናት እራሳችንን ከፊት ማሰለፍ ግዴታችን የሆንን ዜጎችም ጭምር። አንድ መሆናችንን ተቀብለን አንድ አይነት ባንሆንም በአንድነት መፅናት የምንችል መሆናችን ማመን ነው ትልቁ ቁም ነገር።
አገር የዜጎችን አንድነት የልጆችዋን ማበር በምትፈልግበት ወሳኝ ሰዓት ወሳኝ ምላሽ የሚሰጥ የጋራ አቋም ትፈልጋለች። በተለይ ዛሬ ኢትዮጵያ ያለችበት ዘርፈ ብዙ ችግር ይፈታ ዘንድ የልጆችዋ አብሮ መቆም አንድ ሆኖ ችግሮችን መጋፈጥ ግድ ይላል። የተለያየ አመለካከትና እሳቤ መኖሩን ማመን ፣የፖለቲካ አቋም ልዩነትን ማክበር፣ ብዝሀነትን መቀበልና ይህን እውነታ ማመን አንድ ሆኖ ለመቆም ዓይነተኛ መንገድ ነው። አገር ለማዳን ህዝብን ከአደጋ ለመጠበቅ አንድ ሆኖ መቆም ይገባል።
በአንድ እንሁንና አንድ አይነት እንሁን ውስጥ ፍፁም ልዩነት አለ። ከአንድ አይነትነት የራቀ ትርጓሜ በሁለቱ ቃላት ይዘትነና በእነዚህ መሀል የሚገኝ የራስ እንድ ሆኖ መቆምና አንድ አይነት እንሁን መሀል የገዘፈ ልዩነት አለ። መግባባት ያስችል ዘንድ መረዳት ያንን ነው፤ የሁለቱን ልዩነት እና አንድነት መገንዘብ የሚገባው ሀቅ ይህ ነው። ያኔ ወደ ስምምነት ይመጣል።
በእርግጥ ሁለቱንም በየራሳቸው ተርጉመው ባልተገባ መልኩ የሚገለገሉም አሉ። አንድ እንሁን ውስጥ አንድ አይነትነት መሆን ተፈልጎ ነው የሚል ግራ መጋባት ውስጥ የገባ ሞልቷል። አንድ አይነት አይደለንም ሲባል ልዩነት የተሰበከ የሚመስለውም በርካታ ነው። አንድ እንሁን የሚለውን የአንድነት ትርጓሜ በውል ባለመረዳት ወይም በምን መልክ አንድ ሆኖ መቆም እንደሚገባ በትክክል ባለመግለፅ የሃሳቡ ትልቅነት ሊቀጭጭበት ብሎም በተሳሳተ መንገድ ሊተረጎምበት ይችላል።
በአመለካከት ልዩነት ውስጥ፤ በእምነትና አምልኮት መለያየት መሀል አንድ ሆኖ መቆም ይቻላል። አንድ በሚያደርግ ጥላ ስር በፍቅር ማደር አይከብድም። ነገር ግን አንድ አይነት መሆን ነው የማይቻለው። መቀበልም የሚገባው አውነት ይህ ነው።
አንድ እንሁን የሚለው የማይቻለውን አንድ አይነት እንሁን ከሚል አመለካከትና እሳቤ በተለየ መልኩ ትልቅ ሃሳቡን ለሌሎች ማድረስ ቢችል ከስምምነት ይደረሳል። አንድ አይነት አይደለምን ነገር ግን አንድ ነን፤ አንድ አገር አንድ መድረሻ ግብና የጋራ የሆነ ጉዳያችን ይበዛል።
ያለመግባባቱ መነሻና የልዩነቱ ምክንያት የሁለቱም ሃሳብ ልዩነት በውል ካለመረዳት የሚመነጭ ይመስላል። “አንድ ነን” የሚለው በራሱ ልክ የሆነ ሃሳብ ቢሆንም በድርትና በአገላለፅ ከተዛነፈ ሌላኛው ትክክለኝነት ይንዳል። ምክንያቱም አንድ አይነት አይደለንም የሚለውም ትክክል ስለሆነ።
እንደ ዜጋ አንድ አገር ኖሮን አንድ ዜጋ ሆነን በፖለቲካ አቋማችን እንለያይ፤ በአመለካከታችን እንራራቅ ይሆናል። ይህ ተፈጥሯዊና ትክክልም ነው። በተለያየ አመለካከት ውስጥ የተገኘ ምልከታ በሰፊው ለማሰብና በተለያየ አንድ አይነት አስተሳሰብ አገር አይለውጥም።
በዚህች ትልቅ አገር፣ የሚሊዮኖች መኖሪያና የብዙ ባህሎች መድረክ በሆነች አገር ይቅርና በእምነት አንድ የሆኑ በባህል በሚመሳሰሉ ህዝቦች መሀልም ልዩነት አለ። የእኛ የፖለቲካ አመለካከት ልዩነት መብዛት የፍላጎታችን መሰባጠር የሚገርም አይደለም። በአመለካከት ልዩነት መጋጨት በአስተሳሰብ መራራቅ መቃቃር ነው ነውሩ።
የአገርን ህልውና አደጋ ላይ የሚጥሉ፤ የህዝብን አብሮ የመኖር እሴት የሚንዱ ጉዳዮችን እያነሱ ስለ ልዩነት እየሰበኩ ማቃቃር አንድ ሆኖ መቆምን ይንዳል። ለዚህ መፍትሄው ደግሞ የእርስ በርስ መከባበርን ማጎልበት የጋራ የሆነ አንድነትን የሚሰብክ መተባበርን የሚያጠነክሩ ልምዶችን ማጎልበት ይጠቅማል። አንድነትን በማጠንከርና የእርስ በርስ ግንኙነትን በማደርጀት ሀገራዊ ለውጥ ማቅረብ ይቻላል።
አንድ እንሁንን ተቀብለን አንድ አይነት አይደለንም የሚለውን እውነት መዘንጋት አይገባም። በየራሳችን እምነትና አመለካከት ለአገራችን በጎ እንስራ፤ በየራሳችን አቋም ለዚህች ምድር መልካም ነገርን እንፍጠር። በየትኛውም መንገድ ቀርበን የተገበርነው መልካም ከሆነ፣ ውጤቱ ላይ አንድ ይሆናል። የምንወዳትን ኢትዮጵያ መጠበቅ ግዴታ የህዝቦችዋን አንድነት ማፅናት የሁላችን ሃላፊነት ነውና ለዚህ አበክረን መስራት ያስፈልገናል።
ልዩነትን ተቀብሎ በመቻቻል መዝለቅ የሃሳብ መለያየት አክብሮ ተቀራርቦ ወደማመሳሰል ማቅረብ ጥበብ ነው። አገርም የምትሰራው በዚሁ ጥበብ ነው። አንድ አይነት አመለካከት ፈፅሞ በሰው ልጆች በአንዴና በተመሳሳይ ጊዜ ሊሰርፅ አይችልም። ነገር ግን በአገር አንድነት በእናት ምድራችን መፅናት ላይ ልዩነት ካለን ነው ችግሩ።
ይህ ሊያደራድር የማይችል የተሳሳተ እሳቤና ከትልቅነት ወደ ታች የሚያወርድ ደረጃ ነው። እኛ ደግሞ በዚህች ታላቅ አገር ላይ የተገኘን ትልቅ ህዝቦች ነንና ኢትዮጵያ በምትባል ትልቅ ጥላ ስር በፍቅር ማደር የምንፈልግ የምንወድም ነን። አበቃሁ፤ ቸር ይግጠመን።
አዲስ ዘመን ጥር 18/2013