አስመረት ብሰራት
በትምህርቱ ዘርፍ ወደላይ ከፍ ለማለት ወንድነት መሥፈርት የሆነ እስኪመስል በተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች ትልልቅ ደረጃ የሚደርሱት ወንዶች ሆነው ይገኛሉ። የሥልጣኔ ቁንጮ በተባለችው አሜሪካን እንኳን ሣይቀር እንደነዚህ ዓይነት ችግሮችን መመልከት የግድ የሚባልበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ብዙ ትግሎችን ተቋቁማ የቆዳ ቀለምና ፆታ መሥፈርት በሚሆንበት የትምህርቱ ዘርፍ ከአሜሪካው ኮርኔል ዩኒቨርስቲ በኮምፒውተር ሣይንስ ሦስተኛ ዲግሪ (ፒኤችዲ) የወሰደች የመጀመሪያዋ ጥቁር ሴት የዛሬዋ ባለታሪካችን ረድኤት አበበ ነች። ይህችን ወጣት ቢቢሲ አማርኛ አነጋግሯት የነበረ ሲሆን፤ ከዚያ ላይ ያገኘነውን መረጃ ለጋዜጣችን እንደሚስማማ አድርገን አቅርበነዋል፤ መልካም ንባብ።
ትውልዷም ዕድገቷም አዲስ አበባ ውስጥ የሆነው የ28 ዓመቷ ረድኤት አበበ የኮምፒውተር ሣይንቲስት ስትሆን፤ በአልጎሪዝም እና አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ (ኤአይ) ዙሪያ ትሠራለች። ረድኤት ከኮርኔል ዩኒቨርስቲ በኮምፒውተር ሣይንስ ሦስተኛ ዲግሪ (ፒኤችዲ) በማግኘት የመጀመሪያዋ ጥቁር ሴት ነች።የመጀመሪያ ዲግሪዋን የያዘችው ከሀርቫርድ ዩኒቨርስቲ በሒሳብ ትምህርት ሲሆን፤ ሁለተኛ ዲግሪዋን በአፕላይድ ማቲማቲክስ አግኝታለች።ጥናቶቿ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ (ኤአይን) ጨምሮ ሌሎችም የቴክኖሎጂ ውጤቶች ያለ ጾታና የቆዳ ቀለም መድልዎ ፍትሐዊ በሆነ መንገድ አብዛኛውን ማኅበረሰብ መጥቀም የሚችሉበት መንገድ ላይ ያተኩራሉ። ረድኤት ፍትሐዊ የቴክኖሎጂ ተደራሽነት ላይ የሚያተኩሩ ‹‹ሜካኒዝም ዲዛይን ፎር ሶሻል ጉድ›› እንዲሁም ‹‹ብላክ ኢን ኤአይ›› የተሠኙ ተቋሞችን ከሙያ አጋሮቿ ጋር መሥርታለች።
እንደ ሣይንቲስት ረድኤት ገለፃ፤ በርካታ ጥቁር ሴቶች እንደ ኮርኔል ካሉ ትልቅ ዩኒቨርስቲዎች ብቻ ሣይሆን በመላው አሜሪካ ከፍ ያለ የትምህርት ደረጃ ላይ መድረስ ያቅታቸዋል። አሜሪካ ውስጥ ሲአርኤ የሚባል ተቋም በየዓመቱ በሦስተኛ ዲግሪ (በፒኤችዲ) ተመራቂዎች ላይ በሚያደርገው ጥናት ውስጥ ወላጆቻቸው የኮሌጅ ተማሪ ነበሩ? ዲግሪያችሁን በምን ጨረሣችሁ እና ጾታና የቆዳ ቀለም ይጠይቃሉ። የጥናቱ ውጤቱ እንደሚያመለክተው በየዓመቱ በመላው አሜሪካ በኮምፒውተር ሣይንስ ሦስተኛ ዲግሪ (ፒኤችዲ) የሚመረቀው ጥቁር ሴት አምስት ብቻ ነው። በዓመት በኮምፒውተር ሣይንስ በሦስተኛ ዲግሪ (በፒኤችዲ) የሚመረቀው ሰው በአጠቃላይ ወደ ሦስት ሺህ አካባቢ ይሆናል። አሜሪካ ውስጥ ቢያንስ ከአምስት ሺህ በላይ የኮምፒውተር ሣይንስ ፕሮፌሰሮች አሉ። ከነዚህ ውስጥ ጥቁሮች 75 ብቻ ናቸው። በኮምፒውተር ሣይንስ ፕሮፌሰር የሆኑ ሴቶች ሀያ አለመሙላታቸው ሁሌም አግራሞት ይፈጥርባታል።
በእነዚህ ሁሉ ችግሮች መካከል ያገኘችውን ሥኬት ረድኤት ስትናገር ‹‹የምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ በርካታ ጥቁር በትምህርቱ ዘርፍ ከፍ ያለ ደረጃ ያላቸው ሰዎች ተገኝተው ነበር።ጥቁር ሴት ለመጀመሪያ ጊዜ በዚህ ዩኒቨርስቲ መመረቋ ደስ የሚል ቢሆንም በጥረት ተገኘ አንጂ ዕድሉን ያላገኙት መኖራቸው እጅግ አሣዛኝ ነበር›› ትላለች።
‹‹መመረቂያ ጽሑፌን ሣቀርብ አያቶቼ እንኳን ኮሌጅ አንደኛ ደረጃም አልተማሩም›› ብዬ ተናገርኩ የምትለው ረድኤት ‹‹እኔ ግን ሁለቱንም እንደ ሣይንቲስት ነበር የማስባቸው። የአባቴ እናት መሦብ ትሠራ ነበር። ተሰጥዖ ነበራት። መሦቦቹን ጂኦሜትሪክ ዲዛይን ነበር የምታደርገው። በጣም ያምራል። አንድ ቀንም ይህንን ዲዛይን ስትጽፍ አላየሁም። ቁጭ ብላ መሥራት ትጀምራለች፤ ትጨርሳለች›› ብላለች።
አያቷ በመደበኛ /ትምህርት ቤት/ ሣይንስ ባያጠኑም እንደ ሒሣብ ባለሙያ ነበር የሚያስቡት። የአባቷ አባት ደግሞ አርሶ አደር ነበሩ። ትልቅ እርሻ ነበራቸው። የሚያርሱት ራሣቸው በሠሩት መሣሪያ ነበር። ትራክተር የገዙት በጣም ካረጁ በኋላ ነበር። አያቶቿ ባይማሩም እንደ ሣይንቲስት ያስቡ ነበር። አዲስ አበባ ስታድግ እናትና አባቷን ስታይም ራሷን እንደ ሣይንቲስት ታይ እንደነበር በመመረቂያ ጽሑፏ ንግግር ላይ ማውራቷን ታስታውሣለች።
ለትምሀርት አሜሪካ ስትሄድ ጥቁር ሰው ሣይንስ አይችልም፤ ሴት ሣይንስ አትችልም ተብሎ እንደነበረ ታስታውሣለች። ኢትዮጵያ ውስጥ ግን ሴት፣ ወንድ፤ አማራ፣ ኦሮሞ ተብሎ ሣይከፋፈል ሁሉም ሣይንስ መሥራት እንደሚችል ታስብ ነበር። መመረቂያ ጽሑፏን ስታቀርብም የተናገረችው ይህን ነው።”ሣድግ ሣይንቲስት ለመሆን አስብ ነበር። አሜሪካ መጥቼ ‘አንቺ ሣይንስ አትችይም’ ስባል በጣም ገረመኝ፤ አሣዘነኝም። ይኼንን ነገር መለወጥ አለባችሁ። ምክንያቱም እናንተ እንደ ሣይንቲስት ባታዩኝ እንኳን ራሴን እንደ ሣይንቲስት ነው የማየው” አልኳቸው ትላለች።
‹‹አርቴፍሻል ኢንተለጀንስን (ኤአይ) ጨምሮ ዘመነኛ ቴክኖሎጂዎች አካታች እንዳልሆኑ (በተለይ ጥቁሮችና ሴቶችን)፣ ኢ-ፍትሐዊነት እንደሚስተዋልባቸውም የሚናገሩ ባለሙያዎች አሉ›› የምትለው ረድኤት፤ ጉዳዩ ብዙ ችግር እንዳለበት እና አርቴፊሻል ኢንተለጀንት (ኤአይ) በዳታ ላይ የተመረኮዘ መሆኑን ትገልፃለች። ‹‹አልጎሪዝም ስትሰጪ ዳታውን ይወስድና ከዳታ ውስጥ ፓተርን ያያል። እሱን ይዞ ክሬዲት ያደርጋል። ለምሣሌ አሜሪካ ውስጥ ወደ 15 በመቶው ጥቁር ሰው ነው። ዳታውን ስታይ በጣም ትንሽ ጥቁር ሰው ነው የምታይው። ዳታው ብዙ ጥቁር ሰው አካታች አይደለም። ማሽን ለርኒንግ አልጎሪዝም ‘ትሬን’ ሲሠራ፤ የማያየውን ሰው ጉዳይ በደንብ አያጠናም።›› ትላለች።
በዚህ ተመርኩዞ ሲገምት ጥሩ አይሆንም። ለምሣሌ ትምኒት ገብሩ ፌሻል ሪኮግኒሽን ቴክኖሎጂ ላይ አንድ ሥራ አላት። ፌሻል ሪኮግኒሽን ቴክኖሎጂው ያጠናው በአብዛኛው ነጭ ወንዶችን ነው። ስለዚህ ጥቁር ሴት ወደ ቴክኖሎጂው ስትገባ ትክክለኛ ነገር አያሣይም። እንደዚህ ዓይነት ቴክኖሎጂን የሚሠሩ ሰዎች ጥቁሮች አይደሉም፤ ሴቶች አይደሉም። ስለዚህ ቴክኖሎጂዎቹ አካታች አለመሆናቸውን ታስረዳለች።
ለምሣሌነትም አማዞን ሠርቶት ስለነበረው አንድ መሣሪያ ታነሣለች። መሣሪያው ጾታን መሠረት ያደረገ መድልዎ እንዳይፈጠር ተብሎ ጾታና ሥም ከመሣሪያው እንዲጠፋ ተደረገ። ነገር ግን የኮሌጅ ሥም አልጠፋም ነበር። አንዳንድ ኮሌጆች ደግሞ የሴቶች ብቻ ናቸው። ሥምና ጾታ ቢጠፋም የኮሌጁ ሥም ፕሮክሲ ይፈጥራል። ይህንን ሣያውቁ ይጠቀሙበት ነበር። ከዚያ ሴቶችን ማግለል ሲጀምር [ክፍተቱ] ታወቀና እንዲጠፋ ተደገረ።
ግን ይህ ቴክኖሎጂ ሲሠራ ሴት ብትኖርና መናገር ብትችል ችግሮች እንደማይፈጠሩ ትጠቅሣለች።
በመላው ዓለም ማለት በሚቻልበት ደረጃ የቴክኖሎጂ ፍርሀት እየተስፋፋ ይመሥላል። ሥራችንን ልንነጠቅ ነው፣ ቴክኖሎጂ ከመጠን በላይ በሕይወታችን ገብቶ እያመሠቃቀለው ነው ወዘተ. . . በተደጋጋሚ የሚስተጋቡ ሥጋቶች ናቸው። በእርግጥ ታሪክን እንደ ማሣያ ቢወሰድ፤ ሰዎች ለውጥ ሲፈሩ ተሥተውሏል። ፈጠራዎችን እንዲሁም አዲስ ነገሮችን በአጠቃላይ ለመልመድም ጊዜ እንደሚወስድ ትናገራለች።
አሁን እየታየ ያለው ግን ለውጥን መፍራት ሣይሆን መሠረት ያለው ሥጋት እንደሆነ ባለሙያዎች ይናገራሉ። እናም በርካቶች ዘመኑን መፍራታቸው ልክ መሆኑን ትገልፃለች። ‹‹እውነት ነው፤ ሰው ለውጥ አይፈልግም፤ አይወድም። እንኳን አርፊሻል ኢንተለጀንት (ኤአይ) ሌላ ቴክኖሎጂም ሲተዋወቅ እንደዚያ ነው። አሁን በአርቴፊሻል ኢንተለጀንት(ኤአይ) የሆነ ድርጅት ያመርታል። እምቢ ማለት አይቻልም። ነገር ግን ቴክኖሎጂውን ሰው ላይ በግዴታ ከመጫን ትምህርቱን አሥፍቶ፣ ሰው የሚፈልገውን ነገር ራሱ ቢሠራ፤ ያኔ ለውጡን ሊወደው የሚችልበት ሁኔታ ሊፈጠር እንደሚችል ታሥረዳለች።
ሰው ራሱ የሠራው ለውጥ ነውና ሊቀበለው የሚችልበት እድል ሰፊ ነው። ለምሣሌ አንድ ትልቅ ድርጅት ይህንን መሣሪያ ሠርተናል ውሰዱት ብሎ ለአርሶ አደሮች ሲሰጥ ሊያስፈራቸው ይችላል። ልክም ነው። ምንድን ነው የምትፈልጉት? ምን እንሥራላችሁ? ተብሎ ውይይት ከተደረገ የነሱን ሐሳብ ተወስዶ፤ ተሠርቶ ተደራሽነቱን ማሥፋት ወይም ራሣቸው የሥራው አካል ሆነው በፈጠራ ላይ ቢሣተፉ የመቀበልና ያለመቀበል ችግርን የሚያቀል እንደሚሆን ትጠቅሣለች።
ድሮ ታይፕ ራይተሮች ነበሩ። አሁን ሁሉም መጻፍ ስለሚችል አያስፈልግም። እንደዚህ ሥራ ሲለወጥ ችግር የለውም። ሥራዎች ሲለወጡ ግን ሌላ ሥራዎች እየተፈጠሩ መሆን አለበት። ብዙ ቦታዎች የሦፍትዌር ኢንጂነር ሥራዎች ያስፈልጋቸዋል። ጉግል ብቻ ሣይሆን ለትርፍ ያልተቋቋሙ ድርጅቶችም ሦፍትዌር ኢንጂነር ያስፈልጋቸዋል። ግን ለነዚህ ሥራዎች እድሉ ያለው ማነው? ሁሉም ሰው ነው ወይስ ትንሽ ሰው? ስለዚህ አንዳንድ ሥራዎችን ዘመናዊ ስናደርግ ሁሉም ሰው እድሉ እንዲኖረው መጠንቀቅ ያስፈልጋል። አሁን ግን ጥንቃቄ እየተደረገ አይደለም። ሰው የሚፈራውም ለዚህ ነው። መፍራታቸውም ልክ ነው። ግን መለወጥ ይቻላል። በኢትዮጵያም ቴክኖሎጂው ሰፍቶ ችግር ከመሆኑ በፊት ቴክኖሎው የሚያመጣውን ክፍተት እየደፈኑ መሄድ ግድ መሆኑን ታብራራለች።
‹‹በድረ ገጽ ሰዎችን በመጠየቅ ሰርች ዳታ ነበረን። ከ54 የአፍሪካ አገሮች እሱን ዳታ ወሰድንና ሰው ስለሕክምና ምን ዓይነት ጥያቄ እየጠየቀ ነው? በድረ ገፅ መረጃስ እንዴት ነው የሚያገኘው? ብለን አጠናን። አፍሪካ ሕብረት፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና ሌሎችም ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ሪፖርት አላቸው።›› ትላለች።
በተገኘው መረጃ መሠረት አፍሪካ ላይ ስለሕክምና መረጃ የለም። ለምሣሌ ኤችአይቪ ኤድስ ቢወሰድ እንኳን ዝርዝር ዳታ አይደለም። በአንድ አገር በየዓመቱ ስንት ሰው በኤድስ ሞተ? ተብሎ ቢጠየቅ መረጃውን ማግኘት በጣም ይከብዳል። ከተገኘም ስህተት ይኖረዋል። እና እንደዚህ ዓይነት ጉዳዮች ላይ ብዙ መረጃ ቢኖር ጥሩ ነው። ያኔ ያሉትን ሀብቶች መጠቀም እንደሚቻል ትናገራለች።
ጥናቱን የሠሩት ባለሙያዎች ማየት የፈለጉት ስለ ኤችአይቪ ኤድስ ሰው ምን ዓይነት መረጃ እየጠየቀ ነው? እንዴት ዓይነት መረጃ እየተሰጠው ነው? የሚለውን ነው። ስለ አፍሪካ የሕክምና ጉዳይ ሲታሰብ መረጃ የለም። ቴክኖሎጂ የለም። ቴክኖሎጂ ካለ ደግሞ ላይሠራ ይችላል። ለምሣሌ ኢትዮጵያ መብራት ይጠፋል። በባትሪ የሚሠራ ነገር ሊሠራ እንደሚገባ ትጠቁማለች።
ኢንተርኔት ከጠፋ ኮኔክሽን የማያስፈልገው ነገር መሥራት ይቻላል ወይ? ብዙ ማሣደግ የሚቻሉ ነገሮች አሉ። አፍሪካዊ ሰዎችን ማሣተፍ ይቻላል። ብላክ ኢን ኤአይ፣ ዳታ ሣይንስ አፍሪካ እና ሌሎችም ተቋሞች አፍሪካ ላይ ይሠራሉ። ሁሉም የሚያስበው ለአፍሪካ ጉዳይ መልሱ የሚመጣው ከአፍሪካዊ እንደሆነ ነው። ከውጪ አይመጣም። መድልዎን ማቆም፣ አፍሪካን መጠበቅ ይቻላል። ትምህርቱን አስፍቶ ተሰጥኦው እንዲወጣና በዓለም እንዲታይ ማድረግ እንደሚገባ ትገልፃለች።
በኢትዮጵያ ውስጥ ሰዎች ነጭ ሽንኩርት፣ ማር ወይም ሎሚ ከኤችአይቪ ይፈውሣል? ከተፀለየልኝ ኤችአይቪ ይጠፋል? እነዚህ ዓይነት ጥያቄዎች ሲጠየቁ ‘ዌብሣይት’ ላይ “አዎ፤ ነጭ ሽንኩርት ኤችአይቪን ያጠፋል” ተብሎ ይጻፋል። በዚህ ጉዳይ ላይ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ሊያስብብበት እንደሚገባ ትጠቁማለች።
በኢትዮጵያ ብቻ ሣይሆን በሌሎችም አገሮች ሌላው ጥያቄ ስለመገለል ነው። ኤችአይቪ በደሜ በመኖሩ ከሥራ ልባረር እችላለሁ? ሰው ያገለኛል? ብለው ይጠይቃሉ። ኢትዮጵያ እያለሁ ሰዎች እንዳይገለሉ አስተማሪ ድራማ ይታይ ነበር። በጤና ጥበቃ መረጃ የሚሰጡ ንቅናቄዎች በጣም ይረዳሉ። ኢትዮጵያ ግን ብዙ ይቀራታል። ብዙ መሻሻል ያለባቸው ነገሮች እንዳሉም ታሥረዳለች።
አዲስ ዘመን ጥር 16/2013 ዓ.ም