ለ17 አመታት በጫካ፤ ለ27 አመታት ደግሞ በመንግስት ስልጣን ላይ ሆኖ ሃገር ሲዘርፍና ሲያተራምስ የኖረው የህወሀት ጁንታ ቡድን በጥቂት ቀናት የሃገር መከላከያ ሰራዊት የህግ ማስከበር ዘመቻና በመላ ኢትዮጵያውያን ትብብር ላይመለስ እስከወዲያኛው ተደምስሷል። በዚህ ዘመቻም ቀንደኞቹ የጁንታው አባላት በቁጥጥር ስር ውለዋል፤ ከፊሎቹም ተደምስሰዋል፤ የቀሩትም ቢሆኑ በየዋሻው እየታደኑ ለፍርድ እየቀረቡ ይገኛሉ፡፡
ይህ ቡድን ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ በተለይ ለትግራይ ዜጋ ትልቅ ነቀርሳ ሆኖ የኖረ ነው። ነቀርሳ ያለበት ሰው ደግሞ በሽታው ሙሉ ለሙሉ በቀዶ ጥገና ካልወጣለት ፈውስ ሊያገኝ አይችልም። በሽታውን ለማከምና ታማሚውን ወደቀደመ ጤንነቱ ለመመለስ ነቀርሳውን በቀዶ ጥገና ማስወገድ ግድ ይላል።
ይህ በሚሆንበት ጊዜ ታዲያ ታማሚው የሚያጋጥመው ቁስል መኖሩ አይቀሬ ነው። ይህ ጊዜያዊ ቁስል እስከሚሽርና ታማሚው ሙሉ ለሙሉ እስከሚፈወስ ጊዜ መውሰዱ አይቀርም። ከዚያ በኋላ ግን ሰውየው ወደቀደመው ጤንነቱ ይመለሳል፤ ከዚያ በላይ የተሻለ ጤናማ የመሆን እድሉ ይሰፋል፡፡
አሁን በትግራይ እየሆነ ያለውም ይኸው ነው።በክልሉ ህዝብ መካከል ተሸሽጎ የህዝን ደም ሲመጥ የነበረው የጁንታው ሰንኮፍ በሚነቀልበት ጊዜ ያጋጠሙ ችግሮች መኖራቸው እሙን ነው። በተለይ ለአመታት ከጁንታው ጋር የኖረው የሴረኝነት ባህርይና ህዝብን ለግል ፍላጎቱ ማሳኪያነነት ከመጠቀም ውጭ አንዳችም ህዝባዊ ተቆርቋሪነት የሌለው ይህ ቡድን ህልውናውን ለማቆየት ህዝቡን እንደጋሻ ለመጠቀምና ከዚያም አልፎ በአስገዳጅ ሁኔታ እንደምሽግ ለመጠቀም ያላደረገው ሙከራ አልነበረም።
ያም ሆኖ ግን የትግራይ ህዝብ ይህ ክፉ በሽታ እንዲወገድለት ካለው ፍላጎት የተነሳ ከጎኑ ሊሰለፍ አልቻለም። በዚህ የተነሳ እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል እንዳለችው እንስሳ እሱ ለመጥፋት መቃረቡን ሲገነዘብ በተቻለው መጠን ህዝብ ሰላም እንዳይኖረውና ለቀጣይም ልማቱ እንዳይፋጠን የሚያደርግ የተለያዩ ጥፋቶችን ፈጽሟል።
በዚህ መሰረት ጁንታው በሃገር መከላከያ ሰራዊት ሲመታ በዋናነት ከፈፀማቸው ጥፋቶች አንዱ የህዝብ መሰረተ ልማቶችን ማውደም ነበር።በዚህም መሰረት የአክሱም አየር ማረፊያን ማየቱ ለዚህ ማሳያ ሊሆን ይችላል።ከዚህም በተጨማሪ ባንኮችን ፣ የኢትዮ ቴሌኮም መስመሮችን፣ ሆስፒታሎችን የማውደም፣ አምቡላንሶችን በየቦታው የማቃጠልና የመጣል ወዘተ ጥፋቶችን አከናውኗል።
ከዚህም በሻገር በሴት መድፈር ወንጀል ተከሰው የተፈረደባቸው፣ የሰው ህይወት ያጠፉ፣ አደገኛ ወንጀል የፈጸሙና ሌሎች ከአስር ሺህ የሚበልጡ ወንጀለኞችን ከማረሚያ ቤት በመፍታትና በመልቀቅ ህዝቡን እንዲያማርሩ አድርጎ ወደጫካ ገብቷል።ይህ ደግሞ ለህዝብ ከማሰብ ሳይሆን ሆን ተብሎ ህዝብን ለመበቀል የተከናወነ ሴራ እንደሆነ መረዳት አያዳግትም፡፡
የጁንታው ጥፋት በዚህ ብቻ አያበቃም። ዋነኛው የጁንታው አከርካሪ ከተመታና በማይጠበቅ መልኩ ከየቀበሮ ጉድጓድ ተይዞ እየወጣ ባለበት ሁኔታም ጥቂት የጁንታው ርዝራዦችና አብሮአደጎች እዚህም እዚያም በየጥጋጥጉ እየተደበቁ የፈሪ ዱላ መሰንዘራቸውም ይታወሳል።
እነዚህ ሃይሎችም ቢሆኑ በዋናነት የዘመቱት ፊትለፊት ከሃገር መከላከያ ሰራዊት ጋር የመግጠም አቅም የሌላቸው በመሆኑ እያደፈጡ የድጋፍ ስራዎችን የማደናቀፍ ተግባር ሲሆን ይህም በአሁኑ ወቅት ሙሉ ለሙሉ ተወግዶ እነዚህ ሃይሎች በጋንታ ደረጃ እንኳን ለመንቀሳቀስ የሚያስችል አቅም እንዳይኖራቸው ተደርጎ ተደምስሷል።
አሁን በአጋጣሚ ከባህር ማዶ የሄዱ ጥቂት የጁንታው አባላትና ነዚህ ጋሻ ጃግሬዎች ባገኙት አጋጣሚ ሆነው በህዝብ ውስጥ ውዥንብር ለመፍጠር፣ የሃሰት መረጃዎችን የማሰራጨትና መሰል ስራዎች ላይ ተሰማርተው ይገኛሉ።እነዚህ ሃይሎች የጁንታውን ሽንፈት መቀበል ሲያቅታቸው ጁንታው የተሸነፈው በሌሎች ሃይሎች ድጋፍ ጭምር ነው፤ በትግራይ የሰብአዊ ድጋፍ ማድረግ አልተቻለም፤ ሴቶች እየተደፈሩ ነው፤ ወዘተ የሚሉ ውሃ የማይቋጥሩ አሉባልታዎችን ያሰራጫሉ። ነገር ግን ትናንት ጁንታው በሚያስተዳድርበት ወቅት በክልሉ ከ2ነጥብ 5 ሚሊየን በላይ የሚሆኑ ዜጎች የሴፍቲኔት ፕሮግራም ሲጠብቁ እንደነበር አያነሱም።
በክልሉ ተንቀሳቅሶ ድጋፍ ለመስጠትም ይሁን ችግሮችን ለመመልከት የሚያስችል ሁኔታ ፈጽሞ እንዳልነበር ማሰብ አይፈልጉም፤ ከዚያም በላይ ከ50 በላይ ሴቶችን በመድፈር የተከሰሱ እና የታሰሩ ወንጀለኞችን ጁንታው ሆን ብሎ መልቀቁንም መስማት አይፈልጉም፡፡
በሌላ በኩል እነዚህ ሃይሎች ለትግራይ ህዝብ እንዴት በችግሩ ጊዜ እንድረስለት፣ ምንስ እናድርግለት ብለው የማንሳት ሞራላዊ ብቃትና ወኔ የላቸውም።መንግስት በክልሉ ለተቸገሩ ዜጎች እያደረገ ያለው መጠነ ሰፊ የሰብአዊ ድጋፍንም ፈጽሞ ማየት አይፈልጉም፤ ይልቁንም ይህ ያበሳጫቸዋል።
ያም ሆኖ ግን አሁን ይህ ሃይል ተወግዶ በክልሉ የሰላም አየር መንፈስ ጀምሯል። የጁንታው ርዝራዦችም ጥቃት የመፈፀም አቅማቸው ሙሉ ለመሉ በመወገዱ በፕሮፓጋንዳ የጀመሩትን ዘመቻ ቀጥለውበታል። ይህ ግን ፈፅሞ የሚሳካላቸው አይደለም። ምክንያቱም ትናንት በተጨባጭ አብሯቸው ኖሮ ማሳካት ያቃተው ዛሬ በርቀት ሆኖ በወሬ ወለደ የሃሰት ፕሮፓጋንዳ ልቡን መማረክም ሆነ ማሸፈት ፈጽሞ አይሞከርም።
ዛሬ የሚያስፈልገው ጁንታውን ለማስወገድ በተደረገው ቀዶ ጥገና የቆሰለውን ህዝብ ማከም ነው። ይህ ደግሞ በሰብአዊ ድጋፍ፣ ከጦርነት ስነልቦና ወጥቶ ወደስራና ልማት እንዲሄድ የመርዳትና የቀደመውን አብሮነትና የአንድነት ስሜት ይበልጥ በማጠናከር የተጀመረውን የብልጽግና መንገድ እውን ማድረግ ነው። ይህ ሲሆን ትግራይ የጁንታው መቀበሪያ የሆነችውን ያህል አሁን ደግሞ የብልጽግና ማዕከል ትሆናለች፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 16/2013