አዲስ አበባ፡- የዓለም ሚቲዎሮሎጂ ድርጅት የአፍሪካ አህጉር ጽህፈት ቤት መቀመጫውን ከጄኔቭ ወደ አዲስ አበባ ሊያዘዋውር እንደሆነ የብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ ገለፀ፡፡
የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ፈጠነ ተሻለ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ የአፍሪካ አህጉር መቀመጫ ቀደም ሲል ብሩንዲ የነበረ ሲሆን፤ በነበረው እርስ በእርስ ጦርነት ምክንያት አካባቢው ለተባበሩት መንግሥታት ሥራ ምቹ ባለመሆኑ ጄኔቭ በሚገኘው የዓለም ሚቲዎሮሎጂ ድርጅት ሲሠራ ቆይቷል፡፡
ድርጅቱ ከጄኔቭ በመሆን ለአፍሪካ አገራት የተለያዩ ድጋፎችን ሲያደርግ ቢቆይም በቅርበት ለመሥራት ምቹ ባለመሆኑ 17ኛው የዓለም ሚቲዎሮሎጂ ድርጅት ኮንግረንስ በአህጉሩ ጽህፈት ቤት ከፍቶ በቅርበት አገልግሎት አሰጣጡን እንዲያሻሽል ውሳኔ ማሳለፉን ጠቁመዋል፡፡
እ.አ.አ በ2015 በተካሄደው ኮንግረንስ በተወሰነው ውሳኔ መሠረትም ጽሕፈት ቤቱን ተቀብሎ ለማስተናገድ ለሚሹ አገራት ባቀረበው ጥያቄ መሰረት ኢትዮጵያን ጨምሮ 10 አገራት ፍላጎታቸውን ለዓለም ሚቲዎሮሎጂ ድርጅት እንዳሳወቁም አቶ ፈጠነ ተናግረዋል፡፡
በመጨረሻም ኢትዮጵያ ተቀባይነት አግኝታ የዓለም ሚቲዎሮሎጂ ድርጅት የአፍሪካ አህጉር ጽህፈት ቤት ወደ ኢትዮጵያ እንዲዛወር ተወስኗል ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ የአፍሪካ አህጉር መቀመጫ መሆኗ ተመራጭ እንድትሆን ትልቅ አስተዋፅኦ ማበርከቱን የጠቀሱት ዋና ዳይሬክተሩ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሁሉንም የአፍሪካ አገራት በሚባል ደረጃ የሚያዳርስ አገልግሎት መስጠቱ ደግሞ ሌላው የተመራጭነቷ ምክንያት እንደነበር ተናግረዋል፡፡
ከዚህም ባሻገር በአህጉሪቱ በተለይም በቀጣናው ካሉት አገራት የስጋትና የአሸባሪዎች ቀጣና አለመሆኗ፣ የተሻለ ሰላም መኖሩና የተረጋጋች መሆኗ አሸናፊ እንድትሆን አስተዋፅኦ እንደነበረውም አብራርተዋል፡፡
የሚቲዎሮሎጂ አገልግሎት በአህጉሪቱ ከሚገኙ አገራት እያደገና እየተሻሻለ መምጣቱም ጠንካራ የዲፕሎማሲ ሥራ ታክሎበት ዕድሉን እንድትወስድ እንደረዳትም አቶ ፈጠነ ተናግረዋል፡፡
ጽሕፈት ቤቱ በተያዘው የፈረንጆቹ ዓመት በ2019 ከሁለት ወራት በኋላ በይፋ በአዲስ አበባ ሥራ ይጀምራል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፤ የኢትዮጵያ መንግሥትም ጽህፈት ቤት እንደሚያዘጋጅ ታውቋል፡፡
በዚህም የብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ ቀድሞ ይሠራበት የነበረው ህንፃ የመሰነጣጠቅ አደጋ የደረሰበትና እየፈረሰ በመሆኑ አዲስ ግንባታ እንዲካሄድ በመንግሥት አቅጣጫ መቀመጡንና አዲሱ ግንባታ እስኪጠናቀቅም ጽህፈት ቤቱን በነባሩ ተቀብሎ እንደሚያስተናድ ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 27/2011
በፍዮሪ ተወልደ