በሀገራችን መልኩን እየቀያየረ በሰበብ አስባቡ የሚነሳው ግጭትና ሁከት ዜጎች ሰላምና ደህንነት እንዳይሰማቸው ከማድረጉም በላይ የእርስ በእርስ ጥርጣሬ እንዲነግስና መተማመን እንዲጠፋ አድርጓል። በተለይም ሴረኞች በየጊዜው እየሸረቡ በሚለኩሱት እሳት በርካቶች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል፤ ወድ ሕይወታቸውን አጥተዋል።
ሴረኞችና የጥፋት ኃይሎች በለኮሱት እሳት ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ የእርስ በእርስ ግጭቶችና መፈናቀሎች በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ተከስተዋል። በሶማሌና በኦሮሚያ ድንበር፤ በቡራዩ፤ በጉራጌ ዞን በመስቃንና ማረቆ፤ በጌዲዮ፤ በአማራ ክልል፤ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፤ በአዋሳ፤ በኦሮሚያ የተለያዩ አካባቢዎችና በአዲስ አበባ የተከሰቱት ግጭቶች የበርካታ ሰዎችን ሕይወት ያጠፉ፤ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንን ከቤት ንብረታቸው ያፈናቀሉና በርካታ ሰብዓዊ መብት ጥሰቶች የተከሰተባቸው አሳፋሪ ታሪኮቻችን ሆነው ተመዝግበዋል።
በተለይም በቅርብ ጊዜያት በተደጋጋሚ በመተከል ዞን የተለያዩ ወረዳዎች በሚነሱ ግጭቶች በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው ተረጂዎች ሆነዋል። እንደኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ሪፖርትም 500 የሚጠጉ ነዋሪዎች በአሰቃቂ ሁኔታ ሕይወታቸውን አጥተዋል። የሰዎች ሕይወት መጥፋትና መፈናቀል በተለያዩ ጊዜያት መልኩን እየቀያየረ ቢከሰትም እስካሁን የሟቾችንና የተፈናቃዮችን ቁጥር እየጠሩ የዜና ፍጆታ ከማድረግ ውጪ በዘላቂነት የተገኘ ውጤት የለም።
የንጹሃን ዜጎች ግድያ፣ አካል ጉዳት፣ መፈናቀል እና የንብረት ውድመት የተወሳሰበውና ቶሎ ሊቆም ያልቻለው ቀደም ሲል ሀገሪቱን ሲያስተዳድር በነበረው አካል ድብቅ የፖለቲካ አላማ ሕገ መንግሥታዊ መብትን ጥያቄ ውስጥ በሚያስገባ መልኩ ሲነዛ የነበረው የጥላቻ ፕሮፓጋንዳ የራሱን ጥቁር አሻራ አሳርፏል። ባለፉት 27 ዓመታት በተደረገው ስልታዊ የመለያየትና የማዳከም ሥራ የዜጎችን አብሮነት ጥርጣሬ ውስጥ እንዲገባና አለፍ ሲል ለዘመናት አብሮ የኖረው ማህበረሰብ በጥላቻ ዓይን እንዲተያይ በር ከፍቷል።
በሌላም በኩል የተለያየ የፖለቲካ ፍላጎት ያላቸው የውስጥ እና የውጭ የጥፋት ኃይሎች በመንግሥት መዋቅር ውስጥ የሚገኙ አንዳንድ አመራሮች ጽንፈኛ ሚዲያዎችን በመጠቀም መንግሥትን ለማዳከምና የተጀመረውን ሀገራዊ ለውጥ ለመቀልበስ እንዲሁም ይባስ ብሎ ሀገርን ለማፍረስ በሄዱባቸው አፍራሽ መንገዶች ዜጎች ሰለባ ሆነዋል።
ይኸው ጉዳይ ያሳሰበው የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በትናንትናው ዕለት ባካሄደው 5ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 6ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 8ኛ መደበኛ ስብሰባው የዜጎች ሞትና መፈናቀል ለዘለቄታው እንዲቆም የሚያስችል ውሳኔ አስተላልፏል።
ምክር ቤቱ የመተከል ዞንን ጨምሮ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚታየው የዜጎች ሞት፣ መፈናቀልና ንብረት መውደም በአስቸኳይ ስለሚቆምበት ሁኔታ እና ተጎጂዎች ተገቢውን ድጋፍ አግኝተው በዘላቂነት እንዲቋቋሙ ለማድረግ ከምክር ቤቱ አባላት የተውጣጣ ራሱን የቻለ ቡድን እንዲቋቋም ውሳኔ አስተላልፏል።
ውሳኔውም በሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች በሚከሰቱ ግጭቶች በዜጎች ላይ የሚደርሰው ሞት፤ መፈናቀልና የንብረት ወድመት ትኩረት እንዲያገኝና ሁሉም ዜጋ በእኔነት ስሜት ችግሩን በዘላቂነት እንዲፈታ በር የሚከፍት ነው።
የተወካዮች ምክር ቤት ያሳለፈው ውሳኔ መንግሥት ለዜጎች ደህንነት የሰጠውን ትኩረት የሚያሳይ ነው። ይኸ ውሳኔ ፍሬ እንዲያፈራና የዜጎች ሞትና መፈናቀል በዘለቄታው እንዲቆም ሁሉም ኢትዮጵያዊ የዜግነት ግዴታ ያለበት ቢሆንም በዋነኝነት ሀገሪቱን ከሚያስተዳድረው መንግሥት የሚጠበቁ ተግባራት ግን አሉ።
በዋነኝነትም መንግሥት የኅብረተሰቡን የቆየ አብሮነት ለማስቀጠል ሕዝቡን ያሳተፈ ተከታታይና ቀጣይነት ያለው የፖለቲካ ሥራና ሕዝብን የማወያየት ሥራ መስራት ይጠበቅበታል። ቀደም ባሉት ጊዜያት የኢትዮጵያን አንድነት የማይፈልጉና የሕዝቦች አብሮነት የሚያማቸው የውስጥና የውጭ አካላት በሰሯቸው የመለያየትና የመበታተን ሴራዎች የሕዝቦች አንድነት ባይበጠስም መሸርሸሩ ግን የሚካድ አይደለም።
በመሆኑም መንግሥት የተሸረሸረውን አንድነት የመመለስ፤ የተሰበረውን ድልድይ የመጠገን ኃላፊነት ስላለበት ሳይውል ሳያድር ይህንኑ ወደ ተግባር ሥራ መለወጥ አለበት።
በሌላም በኩል የዜጎችን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥም ትኩረት ሊሰጠው ይገባል። ቀደም ባሉት ጊዜያት አንዱ በይ ሌላው የበይ ተመልካች ሆኖ ዓመታትን አሳልፏል። ይህ ደግሞ በዜጎች መካከል ልዩነት እንዲፈጠርና በርካቶችም ተስፋ እንዲቆርጡና በቀላሉም ወደሁከትና ብጥብጥ እንዲገቡ ገፊ ምክንያት የሆናቸው በመሆኑ መንግሥት ሁሉም ዜጋ በእኩልነት የሚኖርባት ሀገር እንድትሆን በርትቶ መስራት አለበት።
በሌላም በኩል መንግሥት እየወሰደ ያለውን እርምጃ አጠናክሮ እንዲቀጥልና ከዚህ ጎን ለጎን አመራሩን በማጥራት ጥፋተኞች ላይ ተገቢውን ሕጋዊ እና ፖለቲካዊ እርምጃ መውሰድና ውጤቱን ለሕዝብ ማሳወቁ በተመሳሳይ የጥፋት ተግባር ውስጥ ሊሳተፉ ለሚፈልጉ ኃይሎች ትምህርት ስለሚሆን ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት አጋዥ ሆኖ ያገለግላል።
መንግሥት ከሚያከናውናቸው ተግባራት ጎን ለጎንም ሁሉም ኢትዮጵያዊ ለፖለቲካዊ ጥቅም ሲሉ የሕዝብን ደም የሚያፈሱና የሚያፈናቅሉ አካላትን በግልጽ በማውገዝ፤ ከተሸሸጉበት መንጥሮ በማውጣትና ለሕግ አሳልፎ በመስጠት፤ መንግሥት የጀመረውን ተፈናቃይ ዜጎችን የመደገፍ ሥራ በማጠናከር ወደነበሩበት ቀዬ መመለስና በዘላቂነት የማቋቋም ሥራዎችን በመደገፍ ችግሩን በጋራ ክንድ ለመመከት ሊረባረብ ይገባል።
አዲስ ዘመን ጥር 14/2013