ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመቋቋም ትኩረት ሰጥታ እየሰራች ትገኛለች በዚህም ላለፉት በርካታ ዓመታት በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ችግኞችን የተከለች ሲሆን በተለይም ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ ለዘርፉ ልዩ ትኩረት ሰጥታ በማሰራቷ በአለም አቀፍ ደረጃ አድናቆት እንድታገኝ ከዛም አልፎ የክብረ ወሰን ባለቤት እንድትሆን በሌላ ጎኑ ደግሞ የተራቆቱ አካባቢዎቿ ልምላሜ እንዲታይባቸው አስችሏል።
የአካባቢ ጥበቃ ስራው በአገሪቱ ከብዙ ዓመታት በፊት ጠፍቶ የነበረውን የተስተካከለ የአየር ጸባይ በማምጣት ክረምትም አንደ ክረምትነት መውጪያና መግቢያውን ጠብቆ የተመጣጠነ ዝናብ ሰጥቶና ሌላም ሌላም እንዲያልፍ በማስቻሉ ለስራው ብዙዎች አድናቆትን እየቸሩ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደስልጣን ከመጡ በኋላ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥተው ከሰሩባቸውና አመርቂ ውጤትም ከታየባቸው ዘርፎች መካከል አንዱ የሆነው የአካባቢ ጥበቃ ስራ አሁን ላይ ለማመን በሚቸግር መልኩ የተራቆቱና ያገጠጡ መሬቶች በደን ለመሸፈን ዳር ዳር እያሉ ሳር እንኳን የማይታይባቸው ቦታዎች ልምላሜያቸው እየተመለሰ ነው።
ከሁለት ዓመት ወዲህ አጠናክረን የቀጠልንበት የአካባቢ እንክብካቤ ስራችን ሰው ከተባባረ ምንም ነገር ማድረግ የተጎዳንም አካባቢ ለም ማድረግ እንደሚችል ስለመሆኑ ምስክር መጥቀስ አያሻም።
ዘንድሮም አካባቢያችንን በችግኝ ለመሸፈን ለምናደርገው ጥረት መነሻ ይሆን ዘንድ አሁን ላይ በርካታ የችግኝ ማፍላት፣ የቦታ መረጣ እንዲሁም ሌሎች አስፈላጊ ነገሮች ሁሉ እየተከናወኑ ይገኛሉ። እኛም ይህንን አስመልክተን የተፋሰሶች ልማት ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ከሆኑት አቶ ጌታቸው ግዛው ጋር ቆይታን አድርገናል።
አዲስ ዘመን ፦በመላው አገሪቱ የተፋሰስ ስራዎች እየተካሄዱ እንደሆነ ይታወቃል፤ እስከ አሁን ባለው ሁኔታ ስራው ምን መልክ አለው?
አቶ ጌታቸው፦ የተፋሰስ ልማት ስራዎችን መስራት ከጀመርን ሁለት አስርተ አመታትን አስቆጥረናል። እነዚህ ስራዎች ደግሞ ያስገኙት ውጤት ቢኖርም የተደከመባቸው ያህል ግን አይደሉም። ይህንን እንደመነሻ በማድረግ ግን ላለፉት ሁለት ዓመታት በተለየ መንገድ ስራው እንዲመራ ተደርጎ በርካታ ተግባራትም እየተከናወኑ ነው።
በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ሃሳብ አመንጪነት አገራዊ የአረንጓዴ አሻራ ፕሮግራም ተቀርጿል። በዚህም መሰረት በአራት ዓመት ውስጥ 20 ቢሊየን ችግኝ ለመትከልም በ2011 ዓ.ም ስራው በይፋ ተጀምሯል። በዚሁ ዓመትም “40 ዛፍ በነፍወከፍ” በሚል መሪ ቃል አራት ቢሊየን ችግኝ እንተክላለን ብለን አቅደን 4 ነጥብ 7 ቢሊየን ችግኝ ለመትከል ተችሏል። በቀጣዩ ዓመትም ምንም እንኳን የኮሮና ቫይረስ ቢከሰትም “እየተጠነቀቅን እንተክላለን” በሚል መሪ ቃል ጥንቃቄ በተሞላበት ሁኔታ ሰፊ የህዝብ ንቅናቄ ስራ በመስራትና አምስት ቢሊየን ችግኝ የመትከል ስራ እንሰራለን ብለን 5 ነጥብ 9 ቢሊየን ችግኝ መትከል ተችሏል።
የሁለቱ ዓመት አፈጻጸም ሲታይም በጠቅላላው 10 ነጥብ 7 ቢሊየን ችግኝ ለመትከል ተችሏል። ከዚህ አንጻር የተከናወኑት ስራዎች በጣም ውጤታማ በመሆናቸው በተያዘው ዓመትም እነዚህን ተሞክሮዎች በመቀመር 6 ቢሊየን ችግኝ እንተክላለን በሚል እቅድ ስራዎች በሁሉም ደረጃ ተጀምረዋል።
በመሆኑም በሁለቱም አመታት የነበረው የተፈጥሮ ሃብት ልማት ስራችን የአመራር ትኩረት በተለየ ቅንጅታዊ አሰራርና በእቅድ የተመራ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የተሻለ ውጤት የተመዘገበበት ነው ማለት ይቻላል።
በሌላ በኩል “ባለቤት የሌለው ችግኝ አንተክልም” በሚል መነሻ ነው እነዚህን ችግኞች ወደመትከል ስራው የተገባው፡፡ በመሆኑም እስከ አሁን የተተከሉት ችግኞች በሙሉ ባለቤት አላቸው፤ በዚህ ስራ ውስጥም ያልተሳተፈ የህብረተሰብ ክፍል የለም። በዚህም ሰዎች ከሚኖሩበት ግቢ ጀምረው በስራ ቦታቸው እንዲሁም ከስራ ባልደረቦቻቸው። ከጓደኞቻቸው። ከቤተሰቦቻቸው ጋር በቡድን እየሆኑ ወጣ ብለው እስከመትከል ድረስ ከፍተኛ የሆነ መነሳሳት የታየበትም ነው።
ከዚህ በመነሳትም ይህ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከህዳሴው ግድባችን ቀጥሎ እንደ አገር ትልቅ አንድነትንና መነቃቃትን የፈጠረ ተግባር ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል።
በሌላ በኩልም ይህ የተቀናጀ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ሁሉንም ተቋማት በአንድ ያሳተፈ የውሸት ሪፖርትንና ድግግሞሽን መቶ በመቶም ባይሆን በጣም የቀነሰ፤ በበቂ ዝግጅት የተገባበት ስራ በመሆኑ ስራው ባለፉት ሁለት አመታት በጣም ውጤታማ ነበር።
አዲስ ዘመን ፦ ይህ የተፈጥሮ ሃብት እንክብካቤያችን ከራሳችን አልፎ ጎረቤት አገሮችም እንዲሳተፉበት ለማድረግ እንደሚሰራ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሲናገሩ ተደምጠዋልና፤ ዘንድሮ እነሱን የሚያሳትፍ ዝግጅት ተደርጓል ለማለት ይቻላል?
አቶ ጌታቸው፦ አዎ በዚህ ዓመት ያቀድነው ሰባት ቢሊየን ችግኞች ለማዘጋጀት ነው። ከዚህ ውስጥ ደግሞ አንዱን ቢሊየን ለጎረቤት አገሮች ነው የምንሰጠው ብለናል። ምክንያቱም የተፈጥሮ ሃብት ስራ በአገር ድንበር የታጠረ ብቻ አይደለም፤ ተፋሰሶቻችንን የምንጋራ ከመሆናችን አንጻር ያንን የሚመጥን ቀጠናዊ የአካባቢ ጥበቃ ስራ በጋራ መስራት ያስፈልጋል። ይህንን አካሄድ እያሰፋን መምጣት ከቻልን ደግሞ አጠቃላይ በአየር ንብረት ተጽዕኖ የመጋለጥ እድላችንን በከፍተኛ ሁኔታ የመቀነስ ሚና ይኖረዋል። በአገር ግንባታ ገጽታ ላይም ከፍተኛ የሆነ ትርጉም ይፈጥራል።
በመሆኑም የእኛን አረንጓዴነት ብቻ ሳይሆን የጎረቤቶቻችንንም ልምላሜ ስለሚያስፈልግ ከእነሱ አገር የአየር ጸባይ ጋር ሊስማሙ የሚችሉ ችግኞችን በመምረጥ እየተዘጋጀም ይገኛል።
በአገር ውስጥ ይተከላል ተብለው ከተያዙት ስድስት ቢሊየን ችግኞች ውስጥም ከ 60 በመቶ የማያንሱት የደን ዝርያ እንዲኖራቸው ነው የታሰበው። ከዚህ የቀሩት ደግም የጥምር ግብርናና የውበት ዛፍ እንዲሆኑ እየተሰራ ነው። አስተካክሎ በዚህ መልኩ መሄዱ ደግሞ በተለይም ለደን ሽፋናችን አስተዋጽዖ እንዲኖረው ከማድረጉም በላይ በተራሮች አካባቢ በአብዛኛው የሚተከለው የደን ተክሎች ስለሚሆኑም ከዚህ አንጻርም የታየ ነው።
አዲስ ዘመን ፦ እዚህ ከላይ ግን ብዙ ጊዜ ችግኞች ሲተከሉ ከውጭ የሚመጡ እንደውም በተፈጥሮ ሀብቱ ላይ የሚኖራቸው በጎና መጥፎ ጎን የማይለይ ተክሎች የሚበዙበት ሁኔታ ነበርና እንደው ዘንድሮ ለአገር በቀል ችግኞች የተሰጠው ትኩረት ምን ይመስላል?
አቶ ጌታቸው፦ አዎ ዘንድሮ ከሚተከለው ችግኝ እስከ 30 በመቶ ድረስ አገር በቀል እንዲሆኑ ታስቦ እየተሰራ ነው። ይህም የአገራችንን ሀብት ከማስተዋወቅ አንጻር፤ ከፍ ያሉ አገር በቀል ዝርያዎችም በደንብ እንዲያገግሙና እንዲስፋፉ እድል የሚሰጥ በመሆኑ፤ በዚህ መልኩ ለማስኬድ ታቅዶ እየተሰራ ነው።
በሌላ በኩልም እስከ 50 በመቶ የሚሆኑት ችግኞች በሚፈሉበት ወቅት በፕላስቲክ መያዣ እንዲሆኑ ታስቧል፤ ይህም ለችግኞቹ በቂ እርጥበት በመስጠት ውጤታማ ስራን ለመስራት ያግዛል።
አዲስ ዘመን ፦ በዚህ ዓመት ለሚፈሉት ችግኞች ምን ያህል ችግኝ ጣቢያዎችስ ተዘጋጅተዋል ማወቅ ከተቻለ?
አቶ ጌታቸው፦ በዚህ ዓመት ለሚፈሉት 108 ሺ ችግኝ ጣቢያዎች ያስፈልጉናል ብለን ለይተናል። 8 መቶ ሺ ሄክታር መሬትም ችግኞቹን ለመትከል እንደሚያስፈልግ ተረጋግጧል። የዘንድሮውን አካሄድ ጥሩ የሚያደርገው መጀመሪያ ቦታዎቹን ከለየን በኋላ ችግኞቹን ወደማፍላት መሄዳችን ነው። ይህ ደግሞ ቀደም ሲል ይኬድበት ከነበረው አካሄድ የሚለይና እቅድ ላይ የተመሰረተ ስራ መሰራቱን የሚያመላክት ነው።
በሌላ በኩልም በመረጃ አያያዝ ስርዓታችን ከምንተክላቸው ችግኞች 2ነጥብ 5 ሄክታር መሬት በላይ ላይ የሚተከሉ ችግኞች በሙሉ ካርታ እንዲሰራላቸው መረጃቸውም በተደራጀ ሁኔታ እንዲያዝ ተደርጓል። በዚህም የተተከለው ችግኝ ከየትኛው ሚኒስቴር መስሪያ ቤት አልያም ከየትኛው የችግኝ ጣቢያ ነው የሚለውን በትክክል የሚታወቅ በመሆኑ ለክትትል ከማመቸቱም በላይ የውሸት ሪፖርቶችንም በማስቀረት በኩል ሚናው ከፍ ያለ ነው።
አዲስ ዘመን ፦ ዘንድሮው የችግኝ ተከላ ከመቼ እስከ መቼ ነው ሊካሄድ የታቀደው?
አቶ ጌታቸው ፦ ችግኝ ተከላው የሚጀምረው ከሀምሌ ጀምሮ ባሉት የክረምት ወራት ነው። ነገር ግን ይህ አጀማመር እንደ የአካባቢው የተፈጥሯዊ አቀማመጥና የአየር ጸባይ ሁኔታ ይለያያል። በዚህም ዝናብ ቀድሞ ከሚገባበት ለምሳሌ እንደ ደቡብ የአገሪቱ ክፍል ያሉት ቀድመው ተከላውን ይጀምራሉ። ወደ ምስራቁ የአገሪቱ ክፍል ደግሞ ዘግየት ብሎ ስለሆነ የሚጀምረው በሚጀምርበት ወቅት እንዲተከል ይሆናል። ለዚህም ነው ባለፈው አመት የችግኝ ተከላ ፕሮግራሙ ስነስርዓት በሃዋሳ የተካሄደው።
በሌላ በኩል ግን የችግኝ ዝግጅቱ በተለይም አገር በቀሎቹ በችግኝ ጣቢያ ላይ እስከ አመት ድረስ መቆየት የሚፈልጉ ስላሉ እነሱን ታሳቢ በማድረግ ቀደም ብሎ የማፍላት ስራው ተጀምሯል። አሁን ላይ የአብዛኛው ችግኝ ቢያንስ የግዢ ሂደቱ ተጠናቋል።
አዲስ ዘመን፦ የችግኝ ተከላ ፕሮግራሙ በተለይም ባለፉት ሁለት አመታት በጥሩ ሁኔታ ከመሰራቱ አንጻር በተፋሰስ ልማቱ ላይ ያመጣው ውጤት እንዴት ይገለጻል?
አቶ ጌታቸው፦ በመሰረቱ እነዚህ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብሮች የሚጠበቅባቸውን ውጤት ለማምጣት ከችግኝነት ወደዛፍነት መቀየር አለባቸው።
በመሆኑም ባለፈው ዓመት ተክለነው በዚህ ዓመት ምን ውጤት አመጣ ብለን አንጠብቅም፤ ነገር ግን ፈጠን ብለው የሚደርሱ የፍራፍሬ አይነቶች ውጤታቸውም በቶሎ ሊታይ የሚችልበት አግባብ ሰፊ ነው።
እዚህ ላይ ችግኝ ተከላ በዚህ ደረጃ የህብረተሰቡን ልብ ሊገዛ የቻለውም የዛሬን ሳይሆን ነገን ታሳቢ የሚቀጥለውን ትውልድ ማዕከል አድርጎ የሚሰራ ስራ በመሆኑ ነው። ዛሬ ላይ የማናያቸው ዛፎች ከኛ ብዙ ቀድመው የነበሩ ወገኖቻችን የተከሉልን ነው። እኛም ዛሬ የምንተክላቸው ችግኞች ለሚቀጥለው ትውልድ ስነ ምህዳሯ የተጠበቀ መሬትን ለማስረከብ የሚያስችል ነው። በመሆኑም የተከልናቸው ችግኞች ዛሬ ላይ ይህንን አምጥተዋል ብሎ መመዘን በጣም ከባድ ነው።
ነገር ግን አሁን ቢሆን ችግኝ የተተከለባቸው አካባቢዎች ከሰውም ሆነ ከእንስሳት ንክኪ ስለሚከለሉና ነጻ ስለሚሆኑ በተለይም የአፈርን መከላት ለመከላከል የሚያስችሉ ሳሮችን ሌሎችንም በማብቀል የአፈር መከላትን በከፍተኛ ሁኔታ እየተከላከሉ ነው።
አዲስ ዘመን ፦ እስከ አሁን በችግኝ የተሸፈነው ምን ያህል ሄክታር መሬት አለን ለችግኝ ተከላውስ የወጣው ሀብት ምን ያህል ነው?
አቶ ጌታቸው፦ አብዛኛው የችግኝ ተከላ ስራ በበጎ ፈቃደኝነት የሚሰራ ነው። በዚህም ከ 90 በመቶ በላይ ስራው በነጻ የሰው ጉልበት የተሰራም ነው። አስር በመቶ ለሚሆነው የሰው ሃይል ደግሞ በጀት ከክልሎችም ከፌደራል መንግስትና በተለያየ መንገድ እየተመደበ የሚሰራ በመሆኑ በትክክል ይህንን ያህል ገንዘብ ወጥቷል ብሎ ለመናገር ይከብዳል። ግን ደግም ቀላል ሃብት እንዳልሆነ መገመት ይቻላል።
አዲስ ዘመን ፦ ህብረተሰቡ ችግኞችን ከመትከል ባሻገር በመንከባከቡ በኩል ያለው ገንዛቤ አድጓል ማለት ይቻላል?
አቶ ጌታቸው፦ እንደ ውስንነት የምናየው በተለይም መትከሉ ላይ ያለው ዘመቻ መንከባከቡ ላይ አይታይም። በዛ ግለትም የተሰራ የመንከባከብ ስራ የለም። በዚህ በኩልም ብዙ መሰራት የሚፈልግ ይመስለኛል።
ባለፈው ወር የ2012 ዓም የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር መላው ክልል የሰራውን ስራ ገምግመናል በዚህም ምን ያህል ችግኝ ተተክሎ ምን ያህሉ እንደታረመና ውሃ እንደጠጣ፤ በወቅቱም ያገኘነው ነገር መሻሻሎች እንዳሉ አመላካች ነበር። ይህ ሁኔታ በፌደራል ተቋማትም ደረጃ ካየነው ጥሩ የሚባሉ ነገሮች አሉት።
ለምሳሌ የእኛ ባለስልጣን በቅርቡ የተከላቸውን ችግኞች ለማየትና ለመንከባከብ እቅድ ይዞ ነበር፤ በአየር ጸባዩ ደመናማነት ምክንያት አልተሳካም። በቀጣይ ግን ሄደን ለማየትና ለመንከባከብ አቅደናል። በዚህ ሁኔታ ስናየው የፌደራል ተቋማት የተከሏቸውን ችግኞች ተመልሰው የማየት ሁኔታ እንዳለ በመገናኛ ብዙሀንም እያየን ነው፤ አንዳንዶቹ እንደውም በቋሚነት ተክሎቹን የሚንከባከብ ሰው ቀጥረዋል። ግን እንደመርህ የያዝነው “ባለቤት የሌለው ችግኝ አንተክልም፤ የተከልነውንም እንከባከባለን” የሚል አቅጣጫ ተቀምጦ ወደ ስራ ስለተገባ እንክብካቤው ከአመት አመት መሻሻሎች እንዳሉ ነው።
ተከላው ላይ በተፈጠረው ከፍተኛ መነሳሳትም አርሶ አደሩም የመንግስት ሰራተኛውም ሌላውም ሌላውም ስለ ችግኝ ሲጠየቅ “የተከልኩትን እየመጣሁ እንከባከባለሁ “ ይላል፤ ይህ ምናልባትም ሰውየው ባያደርገው እንኳን ለሌሎች የሚያስተላልፈው መልዕክት ቀላል አይደለም። በመሆኑም በንቃተ ህሊና ደረጃ ጥሩ ግንዛቤ ተፈጥሯል። በተግባር ደረጃ ግን የሚቀሩት ነገሮች ይኖራሉ።
አዲስ ዘመን ፦ ክልሎችን ሰብስባችሁ ስራዎችን ገምግማችሁ ከነበር እንደው ውጤታማነቱም ከክልል ክልል ይለያያል ብዬ አስባለሁና እናንተ ምን ታዘባችሁ? ለተሞክሮ የሚሆን ውጤታማ ስራን የሰራውስ ክልል የትኛው ነው?
አቶ ጌታቸው፦ በባለፉት ዓመታት ከተከልናቸው ችግኞች 47 እና 48 በመቶ የሚሆኑት ኦሮሚያ ክልል ላይ ነው። በዚህም ክልል ከተከላ ዝግጅቱ ጀምሮ በእንክብካቤ ምዕራፉ ላይም እየሰራ ያለው ስራ በጣምም ተሞክሮ የሚወሰድበት ነው።
አማራም ደቡብም ሌሎችም ካቀረብናቸው ችግኞች 85 በመቶ ሊባል በሚችል ደረጃ ማጽደቅ እንደቻሉ ነው መረጃ ያቀረቡት። በዚህም በርካታ ችግኞች እንክብካቤ ተደርጎላቸዋል፤ ደስ የሚልም አፈጻጸም እንዳለ ነው የሚያሳየው።
ከዚህም በተጨማሪ እንደ ባለስልጣን መስሪያ ቤት ሪፖርቱን ለማጥራት ቡድን አደራጅተን ወደ አካባቢዎቹ ልከናል፡፡ በዚህም የተተከሉት ችግኞች ምን ላይ ነው ያሉት የሚለውን እንዲሁም ለ2013 ዓ.ም የችግኝ ተከላ እየተደረገ ያለው ዝግጅት ምን ይመስላል የሚለውን አይተውም ለመምጣት ወደ ሁሉም ክልሎች ልከናል።
እነዚህ ሁሉ ስራዎች የሚከናወኑትም እንደ አገር በዘርፉ የተሰራውን ስራ የሚያሳይ ትክክለኛ መረጃን ለመያዝ ሲሆን ሌላው ደግሞ ተከላ ብቻ ሳይሆን እንከብካቤውም የስራው አካል መሆኑ ታውቆ ለዛም በቂ ትኩረት እንዲሰጠው ለማመላከት ያለመም ነው።
አዲስ ዘመን ፦ የተፋሰስ ስራ ጠንከር ብሎ ከሚሰራባቸው እንደውም ቀደም ብሎም ከሚጀመርባቸው ክልሎች አንዱ የትግራይ ክልል ነውና ፤ ዘንድሮ እየተካሄደ ካለው የህግ ማስከበር ዘመቻ አንጻር ስራውን እንዴት ለማስኬድ ነው የታቀደው?
አቶ ጌታቸው፦ ባለፈው አመት 79 ሚሊየን ችግኞች በትግራይ ክልል ብቻ ለመትከል ተችሏል። የአካባቢው ማህበረሰብ በአካባቢ ጥበቃ ላይ ጥሩ ተሞክሮ ያለው ነው፤ እንደ አብርሃ አጽብሃ ያሉ ቦታዎች ደግሞ በተፋሰስ ልማቱ ላይ እንደ ሞዴል የሚታዩም ናቸው። ይህ ደግሞ በአገራችን ብቻ ሳይሆን በአፍሪካም እውቅና ያገኘንበት ነው። በመሆኑም አካባቢው በተፈጥሮ ሃብት ልማት ስራዎች ትምህርት ሊሆኑ የሚችሉ ስራዎች ሲሰራ ቆይቷል፤ በባለፈው ዓመት እንኳን ከእቅዱም ከተከላውም አንጻር ጥረት ያለ ስራና መረጃን ሲያቀርብ የነበረ ነው። በተያዘው ዓመትም የባለፈውን ዓመት እቅድ አፈጻጸም መነሻ በማድረግ በእቅድ ውስጥ ተይዟል፤ በቀጣይ የሚኖረውን ሁኔታ እያየንና ጊዜያዊ አስተዳደሩም ሙሉ ትኩረቱን ወደልማት ስራው ማድረግ በሚችልበት ጊዜ የባለስልጣኑ የቴክኒክ ኮሚቴም ተገቢውን ድጋፍ በማድረግ ስራቸውን እንዲቀጥሉ የሚደረግ ይሆናል። ግን እንደ ሁሉም ከልሎች በእቅድ ውስጥ ገብቷል።
አዲስ ዘመን ፦ በዚህ የተፋሰስ ልማት ወይም የአካባቢ ጥበቃ ስራችን ብዙ እየሄድን ከመሆኑ አንጻር በዚህን ያህል አመት እዚህ ጋር እንደርሳለን ተብሎ የተቀመጠ ግብ ይኖር ይሆን ?
አቶ ጌታቸው፦ ፕሮግራሙ የአራት አመት ነው በእነዚህ ዓመት ደግሞ 20 ቢሊየን ችግኞችን እንተክላለን ብለን ግብ ጥለን እየሄድን ነው። እዚህ ላይ ቆመን ደግሞ የሚቀጥለው አካሄዳችን ምን ይምሰል የሚለውን የምናቅድ ይሆናል።
አዲስ ዘመን ፦ እርስዎ በዝግጅቱም ላይ በእንክብካቤው እንዲሁም በጠቅላላው በሂደቱ ላይ ባይሆን ብለው የሚሉት እንዲሁም ሊጠናከር ይገባል ብለው የሚያነሱት ሃሳብ ካለ?
አቶ ጌታቸው፦ የተሰሩት ስራዎች ለችግሮቻችን ሁሉ መድሃኒት ናቸው። የአየር መዛባት የማይነካው ሴክተር የማይነካው ህይወት የለም። ከዚህ አንጻር የተፈጥሮ ሃብታችንን ስንከባከብ ነው መሬት ያላትን ልትሰጥ የምትችለው። የውሃ ሃብታችንም በጥራቱም በመጠኑም መጠበቅ የሚችለው የሰራናቸው ትልልቅ የውሃ መሰረተ ልማቶች ደህንነታቸው ተጠብቆ ረዘም ላሉ ዓመታት ሊያገለግሉን የሚችሉት በውሃ አካላቶቻችን ላይ ያሉት የመጤ አረሞች ከምንጫቸው ሊደርቁ የሚችሉት የተፈጥሮ ሃብታችንን መንከባከብ ስንችል ነው። ምርትና ምርታማነት የሚጨምረው የምንተነፍሰው አየር ጤናማ የሚሆነው የተፈጥሮ ሃብቱን በተንከባከብነው ቁጥር ነው። የተጎሳቆለ ስነ ምህዳር ላይ ጤናማ ኢኮኖሚ መገንባት አይቻልም። በመሆኑም ኢኮኖሚያችን ጤናማ እንዲሆን ከፈለግን በስነ ምህዳር ላይ የምናደርገውን ስራ በቅንጅትና በትብብብር በባለቤትነት ስሜት ልናከናውነው ይገባል።
ችግኝ መትከል ግብ ሳይሆን ጅማሮ ነው። ስለዚህ ያልተከልነውን ቸግኝ ስለማንከባከበው አንዲሁም ያልተንከባከብነውን ደግሞ ዛፍ ሆኖ ለማየት ስለማንጓጓ በመትከል ላይ የምናሳየውን ርብርብና የተጋጋለ ስሜት በመንከባከቡ ላይም ሊደገም ይገባል።
አሁን ዘር የሚዘጋጅበት ወቅት ነው፤ በመሆኑም ዛሬ ላይ ሊደርሱ የሚችሉ ችግኞችን በክረምት ወቅትም ቢተክሉ ፍሬያማ ሊሆኑ የሚችሉትን በማሰብ መዘጋጀቱ ኋላ ለውጤቱ ማማር ድርሻው የጎላ ስለሆነ ዛሬ ለይ ጥራቱን እየተቆጣጠርን መስራት ይገባናል።
ከዝግጅት በተጓዳኝ ግን አምና የተከልናቸው ችግኞች ውሃ መጠጣት የሚፈልጉበት የበጋ ወቅት በመሆኑ የማረም፣ የመኮትኮት እና የመንከባከብ ስራችንን አጠናክረን በመደበኛ ስራችን ውስጥ ልናካትተው እንዲሁም ልምድ ልናደርገው እንደሚገባ መግለጽ እፈልጋለሁ።
አዲስ ዘመን ፦ ለነበረን ቆይታ በጣም አመሰግናለሁ።
አቶ ጌታቸው ፦ እኔም አመሰግናለሁ
አዲስ ዘመን ጥር 10/2013