አዲስ አበባ፡- የማህበረሰቡን ችግር መፍታት ላይ የሚያተኩር ‹‹ሶልቭኢት›› የቴክኖሎጂ ፈጠራ ውድድር ከ1ሺ500 በላይ ወጣቶችን በማሳተፍ ለሁለተኛ ጊዜ ትናንት በይፋ ተጀምሯል፡፡
በኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በተደረገ ይፋ የመክፈቻ ስነስርአት ላይ በኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የኢኖቬሽን ልማት እና ምርምር ዳይሬክተር ጀነራል የሆኑት አቶ ካሊድ አህመድ እንደተናገሩት፤ ተወዳዳሪዎቹ ጥቃቅን እና አነስተኛ ኢንዱስትሪዎች እንዲሁም መሰረታዊ የማህበረሰብ ችግሮችን የሚፈቱ የቴክኖሎጂ ፈጠራዎችን በመስራት ይሳተፋሉ፡፡ በፈጠራ ባለሙያዎቹ የሚሰሩ ችግር ፈቺ ቁሶች ወደገበያው እንዲገቡ ለማድረግ እገዛ ይደረጋል፡፡
በአይኮ ግላብስ ‹‹የሶልቪት›› የፕሮጀክት አማካሪ የሆነው ወጣት ህሩይ ፀጋዬ ውድድሩን አስመልክቶ እንደገለፀው፤ በኢትዮጵያ የተሻሻለ ቴክኖሎጂን በመፍጠር የማህበረሰብን ችግር የማቃለል ልምድ ወደኋላ የቀረ ነው፡፡ ቴክኖሎጂ ቅንጦት እና ለአደጉት አገራት ብቻ የሚሰራ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ በዚህ መነሻ የቀን ተቀን ችግር ለመፍቻ እና ኢንዱስትሪዎችን ለማዘመን ይህን ውድድር ማካሄድ አስፈላጊ ሆኗል፡፡ በሁሉም አገሪቷ የሚገኙ የፈጠራ ሃሳብ ያላቸው ወጣቶች ስልጠና በመስጠት እንዲሳተፉ ይደረጋል፡፡ ሃሳባቸውንም ገበያ ላይ ሊውል ወደሚችል የቴክኖሎጂ ውጤት እንዲቀይሩ ድጋፍ ይደረግላቸዋል፡፡
በሶልቭኢት የመጀመሪያ ዙር ውድድር ላይ የኦክስጂን ቴራፒ (በደም ውስጥ ያለውን የኦክስጂን መጠን የሚለካ) ቴክኖሎጂ፣ከባህላዊ መጠጦች ከሚገኝ ተረፈ ምርት ውጤት የኤሌክትሪክ ማመንጫ ቴክኖሎጂ እንዲሁም በተለያየ ምክንያት እቃዎችን እንዳንዘነጋ የሚያስታውስ ‹‹ሄሎ ሪማይንደር›› ቴክኖሎጂን የፈጠሩ ወጣቶች አሸናፊ ሆነዋል፡፡
የሁለተኛው የሶልቭኢት ውድድር በ15 ከተማዎች የሚካሄድ ሲሆን አዲስ አበባ፣ አርባ ምንጭ፣ አክሱም፣ ድሬዳዋ፣ ጎንደር፣ ጋምቤላ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ውድድሩ ከመካሄዱ በፊት ሁሉም ተሳታፊዎች ሃሳባቸውን ወደ ተግባር የሚቀይሩበትን መንገድ የሚያመላክት የድጋፍ ስልጠና ይወስዳሉ፡፡ ስራቸውን የሚያከናውኑበት የገንዘብ ድጋፍም ይደረግላቸዋል፡፡
‹‹ሶልቭኢት›› የቴክኖሎጂ ፈጠራ ውድድር አሜሪካ ኤምባሲ፣ የጃፓን ዓለም አቀፍ ትብብር ኤጀንሲ እንዲሁም የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እንደሚደግፉት ታውቋል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር26/2011
ዳግም ከበደ