ፍሬህይወት አወቀ
በቡና እርሻ ሥራ ሕይወታቸውን ከሚመሩ ቤተሰቦች የተገኙ ጎልማሳ ናቸው። ከአያት ቅድመ አያታቸው ለተጀመረው የቡና ሥራ እርሳቸው ሶስተኛ ትውልድ ሲሆኑ፤ ቤተሰባቸው ያመረተውን የቡና ምርት በወቅቱ በነበረው ሥርዓት አማካኝነት የኢትዮጵያ ቡና ቦርድ ለተባለ ድርጅት ያቀርቡ ነበር። ቤተሰቦቻቸው ያመረቱትን እንዲሁም ከአካባቢው አርሶ አደር የሰበሰቡትን ቡና ለቡና ቦርድ በሚያቀርቡበት ወቅት እርሳቸው የነበራቸው ተሳትፎ ቀላል ግምት የሚሰጠው አልነበረም።
ምንም እንኳን ዛሬ የአርሶ አደሩን ምርት ለመግዛት ነጋዴው አርሶ አደሩ ማሳ ድረስ የሚጓዝና አርሶ አደሩም በቀላሉ ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሶ በፈለገው ቦታ ምርቱን መሸጥ ቢችልም፤ ያኔ አርሶ አደሩ ያመረተውን የቡና ምርት ለመንግስት ለመሸጥ ቀን ከለሊት ወረፋ መጠበቅ የግድ ይለው ነበር። ታዲያ የቡና አምራች አርሶ አደር ወጣት ልጆችም በቡና ቦርድ ደጃፍ ላይ ቡናቸውን በያዘው ኬሻ ላይ ተቀምጠው ፈቀቅ ፈቀቅ እያሉ ወረፋ እንዳያልፋቸው በመጠበቅ ቡናቸው እንዲሸጥ የጎላ ሚና ነበራቸው።
ቡና እንዲሸጥ ወረፋ በመጠበቅ የጎላ ሚና ከነበራቸው የዘመኑ ወጣቶች መካካል አስተዋዩ አቶ እስራኤል ደገፋ ዛሬ ቡና ለመሸጥ ሲጠብቁት ከነበረው ወረፋ ተሻግረው የቡና ወጭ ንግድ (ኤክስፖርት) ስራ ላይ ተሰማርተዋል። ያኔ በለጋ እድሜያቸው የቤተሰባቸውን ቡና ለመሸጥ ትልቅ ተሳትፎ የነበራቸው አቶ እስራኤል፤ ለማንነት ትልቅ ቦታ የሚሰጥ ስብዕና ያላቸውና የሰው ልጅ ያለፈበትን፤ የኖረበትን፤ የትናንት ማንነቱን መርሳት የሌለበትና ትናንትን ማስታወስ ለውጤት ያበቃል ብለው በጥብቅ የሚያምኑ ናቸው። እኛም በጥልቅ ከሚያውቁትና ከኋላ ታሪካቸው ተነስተው በስኬት ጎዳና መሰለፍ የቻሉትን እኚህን ውጤታማ ሰው በዛሬው የስኬት እንግዳችን አቅርበናቸዋል።
ትውልድና እድገታቸው በደቡብ ክልል ጉጂ ዞን ቡና አብቃይ ወረዳ በሆነችው ቀርጫንሼ አካባቢ ነው። የድርጅታቸው መጠሪያ ‹‹ቀርጫንሼ›› መባሉም በምክንያት የሆነና የዛሬ ማንነታቸው በትናንት መሰረታቸው ላይ የጸና ለመሆኑ ማረጋገጫ ነው።
የቀርጫንሼ ቡና ላኪ ድርጅት ዋና ስራ አስፈጻሚው አቶ እስራኤል፤ እንደማንኛውም የአርሶ አደር ልጅ ከትምህርት ጊዜያቸው ውጭ ያለውን ሙሉ ጊዜ ቤተሰባቸውን በስራ በማገዝ ነው ያደጉት። በተለይም ከቡና አብቃይ አርሶ አደር የተገኙት እንደመሆናቸው ቡናው በሚደርስበት ወቅት የሚኖራቸው ተሳትፎ ከፍተኛ በመሆኑ የቡና ሥራን ጠንቅቀው ያውቁታል።
የሁለተኛ ደረጃ እና የዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን አዲስ አበባ ከተማ በመምጣት ተከታትለዋል። ይሁንና በተማሩት ትምህርት ተቀጥረው መስራት ወይስ ወደ ትውልድ ቦታቸው ተመልሰው ቤተሰባቸውን መርዳትና ካሳደጋቸው ማህበረሰብ ጋር ተጋግዞ ሰርቶ መለወጥ የሚሉ ሁለት አማራጮችን ለራሳቸው አቀረቡ።
በወቅቱ ጓደኞቻቸው የትምህርት ዕድል እያገኙ ወደ ውጭ ሀገር ሄደዋል። ይሄ ያላማለላቸው አቶ እስራኤል፤ ከብዙ ክርክር በኋላ ተቀጥሮ መስራትም ሆነ ወደ ውጭ ሀገር ሄዶ መማር ለምኔ ብለው ወደ ትውልድ ቦታቸው ቀርጫንሼ ተመለሱ።
ቤተሰብን ጨምሮ ጎረቤትና አጠቃላይ ማህበረሰቡ በልጆች ላይ ከፍተኛ ተስፋ እንዳለው ይታመናል። ልጆቼ ተምረው ያልፍልኛል ከሚለው ቤተሰብ ባለፈ ማህበረሰቡ በራሱ ልጆች በመማራቸው አካባቢንና ሀገርን ይቀይራሉ ብሎ የሚያምን በመሆኑ ቤተሰብም ሆነ ማህበረሰቡ ለመማራቸው የጎላ ድርሻ እንደነበረው ያነሳሉ።
በዚህም ለትምህርት ረጅም ርቀት ተጉዘው በሄዱበት ስፍራ ውሃ ጠማን ያሏቸው ሁሉ ተማሪ ይርበዋል በማለት ከውሃ በተጨማሪ የሚመገቡትን በመስጠት ማህበረሰቡ ትልቅ ተሳትፎ ነበረው። የማህበረሰቡ ተሳትፎ ታዲያ በውስጣቸው ሰፊ ቦታ የነበረው በመሆኑ ለዚህም አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ማድረግ የሚያስችል ሥራ ለመስራት እንደተነሳሱ ይናገራሉ።
በወቅቱ የነበረው የገበያ ሥርዓት ነጣቂ ሥርዓት ነው የሚሉት አቶ እስራኤል፤ አርሶ አደሩ ምርቱን ለመሸጥ ቦታ የለንም ተብሎ ምርቱን ጥሎ የሚመለስበት ወቅት እንደነበር ያስታውሳሉ። ይህ የአርሶ አደሩ ችግር ዘልቆ የተሰማቸውና ቁጭት የገባቸው አቶ እስራኤል መነሻቸውን አልረሱምና በአካባቢያቸው የቡና ሥራን ጀመሩ።
ወደ ስራው ሲገቡ በቅድሚያ አርሶ አደሩ ቡናውን የሚሸጥበት ምቹ ሁኔታ በመፍጠር የነበረውን ዋጋ ለማስተካከልም የምርት መሰብሰቢያ ወቅት ሳይደርስ ፋይናንሱን የማዘጋጀትና ከባንኮች ጋር ያለውን ግንኙነት አጠናከሩ። ከዛም የመጀመሪያውን የቡና ማጠቢያ ማሽን በአካባቢያቸው ሲተክሉ በወቅቱ የአንድ ኪሎ እሸት ቡና ዋጋ 75 ሳንቲም የነበረውን ወደ ሁለት ብር ከሃምሳ ሳንቲም ከፍ አደረጉ። አርሶ አደሮችን የተሻለ ተጠቃሚ ለማድረግ በማሰብም ዋጋውን በየዓመቱ በማሻሻል በአሁኑ ወቅት የአንድ ኪሎ እሸት ቡና ዋጋ እስከ 25 ብር ደርሷል።
ይህ ዋጋ ካለፈው የተሻለ ይሁን እንጂ አሁንም ቢሆን በሀገሪቱ ካለው የኑሮ ውድነት አንጻር በቂ እንዳልሆነና ከምርታማነቱ አኳያ አርሶ አደሩ ምርቱን በዚህ ዋጋ ሸጦ ሕይወቱን ያሻሽላል የሚል እምነት እንደሌላቸው የሚናገሩት አቶ እስራኤል፤ አርሶ አደሩን ለማገዝ በርካታ ጥረቶችን እያደረጉ ነው።
በመሆኑም ድርጅታቸው ቀርጫንሼ በሀገሪቱ በተለያዩ ክልሎች በጉጂ፣ በጌዲዮ፣ በጅማ፣ ምዕራብ አርሲና ባሌ ዞን ከሚገኙ 56 ሺ ቡና አብቃይ አርሶ አደሮች ጋር በጋራ እየሰሩ ናቸው። እነዚህ አርሶ አደሮች የድርጅቱ የሼር አባል ሆነው የሚቆጠሩ በመሆናቸው የማህበራዊ ዋስትና ያላቸውና ለየትኛውም ችግራቸው ድጋፍና ክትትል ያገኛሉ።
ድርጅቱ ከሚያደርግላቸው ድጋፍ መካከልም ምርትና ምርታማነታቸው እንዲጨምር በየዓመቱ ችግኞችን በማፍላት እንዲሁም ኮምፖስት አዘጋጅቶ ያቀርብላቸዋል።
ምርቶቻቸው ዓለም አቀፍ እውቅናን እንዲገኝ በራሳቸው ፋይናንስ ድጋፍ ያደርጋሉ። ዓመቱን ሙሉ በየጣቢያዎቹ ለሚገኙ አርሶ አደሮች የእርሻ ባለሙያዎች ሙያዊ ድጋፍና እገዛ ከማድረግ ባለፈ የቁጠባ ባህል እንዲያዳብሩና የቤተሰብ ምጣኔ እንዲያደርጉ ስልጠናዎች ይሰጣቸዋል። አርሶ አደሩን በዚህ መንገድ በመደገፍ ደንበኞች በሚፈልጉት የጥራት መጠን የቡና ምርትን ለገበያ ያቀርባሉ።
ከዚህ ቀደም የነበረው የቡና ንግድ ገበያ ሥርዓት አምራቹንና ላኪውን፤ አምራቹንና አቅራቢውን የተለያየ ነበር። በዚህም ሁሉም ተራርቆ ይሰራ የነበረ በመሆኑ ዓለም አቀፍ ገዥዎችን ፍላጎት ማዕከል ካለማድረጉ ባሻገር ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ አልተቻለም። ይሁንና ከዘጠኝ ዓመታት በኋላ በ2008 ዓ.ም አዲስ አዋጅ ወጥቶ የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን በመቋቋሙ በቡና ንግድ ዘርፍ የትስስር ግብይት ተፈጥሯል። ይህም የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ከፍተኛ እገዛ እያደረገ ይገኛል።
የኢትዮጵያ አርሶ አደር ጠንካራና ተግቶ የሚሰራ የላቡን ፍሬ ማግኘት የሚፈልግ ከመሆኑም በላይ ትንሽ ድጋፍ የሚፈልግና መንገድ ካሳዩት መንገዱን ተከትሎ የሚጓዝ ነው። በዚህም ቀርጫንሼ ቡና ላኪ ላለፉት አምስት ተከታታይ ዓመታት በጥራትም ሆነ በመጠን ከፍተኛው የኢትዮጵያ ቡና ላኪ ድርጅት ለመሆን በቅቷል።
ባለፈው ዓመት ብቻ 28 ሺህ ሜትሪክ ቶን ቡና መሰብሰብ የቻለ ሲሆን፤ ከዚህም ውስጥ 70 በመቶ የሚሆነው ምርት በድርጅቱ ስር ካሉ 56 ሺህ አርሶ አደሮች የተሰበሰበ ነው። ድርጅቱ ከአርሶ አደሮች ጋር የጠበቀ ግንኙነት ያለውና ተከታታይ ድጋፍና ክትትል እያደረገ የሚገኝ በመሆኑና የተሻለ የምርት ዝግጅት እየተደረገ ስለሆነ በተያዘው የምርት ዘመን እስከ 30 በመቶ ጭማሪ ይኖረዋል። እስካሁን ባለው የምርት መሰብሰብ ሂደት ውስጥም ተስፋ ሰጪ የሆኑ ነገሮች አሉ።
በጥራትና በመጠን ለአስር ተከታታይ ዓመታት ቡና ወደ ውጭ ሀገር የመላክ ልምድ ያለውና ለአምስት ዓመታት ደግሞ ቀዳሚ የሆነው ቀርጫንሼ ቡና ላኪ ድርጅት አብረውት ከሚሰሩት 56 ሺ አርሶ አደሮች ውጭ ለ28 ሺ 890 ዜጎች ቀጥተኛ የሆነ የስራ ዕድል መፍጠር ችሏል። ድርጅቱ በተለያዩ የሀገሪቱ ቡና አብቃይ አካባቢዎች 57 የቡና ማጠቢያ ጣቢያዎች እና አራት የቡና እርሻዎች አሉት። በተለይም በዚህ ወቅት የቡና ኢንዱስትሪ ከፍተኛ የሰው ሃይል የሚፈልግ በመሆኑ ከፍተኛ ቁጥር ላለው የሰው ሃይል የስራ ዕድል ፈጥሯል።
ሁለት ሚሊዮን ብር መነሻ ካፒታል ይዞ ወደ ስራ የገባው ቀርጫንሼ አሁን ላይ አንድ ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ካፒታል ደርሷል። ድርጅቱ ከፈጠረው ሰፊ የስራ ዕድል እና ካፒታል በተጨማሪ የተለያዩ መልካም ስራዎችን በመስራት ማህበራዊ ሃላፊነቱን እየተወጣ ይገኛል።
በዚህም ‹‹ቡና ቀላ›› የሚል የራሱን ፋውንዴሽን አቋቁሟል። በፋውንዴሽኑም የተለያዩ የልማት ስራዎችን ይሰራሉ። በዚህም በትውልድ አካባቢያቸው 10 ትምህርት ቤቶችን፣ ስድስት የውሃ ጉድጓዶችን፣ ከ100 ኪሎ ሜትር በላይ መንገዶችን፣ የተለያዩ የትምህርት መርጃ መሳሪያዎችን፣ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ችግኞችን በነጻ ማከፋፈል፣ እንዲሁም የገጠር እናቶች ምግብ ለማብሰል የሚገጥማቸውን ችግር ማቃለል የሚያስችል በጸሀይ ሃይል የሚሰራ ምድጃና ብርሃን እንዲያገኙ አድርጓል።
ዛሬ እዚህ ደረጃ ለመድረሳቸው ከቤተሰቦቻቸው ጀምሮ አጠቃላይ የአካባቢው ማህበረሰብ ሚና የጎላ እንደነበር አንስተው የማይጠግቡት አቶ እስራኤል፤ ባለፉት የስራ ዓመታት ውስጥ በርካታ ውጣ ውረዶችን እንዳለፉ አጫውተውናል። በተፈጥሯቸው ውጣ ውረዶች ከበዙ ጥሩ ዕድሎች አሉ ብለው የሚያምኑ ሰው ናቸውና ብዙዎችን ከዕድል ቆጥረው ተጠቅመውባቸዋል።
በተለይም ባለፉት ዘጠኝ ዓመታት የንግድ ሥርዓቱ አበረታች ካለመሆኑም በላይ ባለሀብቱ በገዛ ንብረቱ ላይ መወሰን የማይችልና በፈለገው ጊዜ ንብረቱን ማንሳት አይችልም ነበር። ይህ ደግሞ በንግድ ዘርፉ ላይ ከፍተኛ ችግር ቢሆንም አሁን ለደረሱበት ስኬት ግን እንደ ዕድል ሆኖ ያለፈ መሆኑን ያምናሉ።
ማህበራዊ ሃላፊነትን የሚወጡት በሆነ ጊዜ ተነስተው ሳይሆን ቀጣይነት ባለው መንገድ በመሆኑ ድርጅቱ ከሚያተርፈው ትርፍ 10 በመቶ የሚሆነውን በየዓመቱ ለቀርጫንሼ ፋውንዴሽን ገቢ ያደርጋል። ይህም በህግ የተቀመጠና በቀጣይም አቶ እስራኤል አጠናክረው መቀጠል የሚፈልጉበት የስራ ዘርፍ ነው።
ለዚህም ዋናው ምክንያታቸው በርካታ ድጋፍ የሚሹና ብዙ ዋጋ የከፈሉላቸው የማህበረሰብ ክፍሎች በመኖራቸው እንደሆነ ይናገራሉ። ‹‹መልካምነት መልሶ ይከፍላል›› እንደሚባለው ለእነዚህ ዜጎች ድጋፍ ማድረግ ለራስ ማድረግ ነው ፤በዚህም እጅግ ደስተኛ ነኝ ይላሉ።
ለሰዎች ጊዜያዊ መፍትሔ ከመስጠትና ለዕለት አብልቶ ከማጠጣት ባለፈ ዘላቂ መፍትሔ መስጠት ቢችሉ መላው የሀገሪቱ ህዝብ ላይ ጋሬጣ የሆነው ድህነት ገለል ማድረግ የዘወትር ምኞታቸው ነው። ለዚህም በተለያየ መልኩ ጥናት እያደረጉ ሲሆን፤ በተለይም ኢትዮጵያ የምታመርተውን የቡና ምርት በጥራትም ሆነ በመጠን ቀዳሚ ማድረግ የረጅም ጊዜ እቅዳቸው ነው። ከዚህ በተጨማሪም በቀጣይ ቡናን በመስኖ በስፋት መመረት የሚቻልበትን መንገዶች ያስባሉ። እንዲሁም አርሶ አደሩ በአንድ ሄክታር የሚያገኘውን የምርት መጠን ከፍ በማድረግ ቀርጫንሼን ከአፍሪካ ትልቁና ቀዳሚው ቡና ላኪ ድርጅት ማድረግ እቅዳቸው በመሆኑ ለተግባራዊነቱ እየተውተረተሩ ይገኛሉ። እኛም ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት የሆነው የቡና ምርት በመጠንም ሆነ በጥራት ቀዳሚ ሆኖ በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ትርጉም ያለው ለውጥ ማምጣት እንዲችል፤ እቅዳቸውም እንዲሳካ ልባዊ ምኞታችንን ተመኘን። ሰላም!
አዲስ ዘመን ጥር 04/2013