ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ ከምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት ባለፈው ዓመት ኢትዮጵያ ውስጥ በነበረው ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ከሪፎርሙ በኋላ በነበረን የኢኮኖሚክ ዘርፍ ግምገማ ከፍተኛ የማክሮ ኢኮኖሚ ያለመመጣጠን እንዳለ ታውቋል ብለዋል፡፡ ማክሮ ኢኮኖሚው ያልተመጣጠነ መሆኑ ብቻ ሳይሆን በፍጥነት የማስተካከያ እርምጃዎች ሊወሰድበት እንዳስፈለገም አብራርተዋል፡፡ ተፈጥሮ የነበረው የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ቀውስ ውህደት ቢቀጥል የኢኮኖሚ ዕድገቱን ሊገታው እንደሚችልም አስረድተዋል፡፡ የመንግሥት ወጪ እያደገና ከፍተኛ የገንዘብ ፍሰት በኢኮኖሚ ውስጥ እያለ ግሽበት እያደገ የሚሄድ ከሆነ ተደምረው ይሄን የማክሮ ኢኮኖሚ ያለመመጣጠን ወደ አደገኛ ነገር የሚያስገቡ ይሆናሉ ብለዋል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የነበረው ኢንቨስትመንት አብዛኛው በብድር ላይ የተመሰረተ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የስኳር ፕሮጀክቶች ፣ የህዳሴው ግድብ እና የኢንዱስትሪ ፓርኮችም ኢንቨስት የሚደረጉት በብድር መሆኑን ገልፀዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ መዋቅራዊ ችግር እንዳለበት የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አንደኛው የመዋቅራዊ ችግር መገለጫው የሥራ ቅጥር ሁኔታ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ በየዓመቱ ሁለት ሚሊየን ሰው አዲስ ሥራ ፈላጊ ሆኖ እንደሚቀርብ በመግለጽ በዓመት ከፍተኛ ሥራ የሚይዘው ግን አንድ ሚሊየን ሰው ብቻ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ በዚህም በየዓመቱ ከሚፈጠው ሥራ አጥ ከግማሽ በላዩን ማስታገስ እንዳልተቻለም ገልፀው፤ ኢትዮጵያ ውስጥ የሥራ ፈላጊው ቁጥር ከአስር ሚሊዮን በላይ እንደሚሆንም አስረድተዋል፡፡ ይንን ችግር ለመፍታትም ዓመታት እንደሚያስፈልጉ ገልጸዋል፡፡ ሥራ አጥነትን ብቻ ሳይሆን የወጪ ንግድ ስርዓታችንን ችግር ማረም እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል፡፡ ከውጭ የምናስገባው ሀብት ወደ ውጭ ከምናስወጣው ቢያንስ በ500 ፐርሰንት እንደሚበልጥም ተናግረዋል፡፡ ስንዴን ከውጭ ከማስገባት ይልቅ የስምጥ ሸለቆ አካባቢዎችን በማልማት ወጪን ማትረፍ እንደሚያስፈልግና በሀገር ውስጥ ሊሸፈኑ የሚችሉ በርካታ ነገሮች ላይ ማስተካከያ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡
ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ የሚደረገው ሽግግር ገና ረዥም ግዜ ይፈልጋል ያሉት ዶክተር ዐብይ፤ በጂቲፒ ውስጥ ግብርና ያለው ሚና በጣም ከፍተኛ ቢሆንም ለኢንደስትሪው የሚያደርገው አስተዋጽኦ እያደገ ካለው ኢኮኖሚ አንጻር ሲታይ አናሳ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ዘመናዊ የግብርና ሥርዓትን በማምጣት በተለይም ብዙም እርሻ ባልተካሔደባቸው ቆላማ ቦታዎች የከርሰምድር ውሀንም ይሁን በሌላመንገድ የሚገኝ ውኃን በመጠቀም በመስኖ ማምረትና ከሚገኘው ግብዓት ተጠቅመን አግሮ ኢንዱስትሪ ማስፋፋት ያስፈልጋልም ብለዋል፡፡
ትልቅ የገቢ አቅም ያለው ሀገር በዚያ ልክ ገቢ መሰብሰብ ካልቻለ ችግር እንደሚሆን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ከበጀት ዓመቱ ወዲህ የብድር ኢንቨስትመንት መግታት እንደተቻለና ለአብነትም ከወርልድ ባንክ 1 ነጥብ 7 ቢሊዮን ዶላር እርዳታ እንደተገኘና ይህም ትልቅ የዲፕሎማቲክ ድል መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ባለፉት 15 ዓመታት በአማካይ የኢትዮጵያ የዋጋ ግሽበት አስራ አራት በመቶ እንደሆነ የገለፁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይሄ የአስራ አራት በመቶ ግሽበት ከባለፈው የካቲት ጀምሮ እስከ ሚቀጥለው መጋቢት መጨረሻ አካባቢ አንድ አሀዝ ለማድረግ ታቅዶ አሁን አስር ነጥብ ሦስት አካባቢ ደርሷል ብለዋል፡፡ ግሽበቱ እንዲቀንስ ማድረግ የተቻለው አንደኛ የመንግሥት ወጪን በመቀነስ ሁለተኛ በመንግሥት የሚደረጉ ሰፋፊ ኢንቨስትመንቶች ያዝ በማድረግ ነው ሲሉም አክለዋል፡፡ የኢኮኖሚውን ስርዓት ለመመዘን ያስችል ዘንድም ባለፉት ስድስት ወራት አዲሱ በጀት ከተመደበበት ግዜ ጀምሮ ልማት ባንክን ሳይጨምር ሁሉም ባንኮች ብድር ያበደሩበት፣ የሰበሰቡበት፣ ያተረፉበት እና አዳዲስ ቁጠባ በአብዛኛው ከእጥፍ በላይ ማደጉን ጠቅሰዋል፡፡
በዚህ ዓመት ከ8.8 እስከ 9 በመቶ እድገት ሊመጣ እንደሚችል ወርልድ ባንክ መተንበዩን አስታውሰዋል፡፡ በአንድ ዓመት ውስጥ 7 ኢንዱስትሪል ፓርኮችን ለመገንባት በታቀደው መሰረት ሦስቱ ሲመረቁ ሦስቱ ደግሞ ለምረቃ እንደተዘጋጁና አንደኛውም በሚቀጥሉት ሦስት ወራት ውስጥ እንደሚጠናቀቅ ተናግረዋል፡፡ የስኳር ፕሮጀክቶችን በተመለከተም በከፍተኛ ፍጥነት እየተከናወኑ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የህዳሴውን ግድብ በተመለከተም በ80 ቢሊዮን በጀት የተጀመረው ፐሮጀክት በመጓተቱ ምክንያት በትንሹ ከ60 በመቶ በላይ የዋጋ ጭማሪ ማሳየቱን በመጥቀስ ከዚህ ውስጥ አንድ አምስተኛው ገደማ የባንክ ዕዳ / ወለድ የተከፈለበት መሆኑን አስረድተዋል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ በሚቀጥሉት አራት ዓመታት ሙሉ በሙሉ ህዳሴን እንጨርሳለን ብለን እየሰራን እንገኛለንም ብለዋል፡፡ ህዳሴን መጨረስ ለኢትዮጵያዊያን የሞት የሽረት ጉዳይ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በእያንዳንዷ ቀን ትልቅ ትኩረትና አመራር የሚፈልግ ዘርፍ ነው ብለዋል ፡፡
የህዳሴ ግድብን መጨረስ የሞራልና የኢኮኖሚ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ባለመጨረስ የምንከፍለውን እዳም ይቀንሳል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፕሮጀክቱን በመጨረስ የምናገኘው ጥቅም ከፍተኛ ነው፤ ለሁሉም ፕሮጀክቶች ጠንካራ የማስፈጸም አቅም ለመፍጠር እየተሰራ ነውም ብለዋል፡፡ የግሉ ዘርፍ ኢኮኖሚው ውስጥ ያለውን ሚና ማሳደግ አለብን፡፡ ምክንያቱም የግሉ ዘርፍ ዋነኛ ቀጣሪን ሥራ ፈጣሪ ነው፡፡ አሁን ኢትዮጵያ በቀላሉ ሥራ መጀመር ከማይቻልባቸው የዓለም ሀገራት መጨረሻ ተርታ 159 ደረጃ ላይ ነው የምትገኘው፡፡ በቀላሉ ፍቃድ የማይወጣባት ፤የታክስ ስርዓቱ ዘመናዊ ያልሆነበት፤ ችግር ቢፈጠር መፍቻ መንገዱ ችግር ያለበት፤ ፍቃድ ማውጣትም መሰረዝም ችግር የሆነበት፤ አዲስ ስራዎች ገና ከመጀመራቸው በቢሮክራሲ የሚሰቃዩበትና ሌሎችም ችግሮች ያሉበት ሀገር ነው፤ ካሉ በኋላ በጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ ስር የተቋቋቋመው ቢዝነስ የማቅለል ቡድን ከአስር ሚኒስቴሮች 80 የሚጠጉ ዋና ዋና እንቅስቃሴዎች ተለይተው በመሰራት ላይ ይገኛልም ሲሉ አስረድተዋል፡፡
በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት አሁን ካለንበት 159ኛ ደረጃ ከመቶ በታች እንሆናለን ብለን እየሰራን ነው፡፡ ለዓለምም ይሄንን እየነገርን ስለሆነ በርካታ ኢንቨስተሮች እየመጡ ነው፡፡ ዘንድሮ ጥቂት ኢንቨስተሮች ብቻ በቢሊየን የሚቆጠር ኢንቨስትመንት ይዘው መጥተዋል፡፡ በኢንዱስትሪያል ፓርኮቻችን ጅማ፣ አዳማ ፣ደብረብርሃን ፣ ድሬዳዋ ሁሉም ሼዶች ማለት ይቻላል ኢንቬስተሮች ገብተው ማሽን እየተከሉ ነው፡፡ አንዳንዶቹም በተመረቁ በወራት ውስጥ ሥራ ጀምረዋል፡፡ ምዕራቡ ዓለም ኢትዮጵያ መጥቶ ኢንቨስት ማድረግ ይፈልጋል፡፡ ትላልቅ ተቋማትን እያስገባን ነው፡፡ በቅርቡም ቮልስዋገን መጥቷል፡፡ አሁን በዋናነት ትኩረት መስጠት የሚያስፈልገን በመንግሥት ኢንቨስትመንት ላይ ብቻ ሳይሆን የራሱ ሀብትና ዕውቀት ኖሮት በዚህ ላይ የካፒታል እሴት የሚጨምሩ የግል ተቋማት ላይ ነውም ሲሉ አስረድተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለወም ተጨማሪ የወደብ ዕድል ተገኝቷል፡፡ የአውሮፓ ህብረት በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ያለውን የመንገድ መሰረተ ልማት ማገዝ ይፈልጋል፡፡ ዓለም ባንክ በኤርትራ ከሚገኙ ወደቦች ጋር የሚያያዙ መሰረት ልማቶችን ለመደገፍ ሙሉ ፍቃደኝነት አለው፡፡ የጣሊያን መንግሥት ፕሮጀክቱን ለማጥናት ሙሉ ወጪ ሸፍኗል፡፡ ዕድሎች አሉ እድሎቹን ተጠቅመንና ጭቅጭቅ ንዝንዝና ጥይት መተኮስን ትተን ፊታችንን ካዞርን በከፍተኛ ፍጥነት ኢኮኖሚያችን እንዲያገግም ማድረግና ወደትክክለኛው መስመር እንዲገባ ማድረግ ይቻላልም ብለዋል፡፡
መንግሥት ክፍተት ባየበት እየገባ የሚፈታ ነው ፡፡ የቆመ ፕሮጀክት ካለ የመጀመሪያ ስራው ያን መጨረስ ይሆናል ማለት ነው፡፡ የሰራቸውን እንደ ስኳር ፋብሪካ ያሉ ተቋማት ለግል ዘርፉ እየተወ በአዳዲስ መስኮች መሰማራት አለበት ሲሉ የገለጹት ዶክተር ዓብይ በመንግስት ተይዘው ኢንቨስት የሚደረግባቸው መስኮች የዕዳ ኢንቨስትመንቶች ናቸው፡፡ ኢኮኖሚ ቢያሳድጉም በዘላቂነት ችግር ሊያመጡ የሚችሉ ናቸው፡፡ ለምሳሌ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አጠቃላይ ያለበት ዕዳ ከ300 ቢሊየን ብር በላይ ነው ይህንን ተቋም እንሽጠው ብንል ከ 99 በመቶ በላይ ኩባንያው የያዘው ዕዳ ነው፡፡ ስለዚህ በኢኮኖሚው መስክ መያዝ የሚገባንን ገባን ሴክተር መያዝ መልቀቅ የሚያስፈልገንን ደግሞ መልቀቅ ይገባል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ዓለም ባንክ ብቻ ሳይሆን አብዛኞቹ ኢትዮጵያን የሚደግፉ ሀገራት ከምንጊዜውም በላይ እርዳታቸውን አሻሽለዋል፡፡ ካበደሩን ሀገራትም 60 በመቶ የሚሆኑት በ10 ዓመት የምንከፍለውን ብድር ወደ ሰላሳ ዓመት ስላራዘሙልን ያለንን ሀብት ዕዳ ለመክፈል ሳይሆን ፕሮጀክት ለመጨረስ እናውለዋለን፡፡ ኢኮኖሚውን ጠብቀን ዕድገት ማስቀጠል የምንችለው የሁሉም ሰው የጋራ ትብብርና ጥረት ሲኖር መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ዋጋ የሚያንሩና ቶሎ ተሰርተው የውጭ ምንዛሬ የማያመጡ ፕሮጀክቶችን ይዘናል፡፡ ለምሳሌ አንዱ የያዝነው ሽሮ ፈሰስ የሚባል አስፋልት ነው፡፡ ሽሮ ፈሰሶች የብድር ገንዘብ ይበላሉ መንገድ አይሰሩም፡፡ ከሰራን ጠንካራሥራ እንሰራለን እንጂ ብር ተበድረን በሽሮ መልክ አናፈስም፡፡ በዚህ አግባብ ኢኮኖሚውን እያረጋጋን ለመሄድ ጥረት ይደረጋል ከፍተኛ መሻሻልም ታይቷልም ብለዋል፡፡
የኢኮኖሚ መቀዛቀዝ አለ የሚል ሀሳብ ያላቸው ሰዎች አንድ አካባቢ ላይ የተሰማሩ ናቸው፡፡ ለምሳሌ ብረት የሚነግዱ ሰዎች እውነታቸውን ነው፡፡ ምክንያቱም ይዘነዋል እኛ ዋና ገዢዎች ስለሆንን፡፡ ሲሚንቶ የሚፈልጉ ሰዎችም ተይዞባቸዋል ትክክል ነው፡፡ ግንባታ ነበርና የኢንዱስትሪውን እድገት እያሳየ የነበረው፡፡ መንግሥት ተበድሮ እያመጣ ለግንባታው ዘርፍ ያውላል ነገር ግን መንገዱም ህንጻውም የሚያስፈልገውን ግልጋሎት መስጠት የሚያስችል ጥራት የለውም፡፡ እነሱም ቆም ብለው አቅማቸውን መፈተሽ አለባቸው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ከ10 ቢሊዮን ብር በላይ ፕሮጀክት የያዘ የግል ኩባንያ አለ፡፡ ኢኮኖሚው የሚቆምበት መንገድ ከአጠቃላይ ማይክሮ ኢኮኖሚ ባላንስ ጋር ካልተያያዘ በሴክተር ደረጃ ካየነው ችግር ያስከትላል፡፡ ነገር ግን መሰረተ ልማት በጣም ወሳኝ ነገር ነው፡፡ ስለሆነም ይዘነው አንቀጥልም መግባታችን ስለማይቀር በዚህ ሴክተር ያላችሁ ሰዎች አቅማችሁን ማጠናከር ራሳችሁን ማዘጋጀትና የጠራ ስራን ሰርቶ ተወዳዳሪ ለመሆን መዘጋጀት ያስፈልጋችኋል ሲሉም መክረዋል፡፡
የቱሪዝም ፍሰትን የሚጨምር አዲስ አበባ ላይ በቅርቡ ይፋ የምናደርገው በቢሊየን ብር የሚቆጠር ፕሮጀክት አለን፡፡ አዲስ አበባን እንደ ስሟ አዲስና አበባ ለማድረግ ከፍተኛ ስራ እየሰራን እንገኛለን፡፡ የዚህ ሥራ የመጀመሪያ ምዕራፍ ግንባታ ቢበዛ አንድ ዓመት ተኩል የሚፈጅ ነው፡፡ ፋይናንስ አፈላልገን ብዙ የሚያግዙን አካላት ስላገኝን በቅርቡ ሥራ እንጀምራለን፡፡ ይህ ሥራ ሲጠናቀቅ ወደ ሀገር ውስጥ የሚመጣው የቱሪስት ፍሰት በከፍተኛ ደረጃ ይጨምራል፡፡ አሁን የሚሸቱ ወንዞችም መዝናኛ ቦታዎች ይሆናሉ ብለዋል፡፡ ከፍተኛ የሥራ ዕድል ይፈጥራሉ፤ እዛ አከባቢ የሚሰሩ ሪል ስቴቶች ዋጋቸው በእጥፍ ይጨምራል ኢኮኖሚውንም ያነቃቃል ሲሉ አክለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ግብርን አሰመልክተው እንደተናገሩትም በግብር ላይ ያለው ዋና ችግር ሁለት ነው፡፡ የመሰብሰብ አቅም አለመጎልበትና ስግብግብነት ካሉ በኋላ ግብር ሰብሳቢ ቢሮው ገቢን ለመሰብሰብ የሚያስችል ስርዓትንና ተክኖሎጂን በፍጥነት መጠቀም አለበት፡፡ ሲያጠፉም በመረጃ መቅጣት አለበት፡፡ ሰውም ደግሞ በተወሰነ ደረጃ ስግብግብነቱን መቀነስ አለበት ሲሉ አሳስበዋል፡፡
ነገር ግን ግብር መክፈል የትም ዓለም በፍቅርና በደስታ ሆኖ አያውቅም የአሜሪካ የግብር ስርዓት በዓመቱ መጨረሻ ላይ ገቢና ወጭህን ይፋ ያደርጋል እንደኛ ሀገር አይደልም፡፡ ምክንያቱም ማንም ሰው ቢሆን ደስ ብሎት የሚከፍለው ጉዳይ አይደለምና:: ስለዚህ ጠንካራ ህግ፣ መንግሥትና የማስፈፀም አቅም ያስፈልጋል በማለት ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡ ግብር ከፋዮችም ቢሆኑ ግዴታቸውን እየተወጡ መብታቸውን ቢጠይቁ የሚያምር መሆኑን በማወቅና ሳይሰጡ መቀበል ችግር ስለሚሆን ግብር መክፈል አስፈላጊ መሆኑ አብራርተዋል፡፡ አያይዘውም ባለፉት ስድስት ወራት ከአምናው አንፃር ሲታይ ገቢያችን ከ8.2 በላይ አድጓል ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ተጨማሪ ገቢ ስላገኘን የበጀት ጉድለቱን እናጠባለን። ነገር ግን ገቢ ካላደገ የበጀት ጉድለትን ማስተካከል አይቻልም ሲሉ አብራርተዋል፡፡
ከወጣት ሥራ አጥነት ጋር ተያይዞ ለተነሱ ጥያቄዎችም ጉዳዩ አሳሳቢ መሆኑን ጠቅሰው የስራ አጥነት ችግር ዘርፈ ብዙ ችግር ነው፡፡ በተዘዋዋሪ ፈንድ ከጥቂት ዓመት በፊት መንግሥት 10 ቢሊዮን ብር ለዚህ ጉዳይ ማዋሉ ይታወሳል፡፡ ነገር ግን እንዳሰብነው አይደለም ተዘዋዋሪ ፈንድ ማለት ሽልማት ማለት አይደለም፡፡ ተዘዋዋሪ ፈንድ ማለት አበድረህ እየሰበሰብክ ለሌላው የሚሠጥ ማለት ነው፡፡ ይሁንና ከ10 ቢሊዮኑ 9.2 ቢሊዮን ለክልሎች ያፈሰስን ሲሆን እስካሁን የተመለሰው 1 በመቶ ብቻ ነው፡፡ አበድረን ሥራ ካስጀመርን በኋላ ከስር ስር መልሰን እራሱን እንዲዘዋወር ካላደረግን በስተቀር የሰጠነው ከቀረ ተጨማሪ ፈንድ ለመስጠት ለመንግሥት ያስቸግራል ሲሉ ገልፀዋል፡፡
በዚህ ዙሪያ ሁሉም ጉዳዩ ይመለከተዋል ካልን ተባባሪ መሆን አለበት፡፡ ምክንያቱም ሥራ አጥነት ለሁሉም ሀገር አስቸጋሪ ቢሆንም ለኛ ደግሞ ቀጣይነት ፈተና መሆኑ አይቀርም፡፡ በ1986 ዓ.ም የኢትዮጵያ ህዝብ ብዛት 53 ሚሊዮን ነበር፡፡ አሁን በእጥፍ አድጓል። ከ30 ዓመት በኋላ ደግሞ በእጥፍ ያድጋል፡፡ በዚህም መሰረት በ2050 የህዝብ ቁጥሩ ወደ 200 ሚሊዮን ገደማ ቢያድግ ወደ ገበያ የሚመጣው 2 ሚሊዮን ነው፡፡ ሥራ የሚይዘው ግን 1 ሚሊዮን ስለሆነ እየተከማቸ ይሄዳል ማለት ነው፡፡ ግብርናን ብቻ ብንመለከት የአርሶ አደር ልጆች ሆነው በአርሶ አደር ላይ ጥገኛ ሆነው የሚኖሩ አሁን 41 በመቶ ገደማ ይጠጋሉ፡፡ ሥራ አጥ እንዳይባል ሥራ እየሞካከረ ይበላል። ግን መስራት በሚገባው ቦታ ሳይሆን አንድ ሰው ሁለት ሰው የሚሰራውን ሥራ እየተሻማና እየሰራ የሚኖር ነው ብለዋል፡፡ ይሄን ካላስተካከልን ህዝብ እየጨመረ በሄደ ቁጥር ፈተናው ከባድ ነው የሚሆነው፡፡
በህዝብ እድገት ልክ እድገትን የማናረጋግጥ ከሆነ አደገኛ ነው። 2.5 ሚሊዮን ህዝብ በየዓመቱ ይወለዳል፡፡ በዓመት ግን 2.5 ሚሊዮን ህዝብ ሥራ አይዝም፡፡ ያሉት ዶክተር ዓብይ ወደ ገበያው የምንጨምረው ሰው እና ወደ ገበያ የምናስገባው ሰው ሚዛናዊ ካልሆነ ችግር ያስከትላል ሲሉም አስረድተዋል፡፡ ሰራተኛ የሚያጡ የስራ ቦታዎች አሉ ለምሳሌ ጥጥ አምራች የሆኑ እንደ ሁመራ አካባቢ ብንሄድ ጥጥና ሰሊጥ የሚሰበስብ የለም፡፡ የኛ ሥራ በዘመናዊ መንገድ ስለማይሰራ ብዙ የሰው ጉልበትን ይፈልጋል። ሰራተኛ ማለት በኛ ሀገር ውስጥ በኛ ቀበሌ ውስጥ ሥራ መፈጠር አለበት የሚል ሳይሆን ሥራ ባለበት ቦታ ሂዶ የሚሰራ መሆን መቻል አለበት፡፡ ማንኛውም ሰው ደግሞ ከየትም ይምጣ ሥራ ባለበት ቦታ ሂዶ መስራት መቻል አለበት። በኢንዱስትሪ ቦታዎች ስናይ ደሞዙ አነስተኛ ስለሆነና የሚከፈለው ክፍያ የቤት ክራይ መክፈል የሚያስችል ስላልሆነ የሰራተኛ እጥረት አለ፡፡ ኢንዱስትሪ ከተሰራባቸው ቦታዎች ጎንለጎን የመኖሪያ ቤት ስላልተሰራ ሰራተኞች በሚያገኙት ደሞዝ ቤት ኪራያቸውን ከፍለው እራሳቸውን ማኖር ይቸገራሉ በማለት የችግሩን አሳሳቢነት ጠቅሰዋል፡፡
ሥራ በሁሉም የሀገሪቱ ቦታዎች ፍትሃዊ በሆነ መንገድ እንዲገኝ ለማድረግስ ምን ማድረግ አለብን ለሚለው ጥያቄ አንደኛው የግል ሴክተር ነው፡፡ ሁለተኛው መነሻ ወይም ስታርት አፕ ነው ካሉ በኋላ ይህንንም እንደሚከተለው አብራርተዋል፡፡ ሊስትሮ፣ ምግብ ቤት፣ ሻይና ቡና ለሚጀምሩ ሰዎች ማድረግ ያለብን ማበረታታት ነው፡፡ ኢኮኖሚያቸው እያደገ ሲመጣ ችግራቸውን ማስተካከል ስለሚቻል እንዳይሰሩ ከምናደርግ ሥራ እንዲጀምሩ ማድረግ በተለይ ደግሞ በከተማ ያሉ ሴቶች የስራ አጥነት ከፍተኛ ስለሆነ በፋይናንስም እየደገፍን ሥራ ውስጥ እንዲገቡ ማድረግ ይኖርብናል፡፡ ይሄን በማድረግ በሂደት ሥራ አጥነቱን ስርዓት እያስያዝን እንሄዳለን፡፡ ይሁንና ሥራ አጥነትን ዜሮ ማድረግ ግን አይቻልም፡፡ አሜሪካና አውሮፓም ዜሮ አይደለም ፡፡ ግን በመንግሥት አቅም ችግሩ እየሰፋ እንዳይሄድ መስራት ያለብንን መስራት ይኖርብናል፡፡ ከዚህ አንፃር ነው ኢንቨስተሮችን እየጋበዝን ያለነው፡፡ እንዲሁም በቱሪዝምና በመስኖ ላይ ብናተኩር በገጠር ከፍተኛ የሆነ ሥራ አጥነትን መቀነስ ይቻላል፡፡ እነዚህን መንገዶች በመከተል የሥራ አጥነት መቀነስና መግታት በሚያስችለን ሁኔታ እንሄዳለን ብለዋል፡፡
ከግብርና ጋር ተያይዞ ለተጠየቁት ጥያቄም እንዲህ በማለት አብራርተዋል፡፡ መስራት የሚገባን ሥራ አለ፡፡ ለማልማት ቦታ ወስደው ሳይሠሩ ያበላሹ ሰዎች አሉ በእነሱ ላይ የማስተካከያ ሥራ እየተሰራ ይገኛል፡፡ በሚቀጥለው የበጀት ዓመት ትኩረት የሚያስፈልገው አንዱ ሴክተር መስኖ ስለሆነ በዚህ አግባብ ግብርናችንን እያዘመንንና ኢምፖርትን እየተካን የውጭ ምንዛሪ ፍላጎታችንንም በተወሰነ ሁኔታ እየቀነስን የምንሄድበት አግባብ ይኖራል ብለዋል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 25/2011
በጋዜጣው ሪፖርተሮች