@ የቀረበው የሠላም ጥሪ የሠላም መርህን የተከተለ ነው
@ የለውጥ ጉዟችን ማዳን እንጂ ማከም አይደለም
@ በኢትዮጵያ ውስጥ ያልታሰረ በመንግስት የሚፈለግ ወንጀለኛ የለም
አዲስ አበባ፡- ለውጡን ተከትሎ የተለያዩ እርምጃዎችን በመውሰድ በተለያየ ምክንያት በውጭ ለነበሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ወደአገር ውስጥ እንዲገቡ የተደረገው የሰላም ጥሪ የሰላም መርህን መሰረት ያደረገ መሆኑን የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ ገለጹ፡፡ በኢትዮጵያ የተጀመረው ለውጥ የማዳን እንጂ የማከም አለመሆኑን እንዲሁም መታሰር ማለት በአንድ ከባቢ ላይ መቆየት እንደመሆኑ መንግስት በወንጀል እንደሚፈልግ ይፋ ያደረገው አንድም ያልታሰረ ግለሰብ አለመኖሩንም ተናግረዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ትናንት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው ከምክር ቤቱ አባላት ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ በሰጡበት ወቅት እንደተናገሩት፤ ለውጡን ተከትሎ በአስርና አስራ አምስት ዓመት ብቻ ሳይሆን ከአርባ አምስት ዓመት በላይ በኢትዮጵያ ውስጥ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ማድረግ የማይችሉ ሃይሎች ካሉበት ዓለም ሃያ የሚሆኑ የታጠቁም ያልታጠቁም ፓርቲዎች ወደ አገር ተመልሰዋል፡፡ በውጭ አገር ተበትነው የነበሩ ፓርቲዎች፣ በወጣትነታቸው ወጥተው አገራቸው መመለስ ባለመቻላቸው እዛው የሸመገሉ ሰዎች እንዲመለሱ መሆኑ ፓርላማው ይቅር በማለቱና ምህረት በማወጁ ስለሆነ እንደ ትልቅ ድል ማየት ያስፈልጋል፡፡ በዚህም አንድም ፓርቲ፣ አንድም ሚዲያ፣ አንድም ሰው ውጭ አገር ሆኖ የሚቃወም የለም፡፡ ይሄን ድል ዘንግቶ ግን እርሱን ተከትሎ የመጡ ችግሮች ላይ ማተኮር ግንዛቤውን ሙሉ አያደርገውም፡፡
እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለጻ፤ ለእነዚህ አካላት የቀረበው የሰላም ጥሪ የሰላም መርህን የተከተለ እንጂ ሌላ ምንም መርህ የለውም፡፡ መንግስት ሃያ ከሚጠጉ ፓርቲዎች ጋር በተለያየ አገርና ቦታ ድርድር ሲያደርግ የመደራደሪያ መርሁ አንድ ነው፤ ከአንድ ፓርቲ ጋር የሚደራደርበትን መርህ ከሌላ ፓርቲ ጋር የሚቀይር ከሆነ መንግስት መሆን አይችልም፡፡ ስለዚህ ለሁሉም ተቃዋሚ ሃይሎች የቀረበላቸው የሰላም ጥሪ የሰላም መርህን የተከተለ ነው፡፡ ይህ ደግሞ መሳሪያን አስቀምጦ በሃሳብ ልዕልና የመታገል አቅጣጫ እንደመሆኑ አባዛኞቹ በዚህ ስሜት እየሰሩ ነው፡፡ ሆኖም አንድ እግራቸውን አዲስ አበባ አንድእግራቸውን ደግሞ ውጪ አስቀምጠው በሁለቱም መንገድ መጫወት የሚያስቡና ጉራማይሌ የፖለቲካ ስልት የሚከተሉም አሉ፡፡
ይሄን አይነት የፖለቲካ ፋሽን ለድል አያበቃም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ መዋጋት ለሁሉም እኩል የተሰጠ ብቃት እንጂ አንዳንዶች መዋጋት የሚችሉት ሌሎች የማይችሉት ባለመሆኑ ይሄን መሰል ጊዜ ያለፈበት አካሄድ ተገቢ እንዳልሆነና መቆም እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ ሆኖም በጠበበ የፖለቲካ ምህዳር በመቶ ሜትር ሩጫ የለመዱ ሰዎች አሁን ምህዳሩ ሲሰፋና ሩጫው በኪሎ ሜትር ሲሆን ትንፋሽ የሚያጥራቸው መሆኑን በመጠቆም፤ በዚህ መልኩ አማራጭ ሀሳብ የሚያጥራቸው ፓርቲዎችም ሰብሰብ ብለው ሃሳብ ሊያዋጡ እንደሚገባ መክረዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም ፓርቲዎች ኢትዮጵያን ተረክቦ ለማስተዳደር የሚያስችላቸውን ዴሞክራሲ በውስጣቸው መለማመድና አሸናፊ ከማያደርጉ ከዋልታ ረገጥ ሀሳቦች ወጥቶም ይሄንኑም ለህዝብ ማሳየት እንደሚገባቸው አሳስበዋል፡፡ የመንግስት ትዕግስትም በዚህ መልኩ ለዴሞክራሲ ስርዓት መጎልበትና ለህዝቦች ተጠቃሚነት እንጂ ከዚህ አልፎ የኢትዮጵያ ሉዓላዊ ግዛትና ሰላሟን ጥያቄ ውስጥ በሚያስገባ ጉዳይ መንግስት ከማንም ጋር እንደማይደራደር አረጋግጠዋል፡፡ ህግን ተንተርሶም የማያዳግም እርምጃ እንደሚወስድ አስገንዝበዋል፡፡
በተያያዘ የለውጥ ጉዞኣችንን ለማደናቀፍ የሚንቀሳቀሱ ሃይሎችን ከመቆጣጠር አንጻር ምን እየተሰራ እንደሆነ ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ “የለውጥ ጉዟችን ማዳን እንጂ ማከም አይደለም”፤ ለማዳን መርፌ በሚያስፈልግበት ጊዜ መርፌ፣ ኪኒን በሚያስፈልግበት ጊዜም ኪኒን፣ እረፍት በሚያስፈልግበት ጊዜም ማረፍ ነው የሚያስፈልገው ብለዋል፡፡ ሆኖም በማዳን ሂደት የተጀመረ መድሃኒት መሃል ላይ ከተቋረጠ በሽታው ስለሚያገረሽ ሐኪም ቤት መሄድ ወይም መድሃኒት መጀመር ፈውስ ስለማያስገኝ የሐኪምን ትዕዛዝ ተከትሎ መድሃኒቶችን ጊዜውንና ሕጉን ጠብቆ መጠቀም፤ ለመዳን የሚወስደውን ጊዜም መገንዘብ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡ ከዚህ አኳያ ለውጡን በማስቀጠል ሂደት በፖለቲካ ውስጥ የሚሳተፉ ሃይሎች አሁን የሚያስፈልጋቸውም ሆነ ኢትዮጵያ የምትፈልገው ሰላም፣ እውነት እና የሀሳብ ልዕልና መሆኑን አብራርተዋል፡፡ ይህ እንዲሆን ደግሞ የድርድር የመጨረሻ ማሰሪያ ሕግ መሆኑን ሁሉም መገንዘብ እንዳለበትም አውስተዋል፡፡
በሌላ በኩል የፀጥታ ሃይሉ እካሄደ ያለውን ሰላምን የማስከበር ሂደት ጋር ተያይዞ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ “የመከላከያ ሰራዊት በሰፈር ውስጥ አንድ ሌባ ቦርሳ ይዞ ሲሮጥ፣ ለምን ቦርሳ አላስጣልክም ተብሎ የሚጠየቅ አይደለም፤” ብለዋል፡፡ ሰራዊቱ በሕገ መንግስቱ የተሰጠውን የአገር ሉዓላዊነት ከመወጣትም ሆነ በክልሎች በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ ምክንያት የሚከሰቱ ችግሮች ላይ ግዳጅ ሲሰጠው ሃላፊነቱን በአግባቡ እየተወጣ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ በምዕራብ ወለጋ ያለውን እውነት ማየት በቂ እንደሆነም አስረድተዋል፡፡ በመቶ ቀናት አፈጻጸም ረገድም ምርጥ ስራ ከሰሩ ተቋማት መካከል አንዱ መከላከያ መሆኑን በመግለጽም፤ መከላከያ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ በተሰጠው ግዳጅ ሁሉ ሕይወቱን እየገበረ ባከናወናቸው ተግባራት ሊመሰገን እንጂ ሊወቀስ እንደማይገባው አስገንዝበዋል፡፡
መንግስት የህግ የበላይነትን ለማስከበር በሚያደርገው ጥረት ውስጥ በህግ የሚፈለጉ ተጠርጣሪዎችን መያዝ አለመቻሉን በተመለከተ ጥያቄ የቀረበላቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ ውስጥ ወንጀል ሰርቶ ወንጀል በመስራቱ በመንግስት ተፈልጎ ያልታሰረ ሰው የለም ብለዋል፡፡ “ልዩነቱ መንግስት ባዘጋጀው እስር ቤት ውስጥ መንግስት እየጠበቀውና እየቀለበው በመታሰርና ራሱን በማሰር ካልሆነ በስተቀር አልታሰረም የሚል እሳቤ እኔ በግሌ የለኝም” ብለዋል፡፡ ሰው የማይታሰረው በህሊናውና በአካል በመንቀሳቀስ መሆኑን ለአብነት በማንሳትም፤ አንድ ሰው በህሊናውም ሆነ በአካሉ በነጻ መንቀሳቀስ ካልቻለና ራሱን በአንድ አካባቢ ገድቦ እስካኖረ፣ መታሰር ማለት በአንድ ከባቢ መቆየት እንደመሆኑ ያ ሰው ከእስር ነጻ እንዳልሆነ አስረድተዋል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 25/2011
ወንድወሰን ሽመልስ