አንድነት መሰረቶች ናቸው!
ሰላም፣ አንድነት እና ፍቅር የሚሉ ቃላት በሁሉም ሃይማኖቶች ልዩ ትኩረት የሚሰጠው ተዘውትረው የሚሰበኩና ምድራዊና ሰማያዊ ዋጋ እንዳላቸው የሚመሰከር የዚህች ዓለም መቆሚያ አዕማዶች ናቸው።
እነዚህ በቁጥር ሶስት ነገር ግን ፋይዳቸው እጅግ የገዘፈ ጉዳዮች በምድር ላይ የሰው ልጆች ያለምንም ስቃይና እንግልት እንዲኖሩና ላባቸውን ጠብ አድርገው በወዛቸው እንዲበለጽጉም መሰረታዊ ጉዳዮች ስለመሆናቸው ከማንም የሚሰወር ሀቅ ሊሆን አይችልም፤አይደለም።
የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ‹‹የሰላም ግንባታ ማሠልጠኛ›› በተሰኘው ጥናታዊ መድብሉ ስለ ሰላም ምንነት እንደሚከተለው አብራርቷል፡፡ ‹‹ሰላም›› የሚለው የአማርኛ ቃል የተሸከመው ጽንሰ ሐሳብ ከጦርነትና ከአመፅ ነፃ መሆን ከሚለው የአንዳንድ መዛግብት ቃላት ውሱን ድንጋጌ የሰፋ ትርጉም ይዟል፡፡
‹‹ሰላም›› ለሰው ልጆች ከእግዚአብሔር የተሰጠ ስጦታና ከመለኮታዊ ዕቅድ ጋር የሚጣጣም ሰብዓዊ ዕቅድ ከመሆኑ በፊት በዋናነት የእግዚአብሔር የራሱ ዓይነተኛ ባህሪ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስም ‹‹እግዚአብሔር ሰላም ነው›› (መጽሐፈ መሳፍንት 6፡ 24) በማለት ማረጋገጫውን ሰጥቷል፡፡
‹‹በቅዱሳት መጻሕፍት ሰላም የሚለው መሠረታዊ ቃል የሚያመለክተው በሰዎች ሕይወት ውስጥ ተሟልቶ መገኘት የሚገባውን ደኅንነት፣ ምሉዕነት፣ ፍፁምነትና ዋስትናን በመሆኑ ቃሉ የያዘው ፍቺ ላቅ ያለ ሃሳብን ነው፡፡ በሌላ አገላለጽ ሰላም ማለት ሰዎች በግል ኑሯቸውም ሆነ በማኅበራዊ ግንኙነታቸው ወቅት ሊኖራቸው የሚገባ ሁለንተናዊና ምሉዕ የሆነ የሕይወት መገለጫ ነው ማለት ይቻላል፡፡
‹‹ሰላም›› የሚለው የዓረብኛው ቃልም እንዲሁ ቀደም ሲል ከተጠቀሱት ጽንሰ ሃሳቦች ጋር ተመሳሳይ ትርጉም ከመያዙ በተጨማሪ በምድራዊም ሆነ በመንፈሳዊ ዓለም ከአደጋ ነፃ የሆነ የጤናማ ሕይወት ማረጋገጫ የሚል ከፍ ያለ ትርጉም ተሸክሟል፡፡
ሰላም ፍቅርም ሆነ አንድነት ምንም እንኳ ፋይዳቸው የጎላ ቢሆንም ሁሌም እንዲኖሩ ብንፈልጋቸውም በምኞትና በዲስኩር ብቻ የሚገኙ ጉዳዮች አይደሉም። መንግስት፣ መላው ህብረተሰብ ፣ የሃይማኖት አባቶችና የጎሳ መሪዎች በአጠቃላይ ሁሉም የአገር ልጅ ለእነዚህ ጉዳዮች መኖርና ስር መስደድ ትልቅ ኃላፊነት አለባቸው።
በተለይም ደግሞ የጥቅማቸው ያህል ጉዳታቸው ከፍተኛ የሆነው መገናኛ ብዙሃን ለእነዚህ የዓለም መሰረቶች መኖርና ዘልቆ መቀጠል ከማንም የበለጠ ኃላፊነት እንደተሸከሙ ግልጽ ነው።
ይህንን ጉዳይ አስመልክቶ ትናንት በራዲሰን ብሉ ሆቴል የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ባደረገው ምክክር ላይ የሃይማኖት አባቶች፣ ከተለያዩ መገናኛ ብዙኃን የስራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች የታደሙ ሲሆን፤ መገናኛ ብዙኃን የሰዎችን ክብርና ሁለንተናዊ ደህንነት አደጋ ውስጥ የሚጥሉ መረጃዎችን ከማሰራጨት እንዲቆጠቡ ጠይቀዋል። በዚህ ረገድ መገናኛ ብዙኃኑ ገለልተኛ ሆነው ሀገራዊ ሰላምና የህዝቦችን አብሮነት፣ አንድነት የሚያጠናክሩ ስራዎች ሊሰሩ እንደሚገባም አመልክተዋል።
እውነት ነው መገናኛ ብዙኃን ለሰላም ያላቸው ሚና እንዲሁ በቃላት ተዘርዝሮ የሚያልቅ አይደለም። መገናኛ ብዙኃን ያላቸው ተጽዕኖ ፈጣሪነት ሚናቸው እጅግ የላቀ እንደመሆኑና ኅብረተሰቡም በመገናኛ ብዙኃን ለሚተላለፉ መረጃዎች ዓይንና ጆሮውን እንደመስጠቱ የሰላም መልዕክታቸው ብዙ ፍሬ እንዳለው እሙን ነው።
መገናኛ ብዙኃን ያላቸው አዎንታዊ ሚና ከፍተኛ እንደመሆኑ ለአሉታዊ ተግባር ሲውሉም የሚያደርሱት ጉዳት ምን ያህል አስከፊ እንደሆነ ርዋንዳን የተመለከተ በቀላሉ የሚረዳው ሀቅ ነው። በወቅቱ የርዋንዳ ኤፍኤሞች በቀሰቀሱት ጥላቻ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ንጹሀን ህይወታቸውን አጥተው በዓለም ታሪክ ጥቁር ነጥብ እንደተው መቼም የማይረሳ እውነት ነው።
በሀገራችንም አሁን አሁን በረድ ቢልም አንዳንድ መገናኛ ብዙኃን ሲረጩት የነበረው የጥላቻ መርዝ በህዝባችን ጨዋነትና አስተዋይነት ባይከሽፍ ኖሮ ሊደርስ የሚችለው አስከፊ አደጋ ከምንገምተው በላይ የከፋ ይሆን እንደነበር ለመገመት አያዳግትም።
አሁን ላይ አገራችን ከአስከፊ ጭቆናና ዘረፋ ወጥታ ወደ ነጻነትና ብልጽግና እየተጓዘች እንደመሆኑ ነገሮችን በጥንቃቄ በማየት በኃላፊነት መንፈስ መስራት ከመገናኛ ብዙኃን የሚጠበቅ ነው።
ኃላፊነት የሚሰማቸው መገናኛ ብዙኃን የአገር ሰላምና አንድነት መሰረቶች ናቸው። በዚህ አስተሳሰብ የተቃኙ መገናኛ ብዙኃን እየበዙ ሲሄዱ የተረጋጋች ሰላሟና አንድነቷ የተጠበቀ ኢትዮጵያ እውን ማድረጉ የቀለለ ይሆናል !
አዲስ መን ታህሳስ 28/2013