በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)fenote1971@gmail.com
(ክፍል ሦስት )
በዚህ ጋዜጣ ደጋግሜ ባነሳው የማልጠግበው የCNNN /GPS አዘጋጅና የዋሽንግተን ፖስት አምደኛ፤ በአንድ ገጽ ዳጎስ ያለ ስንክሳር ያህል የማስነበብ ልዩ ተሰጥኦውን ስለማደንቅለት ነው። ምን አልባት ለማታውቁት ትውለደ ሕንዳዊው አሜሪካዊ ፋሪድ ዘካርያ አሜሪካ ካሏት አንሰላሳዮች ቀዳሚና እጅግ የተከበሩት የሀርቫርድና የል ዩኒቨርሲቲዎች ምሩቅ ነው። የዓለምአቀፍ ጉዳዮች ሊቅ፣ ጋዜጠኛ፣ ደራሲና ተናጋሪም ነው።
በዚህ ሰሞን ዋሽንግተን ፖስት ላይ፤ ” RUSSIA HASN’T JUST HACKED OUR COMPUTER SYSTEMS. IT’S HACKED OUR MINDS. ” በሚል ርዕስ ባስነበበን ማለፊያ መጣጥፉ ሁለት የራንደ ኮርፖሬሽን ምሁራን ዓለማችንን በተለይ አሜሪካንን በመረጃ መረብ ስርሰራና በሀሰተኛ መረጃ እያስጨነቀች ያለችውን የፑቲኗን ሩሲያ “firehose of falsehood” ይሏታል።
እኔ ፣” የውሸት መሰለቂያ ” በሚል ወደ አማርኛ ለመመለስ ሞክሬያለሁ። የሀገራችን ሩሲያ ደግሞ ያው እንደምትገምቱት ከሀዲው ትህነግና ጭፍራው ዲጂታል ወያኔ ነው። ጥሩ የድንጋይ የውሸትና የደባ መከኪያና መሰለቂያ ወፍጮ ነው። የውሸት አባት። የክህደት አያት። የሌብነት ቅማንት። የጭካኔ ምንጅላት ነው።
በቀደሙት ሁለት መጣጥፎቼ ስለ ሀሰተኛና ሆን ተብሎ የተዛባ መረጃ ምንነነትና ስለሚያስከትሉት ዘርፈ ብዙ አሉታዊ ተጽዕኖዎች ያነሳሁ ሲሆን በዚህ የማጠቃልያ መጣጥፌ ደግሞ ተጽዕኖአቸውን ዘርዘር አድርጌ ካየሁ በኋላ መፍትሔዎችን ለማመላከት እሞክራለሁ። በይነ መረብ የክፍለ ዘመኑን ጋዜጠኝነትም ሆነ የመረጃ ዝውውርን በሁለት መንገድ ተፅዕኖውን አሳርፎበታል።
የመጀመሪያው የዜና አጠነቃቀር ባህል እንደገና ከመበየን አልፎ ሒደቱን አመሰቃቅሎታል። በአናቱ የዜጋ ጋዜጠኝነትን citizen journalism ጨምሯል። የእጅ ስልክ፣ ላፕ ቶፕና የዴስክ ቶፕ ባለቤት ሁሉ “ጋዜጠኛ ” ሆነ ማለት ነው። ሁለተኛው የበይነመረብ ፣ የተግባቦትና የመረጃ ማዕዶች platforms ማለትም ፌስቡክ ፣ ዩቲውብ ፣ ቲዊተር ፣ ቴሌግራምና ሌሎች ማህበራዊ ሚዲያዎች መረጃን ዴሞክራሲያዊና ተደራሽ በማድረግ የመረጃ የኃይል ሚዛን ከመንግሥትና ከግል የሚዲያ ኩባንያዎች ወደ ሲቪል ማህበራት፣ ጦማሪያን፣ የዜጋ ጋዜጠኞችና ሕዝብ እንዲያዘነብል አድርጎታል።
በይነ መረብ መረጃም ሆነ ሀሳብ የሚዘዋወሩበትን አግባብ ፍጹም ቀይሯል። በቅድመ በይነ መረብ ዘመን መረጃ የሚዘዋወረው የሚተላለፈው በጋዜጣ፣ በመጽሔት፣ በሬዲዮ፣ በቴሌቪዥን፣ በፖስታ፣ በመልዕክተኛ፣ በስብሰባ፣ በማህበራዊ አጋጣሚዎች (በቡና፣ በማህበር፣ በእቁብ፣ በዳጉ ፣ ወዘተረፈ)ነበር።
በድህረ በይነ መረብ ግን መረጃም ሆነ ሀሳብ በፌስ ቡክ፣ በዩቲውብ ፣ በቲዊተር ፣ በቴሌግራም ፣ በኢሜይል ፣ ወዘተረፈ በስፋት መዘዋወርና መሰራጨት ጀመረ። በዚህም የመረጃ ተጠቃሚው በይዘትም ሆነ በተደራሽነት የተሻለና ቀላል አማራጭ እንዲኖረው አስችሏል።
ዛሬ ዜናም ሆነ ሌላ መረጃ ለማግኘት የአዲስ ዘመንን እትም፤ የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥንን ዜና እወጃና ዝግጅት፤ የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎትን መልዕክትና ቴሌግራም አይጠብቅም። በእጅ ስልኩ ሁሉንም ማግኘት ይችላል። ከማህበራዊ ሚዲያዎች ዜናውንም መረጃውንም በቀላሉ መቀራረም ይችላል።
ሀሳቡን ለመግለጽም ወደ መደበኛ ሚዲያው መሔድ ሳይጠበቅበት ባለበት ቦታ ባሻው ጊዜ በእጅ ስልኩ አማካኝነት ያጋራል። በይነ መረብ መረጃን ተደራሽና ዴሞክራሲያዊ አድርጓል አየተባለ የሚወደሰውም ለዚህ ነው ።
ሆኖም ይህ ተአምረኛ ለውጥ የጥቅሙን ያህል ይዞት የመጣው ጣጣም የትየለሌ ነው። በቅደመ በይነ መረብ ዘመን በመደበኛ ሚዲያው መረጃዎች ከመሰራጨታቸው በፊት በዘጋቢውና በአርታኢው ተጣርተውና ታርመው ያልፉበት የነበረው አሰራር በማህበራዊ ሚዲያው በመቅረቱ ሆን ተብሎ ለሚዛባ መረጃ disinformation፣ ለተሳሳተ መረጃ misinformation እና ለሀሰተኛ ወሬ fake news በር በመክፈቱ የመረጃ መልክዓውን አባጣ ጎርባጣ አድርጎታል ።
ለሴራ ኀልዮት conspiracy theory ፣ ለውዥንብር የተመቸ በመሆኑ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ተቋማትን ክፉኛ እንዲጎዱ ፤ የዜጎች ግንኙነት እንዲሻክር ፤ ዘረኝነትና ጎሰኝነት እንደ ሰደድ እሳት በቀላሉ እንዲዛመት ፤ ጥላቻ ልዩነትና ግጭት እንደ እንጉዳይ እንዲስፋፋ ፤ ሕፃናትና ወጣቶች ለወሲብ ፊልም እንዲጋለጡ ከማድረጉ ባሻገር ለወሲባዊ ጥቃት በር ከፍቷል። የማህበራዊ ሚዲያ ሱስ ዜጎችን ለጭንቀትና ለድብርት ፤ ቤተሰባዊ ግንኙነትን ለዝንፈት ፤ ወዘተረፈ በመዳረግ ሀገራትን ለተለያዩ ህልቁ መሳፍርት ቀውሶች እየዳረገ እያወዛገበ ይገኛል ።
ራሱን ” የጋዜጠኝነት ድምጽ “ብሎ እንደሚጠራው እንደ ኮሎምቢያ ጆርናሊዝም ሪቪው CJR መፅሔት የቅርብ ጊዜ ጥናት ከሆነ ከአሜሪካውያን 60 በመቶው ዜና የሚያገኙት ከፌስቡክ ወይም ከቲዊተር ነው።
ከ200 ዓመታት በላይ የዳበረ ፣ የጎለበተ ፣ የደረጀ ዴሞክራሲና ልምድ ያለው መደበኛ ሚዲያ ባለበት ሀገር ከ10 ሰው ስድስቱ ዜና የሚያገኙት ከማህበራዊ ሚዲያ ከሆነ ፤ የዳበረ ነፃና ገለልተኛ የሆነ መደበኛ ሚዲያ በሌላት ሀገራችንማ ቁጥሩ ወደ 80 ፣ 90 በመቶ ከፍ ሳይል ይቀራል።
ሎሬት አማኑኤል አብዲሳ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ተግባቦት ረዳት ፕሮፌሰር በአንድ ጋዜጣ ላይ ፤ ” ነፃነት ያለ ኃላፊነት ጥፋት ነው ” በሚል ርዕስ ለንባብ ባበቁት ቆየት ያለ መጣጥፍ ይሄን ጥሬ ሀቅ አረጋግጠውልናል። “…በሀገራችን በማህበራዊ ሚዲያዎች የሚሰራጩ መረጃዎች ሁሉ ትክክልና እውነተኛ እንደሆኑ አድርጎ የሚቀበለው ሰው ቁጥር ብዙ ነው። ይህ አጠቃላይ ከሀገሪቱ ዕድገት ጋር የተያያዘ ነው።
…” ፤ ቀደም ባሉት ዓመታት በተለይ በመንግሥት መደበኛ መገናኛ ብዙኃን አመኔታ መታጣቱ አብዛኛው ዜጋ ማህበራዊ ሚዲያን በመረጃ ምንጭነት እንዲመርጥ መግፍኤ ሆኖታል። የዘረኝነት ፣ የጥላቻ እንዲሁም ሀሰተኛ መረጃዎች በማህበራዊ ሚዲያው በፍጥነት በአጭር ጊዜ ለሕዝብ ይደርሳሉ ማለት ነው።
ስለሆነም ጥፋታቸው ከፍተኛ ነው። ጁሊያን ዮርክን የተባሉ የሚዲያ ጎምቱ ተመራማሪ፤ “…ከእንግዲህ መደበኛው ሚዲያ በሚገዛበት ሕግ ማህበራዊ ሚዲያውን ማስተናገድ አይቻልም ::” ብለዋል ፤ ለነገሩ ጉግል ፣ አፕል ሜት እና ፌስቡክ እንደ አልቃይዳ ፣ ታሊባንና አይሲስ ያሉ አሸባሪዎች ማህበራዊ ሚዲያዎችን በመጠቀም የፕሮፓጋንዳ፣ የጥላቻ መልዕክት እንዳያስተላልፉ ፤ አባል፣ ተከታይ እንዳያፈሩ ለመከላከል ከመንግሥታት ጋር በመስራት ላይ ናቸው።
ከአንድ ዓመት በፊት አንድ የአውስትራሊያ ዜግነት ያለው አክራሪ በኒውዚላንድ ክራይስት ቸርች ከተማ በሚገኙ ሁለት መስጊዶች ላይ ተኩስ ከፍቶ 50 ንፁሃን ገድሎ በርካቶችን ሲያቆስል በፌስ ቡክ ቀጥታ ይተላለፍ ስለነበር፤ ሀገሪቱ የሽብር ጥቃቶችን የሚያበረታቱ፣ የጥላቻና ሀሰተኛ መረጃዎች በማህበራዊ ሚዲያ እንዳይሰራጩ የሚገድብ ሕግ ለማውጣት እየሰራች ሲሆን፤ የእንግሊዙ ” ዘ ኢንዲፔንደንት ” ጋዜጣ በበኩሉ የፌስቡክ ገፁን ቀኝ አክራሪዎች እንዳይጠቀሙ አግዷል።
የኤንቢሲ ዘጋቢ ቤን ኮሊንስ ለCJR እንደተናገረው፤ እንደ ፌስቡክ ፣ ቲዊተርና ዩቲውብ ያሉ ኩባንያዎች በማህበራዊ ሚዲያው ለሚስተዋለው የተሳሳተና የተዛባ መረጃ ናዳ ፤ ይህን ተከትሎ ለሚፈጠር ማህበራዊና ፖለተካዊ ምስቅልቅልና ቀውስ ተጠያቂ ናቸው። ከዚህ ቀደም በዚሁ ጋዜጣ ለመግለጽ እንደሞከርሁት፤ ማህበራዊ ሚዲያው በመላው ዓለም በሀሰተኛ፣ በተሳሳተ መረጃ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን በማናጋት ክፉኛ እየተከሰሰና ስሙ እየተብጠለጠለ ይገኛል። እዚህ ላይ ማህበራዊ ሚዲያው አይደለም እንደኛ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እና ለነፃና ገለልተኛ መደበኛ ሚዲያ ግንባታ አርፋጅ ለሆኑ ሀገራት ለምዕራባውያንም አደጋ መደቀኑን ያሳያል።
ዶናልድ ትራምፕንና ጆ ባይደንን ባፋጠጠውና ባወዛገበው የ2020 ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ትራምፕ ምርጫው ተጭበርብሯል በሚል ባይደን ማሸነፋቸው ከተገለጸ ከአንድ ወር ከሳምንት በኋላም ሽንፈታቸውን አምነው አለመቀበላቸው ሲያስገርመን ሴኔቱ የባይደንን አሸናፊነት ያረጋገጠውን የኤሌክቶራል ኮሌጅ ውጤት እንዳያጸድቅ እያሳደሙ ይገኛል። ለነገሩ ተቀበሉትም አልተቀበሉት በውጤቱ ላይ የሚያመጣው ለውጥ የለም። ዜጎች በአሜሪካ ምርጫ ላይ ያለውን እምነት ግን ጥያቄ ላይ መጣሉ አይቀርም። የሚያሳዝነው እዚህ ደረጃ ላይ የተደረሰው ፕሬዚዳንት ትራምፕ ከ72 ሚሊዮን በላይ ተከታይ ባላቸው ቲዊተር በሚነዛ ሀሰተኛ መረጃ መሆኑ ነው።
በተደጋጋሚ በሚነዙት ሀሰተኛ መረጃና የሴራ ፖለቲካ የተነሳ 60 ሚሊዮን አሜሪካውያን ምርጫው ተጭበርብሯል ብለው ያምናሉ። ተሰናባቹ ፕሬዚዳንት በአሜሪካ ታሪክ ታይቶ ፣ ተሰምቶና ተደርጎ በማያውቅ ሁኔታ የተሸነፉበትን ምርጫ ለመቀልበስ የሴራ ኀልዮትንና ሀሰተኛ መረጃን እያጣቀሱ ነው።
ካርል ማርክስ ታሪክ በመጀመሪያ በአሳዛኝ ሁኔታ በማስከተል በአስቂኝ ሁኔታ ራሱን ይደግማል እንዳለው ትራምፕ የሪቻርድ ኒክሰኑን ዋተርጌት በአስቂኝ ሁኔታ ደግመውታል። የጆርጅያ ምርጫ ውጤትን ለማስቀየር አስፈጻሚውን በስልክ ሲያስፈራሩ የተቀረጸን ድምጽ ዋሽንግተን ፖስት እሁድ ይፋ አውጥቶታል። ታሪክ በአስቂኝ ሁኔታ ራሱን ደገመ እንዲሉ። ትራምፕ ከነጩ ቤተ መንግሥት ጓዛቸውን ሸከፈው ለመውጣት ከ20 ያነሱ ቀናት ብቻ የቀራቸው ቢሆንም ከስልጣን እንዲለቁና እንዲጠየቁ ግፊት ተጀምሯል።
በማህበራዊ ሚዲያው የሚራገቡ የደባ፣ የሴራ፣ የጥላቻ እና ሀሰተኛ መረጃዎች የዴሞክራሲያዊ ተቋማት ነፃና ገለልተኛ እንዳይሆኑ እና አጠቃላይ ሥርዓቱን አደጋ ላይ እየጣሉ ከመሆናቸው ባሻገር ሕዝብን እየከፋፈሉ ይገኛል። አሜሪካንን ፣ እንግሊዝንና ሀገራችንን በአብነት ማንሳት ይቻላል። በEBS ቴሌቪዥን ” Teck Talk ” አዘጋጅነት የምናውቀው ሰለሞን ሙሉጌታ፤ ” ግርምተ ሳይቴክ ” በሚል መፅሐፉ ገፅ _ 154 ላይ ፤ ” እንደፌስቡክና ትዊተር ባሉ የማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ የሚናፈሱ በርካታ የሀሰት ወሬዎች ሕዝቡን ግራ ከማጋባት አልፈው የአንድ ሀገር ማህበራዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ላይም አሉታዊ ተፅዕኖ ያሳድራሉ። …” ሲል ተፅዕኖአቸው ከፍ ያለ መሆኑን ያረጋግጣል።
ሆኖም በተለይ ፌስ ቡክ የሀሰት ወሬ ስርጭትን ለመከላከል ” fake news story ” ብሎ ለመፈረጅ እንዲሁም፤ የዜናዎችን እውነተኝነት መጣራት ሲያስፈልግ ደግሞ ” disputed ” የሚል መለያ የሚያስቀምጥ አሰራርን ሥራ ላይ ቢያውልም የሚፈለገውን ያህል ውጤታማ አለመሆኑን በሀገራችንም በመላው ዓለምም እያስተዋልን ነው ።
ለውጡን ተከትሎ በትህነግ ፊታውራሪነት በመደበኛና በማህበራዊ ሚዲያ ቀን ከሌት ይነዛ የነበረ የሴራ ፣ የጥላቻና የልዩነት ሀሰተኛ መረጃ ሀገራችንን እንዴት ወደለየለት ቀውስ ሲያንደረድራት እንደነበር ያስታውሷል።
በሕግ የበላይነት ዘመቻው ወቅት ሕዝብን ውዥንብር ውስጥ የሚከቱ፤ ዓለምአቀፍ ማህበረሰቡን ዛሬ ድረስ የሚያደናግሩ ሀሰተኛና የተዛቡ መረጃዎች በዲጂታል ወያኔ እንዴት እንደሚናፈሱ እየታዘብን እንገኛል። የሀሰተኛና ሆን ተብሎ የተዛባ መረጃ ከሚያስከትለው ፖለቲካዊና ማህበራዊ ቀውስና ምስቅልቅል ባልተናነሰ እውነተኛና ሀቀኛ መረጃዎችና ሀሳቦችን በመድፈቅ የሚያስከትለው ዘላቂ ጉዳት ከፍ ያለ ነው።
እንደ መላ
በሀገራችን የሚዲያ ታሪክ እንደ ከሀዲው ትህነግ ማህበራዊውን ሆነ መደበኛውን ሚዲያ እንደ ጦር መሳሪያ የተጠቀመ እየተጠቀመ ያለ ቡድን የለም ። በዚህም ሀገራችንን በምንም ሊተመንና ሊሰላ የማይችል ውድ ዋጋ አስከፍሏታል። የፊታችን ሰኔ በሀገራችን የሚካሄደውን የመጀመሪያ ዴሞክራሲያዊ ፣ አሳታፊ፣ ነጻ፣ ፍትሐዊና ገለልተኛ ምርጫ የትህነግም ሆነ የሌሎች እኩይ ኃይሎች የጥቃት ኢላማ እንደሚሆን ተገንዝቦ አበክሮ ቅድመ ዝግጅት ማድረግ እንደሚገባ እያሳሰብሁ ሀሰተኛና የተዛባ መረጃን ለመከላከል ያግዛሉ ብዬ የማምንባቸውን ነጥቦች አነሳለሁ።
በአአዩ አጋፋሪነት ከሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች የተውጣጡ ልሒቃን ፤ ከመንግሥትና ከግል መገናኛ ብዙኃንና ከጋዜጠኝነት የሙያ ማህበራት ጋር በመቀናጀት ሀሰተኛና ሆን ተብሎ የተዛባን መረጃ የመከላከያና የመቆጣጠሪያ ስትራቴጂ ሊነድፉ ይገባል። ከዚህ ጎን ለጎን ዜጎች ስለአዲሱ የመገናኛ ብዙኃን አዋጅ ግንዛቤ እንዲኖራቸው በስፋት ማስታወቅ ይጠይቃል። በማስከተልም የሚከተሉትን ተግባራት መውሰድ ይበጃል የሚል እምነት አለኝ ።
የመጀመሪያው ዜጎች ሚዲያውን ጨምሮ በዴሞክራሲያዊ ተቋማት እምነት እንዲኖራቸው መስራት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ዜጎች ስለ ሚዲያ በተለይ ስለታማኝና ሀቀኛ ሚዲያ ግንዛቤ እንዲኖረው media literacy በየአጋጣሚው ማስተማር ነው። እንደ ፌስቡክና ዩቲውብ ካሉም ሆነ ከሌሎች ማህበራዊ ሚዲያዎች ጋር ተቀራርቦ በመስራት ሀሰተኛና የተዛባ መረጃን ለመከላከል የሚያስችሉ አዳዲስ አሰራሮችንና ቴክኖሎጂዎችን በመጋራትና ዘመኑን የሚዋጁ ወቅታዊ ስልጠናዎችን ከስር ከስር በመውሰድ አቅምን ማጎልበት ሌላው ሀሰተኛ መረጃን የመከላከያ ዘዴ ነው።
ከሁሉም በላይ ግን የመንግሥትንም ሆነ የግል ሚዲያውን ማጠናከርና መደገፍ፤ በስልጠናና በተለያዩ ማበረታቻዎች ማነቃቃት፤ ነጻና ገለልተኛ እንዲሆኑ ከየትኛውም አካል ከሚመጣ ተጽዕኖ መጠበቅ ፤ በቀላሉ ተደራሽ እንዲሆኑ በመሰረተ ልማት ማገዝ ፤ የወረቀትና የሕትመት ዋጋን አቅማቸውን ያገናዘበ ማድረግ ፤ የማስታወቂያና የሌሎች አማራጭ ገቢዎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ምቹ ሁኔታ መፍጠር።
የንባብ ፣ የውይይትና የሙግት መድረኮችን ማስፋት ከሁሉም በላይ የጋዜጠኛውን አቅም በተከታታይ የሥራ ላይ ስልጠናዎች ማጎልበት፤ በዩኒቨርሲቲዎች የሚሰጠውን ስልጠና ጥራት በቅርብ መደገፍና መከታተል የበቃ ጋዜጠኛ፣ የተደራጀ ሚዲያና መረጃ ከየት ማግኘት እንዳለበት በውል የተገነዘበ አንባቢ፣ አድማጭና ተመልካች ማፍራት በቀላሉ በሀሰተኛና በተዛባ መረጃ የማይነዳ ትውልድ በሒደት መቅረጽ ያስችላል።
ሀገራችን ኢትዮጵያ በእውነተኛና ጀግኖች ልጆቿ ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር !!!
አሜን ።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 27/2013