አሸብር ሃይሉ
የሰዎች ማንነት በሁለት ዋና ዋና መልኩ ይመነጫል።አንደኛው achieved status ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ascribed status ነው። achieved status ማለት ሰዎች መሆን ፈልገው የሚያገኙት ማንነት ማለት ነው ። ለምሳሌ አንድ ሰው ዶክተር ፣ አናጺ ወይም ሌላ ሙያን ፈልጎ ሲያገኝ፤ ይህ ማንነት achieved status ይባላል።
በዚህ ተመርጦ በሚገኝ በምንይዘው ሙያ ሰዎች ኃላፊነትን ይወስዳሉ። ኃላፊነት መውሰድም የግድ ነው። በወሰዱት ኃላፊነት ልክ ካልተገኙ ይወቀሳሉ፤ ይከሰሳሉ።አንዳንዴም እስከ ሞት ፍርድ ሊፈርድባቸው ይችላል።
በዚህ ማንነት ኃላፊነታቸውን ያልተወጡ ሰዎች በሁለት መልኩ ሊወገዙ ፣ ሊከሰሱ ብሎም ሊገደሉበት የሚችሉበት አግባብ አለ።አንደኛው የተሰጠን ኃላፊነት ካለመወጣት የሚመጣ ተጠያቂነት ነው።በዚህም ኃላፊነቱን ካልተወጣ ከቀላል ማስጠንቀቂያ እስከ ሞት ቅጣት ሊቀጣ የሚችልበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል።
ለምሳሌ አንድ የወታደር ኃላፊ ወታደር የሚሆነው ፈልጎ ነው። ከዓመታት በኋላም ልምድ ሲያካብት የወታደር ኃላፊ ሲሆን በሚያወጋበት ጊዜ ሆን ብሎ ስህተት ቢሰራ እና በአገሩ ላይ የክህደት ወንጀል ቢፈፅም እስከሞት ቅጣት ሊቀጣ ይችላል።
ሁለተኛው ደግሞ ከነፃነት ፍለጋ ጋር ተያይዞ የሚመጣ ማንነት ነው።በዚህም ነፃነት ከሚጠይቁት እና በሚጠየቁት መካከል በመፈጠር ግጭት የሚፈጠር ማንነት ነው።በዚህም ነፃ አውጭዎች ነፃ አውጪ ለመሆን ፈልገው እንጂ ተገደው ነፃ አውጪ ሊሆኑ አይችሉም።
በዚህ የነፃነት ፍለጋ ሂደት ውስጥ ነፃ አውጭው ሊገድልም ሊገደልም ይችላል።በአጠቃላይ በ achieved status በዚህ ሁሉ ሂደት ለሚደርሱ ማንኛውም ችግር ኃላፊነቱን የሚወስደው ራሱ ያንን ማንነት ለመያዝ የፈለገው አካል በመሆኑ ‹‹ለምን ይህ ይሆናል›› የሚያስብል ጥያቄ አያስነሳም።
በተቃራኒው ሁለተኛው ማንነት ከላይ ለመግለፅ እንደተሞከረው ascribed status ነው።ይህ ማንነት ሰዎች ሳይፈልጉ የሚሰጣቸው ማንነት ነው።ለምሳሌ ሰው መሆን ፣ ወንድ ወይም ሴት መሆን፣ የመወለጃው አገር፣ ብሔር፣ ቤተሰብ እና ተያይዞ የሚመጣው የምንቀበለው ሃይማኖት ወዘተ.. ይሁን እንጂ አሁን አሁን በሃገራችን እየተፈጠረ ያለው የመግደል እና የማፈናቀል ብሎም ጎራ ለይቶ የፖለቲካ መርህ ቀርፆ እስከ መፋለም የተደረሰው ፈልገን ባላገኘነው ማንነት መሰረት ተደርጎ ነው።
የሰው ልጅ ፈልጎ ባላገኘው ማንነት የሚገደለው እንደዘበት ነው? የሚሳደደው? ለዘመናት ከኖረበት እና ልጅ ወልዶ ሃብት አፍርቶ ከሚኖርበት ቀየ እንደዘበት የሚፈናቀለው ፈልጎ ባላገኘው ማንነት ነው።ይህ መሆኑ ደግሞ እጅግ ያሳዝናል ብቻ ሳይሆን እጅግ ያበግናል።
የአሜሪካ የእርስ በእርስ ጦርነት የሚባለው በሰሜን የአሜሪካ ክፍል እና በደቡቡ የአሜሪካ ክፍሎች መካከል የተደረገ ጦርነት ነበር ።የጦርነቱ ዋና ዋና ምክንያቶች ሁለት ነገሮች ናቸው።አንደኛው የኢኮኖሚ ልዩነት ሲሆን፤ ሌላኛው በባርነት ላይ የተፈጠረ የፖለቲካዊ ልዩነት ነው።
በዚህ ጦርነት የሰሜኑ ክፍል ባርነት ይጥፋ አሜሪካም አንድ ትሁን የሚል ሲሆን፤ የደቡቡ የአሜሪካ ክፍል ደግሞ የአሜሪካ አንድነት እና የባሪያ መጥፋት በእኔ መቃብር ላይ ነው ይላል።ነገር ግን በመጨረሻ የሰሜኑ የአሜሪካ ከፍል ጦርነቱን አሸነፈ እና ዩናይትድ ስቴስት ኦፍ አሜሪካ የምትባል አዲስ ሃገር በአለም ላይ ተፈጠረች።በዚህ በተፈጠረ አንድነትም አሜሪካ አሁን ለደረሰችበት የዓላማችን የስልጣኔ ቁንጮ እና የዓለማችን ልዕለ ሃያል አገር ለመሆን በቃች ።
እንደ ኤሮፓውያን አቆጣጠር በ1960ዎቹ መጀመሪያ ላይ ቁጥራቸው በርከት ያሉ የአፍሪካ አገራት ነፃ ወጡ።በዚህ ጊዜ ነጻ የወጡ የአፍሪካ ሃገራት ጦርነት ውስጥ አይግቡ እንጂ ልክ እንደ አሜሪካ ለሁለት ተከፈሉ።አንደኛው unionist (ካዛብላንካ) የሚባለው ቡድን ሲሆን ሌላኛው ደግሞ confederates (ሞኖሮቪያ ) የተባሉ ነበሩ፡ ፡
unionist (ካዛብላንካ ) የሚሉ በአንድ መገበያያ ገንዘብ በአንድ መንግስት አፍሪካ ትመራ የሚሉ ሲሆን፤ confederates (ሞኖሮቪያ ) ደግሞ የለም አፍሪካ አንድ መሆን የለባትም በአንድ መንግስት አትመራም፣ በአንድ የመገበያያ ገንዘብ መገበያየት እና አንድነት የሚባሉ ነገሮች ባፍንጫችን ይውጣ የሚሉ ናቸው።
እዚህ ላይ አንድን ነገር ማስተዋል ይገባል።አንድነት ኃይል ነው።ይመስለኛል አፍሪካ አንድ ሆና ቢሆን ኖሮ ዛሬ ላይ በተለያዩ የአፍሪካ አገራት መካከል የሚፈጠሩ የድንበር ግጭቶች፣ አለመግባባቶች አይኖሩም ነበር።በእነዚህ በሚፈጠሩ ግጭቶች እና አለመግባባቶች ምክንያት ደግሞ ስደቶች እና አጠቃላይ በአፍሪካ በመንግስታት መካከል የሚታዩ ቁርሾዎች እና አለመግባባቶች በሚያስከትሉት ልዩነት ለጦርነት እና ላልተገባ ወጭ እንዲሁም አፍሪካውያን ለማያቋርጥ እንግልት አይዳረጉም ነበር ባይ ነኝ።ለምሳሌ በታላቁ የህዳሴው ግድብ ማን ከማን ይጋጭ ነበር።
ምክንያቱም ሁሉም አንድ እንደ አፍሪካ እንጂ ኢትዮጵያ እና ግብጽ ብሎ መጠዛጠዝ አይኖርም ነበር። ግብጽም በተደጋጋሚ በሃገራችን ላይ የምታደርገው ብሔረሰብን ከብሔር ማጋጨት እና ሌሎች ተንኮሎችን በኢትዮጵያ ላይ ባላደረገች እና ለሃገራችን ብሎም ለቀጠናው ስጋት ባልሆነች ነበር።ነገር ግን አፍሪካ አንድ ባለመሆኗ አንድ ሆና መፍታት የምትችላቸው ችግሮቿ እንዳይፈቱ በጠንካራ እና ውሉ በማይታወቅ ገመድ የታሰረ ይመስላል።
ከዚህ ላይ ኢትዮጵያውያን አንድ ነገር መገንዘብ ይገባናል።ይህም መንገዱ አንድ ነው።አንድ ስትሆን አሜሪካ የት እንደደረሰች ከተረዳን፤ አፍሪካ በመበታተኗ ያለችበትን ከተገነዘብን ፈልገን ባላገኘነው ማንነት ምክንያት መበታተን አይኖርብንም።ይህ በማንነት ላይ እየተሰነዘሩ ያሉ ለሰሚ የሚከብዱ እና ለማየት የሚዘገንኑ ድርጊቶችን በወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ላይ መፈጸም በብዙዎች ዘንድ ጥያቄ የሚፈጥር ነው።
እስኪ ሁሉንም ሳንፈልግ ያገኘናቸውን ማንነቶች እናስተውላቸው እና ሰው ሆኖ ለመፈጠር ሰው ልሁን ብሎ መርጦ የተፈጠረ ሰው አለ እንዴ? እንኳንስ የምንወለድበትን ማንነት ቀርቶ ቦታም ሆነ ጊዜ መምረጥ አንችልም። እንደዚሁ ሁሉ የምንወለድበት ጎሳ በፍፁም ለ መምረጥ አለመታደላችንን እንገንዘብ።
ያም ሆነ ይህ ማንም አለ ማን ኢትዮጵያን ascribed status ማፍረስ መጣር አለምን በዶሮ ለማረስ እንደ መሞከር ነው የሚል እምነት አለኝ ።ምክንያቱም ኢትዮጵያን ከጥንት ጀምሮ ለማፍረስ ያልሞከረ አልነበረም። ምክንያቱም ብዙዎች ባልተመረጠ ማንነት ሰው ምንም ዓይነት በደል ሊፈፀምበት እንደማይገባ እና ተጠያቂም እንደማይሆን ይረዳሉ።
ነገር ግን ጥቂቶች (በእርግጥ ሳይረዱት ቀርተው አይመስለኝም) ሳይፈለግ በተገኘ ማንነት ላይ ለሚያደርሱት ጥቃት መላው ኢትዮጵያውያን ልናወግዝ ይገባል። እኛ ኢትዮጵያውያን አንድ ነን። እስከ አሁንም ባልፈለግነው ማንነት በሚፈፀም ደባ ለመበታተን ያልደረስነው ለዚሁ ነው። ሰላም!
አዲስ ዘመን ታህሳስ 27/2013