አብርሃም ተወልደ
ታዋቂ እና በኢትዮጵያ የሙዚቃ ታሪክ ውስጥ አሻራቸውን ካኖሩ አንጋፋ ብሎም ከቀዳሚዎች ተርታ የሚሰለፍ ሙዚቀኛ ነው። አርቲስቱ በርካታ ዘመናዊ ሙዚቃዎችን በመስራት እና በማቅረብ ይታወቃል፤ አርቲስት አለማየሁ እሸቴ፡፡
የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በአርበኞች ትምህርት ቤት ነው የተከታተለው። ባደረበት ጥልቅ የሙዚቃ ስሜትና ባለው ግሩም ተሰጥኦ ተገፋፍቶ ድምጻዊነቱን በፖሊስ ሠራዊት ሙዚቃ ክፍል አሀዱ ብሎ መጀመሩን መረጃዎች ይጠቁማሉ። ብዙዎቹ የአርቲስቱ ሙዚቃዎች ከስሜት በሚያፈልቃቸው ዜማዎች የታጀቡ ናቸው፤ ዘመናዊነት የሚታይባቸውና ከውጭ ሀገር አርቲስቶች ስራዎች ጋር እንደሚመሳሰሉም ይነገራል።
ከአርቲስት አለማየሁ እሸቴ የሙዚቃ ስራዎች መካከል «እዬዬ»፣ «ማሪኝ ብዬሻለሁ» የተሰኙት ዜማዎቹ ወደ እውቅና ማማ እንዳወጡት ይገለጻል። እነ «ስቀሽ አታስቂኝ»፣ «ማን ይሆን ትልቅ ሰው»፣ «እንደ አሞራ ክንፍ አውጥቼ ልብረራ» በተሰኙት ዜማዎቹ በብዙዎች ዘንድ እውቅናን እና ተወዳጅነትን አትርፏል።
ለባለቤቱና ለልጆቹ ማቆላመጫ «ውዷ ባለቤቴ!» የምትል ዜማ ተጫውቷል። “አዲስ አበባ ቤቴ” የሚለው ዜማው የአርቲስቱ ልብ ሰራቂ ከሆኑ ስራዎች መካከል ይጠቀሳል። እስካሁን ድረስ ከ62 በላይ ዜማዎቹ በሸክላ የተቀረጹ ሲሆን ፣15 ሺህ የሚያህል ኮፒም እንደተሸጠለት መረጃዎች ይጠቁማሉ።
አርቲስት አለማየሁ በአሁኑ ሰዓት በኮቪድ 19 ምክንያት ምንም አይነት እንቅስቃሴ እያደረገ አለመሆኑን ይናገራል። የዚህ በሽታ ተጽእኖ በሀገር ደረጃ ብቻም ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ በማየሉ ነገሮች መዘጋጋታቸውን ይገልጻል። የሙዚቃ ስራም ከህዝብ ጋር የሚያቀራርብ መሆኑን ጠቅሶ፣ ብዙም እንቅስቃሴ እያደረገ አለመሆኑን ያብራራል፡፡
አርቲስቱ የልብ ህመም አለበት፤ የኮቪድ በሽታ ደግሞ አርቲስቱ የያዘው አይነት ተጓዳኝ በሽታ ያለባቸውን ሰዎች የሚያጠቃና ለሞት የሚዳርግ በመሆኑ አሁን ጊዜውን እያሳለፈ ያለው ቤት ውስጥ እንደሆነ ይናገራል።
እንደ አርቲስቱ ገለጻ ፤ ከዚህ በፊት የልብ ህክምና ያደረጉለት ጣሊያኖች ወደ ጣሊያን እንዲያመራና ህክምና እና እንክብካቤ እያደረጉለት እንዲቆይ ቢጋብዙትም፣ እሱ ግን በአገር ቤት ያለውን ክብር መወደድ መርጦ ወደ ጣልያን ከማቅናት ተቆጥቧል።
አርቲስቱ የእረፍት ጊዜውን እንዴት እያሳለፈ ይሆን?
አርቲስቱ አስገዳጅ ሁኔታ እና ምክንያት ካልገጠመው በስተቀር ከቤት አይወጣም። አያደርስብህ ከበሽታ በላይ በሙዚቃ መለከፍ ይከብዳል ይላል፤ በልጅነቱም “በሽታው!” ሙዚቃ እንደነበር ያስታውሳል። በእረፍት ጊዜውም ከሚያደርጋቸው ዋና ነገሮች አንዱ ሙዚቃ ማድመጥ መሆኑን ይጠቅሳል።
ማንበብም የአርቲስቱ የእረፍት ጊዜ ማሳለፊያ ነው። አሁን በዚህ የእረፍት ጊዜው ደግሞ የእለት ተዕለት ተግባሩ ይሄው ሆኗል። በውጭ ቋንቋ የሚጻፉ መጽሔቶች ደንበኛ ነው፤ ጥሩ ፊልም ተመልካችም እንደሆነ አርቲስቱ ይናገራል፡፡
ሌሎች የእረፍት ጊዜያቸውን እንዲያሳልፉ ምን ይመክራል?
ሌሎች የእረፍት ጊዜያቸውን በማንበብ እንዲያሳልፉ ሲመክር “ማንበብ …ማንበብ… ማንበብ” ብሎ ያስገነዝባል። ለህጻናት እና ወጣቶች ደግሞ “መማር… መማር… መማር” ምትክ የለሽ እረፍት ማለት ይህ ነው በማለት ገልጿል። ማንኛውም ሰው ብቁ መሆን ፣ ለግል ህይወቱ ፣ለአገሩ ፣ ብሎም ለወገኑ መጥቀም ከፈለገ በማንኛውም ሁኔታ ለንባብ ለትምህርት ትልቅ ትኩረት መስጠት ይኖርበታል ሲል ያስገነዝባል፡፡
ምክር
በአገሪቱ ከአለፉት ሁለት ሶስት ዓመት ወዲህ እጅግ የሚገርም ለውጥ እየታየ ነው። ቀደም ሲል ፍቅርንና መከባበርን የመሰለ ድንቅ ነገር ጠፍቶ እንደ አበደ ውሻ መነቋቆር እና መነካከስ ገኖ ነበ። ይህ ሁኔታ ግን እየተለወጠ ሄዶ አገሪቱ ወደ ፍቅር እየመጣች ነው ሲል አርቲስቱ ይገልጻል ፤ በወጣቱም ላይ ይሄው እየታየ እንደሆነም ነው ያመለከተው፡፡
አርቲስቱ ወቅቱን አስመልክቶም “እየሆነ ያለውን ሳየው ባለችኝ ደካማ አመለካከት አንድ ገበሬ የዘራውን ነው የሚያጭደው፤ የሚያመርተው። ያልዘራውን ከየት ያገኛል፡፡” ሲል ገልጾ፣ ማንኛውም ሰው የሚዘራው ወሬ፣ በቀል፣ ጥላቻ … ከሆነ የሚያጭደውም እንደዘራው ነገረኛ፣ ወረኛ፣ ክፉ … ነው የሚሆነው፡፡›› ሲል ይገልጻል፡፡
ልክ እንደ ገበሬው የቀድሞ ሹማምንቶችን እና ገዢዎችን ብንመለከታቸው በነበሩበት ዘመን ሁሉ የዘሩት ክፋት እና አመጽ ነበር ይላል። ሰው እርስ በእርስ የሚባላ የማይስማማ ሆኖ መቆየቱን ይናገራል።እነሱ የሰዘሩት ደግ፣ ቅን፣ ጨዋ ፣አገር ወዳድ ህዝብ ማበላሸቱን ይጠቁማል፡፡
“ፈጣሪ ይመስገን፤ አሁን ሁሉም ነገር ወደ ሰላም እየተጓዘ ነው። ወጣቱ በፍቅር እና ጓደኝነት እየተጓዘ ነው።ይህም በበዓላት ጊዜ ሁሉ በየቤተክርስቲያኑ በየመስኪዱ አዛውንቶችን በማክበር እየተገለጸ ይገኛል፤ ፈጣሪም ምድሪቷን እየታረቃት ያለበት ጊዜ ላይ እንደሆንን ያሳያል፡፡” ብሏል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 25/2013