ለምለም መንግሥቱ
ነጋዴውና ሸማቹ እየተገበያየ ነው። የሰዎች እንቅስቃሴ ከወትሮው ጨምሯል። በዓልን የሚያደምቁ ሙዚቃዎች በንግድ ቤቶቹ ከፍ ብለው እየተሰሙ ነው። ያሬዳዊ ዝማሬዎችም እንዲሁ። እነዚህ መዳረሻ ዝግጅቶች የበዓሉን ድባብ ከወዲሁ አድምቀውታል።
ይህ በዓል ኢየሱስ ክርስቶስ በ30 ዓመቱ በቅዱስ ዮሐንስ እጅ በዮርዳኖስ ወንዝ መጠመቁን አስመልክቶ ገና ከተከበረ ከ12ኛው ቀን በኋላ የሚከበር ነው። ሁለቱንም በዓል የኦርቶዶክስና ካቶሊክ እምነት ተከታዮች በዋናነት ያከብሩታል። ጥምቀትን ለየት የሚያደርገው ሁሌም እንደምንለው ኃይማኖታዊና ማህበራዊ ክንዋኔ ያለውና በርካታ ህብረተሰብ የሚያሳትፍ መሆኑ ነው።
ጥምቀት በአብዛኛው የዓለማችን ሀገራት የህዝብ በዓል በሚል ይከበራል። ዝግጅቱም የአንዱ ከሌላው በይዘት ይለያያል። መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በቡልጋሪያ፣ ግሪክና ሩሲያ ገንዳ ውስጥ ውሃ ተዘጋጅቶ ይከበራል።
በአውስትራሊያ ሜርቦርን አቅራቢያ ደግሞ በውሃ ዳርቻ፣ በሜክሲኮ ጣፋጭ ዳቦ በማዘጋጀት፣ በጣሊያን ህፃናት በበዓሉ ዋዜማ ከረሜላና የተለያዩ ሥጦታዎችን ለመቀበል ማልደው ይነሳሉ። ለሥጦታ መቀበያ የሚሆን ቅርጫትም አብሮ ይዘጋጃል።
በኢትዮጵያ ደግሞ የእየሱስ ክርስቶስን መጠመቅ መሠረት በማድረግ ቃና ዘገሊላ በሚል ስያሜ ለተከታታይ ሶስት ቀናት ይከበራል። ከሌሎች ሀገሮች ለየት የሚያደርገው ታቦት መኖሩ ሲሆን፣ ታቦታቱ ከማደሪያቸው ወጥተው ወደተዘጋጀላቸው የማደሪያ ሥፍራ በያሬዳዊ ዝማሬ እያጀቡ መሸኘትና የመቀበል ሥነ ሥርዓት ያለው መሆኑ ነው። ለታቦታቱም ማደሪያ ድንኳን ይዘጋጅላቸዋል።
አብዛኞቹ ከአንድ ቀን አዳር በኋላ ወደማደሪያቸው ይመለሳሉ። የተወሰኑት ደግሞ በክብረ በዓላቸው ቀን ለአብነትም በ12 እና በ13 ይሸኛሉ። ታቦታቱ ከማደሪያቸው ሲወጡም ሲመለሱም የሰዎች አጀብ አይለያቸውም። ከመንፈሳዊ ዝማሬ በተጨማሪ በዓሉን ሊታደም በሥርዓቱ ላይ የተገኘው ሁሉ በባህላዊና ዘመናዊ ዘፈን ይጨፍራል። ይጫወታል።
አብዛኛው ታዳሚም በሀገር ባህል ልብስ የሚደምቅ ሲሆን፣ ከእነ አለባበሱም ‹‹ለጥምቀት ያልሆነ ቀሚስ ይበጣጠስ›› ስለሚባል ሴት ወንዱ ተውቦ ነው በሥፍራው የሚገኘው። ከየአቅጣጫው በመምጣት በሚሳተፍበት በዚህ የ ’አደባባይ በዓል ላይ የአካባቢ መገለጫ የሆኑ አልባሳትና ባህላዊ ጭፈራዎች ይታያሉ።
አንዱ የሌላውን በማድነቅ ይደመማል። ማህበራዊ ትስስሩም ይጠናከራል። በአለባበሷ ወይንም በጭፈራዋ አይን ውስጥ የገባች ልጃገረድ የወደፊት ውሃ አጣጯን ታገኛለች። ወንዱም እንዲሁ በአንዷ እይታ ውስጥ ከገባ እንዲሁ ጾታዊ መፈቃቀዱ ይፈጠራል።
በኢትዮጵያ የጥምቀት በዓል የሌሎች ሀገራትን ትኩረት የሚስብ በመሆኑ ከተለያዩ ቦታ የውጭ ዜጎች ሳይቀሩ ወቅቱን ጠብቀው ይመጣሉ። በዓሉ የቱሪስት መዳረሻም እየሆነ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞም አምና በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና ባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) የማይዳሰስ ቅርስ ሆኖ ለመመዝገብ በቅቷል።
ምንም እንኳን የዓለም ስጋት የሆነው ኮቪድ 19 ቫይረስ ወረርሽኝ እያስጨነቀ ባለበት በዚህ ወቅት በምዝገባው ማግሥት ላይ ሆነን የምናከብረው ቢሆንም የቅድመ ጥንቃቄ መከላከያዎችን በመጠቀም በዓሉን ለማክበር ዝግጅቱ መጠናቀቁንም የሚመለከታቸው አካላት አስታውቀዋል።
ጥምቀትና ጎንደር
ጥምቀትና ጎንደር የማይነጣጠሉ የአንድ ሳምንት ገጽታ እስኪመስሉ ድረስ ስለበዓሉ ስናወሳ አካባቢው ይጠቀሳል። የአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሙሉቀን አዳነ ስለ ዝግጅቱ እንዲህ ገልጸውልናል። እርሳቸው እንዳሉት ጎንደር በተለየ ሁኔታ ቢታወስም በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች መንፈሳዊና ባህላዊ ይዘታቸውን ሳይለቁ በደማቅ ሥነ ሥርዓት ይከበራል።
ከጥምቀት በፊት የሚከበረው የልደት በዓል ታህሳስ 29/2013 ዓ.ም በቅዱስ ላሊበላ ቤተ ክርስቲያን ከፍተኛ ቁጥር ያለው አማኝ በሚገኝበት ኃይማኖታዊ ሥርዓቱ ይከናወናል። ልደቱን ቅዱስ ላሊበላ አክብሮ ለጥምቀት ወደ ጎንደር ቀድሞ የሚገባውን እንግዳ ስለሚኖር በጎንደር የእንግዳ አቀባበሉ ቀድሞ ነው የሚጀመረው።
ከሀገር ውስጥም ከውጭም የሚጠበቁ እንግዶች እንደፍላጎታቸው የሚስተናገዱበት ሁኔታ ምቹ ይደረግላቸዋል። በተለይም ከውጭ የሚመጣው እንግዳ ገንዘቡ ብቻ ሳይሆን ጥሩ ገጽታም ይዞ እንዲሄድ ባለው አቅም ሁሉ ዝግጅቱ ያማረ እንደሆን ጥረት እንደሚደረግ ያለፉ ተሞክሮዎች ማሳያ ናቸው። የዘንድሮውን ዝግጅት ከቀድሞ ለየት የሚያደርገው ኮቪድ መኖሩ ነው።
በጎንደር ይህን ታሳቢ ባደረገ አካባቢዎችን ጽዱና ውብ አድርጎ ከመጠበቅ ጀምሮ በከተማ አስተዳደሩ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች፣ የማረፊያ ቦታዎችን ምቹ ማድረግ፣ ጎን ለጎን ደግሞ የማስተዋወቅና ጥሪ የማድረግ ተግባራት በመከናወን ላይ ናቸው።
“ኮቪድ 19 ቫይረስ ወረርሽኝን ከቱሪዝሙ ጋር ተጣጥሞ እንዴት ሊሄድ ይችላል” የሚል ቀድሞ ስትራቴጂክ ሰነድ በማዘጋጀት፣ የደህንነት ፕሮቶኮል የሚባል ማስተግበሪያም ተዘጋጅቶ በቱሪዝም ዘርፍ ውስጥ ድርሻ ላላቸው አካላት እንዲሰለጥኑ በማድረግ ሥራዎች ቀድመው ተጀምሮ ነበር። ሆኖም ሀገር ማስከበር እርምጃው ሥራውን በማዘግየት በተወሰነ ደረጃ ተጽዕኖ አሳድሯል።
ተጽዕኖው ከቱሪዝም ኢንዱስትሪው የሚጠበቀውን ሀብት በመጠኑም ቢሆን አሳጥቷል። ይሄን እንደመልካም አጋጣሚ በመውሰድ የጥምቀት በዓልም እግረ መንገድ ቱሪዝሙ እንደገና የተጀመረ መሆኑን ማብሰሪያ ይሆናል በሚል ታሳቢነት ነው ክልሉ የጀመራቸውን ሥራዎች በማከናወን ላይ የሚገኘው።
በዓል ሲከበር ያልተጠበቁ ነገሮች መከሰታቸው አይቀርም። በጎንደር ባለፈው ዓመት ለታዳሚዎች ማረፊያ ታስቦ የተዘጋጀው ወንበር በመደርመሱ ምክንያት በታዳሚዎች ላይ የሞት አደጋ ጭምር ማጋጠሙ ይታወሳል። ምንም እንኳን ከአቅም በላይ የሆነ ጭነት በመብዛቱ ምክንያት ችግሩ እንደተፈጠረ ቢገለጽም ትምህርት ሊሆን ስለሚገባ ለዶክተር ሙሉቀን ጉዳዩን አንስተንላቸው ተመሳሳይ ችግር እንዳይፈጠር የከተማ አስተዳደሩ የጥንቃቄ ዝግጅት ማድረጉን ምላሽ ሰጥተዋል።
የኮቪድ 19 ቫይረስ ወረርሽኝ አሁን መልኩን እየቀየረ መምጣቱና ወቅቱ ኢትዮጵያ ከቱሪዝም ዘርፉ በገቢ በተለይ በውጭ ምንዛሪ ግኝት በከፍተኛ ሁኔታ ተጠቃሚ የምትሆንበት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ስለሚኖረው ተጽዕኖም የቢሮ ኃላፊው አብራርተውልናል፤ ዳግም ድንበሮቻቸው እስከመዝጋት የደረሱ ሀገራት በመኖራቸው እንደቀድሞ የቱሪስት ፍሰቱ ባይጠበቅም በዐሉ ይደበዝዛል የሚል እምነት የላቸውም።
ከቦታ ቦታ የሚንቀሳቀሰውን ጎብኝ የሚያጓጉዘው ሰፊ የሆነው የትራንስፖርት ዘርፍ፣ ሆቴል ቤቶች፣ በአጠቃላይ ከአነስተኛ እስከ ከፍተኛ ያለው አገልግሎት ሰጪ ቀደም ሲል ከቱሪዝም ኢንዱስትሪው ያገኝ የነበረውን ጥቅም ያገኛል ብሎ መጠበቅ እንደማይቻል ካለው ሁኔታ መገንዘብ ይቻላል።
ቀደም ሲል በነበረው ተሞክሮ በክልሉ ከኢንዱስትሪው በአጠቃላይ ይመነጭ የነበረው ዓመታዊ የገንዘብ መጠን እስከ ሁለት ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ብር ይደርስ እንደነበር የቢሮው ኃላፊ ተናግረዋል። ክልሉ በ2012 በጀት አመት ዕቅዱ ወደ ሶስት ቢሊዮን ብር ከፍ ማድረግ እንደነበርም አስታውሰዋል።
መጋቢት 4/2012ዓም የተከሰተው ኮቪድ ዓመታዊ ዕቅዱን ወደ ኋላ እንደጎተተው አመልክተዋል። ዶክተር ሙሉቀን በመጨረሻ መልእክት ታዳሚዎች እራሳቸውን በመጠበቅና ለሌሎችም ማክንያት ላለመሆን በመከላኩ እንዲያግዟቸው ጠይቀዋል።
የጥምቀት በዓል እንደ አንድ የቱሪዝም ምርት ይወሰዳል ያሉን ደግሞ በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የዓለም አቀፍ የቱሪዝም ፋሲሊቴሽን ዳይሬክተር አቶ ቴውድሮስ ደርበው ናቸው። እርሳቸው እንዳብራሩት በአሁኑ ወቅት ኮቪድ 19 ቫይረስ ወረርሽኝ በቱሪዝም ኢንዱስትሪው ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድሯል። እንደኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ደግሞ ሀገሪቷ ውስጥ የተፈጠሩት የተለያዩ ቀውሶችና የህግ ማስከበር እንቅስቃሴዎች የሀገር ውስጥ ጎብኝዎችንም በማስተጓጎሉ ጎድቶታል።
እንደሀገር ዘርፉን ለመታደግ የሚያግዝ ስትራተጂ በመንደፍ ሥራዎች ተሰርተዋል። በስትራቴጂው የጥንቃቄ ትምህርቶች በተዳረጀ መልክ በመስተንግዶ አገልግሎት ውስጥ የሚገኙ ሆቴል ቤቶች፣ አስጎብኚዎች ድርጅቶችና ተያያዥ ሥራ ለሚሰሩ ባለድርሻ ኣካላት በሥልጠና ግንዛቤ ሲሰጥ ቆይቷል። ኮቪድን በእንዲህ መልኩ ለመከላከል የሚያስችል መርሃግብር ተዘርግቶ ነው ሳይታሰብ የህግ ማስከበር እርምጃ እስከመውሰድ የደረሰ ችግሮች የተከሰቱት።
የጥምቀት በዓል እንደ ከዚህ ቀደሙ ቱሪስት በመሳብ እንደ አንድ የቱሪዝም ምርት ሆኖ እንዲያገለግል በማድረግ ተጠቃሚ ለመሆን ባይቻልም ነገር ግን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና ከሌሎችም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት በመሆን ይሰራል። ኮቪድን ለመከላከል የተደረጉ ዝግጅቶች መኖራቸውን እንዲሁም የውስጥ ችግሮችንም ለመፍታት እንደሀገር እየተወሰዱ ያሉ ህግ የማስከበር እርምጃዎች መጠናከሩን በማሳወቅ፤ ቱሪስቱ ሰላማዊ የሆነ ጉብኝት ማድረግ እንደሚችል የማስተዋወቅ ሥራ ተጠናክሯል።
‹‹ጥምቀት በተለይ በጎንደር የማረፊያ ቦታ እስኪጠፋ እጅግ ከፍተኛ ጎብኝ የሚገኝበት መሆኑ ይታወቃል። በዚህ ዓመትም ቢሆን ኮቪድን ተቆጣጥረው እንግዶቻቸውን ለመቀበል ተዘጋጅተዋል። በዓሉን ለመታደም የጉዞ ሰነዶችን የገዙ ቢኖሩም መቀዛቀዙ እንደሚኖር ይጠበቃል›› ያሉት አቶ ቴውድሮስ በዓሉ ቢያልፍም ኢንዱስትሪውን የማነቃቃቱ ሥራ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ታሳቢ ተደርጎ እየተሰራ እንደሆነ ገልጸዋል።
በጥምቀት በዓል ለመታደም የጉዞ ሰነድ የገዙ የተለያዩ የውጭ ሀገር ጎብኚዎች ወይንም ቱሪስቶች ምን ያህል እንደሆኑ እንዲሁም ከየት ሀገር እንደሆኑ ከአስጎብኚዎችና ከሌሎችም ባለድርሻ አካላት መረጃ የመሰብሰብ ሥራ በመከናወን ላይ መሆኑንም አመልክተዋል።
ወቅታዊውን ሀገራዊ ጉዳይና ኮቪድን ታሳቢ ባደረገ የቱሪዝም መዳረሻ ተብለው የተለዩ አካባቢዎች ይኖሩ እንደሆን አቶ ቴውድሮስ ላቀረብንላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ ለጥምቀት የተለመደው ጎንደር ላይ መታደም ስለሆነ ጎንደርና አካባቢው ዋና መዳረሻ ይሆናል። ቀደም ሲልም የተለመደው ጎንደር፣ ላሊበላና ባህርዳር፣ ትግራይ የሚገኙ መስህቦችን እንዲገበኙ ነበር የሚደረገው። በአሁኑ ትግራይ መሄድ ባይቻልም በሌሎቹ ቦታ ግን እንደተጠበቀ ነው።
የቱሪዝም ልማቱ ዘላቂነት እንዲኖረው የተለያዩ ነገሮችን ታሳቢ ባደረገ ሥራዎች መሰራት አለባቸው ያሉት አቶ ቴውድሮስ፤ የሥራ ዕድል ፈጠራና የውጭ ምንዛሪ ግኝት፣ ማህበረሰቡን ያሳተፈ ሥራ በመሥራት ኦኮኖሚያዊ ጠቀሜታ እንዲኖራቸው ማድረግ የሚሉት መከናወን ካለባቸው ተግባራት መካከል እንደሚጠቀሱ ተናግረዋል። እርሳቸው እንዳሉት በዚህ ሂደት ውስጥ ቱባ የሆኑ ባህላዊ እሴቶችና ሀብቶች ሳይበረዙና ሳይከለሱ እንዲሁም ጉዳት ሳይደርስባቸው ተጠብቀው ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲሸጋገሩና ሀብት እንዲያመነጩ ለማድረግ ያስችላል።
ሌላው ያነሱት አካባቢያዊ ወይንም “ኢንቫይሮመታል ኢኮሎጂን” ማዕከል ባደረገ ሥራ ላይም ትኩረት ማድረግ ጠቀሜታው የጎላ እንደሆነ ነው። ፓርኮችን ጨምሮ ጥብቅ ቦታዎች ሳይጎዱ በአንክብካቤ መያዝ ዘላቂ የቱሪዝም ልማት ያመጣል ተብሎ ይታሰባል።
በቅርብ ጊዜያት ውስጥ ያጋጠሙት ችግሮች መወገዳቸው እንደማይቀር ይጠበቃል። ዘላቂ የሆነውን ነገር ማሰብም ተገቢ ስለሆነ ኢትዮጵያ የቱሪስት ሀብቷን በመሸጥ ከዘርፉ ለመጠቀም ሥራዎችን ማጠናከር ይኖርባታል። ከዚህ ውስጥ አንዱ የቱሪስቱን የቆይታ ጊዜ ማርዘም ይጠቀሳል። ከዚህ ቀደምም በዚህ ረገድ ብዙ ሥራዎች እንደሚቀሩ ሲነገር ነበር። ሰዎች በዓሉን በመታደማቸው ብቻ ቱሪስቶች ሊባሉ እንደማይችሉ መረጃዎች ያመለክታሉ።
ቱሪዝም አንድ ወጥ የሆነ ትርጉም ባይኖረውም በዓለም የቱሪዝም ድርጅት ፍች መሠረት ሰዎች ከመኖሪያ ቀያቸው ተነስተው ለንግድ፣ የዕረፍት ጊዜ ለማሳለፍ፣ ለመዝናናት እና ለተለያየ ጉዳይ ወደ ሌላ አካባቢ የሚያደርጉት ጉዞ ቱሪዝም ይባላል። ግንዛቤ መያዝ ያለበት ሁሉም ተጓዦች ጎብኚዎች አይደሉም። የጉብኝት ዓላማ ሊኖራቸው ይገባል። የጉብኝት የጊዜ ገደብም መኖር አለበት።
የጊዜ ገደቡ ከአንድ ምሽት ወይንም ከ24 ሰአት ያላነሰ፣ ከአንድ ዓመት ያልበለጠ ቆይታ ማድረግ አለባቸው። ኢትዮጵያም ይህን ታሳቢ በማድረግ የቱሪዝም ሀብቶችን የማስተዋወቅና ከዚያም ውስጥ ተጠቃሚ ለመሆን መስራት እንደሚኖርባት በዚሁ አጋጣሚ ጠቁመን ለማለፍ እንወዳለን። ሰላም!
አዲስ ዘመን ታህሳስ 25/2013