በሰው ልጆች የእለት ተእለት ህይወት ውስጥ በመሰረታዊነት ከሚጠቀሱ ጉዳዮች አንዱ ሰላም ነው። የሰው ልጆች ሁለንተናዊ የእድገት እንቅስቃሴ ሰላምን መሰረት ያደረገና በዚሁ የሚለካ ስለመሆኑ ቀደምት ታሪኮች በስፋት የዘገቡትና ዛሬም አበክረው የሚሰብኩት ትልቅ ሰብአዊ እሴት ነው።
የሰላም ጉዳይ የአንድን ግለሰብ፣ ማህበረሰብም ሆነ ሀገር ቀጣይ እጣ ፈንታ ሊወስን የሚችል ነው። በተለይም ባለንበት ዘመን ዓለም ከተሳሰረችበት ብዙ የትስስር መስመሮች አንጻር የሰላምን ጉዳይ አቅልሎ ማየት የሚቻል አይደለም። የሰላም ጉዳይ ዓለም አቀፋዊ ይዘት ያለው ከሆነም ውሎ አድሯል።
በተለይም እንደኛ ያሉ በእድገታቸው ወደኋላ የቀሩ ሀገራት ሕዝቦች ዛሬ ላይ ሆነው ስለነጋቸው የሚያልሟቸውን ትላልቅ ህልሞች እውን ሆነው ለማየትና ከትናንት የመከራ ህይወታቸው ለመውጣት ከሁሉም በላይ ለሰላማቸው ዘብ መቆም ይጠበቅባቸዋል። ይህንን ማድረግ ያልቻለ ማህበረሰብ ሕልሞቹ የሚጨበጥ ተስፋ ሊሆኑ አይችሉም።
የሰላምን አስፈላጊነት ከዚህም ከፍ ባለ መልኩ ማየት ከተቻለ ደግሞ የአንድ ማህበረሰብ አሻጋሪ ህልሞችን እንኳን ለማየት የሰላም ጉዳይ በራሱ ወሳኝ መሆኑን መገንዘብ ተገቢ ነው። የተሻለ ነገር ለማሰብ እንኳን ሰላም መሰረታዊ ጉዳይ መሆኑ መዘንጋት ብዙ አላስፈላጊ ዋጋዎችን ለመክፈል ቀድሞ የመፍቀድ ያህል ነው።
የሰላም ጉዳይ ከግለሰብ ባለፈ የሰውን ልጅ የቱን ያህል ከፍ ያለ ዋጋ እንዳስከፈለው በዓለም አቀፍ ደረጃ የተካሄዱትን ሁለቱን የዓለም ጦርነቶች በአግባቡ ጊዜ ወስዶ ማሰብ በቂ ነው። እነዚህ ጦርነቶች ካስከተሉት ሰብአዊና ቁሳዊ ውድመት ባለፈ ጥለውት የሄዱት ጠባሳ ዛሬም በብዙ የሚያሸማቅቃቸው ህዝቦች መኖራቸውን ማስታወስም አዋቂነት ነው።
ስለ ሰላምና ስለሰላም ዕጦት ዓለም አቀፋዊ ከሆነው ገጽታም ባለፈ ሀገራችን እንደ ሀገር ፤ ህዝቦቿም እንደ ህዝብ የከፈሉት ዋጋ የቱን ያህል ከፍ ያለ እንደሆነ በዘመናት መካከል ከነበርንበት ዓለም አቀፍ ከፍታና አሁናዊ ዝቅታ ማነጻጸር በራሱ በቂ ነው። የብዙ ስልጣኔና ገናና ታሪክ ባለቤት የሆነችን አገር የትናንት የታሪክ ትርክት ዛሬ ላይ የለወጠው ከሰላም ጋር የተያያዘው ችግራችን መሆኑን ማጤን ተገቢ ነው።
ዛሬም ቢሆን ከተኛንበት የረጅም ዘመን እንቅልፍ ነቅተኝ በአዲስ ተስፋ፣ ስለ ትናንት ታሪኮች በማሰብ ከመቆዘም ወጥተን ነገ ላይ ከፍ የምንልበትን የብልጽግና እና የከፍታ ታሪክ ለመገንባት መንፈሳዊና ስነልቦናዊ መነቃቃት በፈጠርንበት ሰአት ትልቁ ተግዳሮት የሆነብን የሰላም ጉዳይ ስለመሆኑ ለመናገር አይከብድም።
በተለይም አሁን ላለምነው ሀገራዊ ህልም ስኬት የሰላም ጉዳይ አልፋና ኦሜጋ ስለመሆኑ በአግባቡ ተረድቶ ለመንቀሳቀስ ትክክለኛው ጊዜ አሁን ነው። ከትናንት የቁዘማ ሕይወት ወጥተን ሕልማችንን ዕውን ለማድረግ ለሰላም ያለን አስተሳሰብ እንደገና በአግባቡ ሊቃኝ ይገባል።
ሀገራዊ የሰላም ጉዳይ ለመንግስት ሆነ ለተወሰነ አካል የሚሰጥ እንዳልሆነ፤ ከእያንዳንዱ ዜጋ የሰላም አስተሳሰብ መሰረት ላይ የሚዋቀርና የእያንዳንዱን ዜጋ ጠንካራ ተሳትፎ የሚጠይቅ ትልቅ ሰብአዊ እና ሀገራዊ እሴት ስለመሆኑ እያንዳንዱ ዜጋ በአግባቡ ሊረዳና ስለ ሰላም በቁርጠኝነት ዘብ ሊቆም ይገባል።
የእያንዳንዱ ዜጋ የነገ ህልም ስኬት ከሀገራዊ ሰላም ጋር የሚኖረውን ሁለንተናዊ ቁርኝነት መገንዘብ የሚያስችል የአስተሳሰብ ዝግጁነት ወሳኝ ነው። የእያንዳንዱ ዜጋ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ የሕይወት ከፍታ ከሰላም ውጪ የሚታሰብ አይሆንም። በተለይም አሁን ባለንበት ዘመን እያንዳንዱ ዜጋ ለሀገራዊ ሰላሙ በቁርጠኝነት ዘብ መቆም ካልቻለ የሰላም እጦቱ ሊያስከትል የሚችለው አደጋ ሌላ የቁዘማ ዘመን ይዞ ሊመጣ እንደሚችል መገመት አስተዋይነት ነው ።
በተለይም ይህ ትውልድ የሰላም እጦት ምን እንደሚመስል፤ ውጤቱም የቱን ያህል አደገኛ እንደሆነ ከታሪክ ትርክት ባለፈ በሕይወት ዘመኑ ማየት የቻለ ነው። ከቀደመው ቀርቶ ከትናንቶች የሰላም እጦት ሕይወቱ የቱን ያህል እንደተናጋ ገና ያልደበዘዘ ትዝታ ባለቤት ነው። ከዚህ በመነጨም ስለሰላም ሀዋሪያ ሆኖ ሊቆም ይገባል። መጪው ትውልድ በተመሳሳይ የሰላም እጦት ሰለባ እንዳይሆን የትውልድም የሞራልም ሃላፊነት አለበት።
ዛሬ ስለ ሰላም በቁርጠኝነት የሚከፍለው ዋጋ በመጪው ትውልድም ሆነ በትውልዶች የታሪክ ምእራፍ ውስጥ የጎላ ስፍራ እንዲኖረው የሚያስችል አቅም አለው፤ ትውልዱ ከታሪክ ተወቃሽነት ይልቅ በታሪክ ተወዳሽ ለመሆን በትውልዶችም መካከል የሰላም ጀግና ሆኖ ለመታወስ ለሰላም ያለውን አስተሳሰብና የአስተሳሰብ መሰረቱን ማስተካከል አለበት።
በተለይ ለኛ ኢትዮጵያውያን አለመመደማመጥ፤ ካለመደማመጥ የሚመነጭ አለመስማማት፤ ካለመስማማት በሚፈጠሩ ግጭቶችና ጦርነቶች በዘመናት መካከል ከከፈልነው ከፍ ያለ ዋጋ አንጻር ከትናንት ታሪኮቻችን ተምረን ለተሻሉ ነገዎች ስለ ሰለማችን በቁርጠኝነት ዘብ መቆም ይጠበቅብናል። ለኛ ሰላም ማለት ሁሉም ነገር ነው። ህልማችን፣ ተስፋችን፣ ስኬታችን፤ ከዛም በላይ ሕልውናችን ሰላማችን ነው!
አዲስ ዘመን ታህሳስ 22/2013