አንተነህ ቸሬ
‹‹መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ›› የተሰኘውና የመዝገበ ቃላት ጣሪያ እየተባለ የሚታወቀው የሊቁ አለቃ ኪዳነወልድ ክፍሌ መጽሐፍ ከጥንስሱ እስከ ፍፃሜው እንዲደርስ መምህር ክፍለ ጊዮርጊስ፣ አለቃ ኪዳነወልድ ክፍሌ እና አለቃ ደስታ ተክለወልድ የተባሉ የሦስት ታላላቅ ሊቃውንት አበርክቶ አስፈላጊ ነበር።ሊቁ መምህር ክፍለ ጊዮርጊሥ የመጽሐፉን ስራ ወጥነውት ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ።
የመምህር ክፍለ ጊዮርጊሥ ደቀ መዝሙር የነበሩት አለቃ ኪዳነወልድ ክፍሌ ደግሞ ስራውን ቀጥለውበት የማጠናቀቅ አደራውን ለደቀ መዝሙራቸው ለአለቃ ደስታ አስተላለፉት። አለቃ ደስታም ከመምህራቸው በተቀበሉት አደራ መሰረት የመጽሐፉን ስራ አጠናቀው ለሕትመት እንዲበቃ አደረጉት።ስለሆነም በመምህር ክፍለጊዮርጊሥ የተወጠነው የግዙፉ መጽሐፍ ስራ ሊጠናቀቅ የቻለው የደቀ መዝሙራቸው ደቀ መዝሙር በሆኑት በአለቃ ደስታ ተክለወልድ አማካኝት ነበር ማለት ነው።
ደስታ የተወለደው ነሐሴ 19 ቀን 1893 ዓ.ም፣ በተጉለትና ቡልጋ አውራጃ ውስጥ ነው።ገና የሰባት ዓመት ልጅ ሳለ አባቱን በሞት ተነጠቀ። ከአጎቱ ጋር እየኖረ አለቃ ተክለሥላሴ ከተባሉ መምህር ዘንድ ትምህርት እንዲማር ተላከ። በትምህርት አቀባበሉ ፈጣንና ጎበዝ ነበር። በ10 ዓመቱ ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ድቁና ተቀበለ። ቀጣዮቹን 10 ዓመታት ደግሞ በደብረ ሊባኖስ ንባብ፣ የግዕዝ ሰዋስው፣ ቅኔና ሌሎች ትምህርቶችን እየተማረ ቆየ።
ከዚያም የዜማ ትምህርት ለመማር ወደ አዲስ አበባ አቀና።የደስታን የቅኔ አዘራረፍ የተመለከቱት አንጋፋው የቅኔና የስነ-ጽሑፍ ሊቅ ብላቴንጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ፤ በደስታ ቅልጥፍና ተደስተው ማተሚያ ቤት ተቀጥሮ እንዲሰራ እድል አመቻቹለት። ደስታም በተፈሪ መኮንን ማተሚያ ቤት (የአሁኑ ‹‹ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት››) ውስጥ በፊደል ለቃሚነትና በሐይማኖት መጽሐፍት አማካሪነት ተቀጥሮ መስራት ጀመረ።
በወቅቱ በማተሚያ ቤቱ ውስጥ በጅምር ላይ ያለ መጽሐፍ የነበራቸው አለቃ ኪዳነወልድ ክፍሌ መጽሐፋቸው ምን ደረጃ ላይ እንደደረሰ ወደ ማተሚያ ቤቱ በመጡበት ወቅት ከወጣቱ ፊደል ለቃሚ ደስታ ተክለወልድ ጋር ተዋወቁ። አለቃም በወጣቱ ደስታ ስራ ደስተኛ ስለሆኑና የሚተካቸውም ሰው እንዳገኙ እርግጠኛ ስለነበሩ አብሯቸው ወደ ድሬዳዋ እንዲሄድና ከእርሳቸው ጋር እንዲሰራ ጠየቁት። ደስታም የአለቃን ጥያቄ ተቀብሎ ወደ ድሬዳዋ ሄደ።
በተፈሪ መኮንን ማተሚያ ቤት የተወጠነው የአለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌና የደቀ መዝሙራቸው የአለቃ ደስታ ተክለወልድ ምሁራዊ ጓደኝነት ድሬዳዋ በሚገኘው በቅዱስ አልአዛር የላዛሪስት ማተሚያ ቤትም ቀጥሎ በእውቀት ሰንሰለት የተሳሰሩት ሁለቱ ሊቃውንት ለ16 ዓመታት ያህል አብረው ሰርተዋል።አለቃ ከመምህር ክፍለጊዮርጊሥ የተረከቡትን የመዝገበ ቃላት ስራ በእርጅናና በሕመም ምክንያት ማጠናቀቅ እንደማይችሉ ሲገነዘቡ ስራውን ለደቀ መዝሙራቸው ለደስታ ተክለወልድ በአደራ ሰጧቸው።
‹‹ነገርን ከስሩ፤ ውሃን ከጥሩ›› እንዲሉ ‹‹መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ›› የተሰኘው የመዝገበ ቃላት መጽሐፉ በቅብብሎሽ እንደተዘጋጀ በሚገባ ለመረዳት መምህር ክፍለጊዮርጊሥ ከጀመሩት መጽሐፉን የማዘጋጀት ውጥን ጀምሮ መመልከቱ ጠቃሚ ነው።
በቀለም አቀባበል እንዲሁም፣ በመራቀቅና ምስጢር በመመራመርና ችሎታቸው ምክንያት «የቀለም ቀንድ»፣ ‹‹የቃላት ጉልላት›› እንዲሁም ‹‹አበ መዝገበ ቃላት›› ተብለው የሚታወቁት፤ አቻ የሌላቸውና አምሳያ ያልነበራቸው የአንድምታ ትርጓሜ ሊቅ እንደነበሩ የሚነገርላቸው እንዲሁም የፋሺስት ኢጣሊያ አስተዳደርን በብርቱ የተቃወሙት የነፃነት ታጋይና አርበኛው፤ እውቁ የቋንቋ፣ የሰዋስውና የመዝገበ ቃላት ሊቅ አለቃ ኪዳነወልድ ክፍሌ፤ በኢትዮጵያ በተለያዩ ቦታዎች ተዘዋውረው የመጻሕፍትን ትርጓሜ ካጠኑና ካስተማሩ በኋላ ወደ ኢየሩሳሌም ሄደው ለመኖር ወሰኑ።
በግብጽ ለአንድ ዓመት ያህል ቆይተው ኢየሩሳሌም ወደሚገኘው የኢትዮጵያውያን ገዳም ገቡ። አለቃ ኪዳነ ወልድ አስኬማ (የመነኩሴ ልብስ) የሚለብሱበትን ቀን በጉጉት እየጠበቁ ሳለ የሕይወታቸውን ጉዞ ሙሉ በሙሉ የሚቀይር አንድ አጋጣሚ ተፈጠረ። ይህም በ1897 ዓ.ም መምህር ክፍለ ጊዮርጊስ የተባሉ የኢትዮጵያ ሊቅ ወደ ኢየሩሳሌም መምጣት ነበር። ሁለቱ ሊቃውንት በፍጥነት ተግባቡ።
ሊቁ ክፍለ ጊዮርጊስ የኪዳነ ወልድ ክፍሌን ልዩ ተሰጥኦ ለመረዳት ብዙ ጊዜ አልወሰደባቸውም። መምህር ክፍለ ጊዮርጊስ ሮም ቆይተው ወደ ኢየሩሳሌም ሲመጡ ጅምር ሥራቸውን ከፍጻሜ የሚያደርስላቸው ሰው በብርቱ ይፈልጉ ስለነበር አጋጣሚውን በመጠቀም በዘመናቸው ሙሉ ያካበቱትን እውቀትና ተሞክሮ ለትጉሁ ኪዳነ ወልድ ለማውረስ ቆርጠው ተነሱ።
መምህር ክፍለ ጊዮርጊስና ኪዳነ ወልድ ለ11 ዓመታት ያህል በኢየሩሳሌም አብረው ከኖሩ በኋላ ሊቁ ክፍለ ጊዮርጊስ በ1908 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ሲለዩ ሥራቸውን ሁሉ በአደራ ያስረከቡት ለኪዳነ ወልድ ክፍሌ ነበር። መምህር ክፍለጊዮርጊስ ለደቀ መዝሙራቸው ‹‹ልጄ ሆይ! ይህንን ግሥ ለማሳተም ብትፈልግ እንደገና ጥቂት ዕብራይስጥ ተምረህ ማፍረስና ማደስ አለብህ።
መጀመሪያ አበገደን ጥፈህ የፊደሉን ተራ በዚያው አስኪደው። አንባቢዎችም እንዳይቸገሩ ከፊደል ቀጥለህ አጭር ሰዋስው አግባበት። የጐደለውና የጠበበው ሞልቶ ሊጣፍ ፈቃዴ ነው። ከሌላው ንግድ ይልቅ ይህን አንድ መክሊት ለማብዛትና ለማበርከት ትጋ።ዘር ሁን፤ ዘር ያድርግህ›› ከሚል ኑዛዜ ጋር ስራውን ከፍፃሜ እንዲያደርሱት አደራ ሰጧቸው።
አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌም ከአስተማሪያቸው የተቀበሉትን አደራ ለመፈፀም መትጋት ጀመሩ። የዕብራይሥጥ፣ የጽርእ (ግሪክ)ና ሌሎች ቋንቋዎችን በማጥናት የመምህራቸውን ህልም እውን ለማድረግ ይጥሩ ጀመር። አለቃ ኪዳነወልድ የመምህራቸውን አደራ ለመፈፀም እየተጉ ሳለ ከአልጋወራሽ ተፈሪ መኮንን «ትችል እንደሆነ መጥተህ ሕዝቅኤልን ተርጉምልኝ» የሚል ደብዳቤ ስለደረሳቸው ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰው ሕዝቅኤልን ንባቡን ከነሙሉ ትርጓሜው ጋር አሳትመው ካስረከቡ በኋላ በኢየሩሳሌም የወጠኑትን ‹‹መፅሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ›› የተባለውን የግዕዝና የአማርኛ መዝገበ ቃላት ድሬደዋ ላይ ተቀምጠው ማዘጋጀት ጀመሩ።
አለቃ ኪዳነ ወልድ የተጣለባቸውን አደራ ለመወጣት በመምህር ክፍለ ጊዮርጊስ የተፃፈውን ጅምር መዝገበ ቃላት ቀን ከሌት ሳይሉ ይሰሩ ጀመር። ይህንን ትጋታቸውን አለቃ ደስታ ተክለወልድ ሲያስታውሱ፤ ‹‹ … በሥራ ውለው ማታ ንፋስ በመቀበል ጊዜ አንድ ሃሳብ ቢያገኙ በማስታወሻ ለመፃፍ ከውጭ ወደ ቤት ይመለሳሉ።በምሳ ወይም በእራት ጊዜ አንድ ትርጓሜ ቢታሰባቸው ምግቡን ትተው ብድግ ይላሉ።ሌሊትም ተኝተው ሳሉ አንድ ምስጢር ቢገጥማቸው ከመኝታቸው ተነስተው መብራት አብርተው ይፅፋሉ …›› በማለት ተናግረዋል።
የእድሜ መግፋትና የፋሺስት ኢጣሊያ እስራት ያደረሰባቸው ስቃይ ተደማምረው ለጤና እክል ዳረጓቸው። እርሳቸውም የአለቃ ደስታ ተክለ ወልድን የግእዝ ችሎታ ተረድተው ስለነበር መጽሐፉን የማጠናቀቅ አደራውን ከአለቃ ደስታ ሌላ የሚረከብ ሰው እንደሌለ ተገነዘቡ። አለቃ ደስታንም ጠርተው «አደራውን ተቀበል ሥራውንም ከዳር አድርሰህ ለህትመት አብቃው» ብለው ሰጧቸው። አለቃ ኪዳነወልድ የመጽሐፉን አደራ ለደቀ መዝሙራቸው ለአለቃ ደስታ ሰጥተው ሰኔ 24 ቀን 1936 ዓ.ም አረፉ።
አለቃ ደስታ ተክለወልድ ጅምሩን ከፍፃሜ በማድረስ መፅሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ የተባለውን በግዕዝና በአማርኛ ተፅፎ በ866 ገፅ የተዘጋጀውን መዝገበ ቃላት፤ መዝገበ ቃላቱን አድሰውና አርመው በ1948 ዓ.ም. (አለቃ ኪዳነወልድ ካረፉ 12 ዓመታት በኋላ) በአርቲስቲክ ማተሚያ ቤት አሳትመው አወጡት። በዚህ መዝገበ ቃላት መግቢያ ላይ የሶስቱን ምሁራን ተሳትፎ በተመለከተ ‹‹መፅሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ፣ በክፍለጊዮርጊስ ተጀምሮ በኪዳነ ወልድ ክፍሌ የዳበረውን ደስታ ተክለወልድ አሳተመው›› ተብሎ ተፅፎበት ይገኛል።
ኪዳነ ወልድ የሞቱበትን (1934 ዓ.ም) እና አለቃ ደስታ መዝገበ ቃላቱን ያሳተሙበትን (1948 ዓ.ም) ጊዜ ስናነጻጽር አለቃ ደስታ የሊቁ ክፍለ ጊዮርጊስንና የአለቃ ኪዳነ ወልድን ህልም እውን ለማድረግ 14 ዓመታት መድከማቸውን እንረዳለን። እንግዲህ በግዙፉ መዝገበ ቃላት ሥራው ላይ ሦስት ታላላቅ ሊቃውንት ተሳትፈዋል ማለት ነው።
ይህ መዝገበ ቃላት በኢትዮጵያ ውስጥ የታተመ የመጀመሪያው ትልቁ የግእዝ-አማርኛ መዝገበ ቃላት ነው። መዝገበ ቃላቱ ሁለት ዐበይት ክፍሎች አሉት። የመጀመሪያው ክፍል (ከገጽ አንድ እስከ 191) ስለ ክፍለ ጊዮርጊስና አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ሕይወት ይተርካል። ሁለተኛው ክፍል (ከገጽ 193 እስከ 908) ደግሞ በአበገደ የፊደል ቅደም ተከተል መሠረት የመዝገበ ቃላቱን ትንተና የያዘ ነው።
ይህ ‹‹መፅሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ›› የተሰኘው መጽሐፍ/መዝገበ ቃላት አንድ ለትውልድ የሚያስቡ ትጉህና ቅን ሰዎች ከዕድሜያቸው ከፍለውና ያበረከቱት ውድ ስጦታ እንደሆነ በርካቶች ይስማማሉ። ይህ እጅግ ጠቃሚ የሆነ መጽሐፉ ለሕትመት በቅቶ ትውልድ እንዲጠቀምበት የአለቃ ደስታ አበርክቶ ተጠቃሽ ነው።
አለቃ ደስታ ስለ አለቃ ኪዳነ ወልድ ታላቅነት ሲመሰክሩ፤ ‹‹ … የግዕዝን መሰረት ያወቅሁት ከአለቃ ኪዳነ ወልድ ነው፤ አሁን ያዘጋጀሁትን ሰፊ የአማርኛ መዝገበ ቃላት ለመፃፍ የበቃሁት ከእርሳቸው ባገኘሁት ትምህርትና እውቀት ነው …›› ብለው ነበር።
‹‹ዐዲስ የአማርኛ መዝገበ ቃላት›› የተሰኘው ግዙፍ መዝገበ ቃላት ሌላኛው የአለቃ ደስታ ስራ ነው። የአማርኛ መዝገበ ቃላት እንዲዘጋጅ ምክንያት የሆነው የኢትዮጵያ ንጉሰ ነገሥት መንግሥት አልጋ ወራሽና ባለሙሉ ሥልጣን እንደራሴ የነበሩት ንጉሥ ተፈሪ መኮንን የካቲት 27 ቀን 1921 ዓ.ም ለአለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ የፃፉት ንጉሳዊ ማዘዣ ነበር። ማዘዣውም እንዲህ የሚል ነበር …
‹‹ይድረስ ከአለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ
እንደምን ሰንብተሃል።እኔ እግዚአብሔር ይመስገን ደህና ነኝ። ያገራችንን የቋንቋ ድህነት የምታውቀው ነው። ስለዚህ ዲክሲዎኔር እንዲገለበጥ አዝዣለሁና፤ ለዚሁ ሥራ ላቶ ብሩ ረዳት ኾነህ የተቻለህን ያህል አብራችሁ እንድትሰሩ ይሁን፡፡››
ንጉሡ ያዘዙት ላሩስ የተባለውን ትልቁን የፈረንሳይኛ መዝገበ ቃላት ወደ አማርኛ ተርጉሞ አማርኛን ከዚያ ለመልቀምና ለመሰብሰብ ነበር፤ ነገር ግን ይህ አሰራር አስቸጋሪ ስለነበር በውጥን ቀርቷል።
ትዕዛዙ የተፃፈላቸው አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ በበኩላቸው ‹‹ግዕዝን ትቼ አማርኛን ልፅፍ አይገባኝም፤ አማርኛውን በአበገደ ተራ አንተ ሰብሥብ›› ብለው ለአለቃ ደስታ ነገሯቸው። በዚህም መሰረት አለቃ ደስታ የአማርኛ ቃላት የመሰብሰብ፣ የመፍታትና መዝገበ ቃላት የማደራጀቱን ግዙፍ ተግባርን በታላቅ አደራ ተረከቡ።
አለቃ ደስታ ተክለ ወልድ ከ1921 ዓ.ም ጀምሮ ከሥራ መልስ በነበራቸው የእረፍት ጊዜ የአማርኛ ቃላትን የመሰብሰብ፤ የመመርመር፤ የማጥናትና የመተርጐምን ሥራ ጀመሩ። ያለረዳትና ያለመተየቢያ መሳሪያ የተጀመረው ይኸው ግዙፍ ሥራ ለመጠናቀቅ ሰላሳ ዓመታት ያህል አስፈልጐታል።
ስራው በተለያዩ ምክንያች ለተጨማሪ 10 ዓመታት ያህል ሳይታተም ቆይቶ በ1962 ዓ.ም ‹‹ዐዲስ የአማርኛ መዝገበ ቃላት›› የሚል ስያሜ ይዞ በአርቲስቲክ ማተሚያ ቤት ታተመ።
አለቃ ደስታ ያዘጋጁት መዝገበ ቃላት የተደራጀው እንደ አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ሁሉ በአበገደ ፊደል ተራ መሰረት ነው። ይህም ማለት መዝገበ ቃላቱ የሚጀምረው በ‹‹ሀ›› ፊደል ሳይሆን በ‹‹አ›› ፊደል ነው ማለት ነው። የተለመደውን የፊደል ተራ ትተው በ‹‹አ›› የጀመሩበትን ምክንያት አለቃ ደስታ ተክለ ወልድ ሲያስረዱ፤ ‹‹ … በኢትዮጵያችን የፊደል መጀመሪያ ‹አ› መሆኑ ቀርቶ ‹ሀ› የሆነው በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ነው፤ ይህ ፈፅሞ ስህተት ነው።
የጥንቱ ፊደል ተራ አበገደ ነበር።የዓለም ፊደል ሁሉ የሚጀምረው በ‹አ› ነው። እኔ በአበገደ ፅፌዋለሁ፤ አለቃ ኪዳነ ወልድን ተከትዬ … ›› ብለዋል። በዚህ አካሄድ ‹‹ሀ›› አምስተኛ ፊደል እንዲሁም ‹‹ለ›› ሠላሳኛ ፊደል ሲሆን የመጨረሻው ፊደል ደግሞ ‹‹ተ›› ይሆናል ማለት ነው።
ከዚህ በተጨማሪም ‹‹ … ማንም ሰው ግዕዝን ጠንቅቆ ካላወቀ አማርኛን ሊያውቅ አይችልም፤ ፊደሉንም አነጋገሩንም ስህተት ያደርጋል።የኔ አረም ለዘመኑ ሰው ሁሉ አይስማማም። ከግዕዝና ካማርኛ ህግ ውጪ ተፅፎ የመጣውን ሁሉ አልቀበልም።ቋንቋዬን ስለማውቀው ማክበር አለብኝ። እንደኔ ከሆነ ‹ዦሮ› ነው እንጂ ‹ጆሮ› አይባልም። እንዲሁም ባንድ ‹ሀ› ‹ዐ› ‹አ› እንጠቀም ከሚሉ ሰዎች ጋር አልስማማም። ያማርኛ አባት ማን ሆነና! ይህ ሁሉ ስህተት የሚመጣው ግዕዝን ጠንቅቆ ካለማወቅ ነው …›› በማለት ተናግረው ነበር።
ባየህ ኃይሉ ተሰማ ‹‹ዐዲስ የአማርኛ መዝገበ ቃላት›› በሚል ርዕስ ባሰፈሩት ጽሑፍ፤ ‹‹ … ‹ዐዲስ የአማርኛ መዝገበ ቃላት› የመጀመሪያ ገፁ ያደረገው የአማርኛ መዝገበ ቃላት እንዲዘጋጅ የታዘዘበትን ንጉሳዊ ማዘዣ ትክክለኛ ግልባጭ ሲሆን በመቀጠል የንጉሠ ነገሥቱ፣ የአልጋ ወራሹ፣ የአለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌንና የደራሲውን ምስሎች በተከታታይ ገፆቹ አስፍሯል። ከገፅ ሁለት እስከ ገፅ 66 ያለው የመዝገበ ቃላቱ ክፍል መነቃቂያ፣ ማውጫ፣ መግለጫ፣ መቅድምና ግጥም፣ አገባብ፣ ነጥቦች፣ ቅፅል፣ ምዕላድና ሰዋስው እና የመሳሰሉትን ርእሶች በዝርዝር የያዙ ምዕራፎችን አዝሏል።
‹ዐዲስ የአማርኛ መዝገበ ቃላት› ‹‹አ››ን አጋፋሪ አድርጐ ገፅ 69 ላይ ይጀምርና በ‹‹ተ›› ፊደል በገፅ 1284 ላይ ይፈፀማል።መዝገበ ቃላቱ በውስጡ 523 አስረጂ ሥዕሎች (Illustrations) ይዟል …
… መዝገበ ቃላት ማደራጀትን የመሰለ ግዙፍ ተግባር ያለረዳት ለብቻ ያውም በእጅ እየፃፉ ማዘጋጀትን እንደ አለቃ ደስታ ተክለወልድ ያለ መንፈሰ ጠንካራ ሰው ካልሆነ በስተቀር ተራ ተርታው ሰው የሚደፍረው ተግባር አይሆንም ነበር።
ይሄው መዝገበ ቃላት በታተመበት ተመሳሳይ ጊዜ የታተመውና 1390 ገፆች ያሉትን ‹‹The Collins Dictionary of the English Language›› ለማዘጋጀት 13 የእንግሊዝኛ ምሁራን የተሳተፉበት ሲሆን ቃላት ለመሰብሰብና ለመተየብ ዘመናዊ መሳሪያዎችን እንደተጠቀሙ ሲታወስ የአለቃ ደስታን ድካም አጉልቶ ለማሳየት ይረዳል …›› በማለት አብራርተዋል።
አለቃ ደስታ እጅግ በርካታ መጽሐፍት እርማትን በመስራት መጽሐፍቱ በተስተካከለ ቋንቋ ለአንባቢ እንዲቀርቡና ለቋንቋው እድገት ከፍተኛ አስተዋፅዖ አድርገዋል። ከሚታወቁበትና ሙሉ ጊዜያቸውን ሰጥተው ከሰሩት የእርማት ስራቸው ባሻገር ‹‹ርባሐ ስም ወአንቀጽ›› (1946 ዓ.ም.) እና ‹‹ገበታ ሐዋርያት›› (1928 ዓ.ም.) የተሰኙትን ጨምሮ ከአስር በላይ የግዕዝ መማሪያና ሃይማኖታዊ መጻሕፍትን አዘጋጅተው አሳትመዋል።
አለቃ ደስታ ተክለ ወልድ ይህ ድካማቸው በዘመኑ እውቅና አግኝቶ በኢትዮጵያ ጥናት ዘርፍ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሽልማት ድርጅት ተሸላሚ በመሆን የብር 15 ሺህ ሽልማት አሸናፊ አድርጓቸዋል። እርጅና መጥቶ አዳከማቸው እንጂ ‹‹ዐዲስ የአማርኛ መዝገበ ቃላት››ን እንደገና አርሞ፣ አስፋፍቶና አሻሽሎ የማሳተም እቅድም ነበራቸው።
አንጋፋው የአማርኛ ሊቅ አለቃ ደስታ፣ ጳጉሜ አንድ ቀን 1977 ዓ.ም አርፈው ስርዓተ ቀብራቸው በአዲስ አበባ መንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተፈፅሟል።
አዲስ ዘመን ታኅሳስ 21/2013