ወራትን የዘለቀው የመተከል ዞን የንጹሃን ዜጎች ጭፍጨፋ መቋጫ ሳያገኝ ቆይቷል። ለችግሩ እልባት ለመስጠትም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጭምር በስፍራው በመገኘት ህዝቡንና አመራሩን አወያይተው አቅጣጫ አስቀምጠው በተመለሱ ምሽት የደም ቀበኞች በንጹሃን ላይ አሰቃቂ ጭፍጨፋ ፈጽመው አድረዋል። በዚህም ከ200 በላይ ንጹሃን በግፍ ተገድለዋል፤ ከ50ሺ በላይ ከቀዬአቸው ተፈናቅለዋል። ሀብትና ንብረታቸውም ተዘርፏል፤ ወድሟል።
በዚህ ዙሪያ ታህሳስ 14 የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ባወጣው መረጃ መንግስት የዜጎችን ደህንነት መጠበቅ የመጀመሪያ ስራው ሊሆን እንደሚገባ ማሳሰቡ ይታወሳል። የኢትዮጵያ የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም በቤንሻንጉል ጉሙዝ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት በመተከል ዞን በተከሰተው ማንነትን መሰረት ያደረገ ጭፍጨፋን አስመልክቶ መግለጫ አውጥቷል።
ተቋሙ በመግለጫው እንዳመለከተውም በቤንሻንጉል ጉሙዝ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት በመተክል ዞን እየደረሰ ባለው የዜጎች ጭፍጨፋ፣ የንብረት ውድመት እና ከቤት ንብረት መፈናቀልን አስመልክቶ ባደረገው ማጣራት፤ በመተከል ዞን በማንዱራ፣ በዳንጉር፣ በጉባ፣ በደባጤ፣ በቡለን እና በወንበራ ወረዳዎች ማንነትን መሰረት ያደረገ የጅምላ ጭፍጨፋ የተካሄደ መሆኑን ለማረጋገጥ ተችሏል።
በወንጀል ድርጊቱም የክልሉ የመንግስት የአስተዳደር አካላት፣ የፓርቲ አመራሮች እና የጸጥታ መዋቅር አካላት የተሳተፉ ስለመሆናቸው፤ እንዲሁም ጉዳዩ የሚመለከታቸው የፌዴራል መንግስት አካላት የነበራቸው ድጋፍና ክትትል በጣም ዝቅተኛ መሆኑን፤ እና ጉዳዩን በቅርበት ሲከታተል የነበረው የኮማንድ ፖስት ከችግሩ ክብደትና ስፋት አንጻር የሰራው የጸጥታ ማስከበር ስራና በአጥፊዎች ላይ የወሰደው እርምጃ ደካማ እንደነበር ለይቷል።
ይሄን መነሻ በማድረግም ተቋሙ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመተከል ውይይታቸው ያስቀመጧቸው አቅጣቻዎች እንዲተገበሩ፤ በወንጀል ድርጊቱ ተሳታፊ የነበሩ አካላት በሕግ እንዲጠየቁ፣ ፖለቲካዊ እና አስተዳደራዊ እርምጃ ተወስዶባቸው ለሕዝብ ይፋ እንዲደረግ፤ እንዲሁም የፌዴራል የፀጥታ አካላት ህገ መንግስቱና ህጉ በሚፈቅደው መንገድ ከሁሉም ክልሎች የተቀናጀ የጸጥታ ሃይል በማዋቀር በክልሉ ተሰማርቶ የዜጎችን ህይወትና ንብረት እንዲታደግ ሊደረግ እንደሚገባ ምክረ ሃሳብ አቅርቧል።
ይሄን መሰል ከተቋማት የሚሰነዘር ሃሳብና መግለጫ ደግሞ መንግስት የንጹሃንን ሰላምና ደህንነት ከማረጋገጥ፤ የዜጎችን ህይወት ከአጥፊዎች እንዲታደግ ማስቻል ነው። በመንግስት በኩልም ቢሆን ችግሮችን ላለማባባስ ይልቁንም ህዝቦች ከፖለቲከኞች ጣልቃ ገብነት በነጻ መልኩ ዘመናትን አብሯቸው በቆየ የሰላም ግንባታ እሴት ተጠቅመው ችግሮችን እንዲፈቱ እድል በመስጠት ጭምር ትዕግስት በተሞላበት አካሄድ ይህን ኃላፊነት ለመወጣት ሲሰራ ቆይቷል።
በዚህ ረገድ ለውጡን ተከትሎ አንድ ብሎ በሶማሌ ክልል ከጀመረው የጥፋት ተግባር በቅርቡ በትግራይ ክልል በህወሓት ጁንታ በመከላከያ ላይ ጥቃት እስከመፈጸም የደረሰውን ወንጀል ፈር ለማስያዝ ያስቻለ የህግ ማስከበር እርምጃ ወስዷል። ይህ ይበል የሚያሰኝ፤ የአጥፊዎችን ጉዞ ገትቶም የንጹሃንን እንባ ያበሰ፤ አገርና ህዝብንም ከአገዳ የታደገ ተግባር ነው።
ይሁን እንጂ ዛሬም ድረስ በተለያዩ አካባቢዎች የንጹሃንን ደም በከንቱ እያፈሰሱ፤ በአሰቃቂ ሁኔታ የሰው ልጆችን ነፍስ እየነጠቁ ያሉ ልጓም ያጡ የጥፋት ተግባራት በተለይ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በደቡብ ክልሎች እየተስተዋሉ ይገኛሉ። እነዚህን አደብ ለማስያዝም እንደ ቀደሙት ሁሉ በመንግስት በኩል እየተወሰዱ ያሉ ዘርፈ ብዙ ተግባራት አሉ።
በዚህ ረገድ ከሰሞኑ በመተከል ተከስቶ ከነበረው ጭፍጨፋ ጋር በተያያዘ በጸጥታ ኃይሉ እየተወሰደ ካለው የህግ ማስከበር እርምጃ በተጓዳኝ፤ ፖለቲካዊ መፍትሄዎችም እየተወሰዱ ይገኛል። በዚህም በተለያዩ ደረጃ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ እጃቸው አለበት ተብሎ የተጠረጠሩ አካላት በቁጥጥር ስር እየዋሉ ነው።
የክልሉ ምክር ቤትም ትናንት ባካሄደው 6ኛ የሥራ ዘመን 6ኛ አስቸኳይ ጉባኤው ከመተከል ዞን የፀጥታ ችግር ጋር በተያያዘ የተጠረጠሩ የአራት የምክር ቤት አባላትን ያለመከሰስ መብት አንስቷል።
ይህ ደግሞ በክልሉ የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ ያለውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ትልቅ እርምጃ ነው። እንደ አገር ሲታይም ቀደም ሲል የተወሰዱ ርምጃዎች ተገቢና የህዝብንም ሆነ የአገርን ህልውና ያስጠበቁ ሲሆኑ፤ በቅርቡ የተወሰደውም ሆነ አሁን እየተወሰደ ያለው እርምጃ ተገቢ እና የመጪውን ጊዜ ብሩንነት አመላካች እንደመሆኑ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 21/2013