‹‹በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ›› በርካታ የመናውያን በጦርነት ከደረሰባቸው መከራና ሰቆቃ በተጨማሪ በኤች አይ ቪ እየተጠቁ እንደሆኑ የተለያዩ አካላትን ጠቅሶ አልጀዚራ ዘግቧል፡፡
የስምንት ዓመቱ ታዳጊ አህመድ ዛካሪያ በየመን ዋና ከተማ አገልግሎት ከሚሰጡት ጥቂት የህክምና ማዕከሎች አንዱ በሆነው ሰንዓ ጁሙሁሪያ ሆስፒታል ወረፋ ይዞ ተቀምጧል፡፡ አባቱ ለአልጀዚራ እንዳስረዳው አህመድ ከሶስት ዓመታት ቀደም ብሎ ባደረገው የጤና ምርመራ ከኤች አይ ቪ ነጻ አንደተባለና ደስተኛና ተጫዋች ልጅ እንደነበርም አስረድቷል፡፡ ‹‹ልጄ ከቅርብ ግዜ ወዲህ የህመም ስሜት ሲሰማውና ባህሪውም ሲቀየርብኝ በመጠራጠር ወደ ሀኪም ቤት አመጣሁት፤ እናም ዶክተሩ የምርመራውን ውጤት ሲነግረኝ ኤች አይ ቪ በደሙ እንዳለበት አሳወቀኝ፡፡ እኔና ባለቤቴም እንዲሁ ከቫይረሱ ጋር ነው የምንኖረው›› ይላል ዛካሪያ፡፡
ዛካሪያ በ2016 እ.አ.አ ከደቡብ ምዕራብ ታይዝ ከተማ ወደ ሰንኣ ያቀናው በአካባቢው የሚንቀሳቀሱት የሁቲ ታጣቂዎች ከተማዋን በመቆጣጠራቸው በሥፍራው የነበሩት ከሰላሳ እስከ አርባ የሚደርሱ ሆስፒታሎች በመዘጋታቸውና የህክምና እርዳታ ማግኘት ባለመቻሉ ነበር፡፡
በየመን ያለው የጦርነት ሁኔታ የኤች ኤይ ቪ/ ኤድስ ህሙማን ህክምናቸውን እንዳይከታታሉ ያደረገ መጥፎ ክስተት ሆኗል፡፡ ያም ሆኖ ዛካሪያና ቤተሰቦቹ እንደ እድል ሆኖ መድሀኒቱን አግኝተው ከሚጠቀሙት ሰዎች መሀከል ናቸው፡፡ እርሱ እንደሚለው ሀኪሙ አንድ ስሙን የማያውቀው ቀይ እንክብል እንደሰጠውና በቀን አንድ ግዜ ይህንን እንክብል እንደሚውጥ ያስረዳል፡፡
ዛካሪያ አያይዞም ‹‹ስለራሴ ሳይሆን ስለልጄ የወደፊት እጣፈንታ ሳስብ በጨለማ ውስጥ እንዳለሁ ይሰማኛል፡፡ በተለያዩ ጉዳዮች የሚረዱኝ አካላት ቢኖሩ፣ እንክብካቤና ድጋፍ ቢደረግልኝ የእኔንም ሆነ የቤተሰቤን የመኖር ተስፋ እያለመለምኩ ህይወታችንን በጥሩ ሁኔታ እመራለሁ ብዬ እገምታለሁ፡፡ ልጄ በጣም ተጎድቶ ለመሞት ተቃርቦ ነበር፤ አሁን ግን በጥሩ ሁኔታ ላይ ይገኛል፡፡ በፈጣሪ አምናለሁ ሁሉም ነገር ያለው በእርሱ እጅ ነውና ታሪኬን ሊቀይረው ይችላል›› ብሏል፡፡
በሰንዓ ለኤች አይ ቪ / ኤድስ ህሙማን ድጋፍ ከሚያደርጉት የህክምና ተቋማት መካካል ድንበር የለሽ የሀኪሞች ቡድን አንዱ ሲሆን በከተማዋ ብቻ ቁጥራቸው ስድስት መቶ ለሚደርስ የኤች አይ ቪ/ ኤድስ ህሙማን እርዳታ ያደርጋል፡፡ በአል ጁሙሁሪያ ሆስፒታል ከኤች አይ ቪ / ኤድስ ጋር በተያያዘ ህክምና የሚሰጡት ኢብራሂም አል ባበሊ እንዳስረዱት ‹‹የአንዳንድ ታማሚዎችን መከራና ስቃይ ስንመለከት በዚህ ጦርነት ውስጥ እያለን እንኳን ችላ እንዳንላቸው የሚያደርጉ ሁኔታዎች እንዳሉ እንገነዘባለን›› ይላሉ፡፡ ሁቲዎች በተቆጣጠሩት የሀገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ አንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን የሚሆኑት የመንግሥት ሰራተኞች ከ2017 ወዲህ በመንግሥት ይከፈላቸው የነበረው የወር ደመወዛቸው ተቋርጧል፡፡ በዚህም ሰዎች ለጤና፣ ለትምህርት፣ ለህክምና ለንጽህናና ለሌሎች ዋናዋና ጉዳዮች የሚሰጡትን ትኩረት እንዲቀንሱ አድርጓቸዋል፡፡
የተባበሩት መንግሥታት በየመን የሰብዓዊ መብት እርዳታ ለማድረግ ቢፈልግም አስቸጋሪ ሁኔታዎች እንዳሉ በተደጋጋሚ ማሳወቁ አይዘነጋም፡፡ በተባባሩት መንግስታት በሰብዓዊ እርዳታ ጀነራል ዳይሬክተር ዘርፍ ክፍል የሚሰሩት ማርክ ሎው ኮክ በቅርብ ግዜ እንዳሳወቁት በተለይም ባለፉት ዓመታት በየመን የሰብዓዊ እርዳታ ለማድረግ አስቸጋሪ ሁኔታዎች እንዳሉ በመጥቀስ በአሁኑ ወቅትም ሃያ አራት ሚሊዮን የሚደርሱ ሰዎች እርዳታ እናደሚያስፈልጋቸው ገልጸዋል፡፡
በሁቲዎች በሚመራው አስተዳደር የጤና ሚኒስትር የሆኑት ጣሀ አል ሙታዋክለ ለአልጀዚራ እንዳስረዱት አስከ አሁን ድረስ ጦርነቱ የሀገሪቱን የጤና ሥርዓት እንደጎዳውና በተለይም ለኤች አይ ቪ ኤድስ የሚደረገው ፈንድ ጥቅም ላይ እንዳይውል ማድረጉን ገልጸዋል፡፡ በቅርቡም ኤች አይ ቪ/ ኤድስን የሳንባ ነቀርሳንና ወባን ለመከላከል በተገኘው ዓለም አቀፍ እርዳታ ስምንት መቶ ሺህ ዶላር ለሀገሪቱ መመደቡን አስታውቀዋል፡፡ አስፈላጊ መድሀኒቶችን ለየአስተዳደሮቹ ለማከፋፈልም ዝግጅት እንደተደረገ በመግለጽ ለህመምተኞቹ ተደራሽ ለማድረግ ግን አሁንም ችግር እንዳለ ተናግረዋል፡፡
ሳዑዲ ዓረብያ እ.አ.አ ከ2015 ጀምሮ በየመን ሁቲ ላይ በከፈተችው የአውሮፕላን ድብደባ በሀገሪቱ ሸቀጣ ሸቀጥና ሰብዓዊ እርዳታ እንዳይደርስ አባባሽ ምክንያት ሆኗል፡፡ በሀገሪቱ ያለው ሁኔታም የኤች ኤይ ቪ ህሙማን የህክምና እርዳታና ሌሎች አገልግሎቶችን እንዳያገኙ መስተጓጎል ፈጥሯል፡፡ የጦርነቱ ተጽዕኖ በጤና መሰረተ ልማቶች ላይ ከፍ ያለ አደጋ በመፍጠሩም ኤች አይ ቪን ለመቆጣጠር በሚደረገው የምርመራና የማማከር አገልግሎት ላይ መጥፎ ጥላውን አጥልቷል፡፡ በዚህም በሽታው ከሚገመተው በላይ በሀገሪቱ እየተሰራጨ እንደሚገኝ አመላካች ነገሮች ተስተውለዋል፡፡
በየመን የዩኒሴፍ ተወካይ ሜሪክሴል ሪላኖ እንደሚሉት ‹‹የየመን እርስ በእርስ ጦርነት የመቆም ምልክት አይታይበትም፡፡ ደርጅታችን እንደ አህመድ ያሉ ታዳጊዎችን ለማዳን እየሮጠ ነው፡፡ ጦርነቱ አሁኑኑ አብቅቶ በመላው ሀገሪቱ በህጻናት ላይ የሚደርሰው እንግልት፣ ሰቆቃና ሞት ማብቃት ይኖርበታል፡፡ ይህ ጦርነት መቋጫ የለውም ማለት የህጻናትን ሞት እያበዛን ሄድን ማለት ነው፡፡ ተቀናቃኞቹ አንድ ፖለቲካዊ ስምምነት ላይ በመድረስና ለችግሩ እልባት በመስጠት ለህጻናት መብት መከበር ቅድሚያ መስጠት ይኖርባቸዋል›› ብለዋል፡፡
እንደ ዓለም ጤና ድርጅት መረጃ መሰረት በየመን የኤች አይ ቪ ስርጭት እንዳለ የታወቀው እ.አ.አ በ1987 ነው፡፡ በዚያን ወቅት በቫይረሱ ተይዘዋል የሚባሉት የሀገሪቱ ዜጎች ቁጥር ወደ ዘጠኝ ሺ ዘጠኝ መቶ እንደሚደርስ ተገምቶ ነበር፡፡ ይህም አጠቃላይ የህዝቡን ዜሮ ነጥብ ሁለት በመቶ እንደነበርና አብዛኛዎቹም በቤተሰቦቻቸውም ጭምር ተገለው ይኖሩ እንደነበር መረጃው ያመላክታል፡፡ አሁን ባለው መረጃ መሰረትም የኤች አይቪ ኤድስ ታማሚ የሆኑ አብዛኛዎቹ የመናዊያን ቤተሰቦቻቸው በሚያደርጉባቸው ማግለል ከመኖሪያ ቤታቸው ወጥተው እንደሚኖሩ ዓለማቀፉ የማህበረሰብ ጥናት ፕሮጀክት አሳውቋል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 21/2011
ኢያሱ መሰለ