ጋዜጠኛ ኢያሱ መሰለ የጋዜጠኝነቱን ዓለም ከመቀላቀሉ በፊት ከ20 ዓመት በላይ በመምህርነት ሙያ አገልግሏል። ወደ መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች መስሪያ ቤት ተቀላቅሎ እየሰራ ባለበት ወቅት መስሪያ ቤቱ መፍረሱን ተከትሎ ወደ ኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅ መቀላቀል ችሏል። በጋዜጠኝነቱም ለሶስት ዓመት ያህል የሰራ ሲሆን፣ በቅርቡም ወደ ራያ ግንባር በማምራት ድርጅቱና አገር የጣለበትን ኃላፊት ተወጥቶ በሰላም ተመልሷል።
ጋዜጠኝነትን ከድሮም ጀምሮ ሊሰራው የሚመኘው ሙያ እንደነበር ይናገራል። በተለይም የህትመት ሚዲያውን እጅግ ይወደው ስለነበር በአገሪቱ አንጋፋ በሆነው የህትመት ድርጅት መቀላቀሉ እንደሚያስደስተውም ይገልጻል። በራያ ግንባር ቆይታ አድርጓልና የነበረው ሁነት እንዲያጋራ አዲስ ዘመን ከጋዜጠኛ ኢያሱ ጋር አጭር ቆይታ አድርጓል።
አዲስ ዘመን፡- የጁንታው ቡድን በአገር መከላከያ ሰራዊት ላይ ያደረሰውን ጥቃት ተከትሎ መንግስት ወደ ህግ ማስከበሩ እንደሚገባ በተነገረ ቅጽበት እንደ አንድ ዜጋ ምን ተሰማህ?
ኢያሱ፡- ከዛ በፊት አንድ ማንሳት የምፈለገው ነገር ቢኖር በፌዴራል መንግስትና በትግራይ ክልል መንግስት መካከል የነበረው ግንኙነት ከሁለት ዓመት ወዲህ እየሻከረ ሲመጣ የትግራይ ክልል መንግስት ራሱን እንደ ክልል መንግስት ሳይሆን እንደ ፌዴራል መንግስት እየቆጠረ ሲያሰራጫቸው የነበሩ መልዕክቶችና የሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች ሁሉ ፈጽሞ አይመቹኝም ነበር።
በዚህ ድርጊቱ የመንግስትም ከልክ ያለፈ ትዕግስት ተጨምሮ አንድ ክልል ራሱን እንደ አገር አይቶ ፈላጭ ቆራጭ ሲሆን መስማቱና ማየቱ ያንገሸግሸኝም ነበር። ራሱ ከሚያስተዳድረው ክልል አልፎ ለምሳሌ እንደ ኦሮሚያ፣ አማራ፣ ሶማሌና ሌላውን አይነት ክልል ሲያተረማምስ እጅግ አዝን ነበር።
በወቅቱ ስሜቴን ይነካኝ የነበረው ነገር ምንድን ነው ብትይኝ የፌዴራል መንግስት ለምንድን ነው አፋጣኝ የሆነ ርምጃ የማይወስደው የሚል የውስጥ ጥያቄ ነበር። በእርግጥ መንግስት በወቅቱ ብዙ ነገር ሲያድርግ ነበር፤ የሰላም አምባሳደር የሆኑ እናቶች ሲማጸኑም ነበር። እነሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴ የተካተቱበት የሽምግልና ሂደትንም እኔም እንደ ጋዜጠኛ ስዘግብ ነበር።
ነገር ግን የተደረገው ሙከራ ሁሉ ፍሬ አልባ ሲሆንና ጁንታው በሰሜን እዝ መከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት ማድረሱን ስሰማ ማመን ነበር ያቃተኝ። መንግስት በወቅቱ አፋጣኝ ርምጃ ወስዶ ህግ ለማስከበር ሲንቀሳቀስ በጣም ደስተኛ ነበርኩ። ርምጃውም ትክክለኛ ነበር። ስለዚህም በውስጤ ሲመላስ የነበረውም ጥያቄ ምላሽ ያገኘበት ሁነት ነበር ማለት እችላለሁ።
አዲስ ዘመን፡- እንደ ሚዲያ ባለሙያ ደግሞ በወቅቱ ወደ ስፍራው ሄደህ ትዘግባለህ ስትባል ምን አይነት ስሜት አደረብህ?
ኢያሱ፡– እንዲውም በወቅቱ የህግ ማስከበሩ ተልዕኮ አንድ አካል የመሆን ፍላጎቱም ነበረኝ። ወደ ስፍራው ሄጄ ልዘግብ የሚስችለኝን እድል ከማግኘቴ አስቀድሜ የድርጅታችንን አንጋፋ የካሜራ ባለሙያዎች ሳገኝ ወደስፍራው መሄድ እፈልግ እንደነበር እንግራቸው ነበር። ህግ በማስከበሩ ስራ ላይ የበኩሌን ነገር ማበርከት እፈልጋለሁ የሚል ምኞቱ ነበረኝ። የድርጅታችን የካሜራ ባለሙያ የሆኑትን እነ ጸሐይ ንጉሴንና ገባቦ ገብሬን በየቀኑ ሳገኛቸው ወደስፍራው አብሬያችሁ እሄዳለሁ እላቸው ነበር።
አጋጣሚ ሆኖ እኔም ከጸሐይ ንጉሴ ጋር እንደምሄድ ተወስኖ ጸሐይ ደውላ ያሰብከው ተሳካ ስትለኝ የምትቀልድ ነበር የመሰለኝ። በወቅቱ መሄዴን ሳረጋግጥ በጣም ደስተኛ ነበርኩ። አስቀድሜም ቢሆን ለቤተቦቼ በዚህ የህግ ማስከበር ሂደት ላይ እንደ ጋዜጠኛ መዘገብ እፈልጋለሁ በማለት እነግራቸው ነበር። ብሞትም ምንም እንደማይመስለኝ ነው የምገልጻላቸው።
ምክንያቱም ሰው ከንቱ ሞት እንኳ ይሞታል፤ በተለይ በዚያኛው ወገን በኩል ያለውን ዓላማ ስታስተውዪ ይዘው የተንቀሳቀሱት ዓላማ ከንቱ ነው። ለእሱም ዓላማ ለመሞት ነበር ሲሯሯጡ የነበረው። እኔ ደግሞ በዚህኛው ወገን ህግ ከማስከበርና የአገሪቱን ሰላም ከማረጋገጥ እንዲሁም የተጀመረውን የብልጽግና ጉዞ ወደፊት ከማራመድ አንጻር ለአገሬ የራሴን አስተዋጽኦ በማበርከት ሂደት ውስጥ ብሰዋ ምንም ነው የሚል ውስጣዊ ፍላጎትና ተነሳሽነት ነበረኝ። በመሆኑም በአለቃዬ አማካይነት ወደስፍራው እንደምሄድ ሲነገረኝ በደስታ መቼ ነው የምንንቀሳቀሰው ስል ነበር ጉጉቴን ሳልደበቅ የገለጽኩት።
የህግ ማስከበሩ ተግባር ጥቅምት 24 ሲጀመር እኛ ደግሞ ጥቅምት 29 ጉዞ ጀመርን፤ ቀጥታ ወደ ራያ ግንባር አቀናን። ሌሎች የመገናኛ ብዙኃንም ነበሩ። በወቅቱ ፕሬስና ኢቲቪ የነበሩ ሲሆን፣ እዛ ስንደርስ የአማራ መገናኛ ብዙኃን ተቀላቀለን፤ ቀስ እያሉ ሌሎች ሚዲያዎችም ተቀላቀሉን። ለአንድ ሳምንት ያህል ኦፕሬሽኑ ስላልተጀመረ የተለያዩ ስራዎችን ስንዘግብ ቆይተን አንድ ሁለት ቀን ሲቀረን የግንዛቤ ማስጨባጫ መድረክ ተመቻችቶ ማድረግ ስላለብን ጥንቃቄ ገለጻ ተደረገልን።
አዲስ ዘመን፡- በቆይታህ ያስተዋልከው ጉዳይና ስሜትህን የተጫነህ እንዲሁም ያስደሰትህ ነገር ካለ ብትገልጽልን?
ኢያሱ፡– እዛ አካባቢ እንደደረስን ሳማትር የነበረው የህብረተሰቡን እንቅስቃሴ ነበር። በተለይ ቆቦ ከተማ ስንደርስ ሁሉም ማለት በሚያስደፍር መልኩ መሳሪያ የታጠቀ ሆኖ ነው ማስተዋል የቻልኩት። ሁሉም ላይ የሚታየው ስሜት ደግሞ ጁንታውን ለመፋለም ያለውን ዝግጁነትና ቁርጠኝነትን የሚያሳይ ነው። ከየአካባቢው የተውጣጡ ሚሊሻዎች በአንድ ቦታ ተጠርንፈው ቁጭ ብለው ወደውጊያው አውድ መሄድ እንፈልጋለን፤ ወደግንባር ውሰዱን እያሉ ስሜታቸውንም ሲገልጹ ነበር።
ውጊያው ከተጀመረ በኋላ እስከተወሰነ ቀናት ድረስ የመከላከያ ሰራዊታችን ዝግጅቱን አጠናቀቀ። ምንም እንኳ ፍላጎቱ ኖሮኝ የመጣሁ ቢሆንም ውስጤ ደግሞ ፍርሃት ብጤ ዳሰስ ሲያደርገኝ አስተውያለሁ። ያው ጉዳዩ ጦርነት ነውና ሌላ ነገር ሊከሰት ይችላል በማለት ማሰቤ አልቀረም።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ዋጃ አካባቢ እግረኛ ገባ፤ በወቅቱ ደግሞ የጁንታው ታጣቂዎች በአካባቢው መሽገው ነበር። ያንን የያዙትን አካባቢ ለማስለቀቅ ለመከላከያ ሰራዊቱ ስምሪት ስለተሰጠው ወደስፍራው እኛም አብረን አቀናን። ይሁንና በጉዳዩ ዙሪያ ያለውን ክስተት እየዘገብንና እቀረጽን ወደ አካባቢው ስንደርስ ከተወሰነ ክልል ማለፍ እንደማይገባን ስለተነገረን ባለንበት ቆየን።
ሰራዊቱ ወደፊት ቀጠለ፤ ይሁንና በዚያች ቅጽበት ምንም አይነት ውጊያ አልነበረም። የጁንታው ቡድንም ወደኋላ አፈግፍጎ አላማጣን አልፈው ግራካሶ ወደተባለበት አካባቢ ሄደዋል። እስከዛ ድረስ ምንም አይነት ውጊያም አልነበረም። የመከላከያ ሰራዊቱም ቦታዎችን እያጸዳና ከተማዎችን እየተቆጣጠረ ማለፍ ጀመረ።
ከተወሰኑ ቀናት በኋላ ግን ውጊያው ተጀመረ። በወቅቱ ሌተናል ጄነራል ባጫ ደበሌ እንደገለጹት፤ በአካባቢው ያሉት ተራራዎች ሲታዩ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያሉ ተራራዎች ሁሉ ተሰባስበው የመጡ ይመስላሉ ነበር ያሉትና እኔም ያስተዋሉኩት ያንኑ ነው። በተራራዎቹ ዙሪያ ደግሞ ልክ ቀለበት በሚመስል አኳኋን ምሽግ ተቆፍሮባቸዋል። አንድ ዙር ብቻ ሳይሆን ሁለት ሶስት ዙር በተራራዎቹ ቀለበት የሰራ ምሽግ ነበር። በእርግጥም በሌሎች አካባቢዎች ካሉ ተራራዎች ይልቅ ትንሽ ጠንከር
ያሉ እንደሆነ ነበር ሲነገር የነበረው። በአፈር ውስጥ የተቀበሩ አፈሙዛቸው ብቻ የሚታይ ታንኮች እንዲሁም ከባድ መሳሪያዎችና ሌሎችም የመሳሪያ አይነቶች ናቸው የነበሩባቸው።
በወቅቱ ያንን መሳሪያ የታጠቀ ምሽግ ሰብሮ ማለፍ በጣም ከባድ ነው። አንድ በአንድ ያሉትን ምሽጎች እያስለቀቁ እያስለቀቁ ወደ ዋናው አዲ ቀዬ መግቢያ የሚባልበት አካባቢ ሲደርስ ትልቅ ፈተና ነበር የተጋረጠው። በእርግጥም ጦርነት ምን ያህል ከባድ መሆኑን ያረጋገጥኩበት ቦታ ነበር።
ውጊያው በቴክኖሎጂ በመታዝ የተካሄደ በመሆኑ ለመከላከያ ሰራዊታችን ትልቅ አስተዋጽዖ ማበርከት ችሏል ብዬ አስባለሁ። በሰው አዕምሮ ይሰበራል ተብሎ የማይገመተውን ምሽግ በድሮን በመታገዝ የተቀበሩ ታንኮች መመታታት ሲጀምሩ የእኛ እግረኛ ደግሞ ወደ ውስጥ መግባት ሲጀምር ምሽጉ መሰበር ጀመረ። በዚህ ሁሉ መስዋዕትነት ተከፍከሎ ምሽጉን ማስለቀቅ በመቻሉ ወደፊት መጓዝ ጀመርን።
ከዛ በኋላ የማስተውላቸው ነገሮች ሁሉ የሚያሳዝኑ ናቸው ማለት ይቻላል። በየቦታው ባክኖ የሚታዩት የአገር ንብረቶች የሚያስቆጩ ነበሩ። ለምሳሌ የድልድይ መፍረስን እንዲሁም የኤሌክትሪክ ኬብሎችን መቆራረጥ ስታዪ እንዳልነበር ሆኖ ሲቀር በጣም ነበር የሚከብደው። እሱ ብቻ ሳይሆን በየቦታው የነበሩ የጦር መሳሪያዎች ሁሉ ዶግ አመድ ሆነው ስናይ ክስረት እንጂ ሌላ ምንም ሊባል ይችላል።
ከአላማጣ ግንባር እስከ መቀሌ ድረስ ስንገባ በየአስፓልቱ ግራ እና ቀኝ ብቻ እንኳ ያሉት ታንኮች ተቃጥለው ሲታዩ ምን ያህል ብክነት እንደደረሰ ለማስዋል የሚክብድ አይደለም። ይህ መሳሪያ በአገር ሀብት የተገዛ የህዝብ ንብረት መሆኑን ስታስተውዪ እና በልበ ድፍን የጁንታ ቡድን ጦርነት ተቀስቅሶ ለዚህ መድረሱ እጅግ ኀዘንን ከፍ የሚያደርግ ነው።
እዛው ስፍራ ዞር ብለሽ የነዋሪው ህይወት ስታስተውዪ ቤታቸውን እንኳ በጭቃ መምረግ አቅቷቸው የሚቸገሩ ደካማ ሰዎችን ትመለከቻለሽ። ድንጋይ ስር በተገኘች አነስተኛ መሬት ላይ እያመረቱ ከእጅ ወደ አፍ የሆነ ኑሯቸውን የሚገፉትን አቅመ ደካማ ስንመለከት እነዚህ የተጎሳቆሉ ወገኖች በዚህ ሁኔታ እየኖሩ የጁንታው ቡድን ግን ድህነታቸውን ይዘው መቀመጣቸው እንኳ አልበቃ ብሎት በሰላም ደግሞ እንዳይቀመጡ ያመጣባቸውን መዘዝ ማየት የህመም ስሜት ይፈጥራል።
እነዚህ ሰዎች ውሃ ከሆነ ገደላገደል ቦታ፣ ጭራሮ ደግሞ ከሌላ ቦታ ለቅመው ኑሯቸውን በደሳሳ ጎጆ ውስጥ በማድረግ ህይወታቸውን የሚገፉ ናቸው። እነዚህ ወገኖቻቸው በዛ አይነት ሁኔታ እየኖሩ ባሉበት ስንት ዋጋ የተከፈለበት ንብረት በየመንገዱ ወድሞ ማየት የሚያንገበግብ ነበር የሆነብኝ። በዚህ ውስጥ የጁንታውን የክፋት ጥግ ነው ማየት የቻልኩት።
ሌላው ቀርቶ የጁንታው ቡድን የማህበረሰቡን ማህበራዊ ኑሮና እሴቶችን የሚያናጋ ሆኖ ነው ማየት የቻልኩት። የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ውስጥ ገብተው ወደ ቤተ መቅደሱም ዘልቀው የከባድ መሳሪያ መጋዘን ማድረጋቸውን ለተመለከተ ለህዝብ ቁብ የሌላቸው አካላት እንደሆኑ መረዳት አያዳትም። በእንዲህ አይነት መቆጨትና መብከንከን ስሜት ውስጥ እያለሁ ነው ወደ መቀሌ ጉዟችንን ያደረግነው።
በእነዚህ ጊዜያ ውስጥ በጣም የተደሰትኩበት ነው ብዬ የምለው ወደ መቀሌ ከመግባታችን በፊት የነበረው ምሽግ ይሰበራል ብለን ሁላችንም አልገመትንም ነበር። ወደ ምሽጉ ከመድረሳችን በፊት ለተወሰኑ ቀናት ስራ አጥተን ቁጭ ብለን ነበር። ምክንያቱም የምንዘግበው አዲስ ነገር ሲያጋጥመን ነው።
በዚህ መሃል ነው ያለአንዳች ማቅማማት ልክ ቀፎው እንደተነካ የንብ መንጋ ሰራዊቱ ተሞ ምሽጉን እንዳልነበር ያደረገው። ሰራዊቱ ያለአግባብ በገዛ ወገኑ የተጠቃ ነው። ጓደኞቹን በጁንታው ምክንያት ያጣ በመሆኑ ልቡ የቆሰለ ሰራዊት ነው።
ከዚህም የተነሳ ቁጣ ላይ ያለ ነው። እንቅስቃሴው ሁሉ ቁጭትን በተሞላ ሁኔታ ነበር ሲያደርግ የነበረው፤ ምሸጉ ዘንድ ሲደርስ ግን ለጊዜውም ቢሆን አግዶት የነበረ ቢሆንም በዚሁ ሰራዊት ጀግንነት ምሽጉን በመደርመስ መታለፍ በመቻሉና ወደመቀሌ በመዝለቅ መግባታችን ያስደሰተኝ ጉዳይ ነው።
አዲስ ዘመን፡- የጦርነት ዘገባን በማስተላለፉ በኩል ያጋጠመህ ፈተና ይኖር ይሆን? አንድ የሚዲያ ባለሙያ በጦርነት ዘገባ ወቅት ምን አይነት ነገርን ነው ከግምት ውስጥ ማስገባት የሚጠበቅበት ትላለህ?
ኢያሱ፡- በወቅቱ እንዴት መዘገብ እንዳለብን የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ስለነበረን ዲሲፒሊን በተሞላት መንገድ ነበር መረጃን ለተደራሲው ስናደርስ የቆየነው። ምክንያቱም አንዳንዴ ጦርነት ላይ ሆነሽ ሊያጋጥሙ የሚችሉ በጣም ሰቅጣጭ የሆኑ ሁኔታዎች አሉ። እነዚያ ምስሎችም ከዜና ጋር በማዋሃድ ለአንባቢው ማሰራጨት አግባብነት የሌለው ጉዳይ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። ግንዛቤው ስለተፈጠረልን ያንን በጥንቃቄ አድርገነዋል ብዬ አስባለሁ።
ከዛ ውጭ ግን እያዳንዱን የየዕለቱን ክስተት ለህብረተሰቡ ተደራሽ ከማድረግ አኳያ በርካታ ስራዎችን ሰርተናል የሚል እምነት አለኝ። በተለይ እዚህ አካባቢ ካለው ህብረተሰብ የበለጠ እዛ በግንባሩ ዙሪያ ያሉ ሰዎች ለምሳሌ አላማጣ፣ ራያና ቆቦ አካባቢ ያለውን ሂደት በጣም በቅርበት የመከታል ጉጉት ነበራቸው። ሌላው ቀርቶ እኛ በግንባር ውለን ወደ ከተማ በምንመለስበት ወቅት በአካል እኛ ዘንድ እየመጡ መረጃ እንድንሰጣቸው ሲጠይቁን ነበር።
አዲስ ዘመን፡- በግንባር ባለህበት ወቅት የተለያዩ ዘገባዎችን በመስራትህ ለህትመት መብቃቱ ይታወቃልና ከእነዛም ውስጥ ቀልብህን የገዛው ዘገባ ይኖር ይሆን?
ኢያሱ፡- አዎ! አለ፤ እንዳጋጣሚ ሆኖ በተናጠል ያነጋገርኳቸው ግለሰቦች አሉ። ከብዙ ሃሳቦች መካከል አንድ ቀልቤን የገዛውና የህብረተሰቡንም ቀልብ ይገዛል ብዬ የማሰበውን ነጠላ ጉዳይ ብቻ መዘዝ አድርጌም ዘገባዬን ስሰራ ነበርና ከማልረሳቸው ጉዳዮች መካከል አንድ ጊዜ አላማጣ ላይ ያገኘኋቸው ሁለት እናቶች አንዷ እመጫት ስትሆን፣ አንዷ ደግሞ የአምስት ወር ነፍሰጡር ናት። እ
ነዚህ ሰዎች መነሻቸውን አክሱም አድርገው አንዴ በመኪና ሌላ ጊዜ ደግሞ በእግራቸው ሲኳትኑ ቆይተው አላማጣ ገብተው ያገኘኋቸው ናቸው። ሁለቱም የወታደር ሚስቶች ናቸው። የትዳር አጋሮቻቸውን ከአጠገባቸው ወስደው እነሱን ግን ምንም ትራንስፖርትም ሆነ የሚበላ በሌለበት ሁኔታ ነፍሰጡርና እመጫት እንደሆኑ እያወቁ ሂዱ እንዳሏቸው ነበር የነገሩኝ። ይህን ነገር ስዘግብ ውስጤን ክፉኛ እየተፈታተነው ነበርና አልረሳውም።
የጁንታው ታጣቂ ቡድን ከሰራው ግፍ ሌላው ደግሞ ሁለት ሴቶች ባሎቻቸው ሲገደሉባቸው ለምን? ብለው ይጠይቃሉ። ባሎቻቸውን ከገደሉ በኋላ ለመጸዳጃ ቤት ተብሎ በተቆፈረ ጉድጓድ ውስጥ ከተዋቸው አፈር እንኳ መለስ እንዳላደረጉባቸው በአካባቢው የነበሩና ያዩ ሴቶች ነገሩኝ።
እነዚያ ባሎቻቸው የሞቱባቸው ሴቶች አንዷ አራስ ልጅ የያዘች ስትሆን፣ አንዷ ደግሞ የአራት ዓመት ልጅ የነበራት ነች። ሁለቱን ሴቶች ያለርህራሄ ከገደሏቸው በኋላ የአራት ዓመት ህጻኑን ልጅ ይዘውት እንደሄዱ በስፍራው ያሉ ሌሎቹ ሴቶች ነገሩኝ። ይህ ሁኔታ ውስጤን የረበሸው ጉዳይ ነበር።
ሌላው ደግሞ አክሱም ላይ የጁንታው ቡድን አንድ ምሽት ላይ ይመጣና የተወሰኑትን ሰራዊቶች ከበዋቸው እጅ ስጡ ሲሏቸው አንሰጥም ይላሉ። ከውስጥ አንደኛው የትግራይ ተወላጅ የሆነ ወታደር ‹እኔ ኢትዮጵያዊ ነኝ እንጂ ለትግራይ ህዝብ ብቻ የቆምኩ ወታደር አይደለሁም› ይላቸዋል።
ይህ እኔ የትግራይ ህዝብ ብቻ ሳልሆን የኢትዮጵያም ወታደር ነኝ ያለው ወታደር የታንክ ተኳሽ በመሆኑ ዘሎ ታንኩ ውስጥ ይገባና እየተኮሰ እስከ ምሽቱ ድረስ ተከላከላቸው። ጠዋት 12 ሰዓት አካባቢ እነርሱም ታንክ ይዘው መጡ፤ በዚህ ውስጥ ከእነሱም የሞቱ ከእኛ የቆሰሉ ወታደሮች ነበሩ።
ታንክ ሲተኩስ የነበረው ወታደር ግን እስከተወሰነ ሰዓት ድረስ ተዋጋቸውና በመጨረሻ ታንኩን መቱት። ቦንብ በመጠቀምም ከጥቅም ውጪም አደረጉት። ይህን ጉዳይ ይነግሩን የነበሩት ሴት የመከላከያ ሰራዊት አባላት ናቸው። ከዳተኛ ወታደር የመኖሩን ያህል ለኢትዮጵያዊነቱ ዘብ እንደቆመ የሚሰዋ የትግራይ ተወላጅ ወታደር መኖሩን ነው መረዳት የቻልኩት።
ከዚህም ሌላ የትግራይ ተወላጅ የሆኑ ሴቶች የትዳር አጋሮቻቸው ከሌላው ብሄር የሆኑ ወታደሮችን ከእነርሱ አንለይም በማለት አብረው ወደ ኤርትራ ተሰደውና ከኤርትራ ደግሞ ተመልሰው መቀሌ ላይ ያገኘኋቸውም አሉ። የአንዷ ታሪክ ግን ከሌሎቹ ሁሉ የሳበኝ የፌዴራል ፖሊስ አባል ናት፤ በአየር ማረፊያው ውስጥ በጥበቃ ላይ የተሰማራች ናት። በወቅቱ ደግሞ እመጫት ናት።
ኦፕሬሽን ተጀመረና አየር ማረፊያው በመከበቡ አለቃዋ መጠበቂያ ማማ ላይ ወጥቶ ይዋጋ ነበር አለችኝ። እኔ እመጫት ስለሆንኩና መዋጋት ስለማልችል ለሌላው ባልደረባዬ ክላሼን እስከነጥይቱ ሰጠሁና ቆርቆሮ በቆርቆሮ በሆነው ቤት ውስጥ ህጻን ልጄን ይዤ ተቀመጥኩ አለች። ውጊያው በጣም ተፋፍሞ ወደ ውስጥ ዘልቀው ማማ ላይ የነበረውን ወታደር እንዲወርድ አዘዙት፤ አውርደውም በጥይት ሳይሆን እፊቷ ደብድበው እንደገደሉት ነገረችኝ። ይህን ሁሉ ትናገር የነበረው እያነባች ነው።
እርሷ ወዳለችበትም መጥተው ማነው እዚህ ውስጥ ያለው እያሉ ሲጮሁባት እርሷ እንደሆነችና ህጻን እንደያዝች እንዲሁም እንዳይተኩሱባት ብትጮህም መተኮሳቸውን አለመተዋቸውና ጥይቱ ግን እሷንም ልጇንም እንዳላገኘ ነገረችን። ከፍተውም ካዩአት በኋላ ቤቱን ፈትሸው ጫማዋን አስወልቀው በእግሯ ወስደዋት ቤተ ክርስትያን አካባቢ ስትደርስ ከሌላዋ እመጫት ወታደር ጋር በመሆን ከጁንታዎቹ ወገን የነበሩ አስክሬኖችን እንዳስጎተቷቸው ነበር ያወጋችኝ። ይህ ድርጊታቸው በጣም ዘግናኝ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ስለሰጠኸኝ ማብራሪያ ከልብ አመሰግናለሁ።
ኢያሱ፡- እኔም አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 16/2013