የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች የቃል ኪዳን ሰነድ፤ የአብሮነት መሠረት እና አንድ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ትስስር ኖሯቸው የመቀጠላቸው አስኳል እንደሆነ የሚነገርለት የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት በ15ኛው አንቀጹ፤ «ማንኛውም ሰው በሕይወት የመኖር መብት አለው።
ማንኛውም ሰው በሕግ በተደነገገ ከባድ የወንጀል ቅጣት ካልሆነ በስተቀር ሕይወቱን አያጣም፤» ሲል አስፍሯል። ይሄንና ሌሎች በርካታ የሰው ልጆችን በሰላም ደህንነታቸው ተጠብቆ በሕይወት የመኖር መብትን የሚያጎናጽፉ ሕገ መንግሥታዊ መብቶች ብቻ ሳይሆን፤ ይሄን ለማስፈጸም የሚያስችሉ አደረጃጀቶች እና ተቋማትም በየፈርጁ አሉ።
ይሁን እንጂ በዚህ መልኩ በቃላት ተከሽነው አምረው የቀረቡ ሕገመንግሥታዊ ድንጋጌዎች፤ እነዚህን ለማስፈጸም የተዋቀሩ አደረጃጀቶች ቢኖሩም፤ ዛሬም በበርካታ የኢትዮጵያ ክፍሎች ሰው በሰው ላይ ጨክኖ የመኖር ዋስትናውን ሲነጥቀው መመልከት የዘወትር ተግባር ሆኗል።
ከዚህ ሁሉ ግን ልክና ገደቡን ያለፈው የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሉ የመተከል ዞን የሰው ልጆች የስቃይ ድምጽ አለመደመጡ፤ እንደ ቄራ ከብት በአራጆች የምታልፍ የሰው ሕይወት ከዕለት ዕለት እየጨመረ መምጣቱ፤ ቀስትና ጦር፤ ጩቤና ሰይፍ ከጥይት አሩር ጋር ተዳምረው ማንነትን በለየ መልኩ ለጥፋት ሲውሉ ማየትና መስማቱ ዘወትራዊ ተግባር መሆኑ በእጅጉ ያሳዝናል፤ እንደ ሰው ሲታሰብ ተግባሩ ከሰውኛ ባህሪ አፈንግጦ መውጣቱን ለመረዳት አያዳግትም።
ይሄን ችግር ለመፍታት ሕግን ከወረቀት ላይ ወደ መሬት ማውረድ፤ አስፈጻሚዎችና ሕግ አስከባሪዎችን በየቦታው ከመመደብ ባለፈ አሠራርና ተግባራቸውን መፈተሽ፤ እንደ ተግባራቸውም እያዩ ማረምና ማስተካከል፤ ካልተስተካከለም ሹመኝነት ከሕዝብ አይበልጥምና አደብ ማስያዝ የመንግሥት ተቀዳሚ ተግባር ሊሆን ግድ ነው።
ይሁን እንጂ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በስፍራው ውለው፣ ሕዝብና አመራሩን አናግረውና አቅጣጫ ሰጥተው በተመለሱ ምሽት መሰል አሰቃቂ ተግባር ሲፈጸም ማየት ደግሞ፤ ችግሩ ምን ያህል ስር የሰደደ፣ የዜጎች ሰቆቃም ምን ያህል እንደተባባሰ በገሃድ ያሳየ ሆኗል። እናም የዜጎችን ደህንነት እና ሰላም ማስጠበቅ፤ በሰው በላዎች የጥፋት አካላት የሚጠፉ የንጹሃ ሰዎችን ሕይወት መታደግ ለነገ ሳይባል ዛሬ መሰራት ያለበት ነው።
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ታኅሣሥ 14 ቀን 2013 ዓ.ም ባወጣው መግለጫም፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ የሰዎች ደኅንነት ማረጋገጥ ቀዳሚው የመንግሥት ግዴታ ስለመሆኑ ያመለከተ ሲሆን፤ በክልሉ በተለይም በዞኑ ከተፈጠረው ተደጋጋሚ ጥቃት ባለፈ፤ ታኅሣሥ 13 ቀን 2013 ዓ.ም ቡለን ወረዳ፣ በኩጂ ቀበሌ ከሌሊቱ አስር ሰዓት ላይ የታጠቁ ኃይሎች በእንቅልፍ ላይ በነበሩ ነዋሪዎች ላይ በለኮሱት እሳት እና በተኩስ ከ100 በላይ ሰዎች መገደላቸው በክልሉ ያለው የሰብአዊ መብቶች ጥበቃ በከፍተኛ ሁኔታ እየተዳከመ መሄዱን እንደሚያሳይ ነው የገለጸው።
ኮሚሽኑ ሁኔታውን እስካጣራበት ጊዜ ድረስ በቡለን ሆስፒታል 36 ተጎጂዎች እርዳታ እየተደረገላቸው ሲሆን፤ አብዛኛዎቹ በጥይት ሌሎቹ በቀስት የቆሰሉ ናቸው። በተጨማሪም ሰዎች ጥቃት የደረሰባቸውን ሁኔታ የሚያሳዩና የሚረብሹ የፎቶግራፍ ማስረጃዎች ደርሰውታል።
ከዚህ መረዳት የሚቻለው ገዳዮች የራሳቸው ዓላማና ፍላጎት ያላቸው ቢሆንም፤ ፍላጎትና ዓላማቸውን ለማስፈጸም ንጹሃንን ኢላማ ያደረጉ መሆናቸውን ነው። ከየስፍራው የሚወጡ መረጃዎች እንደሚያሳዩትም፤ በእነዚህ የሞት መልዕክተኞች በጥይትም፣ በጩቤም፣ በቀስትም እየሞቱ፣ እየቆሰሉና እየተሰቃዩ ያሉት፤ ለፍተው አዳሪ አርሶአደሮች፣ ጠመንጃ ያልታጠቁ ንጹሃኖች ዜጎች ናቸው።
እናም የእነዚህ ንጹሃን እንባ ዛሬም እየፈሰሰ ነው፤ የእነዚህ ንጹሃን ደም ዛሬም ስለ ፍትህ እየተጣራ ነው፤ በንጹሃን ደም ውስጣቸው የሚደማ፣ ለመከራ ተላልፈው የወደቁ ቤተሰብና ዘመዶችም መራር ጩኸት የወገንን ምላሽ አጥብቆ ሽቷል።
ምክንያቱም እንደ ቀድሞው ከጫካ በሚወጡ ሳይሆን ነዋሪዎቹ በስምና በመልክ በሚያውቋቸው ሰዎችና የበኩጂ ቀበሌ ነዋሪዎች ጭምር ተሳትፈውበት ሌሊቱን የጀመረው ጥቃት እስከ ቀኑ አጋማሽ ድረስ ዘልቆ በሰው ሕይወት እና በአካል ላይ ከደረሰው ጉዳት በተጨማሪ የደረሱ ሰብሎችና የተሰበሰቡ ማሳዎች በእሳት ጋይተዋል። በጨላንቆ እና ዶሼ ቀበሌዎች ቤቶች ተቃጥለዋል፤ በድባጤ ወረዳ ዶንበን ቀበሌ ስጋት የገባቸው ነዋሪዎች ቀዬአቸውን ጥለው እየተሰደዱ ነው።
ይሄን የተገነዘበው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በአካባቢው የሚገኘውን የፀጥታ ኃይልና መዋቅር የሰዎችን ደኅንነት ሙሉ በሙሉ ለማረጋገጥ በሚያስችል መልኩ በከፍተኛ ደረጃ በአፋጣኝ እንዲጠናከር አቅርቧል። በመሆኑም እንደተባለው የንጹሃን ሞት ሊያበቃ፤ ይህ እንዲሆንም ከሁሉም በፊት ቅድሚያ ተሰጥቶት ሊሰራ ይገባል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 16/2013