ጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ gechoseni@gmail.com
ታሪክ የአንድ ማኅበረሰብ «የነበር ማከማቻ ጎተራ» እንደሆነ በሚገባ አምናለሁ። ማመን ብቻም ሳይሆን ተምሬዋለሁ፣ ጽፌበታለሁ በጥቂቱም ቢሆን አስተምሬዋለሁ። ለታሪክ ፍቅርና አክብሮት እንዲኖረኝ ዛሬዬን እያሰቡ ላስተማሩኝ መምህራኖቼ ምሥጋናዬ ከፍ ያለ ነው።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የትምህርት ቆይታዬ ታሪክን በተከፈተ ዓይነ ኅሊና እንድመረምር አቅጣጫ የጠቆሙኝ ዶ/ር መርዕድ ወ/አረጋይና በባዕድ ምድር በታሪክ አተረጓጎም ላይ አጠብቀው ያስተማሩኝንና የመከሩኝን ፕሮፌሰሮቼንም እንዲሁ ማመሰገኑ የኅሊናን ዕዳ የማቅለል ያህል ሆኖ ይሰማኛል።
«ነበርን» በየመጻሕፍታቸው ውስጥ በአግባቡ ሰንደው ላቆዩልን ኅሊና-አደር የታሪክ ምሁራንና የግለ ታሪክ ጸሐፍትም እንዲሁ ዛሬያችንን ከትናንት ጋር አስተሳስረውልናልና አክብሮታችንን ብንለግሳቸው አግባብ ይሆናል። ታሪክ የትናንትን ድልና ሽንፈት፣ ክብረትና ውርደት፣ ብልፅግናና ድህነት፣ ማነስና መተለቅ፣ ማንነትን፣ የሆነውንም ይሁን ያልተሆነውን ወዘተ. በመንፈስ የተሸከመ የግለሰቦች፣ የቡድኖች፣ የሀገራትና የዓለማችን ቅርስ ነው።
ችግር የሚፈጠረው ታሪክ «በነበር ጎተራ» ውስጥ ተከማችቶ መቆየቱ ሳይሆን ለዛሬ ኑሯችን ጥላ ሆኖ ሲያገለግል ለበርካታ ተግዳሮቶች ተጋላጭ እመሆኑ ላይ ነው። ሃሳቡ መብራራት ስላለበት ጥቂት ፈታ ማድረጉ ይጠቅም ይመስለኛል። ለምሳሌ፤ በጎተራ ውስጥ ተከማችቶ ዓመታት የሚያስቆጥር የእህል ዘር ለረጅም ጊዜ እንዳስቀመጡት አይቆይም።
አንድም እህሉ በነቀዝ ሊበላሽ ይችላል ወይንም ከሙቀትና ከቅዝቃዜ መፈራረቅ የተነሳ ተፈጥሯዊ ጣዕሙን እንደነበር ማግኘት ሊያዳግት ይችል ይሆናል። የማከማቸው ጎተራ በጥንቃቄ ካልተጠበቀም በአጥቂ ተባዮችና ነፍሳቶች ጉዳት ሊያጋጥመውም ይችላል።
ታሪክም እንደዚሁ ነው። አንድ ታሪክ በመጀመሪያ ሲጻፍ ሚዛኑን ጠብቆና ነገን አስተውሎ ከውስጣዊ የራስ ኅሊናና ከውጭ ተጽኖዎች ነፃ ሆኖ እስካልተመዘገበና ለትውልድ እስካልተሸጋገረ ድረስ (አወዛጋቢ ሃሳብ መሆኑን ሳልዘነጋ) ውሎ አድሮ የሚያስከትለው ችግርና አደጋ ምን ያህል ሊገዝፍ እንደሚችል መገንዘብ አይገድም።
አንድ ኩነት በወቅቱ ትክክል ነው ተብሎ ታምኖበት ቢመዘገብ እንኳን እውነታው ከታሪክ ጎተራ ውስጥ እየተቆነጠረ ሲዘገን መመረዙ፣ መከለሱ፣ ሲከፋም እውነተኛው መልኩ ደብዝዞ ወደ ተረትነት መለወጡ አይቀርም።
እንደ ተረት የሚነገረው ክስተት ደግሞ «የላም በረት» እየተባለ የጭውውት ያህል የሚዝናኑበት ሳይሆን ብረት አማዞም ሊያፋልም ይችላል። ሀገሬ ዋቢ ትቁምልኝ!«የትናንት ታሪክ የዛሬ ጥላ ነው» ያልኩትንም ጠነን ያለ አገላለጽ በጥቂቱ አብራርቼ ልለፍ። «ጥላ» በፀሐይ አማካይነት በምድር ወይንም በቁስ ላይ ተፈጥሮ የምትስለው ምስለ ቅርጽ ነው።
ጥላ በዓይን ይታያል እንጂ አይዳሰስም ወይንም አይጨበጥም። አምሳለ ቅርጹ ከእውነተኛ ሰብዓዊም ሆነ ከቁሱ አካሉ እውነታ ጋር በፍጸም አይገጣጠምም። ጥላው ወይ ይገዝፋል ወይንም ያንሳል አለያም ይሾጥጣል። የአንድ አካል ቅርጽ ነው ስንልም ይህንን እውነታ ከግምት ውስጥ አስገብተን ሊሆን ግድ ነው። ታሪክን በጥላ መመሰል ያስፈለገበት ዋነኛ ምክንያት ዛሬን በትናንት ቅርጽ ውስጥ አስገብተን እንዳንቸገር ለማስገንዘብ ነው።
የጥላ ነገር ከተነሳ አይቀር «ጥላ ወጊ» የሚባሉ የክፉ ድርጊት መሠሪዎችም ቢታወሱ አይከፋም። በማኅበረሰባችን ውስጥ «ጥላ ወጊ» የሚል ቅጽል የተሰጣቸው አንዳንድ የባዕድ አምልኮ ተገዢዎች በባለ ጥላው ግለሰብ ላይ የሚያደርሱት እኩይ ተግባር መዘዙ ብዙ እንደሆነ ሳናደምጥ የቀረን አይመስለኝም።
የእውነት ሃሰትነቱ ንትርክ ለጊዜው ባይጠቅመንም ታሪክም እንዲሁ በነበር ጥላነቱ እንዳይከበር በማወቅም ይሁን ሆን ተብሎ «በጥላ ወጊዎች» ትንተናና ትርጉም መቁሰሉና መለከፉ ስለማይቀር መጠንቀቁ እንደማይከፋ ለመጠቆም ነው።
ታሪክ ለበጎም ይሁን ለክፋት፣ ለማስተማሪያም ይሁን ለማደናገሪያ፣ ለትርፍም ይሁን ለኪሳራ ብቻ ለፈለገው ዓለማ ቢተረጎም ዞሮ ዞሮ ትናንት የሚባለው ኃላፊ ጊዜ፣ ወቅትና ድርጊት የተሰዋበት የመስዋዕት መቅረቢያ መሆኑ ሊጤን ይገባል። ለዚህም ነው አስተዋይ የዘርፉ ጠበብት «ከታሪክ መሰዊያ ላይ አመዱን ሳይሆን እሳቱን ጫሩ!» እያሉ የሚመክሩት።
«የታሪክን ስህተት የሚደግሙ የተኮነኑ ናቸው» የሚለው አባባል ተደጋግሞ ሲነገር እናደምጣለን። ለመሆኑ ታሪክ ራሱን ይደገማል ወይ? ብለን እንጠይቅ:: ይህንን አባባል የቀመረው በፍልስፍና ዕውቀቱ አንቱታን ያተረፈው የሀርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ፈላስፋ የነበረው ጆርጅ ሳንታያና እንደሆነ ታሪኩ ያስረዳል። እንደዚህ ምሁር አገላለጽ ታሪክ የራሱን መልክ አምጦ አይወልድም፤ ጥላውን እንጂ።
የማይቻለውን እንደሚቻል አድርገው የትናንቱን የነበር ታሪክ በዛሬ መልክና አምሳል ካላዋለድን ወይንም መንዝረን ካልከበርንበት እያሉ «ላባቸውን በከንቱ፤ ደማቸውን በደመ ከልብነት» የሚያፈሱ ምስኪኖች እንደምን እንደተኮነኑ ማሳያና ምስክሩ የድንብር ጉዟቸው ውጤት ነው።
ያለፈን ታሪክ በትምህርትነቱ በመውሰድ ከስህተቱ ለመማር፣ ከመልካም ጎንም ለመጠቀም ከመሞክር ይልቅ «ነበርን» የሙጥኝ ብለው አብረው እያንቀላፉ ያሉ ዜጎች ብዙዎች ናቸው። በተለይም የዛሬን ጀንበር እየሞቁና በዛሬ ትራክተር የተመረተ እህል እየተመገቡ የትናንትን ፀሐይ የሚናፍቁና በትናንት በሬ ካልታረሰ እያሉ የነገር ሞፈር ቀንበር የሚጠምዱ መርህ አልባ ግለሰቦች ሊለቀስላቸው ካልሆነ በስተቀር ሊታዘንላቸው አይገባም።
አንዳንድ ፖለቲከኞችና የማኅበር አንቂ ነን እያሉ ግራ ተጋብተው ሌሎቻችንንም ግራ የሚያጋቡን ግለሰቦች ሳስተውልማ ትዝ የሚለኝ የሚከተለው ሀገር በቀል አባባል ነው። «በስብስቴ ዘመን የከሰረ አረብ የዱሮ መዝገቡን ያገላብጣል፤ ለምን ቢሉ ዱቤ የሰጣቸውን ግለሰቦች ስም ሊፈልግ!» ይህ ብሂል የተፈጠረው የሸቀጣ ሸቀጥ መሸጫ የሠፈር ኪዮስኮች በሙሉ «አረብ ቤት/ሱቅ» እየተባሉ በሚጠሩበት በቀዳሚ ዘመን መሆኑን ልብ ይሏል።
በርካታ የሀገራችን «አወቅን ባይ አላዋቂዎች» በነበር ከሚወሰልቱባቸው የትናንት ድርጊቶች ጋር በትዝታና በቂም በቀል ሙጫ ተጣብቀው ከዛሬ እውነታ ጋር ሲጣሉ መስተዋል «አይ የአእምሮ ድንክነት!» አሰኝቶ ለትዝብት ይዳርጋል።
ትናንት የራሱ ዐውድ ነበረው። የማኅበረሰቡ የንቃተ ኅሊና ደረጃም የራሱ ውሃ ልክና አሻራ ታትሞበታል። የእውቀትና የግንዛቤው ደረጃም በራሱ ልክ የተመጠነ ሚዛን ነበረው። የትናንቱ ድልና ሽንፈት፣ ጀግንነትና ብርታት፣ ብልፅግናና ኩስምንና፣ ዕውቀትና ማነስ፣ ስህተትና ውድቀት የተፈጸሙት ትናንት ነው። ፈጻሚዎቹም ስማቸውና ግብራቸው እንጂ አካላቸው በመቃብር ውስጥ ያረፉ ባለታሪኮች ናቸው።
ለዚህም ይመስላል፤ «ታሪክ በአፅመ ባለታሪኮች ላይ የሚፈጸም ክህደት» እንዳይሆን ብዙዎች የሚያስጠነቅቁት። «ለዕለት እንጀራ ማብሰያነት ሲባልም በመቃብራቸው ላይ የበቀለውን የተግባር መታሰቢያ አፀድ ከመቁረጥም ሆነ ከማድረቅ መጠንቀቅ እንደሚገባ» የዘርፉ ጠበብት የሚመክሩት።
እውነት ነው ዛሬ የበቀለው በትናንት ማሳ ላይ መሆኑ ሊዘነጋ አይገባም። ማርቲን ሉተር ኪንግ እንዳለው «እኛ የትናንት ታሪክ ሠሪዎች ሳንሆን፤ በነበር ታሪክ ላይ የተገነባን የዛሬ ፍሬዎች ነን።» ኦማር አህመድ የሚባሉ ምሁር የዚህን የቴክኖሎጂ ዘመን ትውልድ ጥሩ አድርገው የገለጹ ይመስለኛል። «የምንኖረው በዲጅታል ዓለም ውስጥ ይሁን እንጂ የተፈጠርነው ግን በዘመነ አናሎግ መሆኑ ልብ ሊባል ይገባል።»
ይህን መሰሉ ጥበብ የተገለጠላቸው ቲዮዶር ሩዝቬልትን መሰል ታላላቅ ሰዎች ሲመክሩ የኖሩት፤ «ስለ ትናንት እውነታ ይበልጥ እየተረዳን በሄድን ቁጥር፤ ስለ ዛሬያችን ውበት መጨነቅ እንጂ ስላለፈው ስህተት መቆጨትና መፀፀት ምንም ፋይዳ እንደሌለው ነው።»
ብዙ ሀገራዊ መከራዎቻችንንና ቁልል አበሳዎቻችንን እንድናዘምር ምክንያት ከሆኑት ችግሮቻችን መካከል በቀዳሚነት ሊጠቀስ የሚገባው የታሪክ አረዳዳችንና አተረጓጎማችን ሚዛን ሊደፋ እንደሚችል በግሌ እምነቱ አለኝ። እንዲያውም ኮስተር ያለውን ትዝብታችንን እንዘርግፈው ካልን ስለ ረጅም የታሪክ ባለቤትነት ክብር እየዘመርን በትንንሽ «የነበር ጠጠሮች» የምንደነቃቀፍ መስሎ ይታየኛል።
ማስረጃ ይጠቀስ ከተባለም በፖለቲካ ፍርሃት ተጠምቀው የታሪክ ዲፓርትመንታቸውን በር የከረቸሙትና ተማሪዎቻቸው ወደ ሌላ የትምህርት ክፍል እንዲዘዋወሩ ይመክሩ የነበሩ «የርዕዮተ ዓለም መር» ዩኒቨርሲቲዎቻችንን ማስታወስ ይቻላል።
ማስረጃው ይጠናከር ከተባለም ልጆቻችን በየትምህርት ደረጃዎቻቸው ለዓመታት ያህል የታሪክ ማስተማሪያ መጻሕፍት «ድሆች እንዲሆኑ» የበየንባቸው የሚዘነጋ አይሆንም። ከፍ ካደረግነውም ታሪክን እየፈሩ፣ በታሪክ እያፈሩና የታሪክን አንድ ጫፍ በመምዘዝ ብቻ እየተጓተቱ እንዲያድጉ የፈረድንባቸው መሆኑም በታሪክ ጭቡነት ተመዝግቦ የሚያልፍ ይመስለኛል።
ይበልጥ ማስረጃችን ልዕልና ይጎናጸፍ ካልንም በርካታ የታሪክ ፕሮፌሰሮቻችን በጡረታ ሰበብ ከማስተማርና ከምርምር ሥራዎቻቸው ተገልለው በየዋሻዎቻቸው ውስጥ እንዲሰነብቱ አስበርግገናቸዋል። ሜዳውንም ሌሎች ተቆጣጥረውታል። ፖለቲከኛ ተብዬዎችንና «የማኅበረሰብ አንቂ» ማዕረግን ለራሳቸው ያጎናጸፉትን ገመናና ጉድ እንገላልጥ ካልንማ የሚሰነፍጡ ሽታዎች ስለሚያስነጥሱን ወደ ዝርዝሩ ላለመዝለቅ መቆጠቡ ይበጅ ይመስለኛል።
ይህ ጸሐፊ የብዕሩን ቀለም ከህመምተኛ ስሜቱ እየቀዳ ለበርካታ ዓመታት ሃሳቡን ሲገልጽ የኖረው የሀገሩ ጉዳይ ግድ ስለሚለውና የሕዝቡ እንግልትም እንዲያበቃ ካለው የማይናወጥ እምነት የተነሳ ነው። አዲስ የፖለቲካ ፋሽን አስተዋዋቂ «ሞዴሊስቶች» ብቅ ባሉ ቁጥር የታሪካችንን የትናንት ጠባሳ እየቆፈሩ ቁርሾና ቂም እንዲያመረቅዝ ሲያደርጉ ማስተዋል እንኳን እኛን መሰል ዜጎችን ቀርቶ ለባዕዳንም ቢሆን ድርጊቱ አንገት ያስደፋል። ለራስ ውርደት ለማኅበረሰብም ኪሳራ ካልሆን በስተቀር ከዚህን መሰሉ የክፋት ድርጊት የትርፋማነት ትሩፋት ይበቅላል ብሎ መጠበቅ የዋህነት ነው።
በትናንት አስተሳሰብ፣ በትናንት የልቦና ውቅር፣ በትናንት የዕውቀት ልክ በትናንት ዐውድ የተፈጸሙ የታሪክ አካሄዶች ወይንም «ህፀፆች» ብለን የወሰንናቸው የትናንት ድርጊቶችን ምስልን እያጎላን በፖለቲካ ርዕያችንና በአስተሳሰብ ማንነታችን ላይ ተነቅሰን ለማጌጥ መሞከሩ «ሲያጌጡ ይመላለጡ» ካልሆነ በስተቀር ትርጉም ያለው ፋይዳ አይኖረውም።
በሥልጣናችን የፈረጠመ ጡንቻ ላይ የታሪክን ደብዛዛ ሥዕል ሥለን ለአሸናፊነት ራስን ማዘጋጀትስ ምን ያህል ምዕራፍ ያራምደናል? በጋራ ሊያኗኑረንስ እንደምን አቅም ይኖረዋል?
«ትናንት ያደናቀፈንን ድንጋይ በእንቅፋት መታኝ ስሞታ ልናልፈው እንችላለን፤ ያው ድንጋይ ዛሬም መልሶ ካደናቀፈን ግን እንቅፋቱ ድንጋዩ ሳይሆን ለድንጋዩ እንቅፋት የሆነው እኛው ራሳችን ነን።» ሰላም ይሁን!
አዲስ ዘመን ታህሳስ 15/2013