በጋዜጣው ሪፖርተር
ጣሊያን በኮሮና ቫይረስ ስርጭት ምክንያት ከገና በዓል እስከ አዲስ ዓመት ድረስ የሚዘልቅ የእንቅስቃሴ ገደብ በማሳለፏ ምክንያት ጣሊያናውያን የገና እና አዲስ ዓመት በዓልን በእንቅስቃሴ ገደብ ውስጥ እንደሚያሳልፉ መገለጹን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
እንደ ዘገባው፤ ምዕራባውያኑ የገና በዓላቸውን ታኅሣሥ 16 እንዲሁም የዘመን መለወጫ በዓልን ታኅሣሥ 23 ያከብራሉ።
ይሄን ተከትሎም የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ስርጭትን ለመግታት በሚል ጣሊያን የእንቅስቃሴ ገደብ የጣለች ሲሆን፤ የእንቅስቃሴ ገደቡ ተጥሎ በሚቆይበት ወቅት መጠጥ ቤቶች እና ምግብ ቤቶች ዝግ ይሆናሉ።
ጣሊያናውያንም ከቤታቸው መውጣት የሚችሉት ወደ ሥራ ገበታቸው ለመሄድ አልያም የሕክምና አገልግሎት ካስፈለጋቸው ብቻ ነው።
የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጁሴፔ ኮንቴ አስተዳደራቸው በበዓላት ወቅት የሰዎችን እንቅስቃሴ ለመገደብ ውሳኔ ማስተላለፉ ቀላል አልነበረም ብለዋል።
“በገና በዓል ወቅት የሰዎች እንቅስቃሴ ሲጨምር በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ያሻቅባል የሚል ስጋት በመኖሩ” ይህን ውሳኔ ለመወሰን መገደዳቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስረድተዋል። ከእንቅስቃሴ ገደቡ በተጨማሪ በጣሊያን ተጥሎ የሚገኘው የሰዓት እላፊ ተፈጻሚነቱ ይቀጥላል።
በሌላ በኩል፤ በኮሮና ቫይረስ መያዛቸው የተረጋገጠው የፈረንሳይ ፕሬዚደንት ኢማኑኤል ማክሮን በቤተ-መንግሥታቸው እራሳቸውን ለይተው ይገኛሉ። ማክሮን ድካም፣ ራስ ምታት እና ደረቅ ሳል እንዳላቸው ተናግረዋል።
ከፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ጋር ባሳለፍነው ሳምንት በአውሮፓ ሕብረት ስብሰባ ላይ የተገናኙት የስሎቫኪያው ጠቅላይ ሚኒስትር ኢጎር ማቶቪች በኮሮናቫይረስ መያዛቸውን ይፋ አድርገዋል። በስብሰባው የተሳቱፉ የቤልጄም፣ ስፔን እና ፖርቹጋል መሪዎች ለጥንቃቄ እራሳቸውን ለይተው እንደሚያቆዩ አስታውቀዋል።
የገና በዓል መቅረቡን ተከትሎ በርካታ የአውሮፓ አገራት ጥብቅ የኮሮና ቫይረስ መመሪያዎችን እያወጡ ይገኛሉ። ኔዘርላንድስ እና ጀርመን ለመጪዎቹ 10 ቀናት የእንቅስቃሴ ገደብ ውሳኔ አስተላልፈዋል። ኦስትሪያ በበኩሏ ከገና በዓል በኋላ የዜጎችን እንቅስቃሴ እንደምትገድብ አስታውቃለች።
የስዊድን ባለስልጣናት በርካታ ሰዎች በሚሰበሰቡበት ቦታ ዜጎች የአፍ እና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል እንዲያደርጉ ምክረ ሃሳብ ለግሰዋል። በምግብ ቤቶች ከአራት ሰዎች በላይ በአንድ ላይ እንዳይቀመጡ እንዲሁም የአልኮል መጠጥ እንዳይሸጥም መመሪያ አስተላልፋለች።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 11/2013