ዋቅሹም ፍቃዱ
የህክምና ባለሙያው ዶክተር አድናን ጃሰም፣ በጦርነት በምትታመሰው ሶሪያ ውስጥ ነበር በሙያው ህዝቡን ሲያገለግል የቆየው፡፡ ምንም እንኳ በርካታ ሶሪያውያን ጦርነቱን ምክንያት በማድረግ አገራቸውን ለቀው ወደ ተለያዩ የጎረቤት አገራት ቢሸሹም ዶክተር አንድናን ግን እስከ ህልፈተ ህይወቱ ድረስ በሶሪያ መኖርን መረጠ ሲል አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡
ዶክተር አድናን፣ ከአራት ዓመት በፊት በቦምብ ፍንዳታ እግሮቹ ክፉኛ ከመጎዳታቸው ባለፈ ከተለያዩ አገራት ለተሻለ የስራ ዕድል ጥሪ እየተደረገለት እንኳን ህመሙን ችሎ ጦርነት፣ ረሃብና በሽታ የተፈራረቀባቸውን የሶሪያ ህዝብ ማገልገሉን ስለመቀጠሉ ነው ዘገባው የሚያትተው፡፡
ዶክተር አድናን፣ ህዝብን ለመርዳት ካለው ቁርጠኝነት አንፃር ዓለምን እያስጨነቀ ያለው የኮሮና ወረርሽኝ በሶሪያ ሰሜን ምዕራብ ሲከሰት በግንባር ቀደምትነት መሰለፉ እምብዛም የሚያስደንቅ አይደለም ብሏል፡፡
አገልግሎት እየሰጠ ባለበት የመስከረም ወር መጀመሪያ አካባቢ ህመም ሲሰማው ከቆየ በኋላ ከአራት ቀን በፊት በ58 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት መለየቱ በሶሪያውያን ዘንድ ጥቁር ጠባሳ ጥሎ አልፏል፡፡
በዶክተሩ ሞት ልቡ የተሰበረው በፈረንሳይ አገር የሚኖር የአጎቱ ልጅ ዶክተር ዘይድ አሊሳ፣ እየሆነ ያለው ነገር ለማመን እንደሚከብድ በሃዘን ይገልጻል፡፡ “የብዙዎችን ህይወት ያተረፈውን ሰው ሳንደርስለት በአራት ቀን ውስጥ ህይወቱንአጥቷል” በማለት በቁጭት ይናገራል፡፡
ዶክተር ዘይድና ዶክተር አድናን ተወልደው ያደጉት የግብርና ስራ የሚዘወተርበት አካባቢ ሲሆን፤ ዶክተር ዘይድ ገና በወጣትነት ዕድሜው ነበር በትምህርት ምክንያት ከቤተሰቡ ተለይቶ ወደ አገሪቱ ዋና ከተማ ወደ ደማስቆ ያመራው፡፡ የያኔው ዘይድ የዛሬው ዶክተር ዘይድ ህክምና ተምሮ በሙያው ህዝቡን እንዲያገለግል አባቱም ትልቅ ፍላጎት ነበረው፡፡
በመጨረሻም ህልማቸው ተሳክቶ ዶክተር ዘይድም ትምህርቱን በህክምና ካጠናቀቀ በኋላ ወደ ትውልድ መንደሩ ተመልሶ ህዝብን ማገልገል ጀመረ፡፡
ዶክተር ዘይድ እንደ ዶክተር አድናን በህይወቱ ፈርዶ ከላይ በአየር ሃይል የምትደበደብ፣ በመሬት ደግሞ በከባድ መሳሪያ የምትደቆስ የምስራቋን ሶሪያ ህዝብ እያገለገለ ይገኛል። በዚህ ለአፍታ እንኳ መቆየት እጅግ አስቸጋሪ በሆነበት አካባቢ ዶ/ር ዘይድ ህዝቡን ብቻ ሳይሆን አንዳንዴ አብረው የሚሰሩ በቦምብ ፍንዳታ የቆሰሉትን ባልደረቦቹንና ሌሎች የጤና ባለሙያዎችንም ያክማል፡፡
ሶሪያ ዛሬም ቢሆን በጦርነት፣ በረሃብና በበሽታ እየማቀቀች ትገኛለች፡፡ እስካሁን በጦርነቱ ምክንያት ወደ ግማሽ ሚሊዮን ገደማ የአገሪቱ ህዝብ ህይወቱን አጥቷል፣ ወደ አንድ ሚሊዮን ገደማ የሚሆኑ ሲቆስሉ ከ5 ነጥብ 6 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት ደግሞ ቀዬአቸውን ጥለው ተሰደዋል፤ በርካታ ሃኪሞችም ስፍራውን ጥለው ወጥተዋል፡፡
ይሁን እንጂ እነዶ/ር ዘይድ ዛሬም በቱርክ የሚታገዙ ተቃዋሚ ሃይሎች ቁጥጥር ስር ባለችው በሶሪያ ሰሜን ምዕራብ በህክምና ሙያ እያገለገሉ መሆናቸውን ዘገባው ያስረዳል፡፡ ነገር ግን ሳይታሰብ ዶ/ር አድናንን በኮሮና በሽታ ምክንያት ከመካከላቸው አጥተዋል፡፡
ዶ/ር አድናንና ቤተሰቡ በጦርነቱ ምክንያት ለብዙ ጊዜያት ከቀዬአቸው ቢፈናቀሉም እንደሌሎቹ ለቀው አልሄዱም፡፡ ዶ/ር አድናን ሁለቱ እግሮቹ በቦምብ ፍንዳታ ቢቆስሉም ህዝብና አገርን ከማገልገል አላገዱትም፡፡ ይልቁንስ የቀዶ ጥገና ህክምና ከተደረለት በኋላ በቁርጠኝነት ማገልገሉን ቀጠለ፡፡
በሶሪያ ሆስፒታሎች የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ፣ የሳኒታይዘር፣ ጓንት፣ የሳሙናና የመሳሰሉት የኮሮና ወረርሽኝ መከላከያ ቁሳቁሶች እጥረት እጅግ ከፍተኛ ቢሆንም እነዶክተር አድናን አቅማቸውን አሟጠው ሙሉ ህክምና ሲሰጡ እንደነበር ዘገባው ይጠቁማል፡፡ ይህ ዓይነቱን ለነብሱ እንኳ የማይሳሳ፣ አገርና ህዝብን ወዳድ ሰው ነው ሶሪያ ያጣችው፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 11/2013