ይህ በተለምዶ “ደም ብዛት” ወይንም “ደም ግፊት” በሽታ በመባል ይታወቃል፡፡ከፍተኛ ደም ግፊት የሚባለው በትክክል በሚሰራው መለኪያ በተለያዩ ጊዜያት ቢያንስ ሁለት ጊዜ ተለክቶ የላይኛው ግፊት (systolic) 140mmHg እና በላይ ወይም የስረኛው ግፊት (diastolic) 90 mmHg እና በላይ ሲሆን ነው፡፡የላይኛው ወይም የስረኛው አንዱ ከተጠቀሰው አሀዝ በላይ ከሆነ ከፍተኛ ደም ግፊት አለ ለማለት በቂ ነው፡፡የግድ ሁለቱም ከፍተኛ እንዲሆን አይጠበቅም፡፡ትክክለኛው የደም ግፊት መጠን የላይኛው ከ90-140 ሲሆን የታችኛው ከ60-90 ነው፡፡ነገር ግን ከ130 በ80 በታች ቢሆን ለጤንነት የተሻለ ነው፡፡በየዓመቱ በዓለማችን እስከ 7.6 ሚሊዮን ሰዎች በከፍተኛ ደም ግፊት የተነሳ ህይወታቸውን ያጣሉ፡፡92 ሚሊዮን የሚሆኑት ደግሞ ለአካል ጉዳት ይዳረጋሉ፡፡ስርጭቱን ስናይ ከሀገር ሀገርና ከጎሳ ጎሳ ይለያያል፡፡
በምዕራቡ የዓለም ክፍል ስርጭቱ ከፍተኛ ሲሆን በታዳጊ ሀገሮችም ከአኗኗር ዘይቤ መለወጥ ጋር ተያይዞ ችግሩ እያንሰራራ ይገኛል፡፡በተጨማሪም የሚሰጠው ህክምና አናሳ በመሆኑ እየደረሰ ያለው ጉዳት በታዳጊ ሀገራት ላይ ያመዝናል፡፡
ለከፍተኛ ደም ግፊት የሚያጋልጡ ነገሮች ምንድን ናቸው?
ዘጠና በመቶ የሚሆነው ከፍተኛ የደም ግፊት ዋና መንስኤው የማይታወቅ ሲሆን ቀሪው በኩላሊት ህመምና በሌሎች የተለያዩ ህመሞች ምክንያት ሊመጣ ይችላል፡፡ከፍተኛ የደም ግፊት የመያዝ እድልን ከሚጨምሩ ችግሮች መካከል በቤተሰብ ውስጥ ከፍተኛ ደም ግፊት ያለበት ሰው ካለ፤ ለምሳሌ ወላጆቹ ከፍተኛ ግፊት ካለባቸው ከ15-30% የመያዝ እድል ይኖረዋል፣ እድሜ ሲጨምር በከፍተኛ ደም ግፊት የመያዝ እድል ይጨምራል፡፡ከመጠን በላይ ክብደት ወይም የውፍረት በሽታ፣ አልኮል አብዝቶ መጠጣት፣ ሲጋራ ማጨስ፣ ጨው አብዝቶ መመገብ፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አለማድረግ፣ በስነ-ልቦናዊ ወይም ማህበራዊ ችግሮች የሚፈጠር ከፍተኛ ጭንቀትና ውጥረት፣ ስኳር ህመም እና በደም ውስጥ ከፍተኛ የኮሊስትሮል መጠን መኖርም ለከፍተኛ ደም ግፊት ከሚያጋልጡ ችግሮች ይገኙበታል፡፡
የከፍተኛ የደም ግፊት ምልክቶች
ከፍተኛ ደም ግፊት “ያለምልክት ገዳይ” (“silent killer”) በመባል ይታወቃል፡፡ምንም ምልክት ሳያሳይ ለረጅም ጊዜ ከችግሩ ጋር በመቆየት ልብ ድካም፣ ኩላሊት ድካም፣ የእግር መመርቀዝ፣ አይነ ስውርነትና ድንገተኛ የሆነ ደም መፍሰስ አንጐል ውስጥ ሊከሰት ይችላል፡፡አንዳንድ በጣም ከፍተኛ ደም ግፊት ባላቸው ሰዎች ላይ ራስ ምታት፣ ማዞር፣ ልብ መምታትና የድካም ስሜት ምልክቶች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡
ከፍተኛ ደም ግፊት የሚያመጣቸው ውስብስብ የጤና ጠንቆች፡–
ልብ ድካም፡- ይህ ከፍተኛ ደም ግፊት ባለባቸው ሰዎች ላይ ዋነኛው የሞት መንስኤ ነው፡፡ከፍተኛ ደም ግፊት ልብ ላይ ስራ በመጨመር የልብ ጡንቻዎችን በማወፈር፣ የልብ ደም ስሮችን በማጥበብና በተጨማሪም የልብ ምት ስርአትን በማዛባት ለልብ ድካም ይዳርጋል፡፡
አንጎል ውስጥ ድንገተኛ የደም መፍሰስ/Stroke/፡- ይህ ሁለተኛው የሞት መንስኤ ሲሆን አንጎል ውስጥ ያሉ ደም ስሮች በከፍተኛ ደም ግፊት ከተጎዱ በኋላ ድንገት ሲፈነዱ የሚከሰት የደም መፍሰስ ነው፡፡
እግር መመርቀዝና መቆረጥ አደጋ፡- ይህ ወደ እግር የሚሄዱትን ደም ስሮች በማጥበብና በመዝጋት የተነሳ የሚከሰት ነው፡፡የኩላሊት ድክመትና ዓይነ ስውርነት በከፍተኛ ደም ግፊት ሳቢያ የሚከሰቱ የጤና ጠንቆች ናቸው፡፡
የከፍተኛ ደም ግፊት ህክምናና መከላከያ መንገዶች
የህክምናው አላማ ግፊትን ከ140 በ90 በታች ማድረግ ሲሆን ስኳርና ኩላሊት ህመም ላለባቸው ከ130 በ80 በታች ዝቅ ማድረግ ነው፡፡
የአኗኗር ዘዬን ማሻሻል፡- (ለተጨማሪ መረጃ ጤናማ የአመጋገብ ስርዓትን ይመልከቱ)የሰውነት ክብደት መቀነስ፡- BMI ከ25 በታች እንዲሆን ይመከራል፡፡ ስለዚህ የአመጋገብ ስርዓታችንን በመቀየርና የአካል እንቅስቃሴ በማድረግ ክብደትን ማስተካከል ያስፈልጋል፡፡
ጨውን ከምግብ ውስጥ መቀነስ፡- በቀን የምንወስደው የጨው መጠን ከ6 ግራም በታች መሆን አለበት፤ አልኮል መጠጥን መቀነስ፤ ሲጋራ ማጨስን ማቆም፤ ፍራፍሬ፣ አትክልትና ፋይበር ምግቦችን አዘውትሮ መመገብ፤ ስብን ከምግባችን ውስጥ መቀነስ፤ አዘውትሮ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ፡- ቢያንስ በቀን ለ30 ደቂቃ ፈጣን የእግር ጉዞ ማድረግ፤በሀኪም የሚታዘዙ መድሃኒቶችን ሳያቋርጡ በአግባቡ መውሰድ፤ የአኗኗር ዘያቸውን በማሻሻል (lifestyle modification) ግፊታቸውን ከ140 በ90 በታች ማውረድ ያልቻሉ ሰዎች መድሃኒቱን እንዲጀምሩ ይመከራል፡፡የመድሃኒቱ አይነት የሚመረጠው የእያንዳንዱን ታማሚ እድሜ፣ የግፊት ደረጃ፣ የመድሃኒቱን ዋጋ፣ አወሳሰድ፣ የጎንዮሽ ጉዳት እንዲሁም አጠቃላይ የታካሚውን የጤና ሁኔታ በማገናዘብ ነው፡፡
በብዛት የምንጠቀማቸው መድሃኒቶች
ሄድሮክሎሮታያዛይድ፣ ፍሮሴማይድ (ላሲክስ)፣ ስፖይሮን ላክቶን፣ አሚሎራይድ፣ ንፊዲፒን፣ ሚታይልዶፓ፣ ካፕቶፕሪል፣ ሀይድራላዚን፣ አትኖሎል፣ ሜቶፕሮሎል፣ ፕሮፖራኖሎል፣ ለቤቴሎል፣ ካርዴሎል፣ ኢናላፕሪል ተጠቃሽ ናቸው ።
ምንጭ፦ከኢትዮ ሀኪምቤት
አዲስ ዘመን ታኅሳስ 8/2013