በጋዜጣው ሪፖርተር
የአሜሪካ ምግብና መድኃኒት አስተዳደር የፋይዘር/ባዮንቴክ የኮሮናቫይረስ ክትባት ለአስቸኳይ ጊዜ አገልግሎት እንዲውል ፈቃድ መስጠቱን ቢቢሲ ዘግቧል። በዘገባው እንደተመላከተውም፣ ተቋሙ እንዳለው ክትባቱ ጥቅም ላይ እንዲውል ፈቃድ መስጠቱ እስካሁን በአሜሪካ ውስጥ ከ295 ሺህ በላይ ሰዎችን ለሞት የዳረገውን ወረርሽኝ በመከላከል በኩል “ታላቅ እርምጃ” እንደሆነ አመልክቷል።
በዘገባው እንደተመላከተው፣ በሽታውን በመከላከል በኩል እስከ 95 በመቶ ድረስ አስተማማኝ እንደሆነ የተነገረለት ክትባቱ ደኅንነቱ የተጠበቀና ውጤታማ መሆኑን የምግብና መድኃኒት አስተዳደር መስክሯል። የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕም የመጀመሪያው የኮሮና ቫይረስ መከላከያ ክትባት “ከ24 ሰዓት ባነሰ ጊዜ ውስጥ መስጠት ይጀመራል” ብለዋል።
ፕሬዚዳንቱ ይሄን ባሉበት መልዕክታቸውም፣ “አገራችን በህክምናው ዘርፍ ታላቅ የሚባል እመርታን አስመዝግባለች” በማለት የተናገሩት ፕሬዚዳንት ትራምፕ “በዘጠኝ ወራት ውስጥ ብቻ ውጤታማና ደኅንነቱ የተጠበቀ ክትባት መስራት ችለናል” ብለዋል።
የአሜሪካ ምግብና መድኃኒት አስተዳደር አርብ ምሽት ለክትባቱ ፈቃድ ከመስጠቱ ቀደም ብሎ ከፕሬዚዳንት ትራምፕ አስተዳደር በኩል ክትባቱ ጥቅም ላይ እንዲውል ፈቃድ እንዲሰጥ ከፍተኛ ጫና ሲደረግበት ቆይቷል። የድርጅቱ ዋና ኃላፊ ስቴፈን ሃህን “ሐሰት ነው” ቢሉም ክትባቱ በቶሎ ለአስቸኳይ ጊዜ ግልጋሎት እንዲውል
እንዲያጸድቁት ወይም ኃላፊነታቸውን እንዲለቁ በዋይት ሐውስ መጠየቃቸውን የአሜሪካ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
የአሜሪካ ጤናና የሰብዓዊ አገልግሎት ኃላፊ አሌክስ አዛር ትናንት እንዳሳወቁት፤ መጠነ ሰፊ የኮሮና ቫይረስ ክትባት ፕሮግራም ሰኞ ወይም ማክሰኞ ለማስጀመር መስሪያ ቤታቸው ከፋይዘር ጋር ይሰራል ብለዋል።
ይህ የፋይዘር ክትባት አስካሁን ድረስ በዩናይትድ ኪንግደም፣ በካናዳ፣ በባህሬንና በሳዑዲ ዓረቢያ ፈቃድ አግኝቷል። በእነዚህ አገራት ውስጥ እንደታቀደው በአሜሪካም ክትባቱ በቀዳሚነት ለአዛውቶች፣ ለጤና ሠራተኞችና ለአደጋ ጊዜ ሠራተኞች የሚሰጥ ይሆናል።
ከታህሳስ ወር ጀምሮ በአሜሪካ ውስጥ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ሰበብ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ መጠን ካለፈው ወር ጀምሮ ጨምሯል። ባለፈው ረቡዕ ብቻ ከሦስት ሺህ በላይ ሰዎች በበሽታው ሳቢያ እንደሞቱ የተነገረ ሲሆን፤ ይህ የኮሮና ቫይረስ ሞት አኃዝ ከፍተኛነቱ ለአሜሪካ ብቻ ሳይሆን በዓለም ከፍተኛው ተብሎ ተመዝግቧል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 5/2013