ዓበጋዜጣው ሪፖርተር
የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመግታት የተወሰዱ እርምጃዎች ከዚህ ቀደም ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ የአየር ብክለት እንዲቀንስ ማገዛቸው ተገለጸ። በዚህ ምክንያትም ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ የካርቦንዳይኦክሳይድ ልቀት የቀነሰው ዘንድሮ መሆኑን ቢቢሲ ዘግቧል።
እንደ ዘገባው ከሆነ፣ የልቀት መጠኑ በሰባት በመቶ የቀነሰ ሲሆን፤ ዝቅተኛ የካርቦንዳይኦክሳይድ ልቀት ያስመዘገቡት ፈረንሳይ እና ዩናይትድ ኪንግደም ናቸው። በዚህ መልኩ የአየር ብክለትን መቀነስ ምክንያት የሆነው ደግሞ የወረርሽኙን ሁለተኛ ዙር ስርጭት ተከትሎ የእንቅስቃሴ ገደብ በመጣላቸው ነው። ይሁን እንጂ ከወረርሽኙ ያገገመችው ቻይና በቀጣዩ ዓመት የካርቦንዳይኦክሳይድ ልቀቷ እንደሚጨምር ተገልጿል።
“ግሎባል ካርቦን ፕሮጀክት” እንዳለው፤ ዘንድሮ የካርቦን ልቀት ወደ 2ነጥብ4 ቢሊዮን ቶን ወርዷል። እአአ 2009 ላይ የምጣኔ ሀብት ቀውስ ሲከሰት የካርቦን ልቀት የቀነሰው በግማሽ ብቻ ነበር። በያዝነው ዓመት አሜሪካ እና አውሮፓ 12 በመቶ ቀንሰዋል።
በዚህም ከፍተኛ መቀነስ የተስተዋለው በፈረንሳይ ሲሆን፤ የቀነሰውም በ15 በመቶ ነው። በዩናይትድ ኪንግደም ደግሞ 13 በመቶ ሆኖ ተመዝግቧል። በዚህ ላይ አስተያየታቸውን የሰጡት የዩናይትድ ኪንግደሙ ፕሮፌሰር ኮርኒ ለኩዌሬ
“የሁለቱ አገሮች የካርቦን ልቀት ዋነኛ ምንጭ የመጓጓዣ ዘርፍ ነው፤ ኢንዱስትሪ እና ሌሎች ዘርፎች በሁለተኛ ደረጃ ይገኛሉ” ይላሉ።
በመላው ዓለም በወረርሽኙ ሳቢያ የበረራ ቁጥር በእጅጉ ቀንሷል። ይህም ለካርቦን ልቀት መቀነስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው። ከዚህ ዘርፍ የሚመዘገበው የካርቦን ልቀት 40 በመቶ ሲሆን፤ ይህም ከአምናው ያንሳል።
ስለዘንድሮው የካርቦን ልቀት መጠን ጥናት የሠሩት ባለሙያዎች እንደሚሉት፤ ቻይና በዚህ ዓመት የካርቦን ልቀቷን በ1ነጥብ7 በመቶ ቀንሳለች። ሆኖም ባለፉት ጥቂት ወራት የወረርሽኙን ስርጭት በተሻለ ሁኔታ መቆጣጠሯ የካርቦን ልቀት ዳግመኛ እንዲጨምር ምክንያት ሆኗል።
የጥናቱ ተሳታፊ ጃን አይቨር ኮርስባክን እንዳሉት፤ እኤአ በ2020 መጨረሻ ላይ የቻይና የካርቦን ልቀት ከ2019 ጋር ተቀራራቢ ነው። “እንዲያውም አንዳንድ መላ ምቶች እንደሚጠቁሙት የቻይና የካርቦን ልቀት እየጨመረ ሳይመጣ አይቀርም” ብለዋል አጥኚው።
የፓሪስ የአየር ንብረት ስምምነት ላይ የተቀመጠው ግብ እንዲሳካ ለቀጣይ 10 ዓመታት፤ በየዓመቱ ሁለት ቢሊዮን ቶን የካርቦን ልቀት መቀነስ እንዳለበት ባለሙያዎች ይናገራሉ። ፕሮፌሰር ፒዬሬ ፍሪድልግስተን እንደሚሉት፤ የዓለም አየር ንብረት በአስተማማኝ ሁኔታ ሊስተካከል የሚችለው የካርቦን ልቀት ዜሮ ሲደርስ ነው።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 5/2013