ከመምህር አሰምሬ ሣህሉ
ሒትለር በ1933 ዓ.ምህረት በዲሞክራሲያዊ ምርጫ ወደ ሥልጣን መምጣቱን ታሪከ-ጀርመን ዘግቦታል። በወቅቱ ዓለም በከፍተኛ የኢኮኖሚ ድቀት (The great Economic depression) የተመታችበት እና በተለይ አውሮፓውያን ገንዘባቸው የመግዛት አቅሙ ተሸመድምዶ 100 ግራም ስኳር መግዛት የሚሻ ሸማች ገንዘብ በዘንቢል አጭቆ ለመውጣት የሚገደድበትና ከአራትና አምስት ዓመት በፊት 60 እና 70 ሺህ የጀርመን ማርክ ወይም የፈረንሳይ ፍራንክ ይዞ ገበያ የወጣ ሰው መሬት ሸምቶ፣ መኪና ገዝቶ በዚያ ላይ የቤት እቃውን አጭቆ የሚመለስባት ሀገር በሚያስደንቅ ሁናቴ ያንኑ ያህል ብር ከቆዳ የተሰራ ቦርሳ ለመግዛት አቅም ያጣበትና ባንኮችም “ውድ ደንበኛችን፣ በባንካችን የነበረው ገንዘብዎ በአሁኑ የሸመታ ዋጋ ጥቅም ስለሌለው ከይቅርታ ጋር እንዲያወጡ እንጠብቅዎታለን፤” ብለው ማስታወሻ ወደሚጽፉበት ወቅት ላይ የተመለሱበት ጊዜ ነበረ።
ይህ ድቀት ነበረ፤ ጀርመናውያንን መፍትሔ ፈላጊ ሰው፣ ክብር መላሽ ጀግና ሲፈልጉ ሒትለርን የመሠለ በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ለሀገሩ የተዋጋ ወታደርና፣ ሀገሩ ኪሳራ ስለገባችበት ጉዳይ የሚቆጭና “ዘራችን ከሁሉም በላይ” በሚል መፈክር ዙሪያ ወቅቱ ፈቀደለትና፤ ሚሊዮኖችን ማሰለፍ የቻለ ሰው ተገኘ።
እናም ወደ ሥልጣን እርካብ ያላንዳች ማንገራገር ወጣ፤ ተቀበሉትም ፤ ከዚያም አንዳንድ ለእርሱ ፍላጎትና አሠራር የማይመቹ ድንጋጌዎችን በማስሻር፣ በሀገሪቱ ቡንደስታግ ( ፓርላማ) ሆነ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ሙሉ ስልጣን በእጁ የሚያስጨብጠውን አናቅፆች እንዲታከሉ በማድረግ ገነነበት። ለዚህም እንዲረዱትም፤ ከሻይቤቱ ስብሰባ ዘመኑ ጀምሮ፣ ከጎኑ ያልጠፉትን ጓደኞቹንና አምላኪ እርሱ የሆኑ ጸሐፍትን በመሰብሰብ ወደ ድርጊት መርሐ-ግብሩ ዘለቀበት።
ጀርመንም፣ ናዚዝምን መመሪያዋ፣ ሒትለራዊ ሰንደቋን መገስገሻ ዒላማዋ በማድረግ ቀጠለች። ይህንንም ተግባሩን ለማስፈፀም ብርቱ ክንድ የሆኑ ግብረ-በላዎች አላጣም። ጥቂቶቹን የእርሱን የቅርብ ሰዎች ላስተዋውቃችሁና እንቀጥል።
ሔኔሪክ ሒምለር፣ ይህ ሰው ጀርመናዊ ሲሆን ለዕድገታችን ጠንቅ ናቸው፤ ተብለው የተፈረደባቸውንና የተወገዙትን አይሁዶች ሙሉ በሙሉ ከአውሮፓ በማጥራት፣ በታሪካችን “ግርማዊ” የሆነውን የጀርመኖችን ታሪክ እንጽፋለን፤ ያለ ሰው ነው።
ሬይንሐርድ ሄንድሪሽ፣ ልበ-ብረቱና የማይራራው በመባል የሚታወቀው የናዚ ፓርቲ አባል ነው። ይህ ሰው የመጀመሪያዎቹን ነፍሰ-ገዳይ ህዋሶች (ቡድኖች) በየሥፍራው ያደራጀ ሰው ነው። በዋናሴ የናዚ ጠቅላላ ጉባኤ ላይም፣ በስፋት ፀረ- አይሁድ ግድያውን ለማስፈፀም፣ በመልክ በመልክ ስውርና ግልፅ በሆነ መንገድ ያቀናጀና ያደራጀ ሰውም ነው፤ ግድያ መልክ ካለው።
ጆሴፍ ጎብልስ፡- የታወቀ፣ የፕሮፖጋንዳ ሰው፣ ነው። የሒትለር ልዩ ረዳትና የፓርቲው ልሳን መቃኛ ነው። አንዳንዴም ጎብልስ ሒትለር፤ ሒትለር ጎብልስ ነው፤ ሲሉ የልሳን ስምምነት እንዳላቸው ይነገርለታል።
ሦስተኛው ራይኽ በመባል በናዚዎች ታሪክን የማደስ በሚሉት ቅስቀሳቸው፣ ዋና አስኳል ጉዳይ ጥራታችንን ለማስጠበቅ “ቆሻሻዎቹን አይሁዶች” ማስወገድ በሚል መርህ ነበረ፤ የሚሰሩት የሚያሰሩትም። መቼም ግድያ ሥራ ከተባለ።
አዶልፍ ኤክማን፡- ሁሉን የግድያና የፍጅት ሰነድ ያዘጋጀና ያደራጀ ሰው ነው። ከከተሞች ከመሰብሰብ ጀምሮ እስከ መጓጓዝ እና ወደግድያ ማዕከሉ እስከማምጣት የሚሰራውን የሎጂስቲክ ሥራዎች የሚያቀናብርና መፈፀማቸውን የሚያረጋግጥ ናዚ ነበረ። እና እነዚህ ፍጅቶች፣ የሚፈፀሙባቸውም ስፍራዎች እንደ ትሬብሊንካ፣ ቡከንዋልድ፣ ዳቻው፣ ኦሽዊትዝ፣ ሶቢቦርና ሌሎች ስፍራዎችን ያዘጋጀ ሰው ነው።
ታሪክ እነዚህን እውነቶች ዘግቦ አኑሮልናል። በእነዚህ ሰዎች አማካይነት የተጀመረው ጭፍጨፋ እና ግድያ አይሁድ ሆነው ከመወለዳቸውና በምድር ላይ ከመኖራቸው ውጭ የተገኘባቸው ወንጀል ባይኖርም አንድ ቀን እንደተጀመረ ያም የፍፃሜ ቀን ደረሰና በ1945 ዓ.ም. ግንቦት ወር መጀመሪያ አንድ ቀን ላይ ፍፃሜ አገኘ።
በዚህ መሐል ያለው ስቃይና የእያንዳንዱ ቀን ሰቀቀን ተነግሮ በማያልቅ ግፍ የተሞላ፤ ዘላለማዊ የመሰለና ማለቂያው የማይታወቅ ቢመስልም አለቀና ታሪክ ዘገበው።
የእነዚያ ናዚዎች ፍፃሜስ ምን መሰለ ትሉ ይሆናል። ሒትለር ራሱን ልጁንና ባለቤቱን ከበርሊን የምድር ቤት ውስጥ በማኖር ሚስትና ልጁን በቅድሚያ ገድሎ፣ በኋላም ሳይናይድ የውሻ መግደያ መርዙን ለራሱ ከዋጠ በኋላ ጭንቅላቱን በጥይት በመበርቀስ ገድሎ ነው፤ የሞተው።
ጆሴፍ ጎብልስ ሚስቱንና ስድስት ልጆቹን ከገደለ በኋላ ራሱን ገደለ።
ሒምለር ለፍርድ ከመቅረቡ በፊት ለመኖር እንደጓጓና ሲሽለኮለክ የተደረሰበት በመሰለው አንድ ቀን ፣ ራሱን በሣይናይድ መርዝ ገደለና ሞቶ ተገኘ። አዶልፍ ኤክማን፣ ራሱን ቀይሮ ሪካርዶ ክሌሜንት በሚል ስም፣ አርጀንቲና ውስጥ በውሸት ፓስፖርት፣ በውሸት ስም፣ በውሸት አድራሻ ለመኖር ሞክሮ በእሥራኤል የስለላ ድርጅት ድንቅ ጥረት ከላቲን አሜሪካ ከ15 ዓመት በኋላ የተያዘ የሰይጣን ቁራጭ ነው። አንድ ቀን እንደምያዝና፣ ስያዝ ሁሉን አውቄና ራሴን አሳምኜ ነበረ፤ ከማለት ውጭ ምንም አላለም ። ድሮስ ምን ሊል ይችላል።
ሪቻርድ ሐይድሪሽም፣ በቼኮዝሎቫኪያ ጎዳና ላይ መኪናውን ወደ አንድ ጥግ ካቆመ በኋላ የሳይናይድ መርዙን በመዋጥ ሞቶ ነው፤ የተገኘው። አስከሬኑን ለማንሳት ሰው እስኪጠየፍ ድረስ ሁለመናው ተብሰክስኮ ነበረ። ሌሎቹም ነፍሰ ገዳይ ናዚዎች፣ አንድ በአንድ ተይዘው በኑረምበርግ ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት ከቀረቡ በኋላ የእጅ እጃቸውን አግኝተዋል።
ሌላው ቀርቶ እርሱን ያገዘውና ኢትዮጵያን ወርሮ የተሳለቀው ፋሺስቱ ቤኔቶ ሞሶሊኒም በገዛ ህዝቡ ሚላኖ ላይ ተይዞ ቁልቁል ከሴት ወዳጁ ጋር ነው፤ በአደባባይ የተሰቀለው። ኢትዮጵያን የነካ ሆነና፤ የዚህ የዋህ ህዝብ ጸሎትና ልመና ያልጣለው ጠላት የለም። ፋሺዝምና ናዚዝም በዓለም ታሪክ የጭካኔ መገለጫ ሆነው ከትውልድ እስከ ትውልድ እንዲገለፁ ሆኑና ቀሩ።
አስቀያሚና ጭካኔ የሞላው ግድያ በምድር ላይ ተፈጽሞ ሲገኝ ፋሺስትና ናዚ መባል ቅጽል ስም ሆነ። ታዲያ፣ የሒትለርንና የተባባሪዎቹን ፍፃሜ ያየ ማንኛውም ወገን፣ በሰው ልጅ ላይ ግፍንና አመፃን ከቶውንም አይፈፅምም።
ኢትዮጵያም በዚህ ጊዜ፣ እኒህን መሰል ድርጊቶች በሀገራችን የመፈፀማቸው እውነቶች በስፋት እየተገለጡና እየታዩ በመሆናቸው፣ ይህን ዘር ተኮር የናዚ መንፈስ እንዳይነሳ በመድፈቅ እርስ በእርሳችን የምንተሳሰብበትና የምንተጋገዝበት፣ ጥላቻንና መገፋፋትን አብዝተን በመኮነን የተሻለች ሀገር እንድትፈጠር ልንተጋ የሚገባበት ጊዜ ላይ ያለን ይመስለኛል።
ሲጀመር በጦርነት የተዳከመውን የኢትዮጵያ መንግሥት ጦር ገፍተው ወደሥልጣን የመጡት፣ የወቅቱ ሽምቅ ተዋጊዎች ካመጡት ይልቅ የመጡበት መንገድ እጅግ ዘግናኝ ስለነበረ፣ ያለፈው ግፋቸው እንዲሁ አላስቀምጥ ብሏቸው በሥልጣን ላይ የቆዩት ከመጡበት የግፍ መንገድ ባልተለየ ነበረ።
በሰይፍና ስለት መጥተዋልና፣ በዙፋኑ ላይ በሰይፍና ስለት ማፋጨት ቆይተው፣ አስለቅሰውና አስጨንቀው ለ27 ዓመታት ሲደመር ሦስት ዓመት በመቆየት ነው፤ ወደ ፍፃሜያቸው የገሰገሱት።
አንባቢው ደግሞ፣ በመገረም፣ “ፍፃሜ ደግሞ ምን ግስግሳ ያስፈልገዋል፣ ማደባየት መፍገምገም እንጂ፣” ብሎ ሊያስብ ይችላል፤ ይሁንናም ፍፃሜም የቆይታ ዘመንን ያህል አያዘግምም።
ከደደቢት እስከ መቀሌ አደባባይ ለመምጣት 15 ዓመት የፈጀባቸውን ያክል እና በስልጣን ላይ ለመውጣትና የደርግን ፍፃሜ ለማረጋገጥ ሦስት ዓመት ብቻ ከዚያም 27 የሰቆቃና የእብሪት ዓመታት ቢያሳልፉም፣ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ምናልባትም የማይነቃነቅ የሚመስለውን የብረትና የኩራት ወንበራቸውን በ15 ቀናት ጦርነት ነው፤ የኢትዮጵያ የመከላከያ ሠራዊት የተቆጣጠረው። ታዲያ 15 ቀናት ለ27 ዓመታት ንጉሥ ግስገሳ አይሆንምን?!!
እነርሱ ግን ሲገድሉ ሲያኮላሹና የኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያውያንን ዕጣ ፈንታ እንደ ከሸፈ ጥይት ሲያደነብሹ ቆይተው የቁልቁል ጉዟቸውን ተያይዘውታል። የሚያስገርመው ግን ወድቀውም ያስፈራሩናል፤ ተደቁሰውም ይገስሉብናል።
በነገራችን ላይ ከዱር አውሬዎች ሁሉ ምስኪኑ ግስላ ነው፤ ግስላን ለማደን የሚወጣ አዳኝ፣ ወደ እንስሳው መገኛ ዱር (ጎሬው) ከገባ በኋላ፣ በራሱ ቁመት ልክ ጉድጓድ ቆፍሮ ይቀመጥና፣ እንቅስቃሴውን በዓይኑ እየተቆጣጠረ ድምጽ በማውጣት ይረብሸዋል። ቀጥሎም ዘሎ ይገባና በጋሻው ጉድጓዱን ይሸፍንና ይቀመጣል፣ ከዚያ እንደምንም ያዘናጋና ታይቶት አበሳጭቶት ተመልሶ በመግባት ግስላውን አበሳጭቶ ይገድለዋል እንጂ፤ ራሱ ፊት ለፊት አይገጥመውም። እነዚህ አዳኝ ነን ባይ ስግብግቦች በማበሳጨት ሊያጎሳቁሉንና ሊረብሹን ይሞክሩ ይሆናል እንጂ የገጠማቸው ኃይል ከቶውንም አይችሉትም። እውነት ከዚህ ትሁት ከሆነ የኢትጵያውያን ሁሉ ጀግና ሠራዊት ጋር ነውና።
ለእነዚህ በናዚ መንፈስ ለሚመሩ ነፍሰ-ገዳይና አጥፊ የትህነግ አባላት ቀኑ መሽቶባቸዋል። የመሸበት “አሳድሩኝ” ብሎ አጉራህ ጠናኝ ይል ይሆናል እንጂ፤ ነገር እንደአፉ አይቀለውም። የእነርሱ ጎብልሶች የእነርሱ ሂምለሮች፣ የእነርሱ አዶልፍ ኤክማኖች ፍፃሜ እየተቃረበ ነው። ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን እጅግ ታግሰዋቸዋል። እጅግም ስለሕግ አግባብነትና ፍትሐዊነት ተንበርክከው ጠይቀዋቸዋል። ሕግ ያልገዛውን ርትኣዊ ነፃነት፣ ሃይል የግድ እንዲገዛው ካስገደዱም አይቀርላቸውም ።
ሲጨንቃቸው የፌዴራሊስት ኃይሎች ያለህ ተባበሩን፤ መሬት ስትጠባቸው የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ሆይ፣ ምነው ዝም አላችሁ? እኛ የለውጥ ሐዋሪያቶቻችሁ ሊያልቅልን ነውና ተለመኑን፤ በማለት ሲያላዝኑ ተሰምተዋል። ለመሆኑ ለየትኛው ሥነ-ምግባራዊ አስተዳደራችሁና ሰብዓዊነታችሁ ነው ጩኸቱ? ለመሆኑ ከእናንተ ጋር የምር ቡና የተጣጣና ቁርስ በመብቱ፣ የተቋረሰስ ማንነት በየትኛው የሀገሪቱ ክፍልስ ነው፤ የሚገኘው። ኧረ ሌላው ይቅርና፣ እናንተ በትግራይ ክልል ላሉ አናሳ ብሔረሰቦችስ እውቅናና ወንበር …. ድጋፍስ መቼ ሰጣችሁና ሌላውን የምትጣሩት፤ ወለፈንዶች!!
ነፃነት አስገኘንላቸው የሚባሉትን ምልምል ምስለኔዎቻችሁን አጀንዳ ሰጥታችሁ፤ ቃል አቀብላችሁ ለቃሉ እንኳን ቅርጽ እንዳታወጡለት፣ ግስ እንዳትገስሱ ብላችሁ “የእንትን ዞን” አስተዳዳሪን ጠርታችሁ በየኮሪደሩ በጥፊ ለምትጠፈጥፉት “ዲሞክራትነታችሁ” ነው፣ ድረሱልን የምትሉት…… ????!!! ። እነዚህ ሰዎች እኮ፣ የት አግኝተዋችሁ በጥፊ እንደሚወለውሏችሁ እንደሚያስቡ ሰዋዊ ግምትና ጥርጣሬ እንኳን የላችሁም ? ስም እንጥራ እንዴ…? ለተደብዳቢዎቹ ክብር ስንል ስማቸውን እንተወው እንጂ፤ ደብዳቢዎቹ የትህነግ እንደራሴዎች ሁሏንም ነገር ታውቋታላችሁ።
ዛሬ እንደ ተረቱ ነው፤ የሆነባችሁ። አደን አብረው ወጥተው አባት ጅብ፣ ልጆቹን አስቀምጦ ብቻውን ሲበላ የአህያው ባለቤት ደረሰበትና ሲፈራ ፣ “ልጄ ማንሾሎላ!” ብሎ አባት ጅብ ሲጣራ፣ “ምን ሰጠኸኝ ካንድ ጆሮ ሌላ” ፣ “ኧረ ልጄ መዝሩጥ…” ብሎ ደግሞ ሲጣራም “አባባ፣ እንደበላህ እሩጥ” እንዳለው ሆኖባችኋል።
እናም ኢትዮጵያን ብቻችሁን ግጣችኋልና፣ ኢትዮጵያን ያለበደሏ በድላችኋታልና፣ የኢትዮጵያን ልጆች በአመፃ ፈጅታችኋልና፤ የኢትዮጵያን ጎበዛዝት ቅጽል ስም በማውጣት ትምክህተኛ፣ ጠባብ፣ ተለጣፊና ተቸካይ፣ ህዝበኛና አድሃሪ በማለት አቆሽሻችኋቸዋልና፤ አሁን ተራው የእናንተ ነው፤ ተወግተን ብንተዋችሁም፣ ወግታችሁ እንቅልፍ ስላጣችሁና ስለተቅበዘበዛችሁ፣ የኢትዮጵያ አምላክ እጁን አንስቶባችኋል።
ወትሮውንም የነሒምለርና የነጎብልስ ፍፃሜ እንዳላማረ ሁሉ፣ የእናንተም ፍፃሜ እንደማያምር ሳይታለም የተፈታ ነው። አዛኝ፣ ደግና ከራሱ በላይ ለሌላው የሚጨነቀው የዋሁ የትግራይ ህዝብ፣ የእናንተ ቀንበር ከብዶበት፤ የእናንተ ጫማ ጨቁኖት እንጂ መቼውንም በዚያ ትሁትና እውነተኛ ማንነቱ፣ የምትገቡት ሆናችሁ አልነበረም፣ እጅግ ታንሱበታላችሁ። ዛሬ ጊዜው ተለውጧል፤ በዓለም ዙሪያ ያሉ የዚህ ህዝብም ልጆች ግፍና መከራ በቃን ብለዋል፤ በስሜ መነገዳችሁን አቁሙ ብለዋል። ኢትዮጵያውያን ከዓለም ዙሪያ ተሰባስበው የእናንተን መከረኛ አካሄድ ኮንነዋል።
መቼውንም ኩነኔ የማይሰማችሁና ጆሮም ልበ-ድፍንም ሆናችሁ እንጂ ተው ስትባሉ፣ ለዓመታት ኖራችኋል። ስታፌዙ ነበረ፤ ስትሳለቁ ነበረ፤ ስታሽካኩ ነበረ፤ አሁን ግን ጊዜው ተለወጠና ፌዝ ወደ ቁዘማ፣ ማሽካካት ወደመቁነጥነጥ፣ ትእቢት ወደውድቀት ተለውጠው ቦታ ተቀያየሩ። ማነህ የኛ ጎብልስ እስቲ ወጣ፣ ሂምለርም፣ ጆሴፍ ሜንግሌም፣ አዶልፍ ኤክማንም ወጣ ወጣ በሉና እንያችሁ ፤ አትሽኮርመሙ!!
በእናንተ በክፉዎቹ ክፉ ፍፃሜና ማጎንበስ አገራችን ቀና ትላለች፤ በእናንተ ተገቢ ቦታ መያዝ ምድራችን ትባረካለች፤ በተለይም አጣብቂኝ ውስጥ ወድቆ የነበረው የትግራይ ህዝብ ዕረፍትና ሰላም ይሆንለታል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 2/2013