ዋለልኝ አየለ
ከዛሬ 17 ዓመታት በፊት፤ በዚሁ ወር በዚሁ ሳምንት ነው፡፡ በአምባገነንነት ብቻ ሳይሆን በአሸባሪነትም ስማቸው በዓለም የናኘው የኢራቅ ፕሬዚዳንት ሳዳም ሁሴን እንደ ፍልፍል መሬት ምሰው የገቡበት ዋሻ በአሜሪካ ወታደሮች አሰሳ ተገኘ፡፡ እነሆ በዚሁ ወር በዚሁ ሳምንት በአገራችን ኢትዮጵያ ‹‹የደብረጽዮን ዋሻ›› የሚሉ ዜናዎችን ሰማን፡፡ የትግራይ ክልል ርዕሰ መስተዳድር የነበሩት ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል የሰሜን ዕዝን ከመንካታቸው በፊት የጦርነት አዋጅ የሚመስል ንግግር ሲያደርጉ ነበር፡፡ ከጦርነቱ በኋላ ደግሞ መሰረተ ልማቶችን ጨምሮ የራሳቸውን የአውሮፕላን ማረፊያ ሳይቀር እንዲጋይ አስደርገዋል፡፡
የሀገረ ኢራቅ ፕሬዚዳንት የነበሩት ሳዳም ሁሴን ከ600 በላይ በሚሆኑ የነዳጅ ጉድጓዶች ላይ እሳት በመልቀቅ አገራዊ ውድመት አድርሰዋል፡፡ ኩዌትን ወርረው የነበሩት የቀድሞው የኢራቅ መሪ ሳዳም ሁሴን በአገሪቱ ላይ መጠነ ሰፊ ጉዳት ማድረሳቸው ይነገራል፡፡ ኢራቅ ከኢራን ጋር ንብረት ደምሳሽና ሕዝብ ጨራሽ ጦርነቶችን አካሄደች:: የዘመኑ የኢራቅ ፕሬዚዳንት ሳዳም ሁሴን በነዳጅ ዘይት የምርት መጠንና ኮታ የተነሳ ከትንሿ ጐረቤታቸው ኩዌት ጋር አተካሮ ውስጥ የገቡት ወዲያውኑ ነበር፡፡
ኩዌት ከተቀመጠላት ኮታ በላይ ነዳጅ ለዓለም ገበያ እያቀረበች ነው ብለው በንዴት ጦፉ፡፡ ሳዳም ሌላም ሰበብ ፈጠሩ:: በድንበር አካባቢ ጉድጓዳችን ነዳጃችንን እየዘረፈች ነው ሲሉ ነገር ፍለጋውን ከፍ አደረጉት፡፡ ኩዌትን ‹‹ነብር አየኝ በይ›› በማለት ዛቱባት፡፡ ጦር ሰበቁባት፡፡ እንደዛቱትም አልቀሩም፤ ኩዌትን አጭር በሚባል ጊዜ ወርረው ያዟት፡፡ ሳዳም በዚህ ብቻ ሳይወሰኑ ኩዌትን 19ኛ ክፍለ ሃገሬ ነች ብለው ከኢራቅ መቀላቀላቸውን አወጁ፡፡ አብዛኛው ዓለም የሳዳምን ወረራ አወገዘው፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በፀጥታው ምክር ቤት በኩል ኢራቅ ያለ አንዳች ማንገራገር ኩዌትን ለቃ እንድትወጣ ወሰነ:: አስጠነቀቀ:: ሳዳም ሁሴን ክንዴን ሳልንተራስ እንዲህ አይነቱ ነገር በፍፁም የማይሞከር ነው ሲሉ ፎከሩ:: ዲፕሎማሲያዊ ተማፅኖውን ከቁብ አልጣፉትም፡፡ ከዓለም ዙሪያ ይደርስባቸው የነበረውን ውግዘት ከምንም አልቆጥር አሉ፡፡ አሜሪካ በተባበሩት መንግስታት ውሳኔ ታግዛና የበረከቱ የዓለማችንን አገሮች በአጋርነት አሰልፋ በበረሃው ማዕበል ዘመቻ ኩዌትን ነፃ ወደማውጣቱ ዘመቻ ገባች::
የበረሃው ማዕበል ዘመቻ ኩዌትን ወርሮ ይዞ በነበረው የኢራቅ ጦር ላይ ማዕበል ሆነበት፡፡ የኢራቅ ጦር ማዕበሉን መቋቋም ተሳነው፡፡ ሳይወድ በግዱ ኩዌትን ለቆ የሚወጣ መሆኑን በተረዳ ጊዜ ከ600 በላይ በሆኑት የነዳጅ ጉድጓዶቿ ላይ እሳት ለቀቀባቸው፡፡ ከቁጥጥር ውጭ ሆኖ የከረመው የድፍድፍ ነዳጅ ቃጠሎ ኩዌትን ብቻ ሳይሆን መላ ቀጣናውን በከባድ ጥቁር ጭስ ጭጋግ ሸፈነ፡፡
በተፈጥሮ አካባቢ ላይ ያደረሰው ብክለትም እጅግ ከፍተኛ ነበር ይባላል፡፡ ብዙዎችን ለመተንፈሻ አካል የጤና እክል ዳርጓል፡፡ ቃጠሎው ተጀምሮ እስኪያልቅ በየቀኑ 6 ሚሊዮን በርሜል ነዳጅ በላ፡፡ በገንዘብ ረገድ ኩዌትን አንድ ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ኪሳራ አደረሰባት:: ቃጠሎው ለአንድ ወር ሲዘልቅ የመጨረሻውን ጉድጓድ እሳት ማጥፋት የተቻለው ሳዳም ሁሴን ሲወገዱ ነው፡፡
እነሆ አምሳለ ሳዳም ሁሴን የሆነ የነደብረጽዮን ዋሻ ተገኘ፡፡ ድንቅ የሚያደርገው ደግሞ በፕሬዚዳንቱ ጽሕፈት ቤት ውስጥ መሆኑ ነው፡፡ በሳዳም ሁሴን ዋሻ አጃኢብ ያልነውን ይሄኛው ደግሞ ‹‹የባሰም አለ›› ያሰኛል:: የእነዚህ ሰዎች ዓላማ መጀመሪያውኑም ጦርነት ነበር ማለት ነው፡፡ የዚህ ዋሻ መገኘት ከሁለት ዓመት በፊት የሰማሁት አንድ አስገራሚ ገጠመኝ ትዝ አለኝ፡፡ በወቅቱ ነገሩን ለማመን በጣም ተቸግሬ ነበር፡፡ ሀሜት ነው ብዬ ነበር ያለፍኩት:: በፕሬዚዳንቱ ጽሕፈት ቤት እንዲህ አይነት ዋሻ ከተገኘ ግን ያንን የማላምንበት ምክንያት የለም፡፡ ለማንኛውም የሰማሁት ገጠመኝ እንዲህ ነበር፡፡
እዚሁ አዲስ አበባ ውስጥ ነው፡፡ ቤቱ መጠጥ ቤት ነው፡፡ በዚህ ቤት ውስጥ ያሉ አስተናጋጆችም ሆኑ ተጠቃሚዎች የህወሓት ሰዎች የሚያስቀምጧቸው የራሳቸው አካባቢ ሰዎች ናቸው፡፡ ይሄን ድርጊት አስተዋለው የተባለው ሰውም ከውጭ አገር የመጣ ስለሆነና ብዙ ነገር አያውቅም ተብሎ እንጂ ለሌሎች ሰዎች ወደ አካባቢው ዝር እንዲሉ አይፈቀድም፡፡ የተለመደውን የመዝናኛ አገልግሎት የሚሰጥ እንጂ ሌላ ምንም አይነት ምልክት የለውም፡፡ እንዲያው ባጋጣሚ የሚገባ ካለ ተብሎ ግን ወደዋናው ቤት ከመድረሱ በፊትለአይን በማይጋብዝ ቤት ውስጥ የመጠጥ አይነቶች ይሰቀላሉ፡፡
በመንገድ ለሚያልፉ ሰዎች የሚታየው አሮጌ ቆርቆሮና ሸራ ነገር ነው፡፡ ወደ ውስጡ የሚያስገባው መንገድም በቆሻሻ የተሞላ ነው፡፡ በዚያ ቆሻሻ መንገድና አሮጌ ሸራ ውስጥ ግን ቅንጡ መዝናኛ አለ፡፡ መዝናኛው ወደ መሬት ውስጥ ገብቶ የሚገኝ ነው፡፡ ቤቱም ለመጠጥና ለሚሰሩ የሴራ ሥራዎች ይውላል፡፡ እዚህ ቤት ውስጥ ጨዋታው በውስኪ እና በሻንጣ በተጠቀጠቁ ብሮች ነው፡፡ ያ ዳያስፖራ ሲገባ ለምን ዝም እንደተባለ እንግዲህ እነርሱ ይወቁት፡፡ በወቅቱ ወሬውን የሰማን ሰዎች የተጋነነ መሆኑ ገርሞን በውሸትነት ስለተረዳነው አጥብቆ ለመጠየቅም አልዳዳንም ነበር፡፡
እንግዲህ በመዝናኛ ቤት ውስጥ እንኳን እንዲህ አይነት ጉድጓድ ያስቆፍር የነበረ ሥርዓት አሁን በፕሬዚዳንቱ ጽሕፈት ቤት ውስጥ ምሽግ መገኘቱ ብዙም አይገርምም ማለት ነው፡፡ ከሁሉም ሥራዎቹ መረዳት የሚቻለው ግን ዝግጅቱ የጥፋት እንደነበር ነው:: መንግስት አልጀምርለት ሲል ራሱ ጀመረው እንጂ ዓላማው ጦርነት እንደነበር ሲያቅደው የኖረ ነው፡፡
በሳዳም ሁሴን ታሪክ ውስጥ እነዚያ ጥፋቶች በታሪክ እንደተሰነዱት ሁሉ በእነደብረጽዮን ታሪክ ውስጥም ይሄኛው ታሪክ ይመዘገባል፡፡
‹‹ከሁመራ በቅርብ ርቀት በምትገኘው ማይካድራ ጭፍጨፋ ሲፈፀም ስጋት ላይ ወድቀን ነበር›› ሲሉ የአካባቢው ነዋሪዎች ለተለያየ መገናኛ ብዙኃን ሲናገሩ ነበር፡፡ ከሁኔታው ተነስተው ቀድሞም ሥጋትና ጥርጣሬ ነበራቸው ማለት ነው፡፡
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን(ኢሰመኮ) ጥቅምት 30 ቀን 2013 ዓ.ም በማይካድራ ከተማ ነዋሪዎች ላይ የተፈጸመውን ጭፍጨፋ በማውገዝ፣ በሰብዓዊነት ላይ የተፈጸመ ወንጀል መሆኑን በግልጽ አሳውቋል፡፡ በተለይ የአማራ ብሔር ተወላጆች በብዛት በሚኖሩበት ልዩ ስሙ ‹‹ግንብ ሠፈር›› በሚባለው መንደር እስከ ወልቃይት ቦሌ ሠፈር ድረስ የሚገኙ ዜጎች፣ ግፍና ጭካኔ በተሞላበት መንገድ መጨፍጨፋቸውን ገልጿል፡፡
ከኅዳር 5 እስከ ህዳር 9 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ በማይካድራ ከተማ፣ በአብርሀጅራ፣ በሳንጃ፣ በዳንሻ፣ በሁመራና በጎንደር ከተሞች በጉዳዩ ላይ አደረግኩት ያለውን ምርመራና የደረሰበትን የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርት ማክሰኞ ኅዳር 15 ቀን 2013 ዓ.ም ይፋ አድርጓል::
ኢሰመኮ በጥቃቱ ሕይወታቸው ያለፈ፣ የአካልና የንብረት ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ብዛት ገና በትክክል ተጣርቶ ያልተረጋገጠ ቢሆንም፣ ከጥቃቱ በኋላ ከተቋቋመው የቀብር ኮሚቴ፣ ከምስክሮችና ከሌሎች የአካባቢው ምንጮች ሰበሰብኩት ባለው መረጃ መሠረት በትንሹ 600 ሰዎች እንደተገደሉና ትክክለኛው ቁጥር ሊያሻቅብ እንደሚችል ሪፖርት አስቀምጧል፡፡
የጥቃቱ ሰለባ የሆኑት ዜጎች በተለይም በሰፋፊ የሰሊጥና የማሽላ እርሻዎች የጉልበት ሥራ ለመሥራት በአብዛኛው ከአማራ ክልል፣ የተወሰኑት ደግሞ ከሌሎች አካባቢዎች የመጡ እንደሆነ ኮሚሽኑ በሪፖርቱ ገልጿል::
ጥቃቱ ከመከሰቱ ጥቂት ቀናት አስቀድሞ፣ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ወደ ማይካድራ ለመግባት ሲቃረብ፣ ሁሉም ከማይካድራ የሚያስወጡ ኬላዎች በአካባቢው አስተዳደር፣ በሚሊሻና በፖሊስ ኃይሎች በመዘጋጀታቸው፣ በመከላከያ ሠራዊት ተሸንፎ እየሸሸ የነበረው የትግራይ ሚሊሻና ልዩ ኃይል ያጠቃናል በሚል ሥጋት እነዚህ ወገኖች ሸሽተው ወደ በረሃው የእርሻ ቦታ ‹‹በረኸት›› ወደምትባል የሱዳን አዋሳኝ ከተማ ለመውጣት እንዳልቻሉ ሪፖርቱ አሳይቷል፡፡
በከተማው አራት ዋና ዋና መውጫዎች በተቋቋሙ ኬላዎች ላይ በተሰማሩ ሚሊሻና ‹‹ሳምሪ›› የሚባል የትግራይ ተወላጆች መደበኛ ያልሆነ የወጣቶች ቡድን ተመልሰው ወደ ቤታቸው እንዲገቡ መገደዳቸውን፣ የትግራይ ተወላጅ የሆኑና ያልሆኑ ሰዎችን ለመለየት መታወቂያ ካርድ እየተመለከቱ ማጣራት እንዳደረጉ በሪፖርቱ ተጠቅሷል፡፡
የዓይን ምስክሮችን ዋቢ አድርጎ በወጣው ሪፖርት ዓብይ ፀጋዬ የተባለን የአማራ ብሔር ተወላጅ ከቤቱ ፊት ለፊት በጥይት በመግደል፣ ቤቱንና አስከሬኑን በእሳት በማቃጠል ጥቃቱ እንደ ጀመረ ተገልጿል፡፡
ግለሰቡ በአንድ ወቅት በወታደርነትና በሚሊሻነት ሠርቶ ከአገልግሎት የተሰናበተ እንደሆነ፣ በቅርቡ በተፈጠረው የጦርነት ሥጋት በአካባቢው መስተዳድር ወደ ውትድርና አገልግሎት እንዲመለስ ተጠይቆ ፈቃደኛ አለመሆኑን ገልጾ ስለነበር በዚህ የተነሳ የጥቃት ዒላማ ሳይሆን እንዳልቀረ የአካባቢው ነዋሪዎች ማስረዳታቸው በሪፖርቱ ተካቷል፡፡
ይህንን የመጀመሪያ ክስተት ተከትሎ ‹‹ሳምሪ›› የሚባለው የወጣቶች ቡድን በአካባቢው ፖሊስና ሚሊሻ እየተደገፈ በየጎዳናውና ከቤት ቤት በመዘዋወር አማሮችንና ወልቃይቴዎች ያሏቸውን ሲቪል ሰዎች በከፍተኛ ግፍና ጭካኔ በዱላ በመደብደብ፣ በጩቤ በመውጋት፣ በገጀራና በፈራድ (ወይም ፋስ መጥረቢያ) በመምታትና በገመድ በማነቅ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ገድለዋል፣ ንብረት ዘርፈዋል፣ አውድመዋል ይላል የኮሚሽኑ ሪፖርት፡፡
‹‹ሳምሪ›› የሚባለው የወጣቶች ስብስብ በአንድ ቡድን በአማካይ ከ20 እስከ 30 ወጣቶች በመሆን፣ በየቡድኑ በግምት ከሦስት እስከ አራት በሚሆኑ መሣሪያ የታጠቁ ፖሊስና ሚሊሻዎች እየታጀቡ ጭፍጨፋውን ሲፈጽሙ፣ በየመንገዱ መታጠፊያዎች አድፍጠው ይጠባበቁ የነበሩት ሚሊሻዎችና ፖሊሶች ደግሞ ከጥቃቱ ለመሸሽ የሚሞክርን ሰው በተኩስ በመመለስ የአጥቂውን ቡድን ጭፍጨፋ በቀጥታ ይፈጽሙና ያስፈጽሙ እንደነበር ተገልጿል፡፡
የኢሰመኮ ሪፖርት ከሞቱት ሰዎች ብዛትና በአቅም ማነስ ምክንያት የቀብሩ ሥነ ሥርዓት ሦስት ቀናት መውሰዱን፣ ሰዎች በጅምላ መቀበራቸውን፣ እንዲሁም በምርመራ ቡድኑ ጉብኝት ወቅት ገና ያልተቀበሩ በመንገድ የወደቁ አስከሬኖችም እንዳሉም ያመለክታል፡፡
እንግዲህ ይሄ ሁሉ የጅምላ ጭፍጨፋ የተፈጸመው አሁን እየተፈለገ ባለው ወንጀለኛ ቡድን ነው፡፡ ይሄ ቡድን በደብረጽዮን የሚመራ ነው፤ ትዕዛዝ የሚሰጠው ነው:: ታዲያ ይሄ ከሳዳም ሁሴን ሥራዎች ቢበልጥ እንጂ ያንሳል? የአሸባሪዎች መጨረሻ ጉድጓድና ዋሻ ነው:: የሳዳም ሁሴን ዋሻ ተደብቆ አልቀረም፤ በወታደሮች ተይዟል፡፡ የደብረ ጽዮን ዋሻስ መጨረሻው ምን ይሆን? ወደፊት የምናየው ይሆናል!
አዲስ ዘመን ታህሳስ 1/2013