በቁምላቸው አበበ ይማም ( ሞሼ ዳያን )
fenote1971@gmail.com
ከሀዲውና የባንዳ ዲቃላው የትህነግ ገዥ ቡድን በ1968 ዓ.ም ባሰናዳው የርዕዮት ዓለም መርሀ ግብር / ማንፌስቶ / የአማራን ሕዝብንና ባህሉን በጠላትነት እንዲህ ይፈርጀዋል። “ጨቋኟ የአማራ ብሔርም ጭቆናዋን እስስካላቆመች ድረስ ህብረተሰባዊ እረፍት አታገኝም። የትግራይ ሕዝብ ብሔራዊ ትግል ጸረ አማራ ብሔራዊ ጭቆና ጸረ ኢምፔራሊዝም እንዲሁም ጸረ ንዑስ ከበርቴያዊ ጠጋኝ ለውጥ ነው።
ስለዚህ የአብዮታዊ ትግል ዓላማ ከባላባታዊ ሥርዓትና ከኢምፔራሊዝም ነጻ የሆነ የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክን ማቋቋም ይሆናል። አሁን ያለውን አሮጌና አድሃሪ የአማራ ባህል ደምስሶ በአዲስ አብዮታዊ ባህል መተካት የተህሐት/የህወሓት/ ዓላማ ነው። “በዓለማችን ከናዚው አዶልፍ ሒትለር ቀጥሎ አንድን ሕዝብ በጠላትነት የፈረጀ ፓርቲ ቢኖር ከሀዲው ትህነግ ሁለተኛው ነው። ሒትለር አይሁዶችን በጠላትነት ፈርጆ ፖለቲካዊ ሀቲቱን አዋቅሯል። አማራ የሚባል ገዥ መደብም ኖሮ እንደማያውቅ ልቡ እያወቀ።
ለመሆኑ ከሀዲው ትህነግ ለአማራ ሕዝብ እንዲህ ያለ ከልክ ያለፈ መሪር ጥላቻ እንዴት ሊኖረው ቻለ!? የሚለው ጥያቄ ጥናትና ምርምር የሚጠይቅ ቢሆንም በተደጋጋሚ የምንሰማቸው ምን አልባቶች ወይም መላምቶች መኖራቸው አይካድም ።
አንዳንድ ትግራዊ ልሒቃን አፄ ዮሐንስ የሀገራቸውን ዳር ድንበርና ሉዓላዊነት ለማስከበር ከደርቡሾች ጋር በጀግንነት ሲዋጉ መተማ ላይ መስዋዕት በመሆናቸው ዘውዱም ሆነ ዙፋኑ ከትግራይ ወደ ሸዋ መዛወሩ በታሪክ አጋጣሚ ሳይሆን ሆን ተብሎ ተዶልቶበትና ታቅዶ የተፈጸመ ደባ አድርገው መውሰዳቸው ለአማራ በጠላትነት መፈረጅ አንደ ሰበብ ይወሳል።
ሆኖም እንዲህ ባለ የዘውድ ሽኩቻ ገዥው መደብ እንጂ መላ ሕዝቡ እንደማይሳተፍ እየታወቀ ሕዝቡን በጠላትነት መፈረጅ ውሃ አያነሳም። ሁለተኛው ፋሽስቱ ጣሊያን ከፋፍሎ ለመግዛት ሲል አንዱን ብሔር በሌላው ብሔር እንዲሁም ክርስቲያኑን ከሙስሊሙ ያጋጭ፤ በጥርጣሬ እንዲታይ ያደርግ ስለነበር የትናንቱ ትህነግ ለአማራ ያለው ጥላቻ ከዚህ የሚመዘዝ ሊሆን ይችላል የሚሉ ወገኖች ሲኖሩ ሌሎች ደግሞ መለስ ዜናዊ፣ ቴዎድሮስ ሐጎስና ሌሎች የትህነግ መስራቾች አባቶች ለጣሊያን ያደሩ አስካሪዎች፣ ሹምባሾችና ባንዳዎች ስለነበሩ ከነጻነት በኋላ የበታችነት ስሜት እና ራሳቸውን እምነት የማይጣልበት ዜጋ አርገው ያዩ ስለነበር ለዚህ ሁሉ የሥነ ልቦና ቀውስ ራሳቸውን ተጠያቂ ማድረግ ሲገባቸው አማራውን ኃጢያት ተሸካሚ አድርገው ያቀርቡ ስለነበር፤ ይህን እየሰሙ ያደጉት ልጆቻቸው ደግሞ አሻሽለው የማንፌስቷቸው አካል አድርገው አሰፈሩት የሚሉ ወገኖች አሉ።
ሶስተኛው በትግራዋይ ዘንድ ቁጭትን ፈጥሮ ለትግል ለማነሳሳት ሲል አማራውንና ባህሉን በተለይ የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንን ለፖለቲካዊ ጥቅም ሲሉ በፈጠራ ሀቲት በጠላትነት ፈረጁት ሲሉ የሚሞግቱ አሉ። ያው የሶሻሊዝም ጠላት የአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝም እንደነበረው ማለት ነው። ይሁንና ባንዳው ትህነግ ለአማራ ሕዝብና ባህል የነበረው ጥላቻ ምን ያህል የመረረና የከፋ እንደነበረ ላስተዋል እንደኔ ላለ ሰው ግን ትህነግ አማራን በጠላትነት ከፈረጀባቸው ምክንያቶች ባሻገር ጥናትና ምርምር የሚጠይቅ ሆኖ ይሰማኛል።
አራተኛው ምክንያት ግን በባንዳው የትህነግ ስብስብ ተወልዶ የጎለመሰው የትንሽነት አባዜ /ኢንፌሬሪቲ ኮምፕሌክስ / አማራንና ባህሉን አእምርሮ እንዲጠላ አድርጎታል የሚሉ አሉ። አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ፣ “ በዓለም ላይ የሚጠላትን ሀገር መሪ ሆኖ ያስተዳደረ ብቸኛ ፓርቲ ህወሓት ነው።”
እንዳሉት፤ እንደ ከሀዲውና ባንዳው ትህነግ ሀገራችን ኢትዮጵያ የሚጠላ የለምና ከፍጥረቱ አንስቶ ይቺን ሀገር ለማፍረስና ለመበታተን ያልፈነቀለው ድንጋይ የለም። አማራን፣ ባህሉንና ኦርቶዶክስ አምርሮ የሚጠላው የኢትዮጵያዊነት አእማዶች ከቆሙባቸው መሰረቶች አንዱና ቀዳሚው ስለነበር ኢትዮጵያን ለመበታተን ይሄን መሰረት ቀድሞ የጥቃቱ ኢላማ አድርጎታል የሚለው መላምት ሚዛን የሚደፋ ሆኖ ይወሳል።
ባንዳው ትህነግ አገዛዝ ላይ በነበረባቸው 27 ዓመታትም ሆነ ከስልጣኑ በሕዝባዊ ተቃውሞና በለውጥ ኃይሉ ተፈንግሎ በመማፀኛ ከተማው በመሸገባቸው ከሁለት ዓመት ከመንፈቅ በላይም ሆነ በትጥቅ ትግል ላይ በነበረባቸው 17 ዓመታት በተለይ አማራን ኢላማ ያደረጉ ህልቁ መሳፍርት የሌላቸው ለማየት የሚዘገንኑ ለመስማት የሚሰቀጥጡ ጥቃቶችን ሰንዝሯል። ከ70ዎቹ መጀመሪያ አንስቶ በወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ ላይ የፈጸመው ጭፍጨፋ፣ ዘር ማጽዳትና ግፍ ይህ ጦርነት እስከተቀሰቀሰበት ድረስ የቀጠለ ሲሆን በጀግናው የአማራ ልዩ ኃይልና በመከላከያ ሰራዊት የሽንፈት ማቁን እስከተከናነበበት ዕለት ድረስ የቀጠለ ነበር።
ወልቃይቴዎች በማንነታቸው በግፍ ተገለዋል፣ ተሰቃይተዋል፣ ተደብድበዋል፣ ተግዘዋል፣ ታስረዋል። በቋንቋቸው እንደይናገሩ እንዳይማሩ ተደርገዋል። በቁማቸው ከአንገት በታች ተቀብረው ከብት ተነድቶባቸዋል ። ግህንብ በተሰኘ የምድር ውስጥ /አንደርግራውንድ / እስር ቤት ይሰቃዩ በመርዝ ይገደሉ፤ ይታፈኑና በዛው ጠፍተው ይቀሩ እንደነበር በሙሉቀን ተስፋው፣ “ የጥፋት ዘመን “ መፅሐፍ ተሰንዶ ይገኛል ።
መች ይህ ብቻ የወልቃይት ሴቶችን በትግራዋይ ወንዶች በግዳጅና በጠለፋ እየተወሰዱ እየተደፈሩ ማህበረሰቡን ከአካባቢው የማጽዳት ስራ / ኤትኒክ ክሌንሲግ / ሆን ተብሎ በዕቅድ ተሰርቷል ። የሚያሳዝነው ከሀዲው ትህነግ በወልቃይት ጠገዴ አማራዎች ላይ ግፍ ሲፈጽም የነበረው ከሱዳን ጋር እየተቀናጀ መሆኑ ነው።
ይህ የከሀዲዎችና የባንዳዎች ዲቃላ ወደ ገዥነት ከመጣ በማንፌስቶው መሰረት በኋላ አማራን ለማዳከም፣ ለማሸማቀቅ፣ አንገት ለማስደፋት፣ ለማደህየት፣ ቋንቋውን ለማኮስመን፣ ማህበራዊ ወረቱን /ሶሻል ካፒታል/ ለማክሰር፣ መሬቱን በመውረር፣ አማራን በተለይ ለማዳከምና ለመከፋፈል በሌሎች ክልሎች ያልተደረጉ የብሔረሰብ ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች መፍጠር፤ ከሽግግሩ ጀምሮ ፖለቲካዊ ውክልናና ተሳትፎ እንዳይኖረው በማድረግ፤ የአማራ ክልል በልጆቹ ሳይሆን እሱ በመደባቸውና አማራ ባልሆኑ ተላላኪዎች እንዲገዛ በማድረግ ቅስሙን ለመስበር ሌት ተቀን ሰርቷል ።
ከሀዲውና አማራ ጠል የሆነው ትህነግ አማራ በሌሎች ብሔሮች እንዲጠላ በጥርጣሬ እንዲታይ አቅዶ በስፋት ሰርቷል። እንደ ኦነግ ባሉ ተላላኪዎቹ ጥቃት እንዲፈጸምበት ስምሪት ሰጥቷል። ስፖንሰር አድርጓል። በዚህም በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ አማራዎች ተገለዋል። አካላቸው ጎድሏል። ተፈናቅለዋል። ከሀዲው ትህነግ አገዛዝ ላይ በነበረባቸው 27 የግፍ ዓመታት በበጀት ተደግፎ መዋቅራዊና ተቋማዊ በሆነ አግባብ በአማራ ሕዝብ ላይ ለማየት የሚዘገንን ለመስማት የሚሰቀጥጥ ጭፍጨፋ ፈጽሟል። አስፈጽሟል።
ከሽግግር መንግስቱ አንስቶ ከአገዛዝ እስከተፈነገለባቸው ዓመታት አማራ በመላው የሀገሪቱ ክፍል በማንነቱ እንዲጠቃና እንዲጨፈጨፍ አድርጓል። በምስራቅ ሐረርጌ በጋራ ሙለታ፣ በወተር፣ በበደኖና በድሬዳዋ፤ በምዕራብ ሀረርጌ በገለምሶ፤ በአሰቦት ገዳም፣ በአርሲ፣ በአርባ ጉጉ፣ በአጋሮ፣ በሸቤ፣ በጉራ ፈርዳ፣ በወለጋ፣ በኖኖ፣ በአማያ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በከማሺ፣ በመተከል፣ በአፋር እና በራሱ ክልል ዘርፈ ብዙ ጥቃት እንዲፈጸም አድርጓል።
በዚህ የተነሳም ከፍ ብዬ እንደገለጽሁት በበዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ተገድለዋል፣ አካለ ጎደሎ ሆነዋል፣ ተፈናቅለዋል፣ ተዘርፈዋል። ከለውጡ ወዲህ ደግሞ በዚህ ብሔር ላይ የሚፈጸመው ግግፍ ተባብሶ ቀጥሏል ። በሶማሌ ክልል በተለይ በጅግጅጋ፤ የአርቲስት ሀጫሉን ግድያ ተከትሎ፤ በቤኒሻንጉል ጉሙዝና በሌሎች የተፈጸሙ ጭፍጨፋዎችን በአብነት ማንሳት ይቻላል ። በሰሜን ዕዝም ሆነ በማይካድራ ንጹሐን ማንነትን መሰረት አድርጎ የተፈጸመው ጭፍጨፋም የከሀዲው ትህነግ የ47 ዓመታት የጸረ ኢትዮጵያና አማራ ፕሮጀክት አካል ነው።
በታላቁ ቅዱስ መፅሐፍ በማቲዎስ ወንጌል ምዕራፍ 27 ላይ ከቁጥር ሶስት እስከ 10 ላይ እየሱስ ክርስቶስን፤ “አስረውም ወሰዱት፥ ለገዢው ለጴንጤናዊው ጲላጦስም አሳልፈው ሰጡት። በዚያን ጊዜ አሳልፎ የሰጠው ይሁዳ እንደ ተፈረደበት አይቶ ተጸጸተ ሠላሳውንም ብር ለካህናት አለቆችና ለሽማግሎች መልሶ፦ ‘ንጹሕ ደም አሳልፌ በመስጠቴ በድያለሁ አለ።’ ‘እነርሱ ግን፦ እኛስ ምን አግዶን? አንተው ተጠንቀቅ አሉ። ብሩንም በቤተ መቅደስ ጥሎ ሄደና ታንቆ ሞተ።የካህናት አለቆችም ብሩን አንሥተው፦ ‘የደም ዋጋ ነውና ወደ መባ ልንጨምረው አልተፈቀደም አሉ።
‘ተማክረውም የሸክላ ሠሪውን መሬት ለእንግዶች መቃብር ገዙበት። ስለዚህም ያ መሬት በቋንቋቸው አኬልዳማ ተብሎ ተጠራ። እርሱም የደም መሬት ማለት ነው። በዳዊት አፍ የተናገረው የመጽሐፍ ቃል ይፈጸም ዘንድ ይገባ ነበር። በእኛዋ አኬልዳማ ማይካድራ ግን ቃልም ክህደትም አልነበረም ። አምላኩን ቀርቶ የከሀዲውን ትህነግ ካድሬ የመሸጥ ሀሳብ አልነበረም ። ማይካድራ አኬልዳማ /የደም መሬት/ የሆነችው በደም ዋጋ ስለተገዛች አይደለም።
አማራ መሆኑ በአባቶቹ እርስት እንደሁለተኛ ዜጋ በመኖሩ እንደወንጀል ተቆጥሮበት በግፍ ተጨፈጨፈ እንጂ ። ማይካድራስ የደም መሬት ሳትሆን የወልቃይቴዎች መሬት ነበረች ። ናትም ። ለመሆኑ የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪዎች፤ ዓለምአቀፍ ሚዲያው፤ የመንግስታቱ ድርጅት፤ ምዕራባውያን የተቀባበሏት የጦር ወንጀል፤ የዘር ማጥፋትና በሰብዓዊ ፍጡር ላይ የሚፈጸም ወንጀል የተከናወነባት መላው ኢትዮጵያዊ ከቤተሰቡ አባል እንዳንዱ በቀላሉ የሚጠራት የደም መሬቷ ማይካድራ ማን ናት!?
ማይካድራ ከተማ በትግራይ ክልል በምዕራባዊ ዞን በሃፍታ ሁመራ ወረዳ የምትገኝ የከተማ አስተዳደር ናት። ከተማዋ ከሁመራ ከተማ በስተደቡብ በ30 ኪ.ሜ. ርቀት ላይ እንዲሁም ከምድረ ገነት ከተማ (ወይም አብዱራፊ በመባል የምትታወቅ) ደግሞ በ60 ኪ.ሜ. ርቀት በስተሰሜን አቅጣጫ ላይ ትገኛለች። በከተማዋ የትግራይ፣ የወልቃይትና የአማራ ተወላጆች እንዲሁም የሌሎች ብሔረሰብ ተወላጆችን ጨምሮ ከ45 እስከ 50 ሺህ የሚገመት ሕዝብ ይኖራል።
በወልቃይት የተወለዱ ወይም ለረጅም ጊዜ የኖሩ የአማራ ተወላጆች በአካባቢው በተለምዶ ወልቃይቴዎች በሚል ስያሜ ይጠራሉ ። ይህ መጠሪያቸው ወንጀል ሆኑ ከ1972 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ማይካድራው ዘግናኝ ጭፍጨፋ ድረስ ግፍ ተፈራርቆባቸዋል።
በማይካድራ ከተማ ነዋሪና ለቀን ስራ ከክልሉ አጎራባች ዞኖቸ በመጡ አማራዎችበተፈጸመው ግፍ ቢያንስ 600 መገደላቸውንና ቁጥሩም ከዚህ እንደሚበልጥ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ያወጣው ሪፖርት ይፋ አድርጓል። ከዚህ ቀደም ብሎ የመንግስታቱ ድርጅት በማይካድራ የጦር ወንጀል ሳይፈጸም እንዳልቀረ የገለጸ ሲሆን አመነስቲ ኢንተርናሽናልም የዘር ማጥፋት ወንጀል ሳይፈጸም እንዳልቀረ የሚያመለክቱ መረጃዎች ማግኘቱቱን ጠቁሟል። ከሁለት ሳምንት በፊት በትግራይ ክልል ምዕራባዊ ክፍል በምትገኘው የማይካድራ ከተማ የተፈጸመው ጥቃት በአካባቢው መስተዳድር የጸጥታ መዋቅርና ‘ሳምሪ’ በተባለ ኢ-መደበኛ የወጣቶች ቡድን የተፈጸመ ነው።
የአካባቢው መስተዳድርና ‘ሳምሪ’ በተባለው ቡድን የተፈጸመው ጥቃት፤ ግድያ፣ ጉዳትና ውድመት ጠቅላላ ድርጊቱና ውጤቱ” ግፍና ጭካኔ የተሞላበት በሰላማዊ ሰዎች ላይ የተፈጸመ የጭፍጨፋ ወንጀል” ነው ። ኮሚሽኑ ይህ ከፍተኛ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት “በሰብአዊነት ላይ የተፈጸመ ወንጀል እና የጦር ወንጀል ሊሆን እንደሚችል” ለዚህም ኢሰመኮ ዝርዝር ማስረጃዎቹን እና ወንጀሉን የሚያቋቁሙትን የሕግና የፍሬ ነገር ትንተና በሙሉ ሪፖርቱ ላይ በዝርዝር አጣርቶ የሚያቀርብ መሆኑን አሳውቋል። በማይካድራ የነበረው የሚሊሽያና የፖሊስ መዋቅር የፌዴራሉ ሠራዊትን እርምጃ ሸሽቶ አካባቢውን ለቆ ከመውጣቱ በፊት “ሳምሪ” ከተባለ መደበኛ ያልሆነ የትግራይ ወጣቶች ቡድን ጋር በመተባበር በተለይ “አማሮችና ወልቃይቴዎች” ያሏቸው በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጥቃት” መፈጸማቸውን አመልክቷል። በዚህም ቡድኑ “ከቤት ቤት እየዞሩና በየጐዳናው ላይ ያገኙትን ሰው በገመድ በማነቅ፣ በስለት በመውገጋት፣ በመጥረቢያ በማጥቃት፣ በዱላ በመደብደብ ገድለዋል። የአካል ጉዳት አድርሰዋል። እንዲሁም ንብረት አውድመዋል”።
“ሳምሪ’’ የሚባለው የትግራይ ወጣቶች ቡድን በዚህ ከባድ ወንጀል ላይ ቢሰማራም፤ በአንጻሩ የትግራይ ብሔረሰብ ተወላጆች የሆኑ አንዳንድ የአካባቢው ነዋሪዎች አጥቂው ቡድን ሲያሳድዳቸው የነበሩ ሰዎችን በቤታቸው፣ በቤተክርስቲያንና በእርሻ ቦታ ደብቀው እንዳተረፏቸው” የኢሰመኮ የምርመራ ቡድን ያነጋገራቸው የአካባቢው እማኞች ገልፀዋል ። ይህ ዛሬም ሰብዓዊነትና ኢትዮጵያዊ ማንነት ቢደበዝዝም ጨርሶ አለመጥፋቱን ያሳያል።
እንደማጠቃለያ
የማይካድራ ዘር ማጥፋት፣ የጦር ወንጀልና በሰብዓዊ ፍጡር ላይ የሚፈጸም ወንጀል የከሀዲው ትህነግን ማንነት በአደባባይ ያሰጣ ግፍ ከመሆኑ ባሻገር በአማራ ሕዝብ ላይ ከ1972 ዓ.ም ጀምሮ የተፈጸሙ ግፎች ወካይና መገለጫ ነው። በሰሜንን ዕዝ ላይ የፈጸመው ክህደትና አረመኔያዊ ተግባር የትህነግን የክህደት ጥግና በላዬ ሰብዕነት ያረጋግጣል ።
መቀጣጫና መማሪያ እንዲሆን ቢያንሽ ባለፉት 30 ዓመታት የፈጸማቸው ግፎች በተለይ የዘር ማጥፋትና በሰብዓዊ ፍጡር ላይ የተፈጸመ ወንጀል እንዲሁም የጦር ወንጀሉ በማስረጃ በደንብ ደርጅቶ ክስ ሊመሰረትበት ይገባል። በአሸባሪነት ሊፈረጅና በዚች ሀገር ከፖለቲካ እንቅስቃሴ ሊታገድ ይገባል።ሀገራችን ኢትዮጵያ በሀቀኛና በጀግኖች ልጆቿ ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር!!! አሜን ።
አዲስ ዘመን ህዳር 28/2013