በአገራችን የፊልም ጥበብ ውስጥ የራሳቸውን ጉልህ አሻራ ካሳረፉት ውስጥ አንዱ ነው። ከ41 በሚበልጡ አገራዊና አለማቀፍ ፊልሞች ላይ በመተወን ልዩ ችሎታውን አስመስክሯል። ብዙዎች በአተዋወን ብቃቱ ያወድሱታል።
በሙያው ባሳየው ትጋትና ችሎታ ምክንያት ከሁለት ጊዜ በላይ በኢትዮጵያ ኢንተርናሽናል ፊልም ፌስቲቫል ላይ የዓመቱ ምርጥ ተዋናይ በመሰኘት ሽልማት ተበርክቶለታል። ‹‹የመጨረሻ ቀሚስ›› እና ‹‹ቫላንታይን›› ለማሸነፉ ምክንያት የሆኑ ፊልሞች ናቸው።
የሙያ አጋሮቹ ‹‹ከትወናው ባሻገር በሚሳተፍባቸው የጥበብ ስራዎች ሁሉ ትልልቅ ሀሳቦችን በመጨመር የራሱን የሆነ በጎ አሻራ ማሳረፍ የሚችልና የሚተጋ ባለሙያ›› እንደሆነ ይገልፃሉ።የሚተውነው መስሎ ሳይሆን እራሱ ገፀ ባህሪውን ሆኖ ነውና ብዙዎቹን በብቃቱ ከማስደመም አልፎ ግራ አጋብቷቸዋል።
ኧረ እንደውም እርሱ ሳይሆን የተጫወተው ገፀ በህሪ እየመሰላቸው በአካል ሲያገኙትም ጠልተውታል መንገድ ላይ ሳይቀር ስድብ ወርዶበታል። የዚህን ያህል የመተወን ክህሎትን የተላበሰ ነው።
ቄራ አካባቢ ነው ተወልዶ ያደገው። አንደኛ ደረጃ ትምህርቱን በአፄ ዘረ ያዕቆብና በፊታውራሪ ላቀ አድገህ የተከታተለ ሲሆን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ደግሞ አብዮት ቅርስ (ጂሴ) ተከታትሏል። በልጅነቱ ጎበዝና የተዋጣለት የእግር ኳስ ተጫዋች ነበር። በዚህም ለማሩ ብረታ ብረት የእግር ኳስ ቡድን “ሲ” ተሰላፊ በመሆን ድንቅ ችሎታውን ማስመስከር ችሏል። ፊልምና ቲያትሮች ላይ በመሳተፍ በብዙዎች አድናቆትን የተቸረው አርቲስት አስራት ታደሰ።
የኪነ ጥበብ ተሳትፎ ጅማሮ
በትምህርት ቤት ህይወቱ በተለይ በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሳለ በተለያዩ የኪነጥበብ ዝግጅቶች በመሳተፍና ፅሁፎችን አዘጋጅቶ ውድድሮችን በመሳተፍ ከመምህራኖቹ አድናቆትን አተረፈ። በሙያው እንዲበረታና እንዲገፋበት የቃል ማበረታታትን ቸሩት። የቅርብ ጓደኛው ወንድም የሆነው (በወቅቱ የበዙ በድራማዎችና ቲያትሮች በማዘጋጀት አድናቆትን ያተረፈው የፊልም ባለሙያው ደራሲና ዳይሬክተር ቢኒያም ወርቁ) ደግሞ ወደ ፊልም ሙያው እንዲቀላቀል በአጋጣሚ ጥሩ መንገድ ፈጠረለት።
ከትምህርት ሰዓት ውጪ ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ
ለመተወን የሚያስችለውን እድል ለመጠቀም ባደረገው ተከታታይ ጥረት ከተዋናይ ሰለሞን፣ ሳምሶን ታደሰ (ቤቢ) እንዲሁም ፍቃዱ ከበደ ጋር በመሆን የተለያዩ ፊልሞች ላይ መሳተፍ ጀመረ። ብዙም ሳይቆይ በሚያሳየው ድንቅ የትወና ችሎታ እምነት የጣሉበት የፊልም ባለሙያዎች እየጋበዙት በተለያዩ ፊልሞች ላይ በመተወን ለጥበቡ እድገት የራሱን ክፍተኛ አስተዋፅዖ አበረከተ። በተለይ በቲያትር መድረክ ላይ በሚያሳየው የትወና ክህሎቱ ብዙዎች እንዳይረሱት እና አድናቆት እንዲቸሩት አስገድዷቸዋል።
የአርቲስቱ የእረፍት ጊዜ
የእረፍት ጊዜውን ሙያውን ሊያሳድጉለት የሚችሉና የተለያየ የህይወት ልምዶች የሚቀስምባቸውን መፅሀፍት በመምረጥ አብዝቶ ያነባል። በሚሳተፍባቸው ፊልሞች ላይ የሚሰጣቸው ገንቢ አስተያየቶችና አተያዮች መሰረት የማንበቡ ውጤት ይመስላሉ። የተመረጡ ተከታታይና ወጥ ፊልሞች ማየትም ያስደስተዋል። የእግር ሽርሽር ማድረግና ከጓደኞቹ ጋር በመሆን ጥሩ ጊዜ ማሳለፍ ሌላኛው ምርጫው ነው።
የተለያዩ ትልልቅ ጉዳዮችን እያነሱ መወያየት፣ ግጥሞችን መፃፍ፣ የፈጠራ ጽሁፎችን ማዘጋጀትም ያዘወትራል። ከልጅነቱ ጀምሮ በአንድ መስክ ተፅዕኖ ፈጣሪ የመሆን ህልም የነበረው አርቲስት አስራት፣ በትወናው መስክ የተሻለና ተፅዕኖ መፍጠር ያስቻለው መክሊት ታድሏል።ያነበባቸው ቁጥራቸው የበረከቱ መፅሀፍት በድርሰቱ ረገድ የራሱን ሚና ለመወጣት መንገድ እንደከፈቱለትና ጽሁፎችን ማዘጋጀት እንደጀመረም ይገልፃል።
‹‹በፊልሙ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ኢትዮጵያ ከሌሎች አለማት ጋር ስትነፃፀር እጅግ በጣም ብዙ ስራ ይጠብቃታል›› በማለት አስተያየቱን ይሰጣል። ሙያው እንዲያድግ ይፈልጋል፤ለአገር ሰፊ ጠቀሜታን ማበርክት የሚችለው ይህ ዘርፍ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል የሚል መልዕክት አለው። ባለሙያውም የሚገባውን ያህል ክብርና ጥቅም ያላገኘበት ምክንያት ለዘርፉ ትኩረት በመነፈጉ መሆኑን ያስረዳል።
የዝነኛው መልዕክት
የረጅም ዘመን ታሪክ ያላት አትዮጵያ አንድነትዋን አጠንክሮ ለማስቀጠል ሁሉም የበኩሉን በጎ ተግባር ማድረግ ይጠበቅበታል ይላል። እንደ አገር መልካም የሆነ ሀሳብ ይዘው የሚቀርቡ ሰዎችን እውቅናን መስጠት ይገባል። ኢትዮጵያን የሚወድ ሁሉ ለአገሩ ለውጥ ያለመታከት መስራት ይገባዋል። አንድነትን የሚያጠናክር እንጂ ልዩነትን የሚፈጥር ሀሳብ ማንሳት ተገቢ አይደለም። ከዘረኝነት የተላቀቀና የሰዎችን እኩልነት ተቀብሎ በመቻቻል የሚዘልቅ ትውልድ ማፍራት ላይ ትኩረት እንዲደረግ ምክረ ሃሳቡን ይለግሳል።
አርቲስቱ በመቋጫ ሃሳቡ ላይ ‹‹ለአገራችን ለውጥ ለህዝባችን መሻሻል ያላሰለሰ ጥረት እናድርግ›› በማለት ሁሉም ይህን ማድረግ ከቻለ የቀድሞ የኢትዮጵያን ክብር መመለስ ይቻላል ይላል።
አዲስ ዘመን ህዳር 27/2013