እፀገነት አክሊሉ
ሴቶች የማህበረሰብ ዋልታ የቤተሰብም መሰረትና አናፂ ናቸው። ጥያቄው ግን ሴት ለሀገር፣ ለማህበረሰብና ለቤተሰብ የምትጫወተው ሚና ያህል ጥበቃ፣ ከለላና ክብር አግኝታለች ወይ? የሚለው መሆን አለበት። ይህንን ጥያቄ ለመመለስ ብዙ ነገሮችን ማገላበጥ አልያም መጨነቅና መጠበብ ላያስፈልግ ይችላል። ምክንያቱም የአገራችንን ሁኔታ እንኳን ብንመለከት፤ መልሱ ከሁላችንም የተደበቀ አይደለም። ምን አልባትም መልሱን አውቀን፤ ገሀዱን የኢትዮጵያ ሴቶች ከውጣ ውረድ አልፎ የሚደርስባቸውን ትንኮሳና ጥቃት የማህበረሰብ ቀውስ ነው ብለን ብንረዳም አንዳች መፍትሄ አለማፈላለግ ግን ችግሩ ከቀን ቀን ከዓመት ዓመት አብሮን እንዲዘልቅ ከማድረጉም በላይ መፍትሔውም የራቀ አስመስሎታል።
ፆታዊ ጥቃት ምንድን ነው? ብለን ስንል ጥቃት በጥሬ ትርጉሙ በተለያየ መልኩ የሚፈጸምና በሰዎች አካል፣ ህይወት እና ንብረት ላይ ጉዳት የሚያደርስ ድርጊት ነው። ይሆናል መልሱ፤ ግን ደግም ሃይል፣ አቅም/ስልጣን/፣ ነጻ ፈቃድ እና ሰብዓዊ መብት የሚሉት እሳቤዎች፤ ጥቃት ሲነሳ አብረው የሚነሱ መገለጫዎች ናቸው።
በሴቶች ላይ የሚፈጸም ጥቃት ማለት ደግሞ ፆታን መሰረት ያደረገና አካላዊ፣ ወሲባዊ ወይም ስነ ልቦናዊ ጉዳት ሊያደርስ የሚችል ማንኛውም ድርጊት፣ ማስገደድ ወይም ተገቢ ያልሆነ ነጻነትን የማሳጣት ተግባር በጾታዊ ጥቃት ውስጥ ይካተታል። ይህም በሴቶች የግል ህይወትም ሆነ በማህበራዊ ኑሮ ላይ ሊደርስ የሚችለው ተጽዕኖ እንደሆነ በተለያዩ ድንጋጌዎች ተቀምጧል።
በሴቶች ላይ የሚደርስ ጥቃት የተለያየ ነው የኢፌዴሪ አቃቤ ህግ ከአምስት ዓመት በፊት በሴቶችና ሴት ህጻናት ላይ የሚፈጸም ጾታዊ ጥቃት እና የመብት ጥሰቶች በሚል ባወጣው ጽሁፍ በሴቶች ላይ የሚደርሱ የጥቃት አይነቶችን ለመዘርዘር ሞክሯል።ከዝርዝሩ ውስጥም የቤት ውስጥ ጥቃት ግንባር ቀደሙን ተርታ የያዘ ሲሆን በሃይለ ቃል በምልክት በአካል ላይ በሞራልና ስነልቦና እንዲሁም በማንኛውም መንገድ ነጻነትን የሚጋፋ ድርጊቶችን አካቷል።
በሌላ በኩልም የሴቶችን የኢኮኖሚ መብት መጋፋት እንደ ኢኮኖሚያዊ ጥቃት እንደሚቆጠርም በጽሁፉ ላይ አስፍሯል። ብዙ ጊዜ ሴቶችና ሴት ህጻናት ንብረት እንዲያፈሩና በንብረታቸውም እንዲያዙ አይደረግም፤ ለሰሩት ስራ ተገቢውን ክፍያም እንዲያገኙ አይፈቀድም፤ ከዛ ይልቅ በጥገኝነት እንዲኖሩ ነው የሚፈለገው፤ ይህ ደግሞ ኢኮኖሚያዊ ጥቃት ከመሆኑም በላይ የሰብዓዊ መብት ጥሰትም የሚሆንበት ጊዜ አለ።
ሌላኛው ጥቃት አካላዊ ጥቃት ሲሆን በየትኛውም መንገድ በአካል ላይ የሚፈጸም የሀይል እርምጃን ያካትታል። ሴቶችን መምታት መገፍተር መተንኮስ አንዳንዴም እስከ ነፍስ ማጥፋት የዘለቁ ድርጊቶች አካላዊ ጥቃት ተብለው ነው በአቃቤ ህግ ጽሁፍ ላይ የተቀመጡት።
ስለሴቶች መብት መከበር ብዙ በሚነገርበት በዚህ ዘመን ግን በሴቶች ላይ የሚፈፀሙ ፆታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች ከዕለት ወደ ዕለት እየጨመሩ መሄዳቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ። ኢትዮጵያ ውስጥ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚከበረው የሴቶች ቀን መታሰብ ከተጀመረ 44 ዓመታት እንደዋዛ አልፈዋል። በዚህ ጊዜ ውስጥ ምንም እንኳን ጠንካራ ሴቶች የተለያዩ መሰናክሎችን አልፈው ለስኬት ቢበቁም በተለይ በጓዳ የሚፈፀመው ፆታዊ ጥቃት ተባብሶ መቀጠሉ ይነገራል።
በነገራችን ላይ ባለፉት ጊዜያት እስከ አሁንም ለማለት ይቻላል ለጆሮ የሚዘገንን አንገት የሚያስደፉ በጠቅላላው ለሰሚው ግራ የሆኑ ዘግናኝ ጥቃቶች በሴቶች ላይ ተፈጸሙ ተብሎ በተለያየ መንገድ ሰምተናል፤ ሆኖም ሁሉም በተፈጸሙበት ጊዜና ሰሞን ብቻ ለመገናኛ ብዙሀኑም እንዲሁም በሴት ጥቃት ላይ እንሰራለን ለሚሉ አካላት ሆይ ሆይታ ከማገልገላቸው ባለፈ ከምን እንደደረሱ እንኳን ሳይታወቅ የሚቀርበት ጊዜ ብዙ ነው።
በሌላ በኩልም ሴቶች ከቤት ስራ ጀምሮ በውጪም በተለያዩ የስራ መስኮች ላይ ተሰማርተው ቢሰሩም አስተዋጿቸውን በማቅለልና ስራቸውን ሊደግፏቸው የሚችሉ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን እንኳን እንዳያገኙ ችላ የሚባልበት ሁኔታ ብዙ ነው።
የሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ሚኒስቴር ጾታዊ ጥቃት ያለበትን ደረጃ ለማወቅ ጥቅል ጥናት ያስፈልጋል ቢልም እኤአ በ2016 የተጠና ጥናት የሚያመለክተው ግን በአገራችን 23 በመቶ የሚሆኑ ሴቶች ፆታዊ ጥቃት እንደሚደርስባቸው ነው፤ ይህ እንግዲህ ቆየት ያለ ጥናት እንደመሆኑ አሁን ላይ የሚደርስበትን ደረጃ መገመት አያዳግትም። በዚሁ ጥናት ላይ ከአገሪቱ ሴቶች 68 በመቶ የሚሆኑት በትዳር አጋራቸው ጥቃት የሚደርስባቸው ናቸው።
በሌላ በኩልም የኢትዮጵያ የህግ ባለሙያ ሴቶች ማህበር አጠናሁት በሚለው ጥናት መሰረት የጥቃቱ ሰለባዎች በሁሉም የኑሮ ደረጃና የህብረተሰብ ክፍል ውስጥ የሚገኙ ሴቶች መሆናቸውን ይገልጻል። አሁን ላይ በኢትዮጵያ ውስጥ በአብዛኞቹ ክልሎች ማለት ይቻላል ጾታን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች በመበራከታቸው አንገብጋቢ ችግር እየሆነ መጥቷል።
ህዳር ወር ደግሞ የሴቶች ጥቃት የሚታሰብበት፣ስለ ጥቃቶች ብዙ ነገሮች የሚወሩበትና በተቻለ መጠን በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች እንዲቆሙ በዘርፉ የሚንቀሳቀሱ ሁሉ ጥሪያቸውን የሚያቀርቡበት ነው። በዚህ ዓመትም የሴቶች ጥቃት ሊቆም ይገባል በማለት “የአፍሪካ ሪነሰስ ዴያስፖራ ኔት ዎርክ” የተሰኘ መቀመጫውን አሜሪካን አገር ያደረገና በቅርቡም በኢትዮጵያ ውስጥ ቢሮ በመክፈት ጾታዊ ጥቃቶችን አስመልክቶ እንቅስቃሴ የጀመረው ድርጅት ነው። ድርጅቱ የዘንድሮውን የህዳር ወር እስከ 2022 የሚቆይ የቀይ ካርድ ዘመቻን ይፋ በማድረግ ስራውን ጀምሯል። ከድርጅቱ ጋር በተባባሪነት የሚሰራው አሻጋሪ የወጣቶችና የሴቶች ድጋፍ ተቋም ይህንን ዘመቻ በመቀላቀልና አይነተ ብዙ ስራዎችን በመስራት በአገሪቱ የሚስተዋለውን የሴቶችን ጥቃት ለማስቆም የበኩሉን እያደረገ ይገኛል።
የድርጅቱ የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ወይዘሮ አስራት ጥላሁን እንዳሉት የሴቶች ጥቃት በመላው ዓለም ያለ ቢሆንም በአፍሪካ በተለይም ደግሞ በኢትዮጵያ አይነቱና መጠኑ እየጨመረ በየጊዜውም በርካታ ሴቶችን ተጎጂ እያደረገ ስለመሆኑ ይናገራሉ።
ለሴቶች ጭቆና አድሎና መገለል በቃ ለማለት ዘንድሮ “የቀይ ካርድ ዘመቻ” ተጀምሯል። አድሎና መገለል በኢትዮጵያ እንዲሁም በዓለም ልጃገረዶችና ሴቶች ላይ መቆም አለበት ያሉት ወይዘሮ አስራት በእግር ኳስ ጨዋታ ላይ ለአንድ ተጫዋች ቀይ ካርድ ተሰጠው ማለት ከጨዋታው ውጪ ይሆናል። በዚህ መሰረትም ጥቃትና አድሎ በኢትዮጵያውያን ልጃገረዶችና ሴቶች ላይ ቀይ ካርድ ሊሰጠው ይገባል።
ለዚህም የህግ አውጪዎችና አስፈጻሚዎች እንዲሁም ማህበረሰቡ ያገባኛል ብሎ እንዲነሳም በማሰብ ድርጅቱ በአገሪቱ ቢሮ ከፍቶ እየተንቀሳቀሰ መሆኑንና በዚህ ቀይ ካርድ ዘመቻውም በርካታ ወገኖች ጋር ደርሶና ስለ ጉዳዩ ተገቢውን ግንዛቤ ፈጥሮ ውጤታማ ስራንም ይሰራል የሚል እምነት እንዳላቸው አስታውቀዋል።
ድርጅቱ ዘመቻውን በማስተባበር ይህንን ጥቃትና አድሎ ይብቃ በማለት የግለሰቦችና የድርጅቶችን ጥረትና ሃላፊነትን ለማጉላት ከተለያዩ አካላት ጋር በመሆን የአህጉሪቷን ህዝቦች በማስተባበር ይሰራል ብለዋል።
ድርጅቱ ይህንን የቀይ ካርድ ዘመቻ በተባበሩት መንግስታት የኒውዮርክ ቢሮ እንዳስጀመረው ገልጸው እስከ 2022 አንድ ሚሊዮን የሚደርሱ ፊርማዎችን በማሰባሰብም ዘመቻውን እንዲፋፋም ብሎም ውጤታማ እንዲሆን ይሰራል።
የአሻጋሪ ማማከር አገልግሎት መስራችና ባለቤት ወይዘሪት መቅደስ ገብረወልድ በበኩላቸው ትውልድን ማሻገር በሚል የሚሰሩ ስራዎች አሉ ከስራዎቹ መካከልም ሴቶችን ማብቃት ሲሆን ይህ ለማድረግ ደግሞ ሃላፊነታቸውን በደንብ እንዲወጡ ከተፈለገ መብታቸው ጤንነታቸው መጠበቅ አለበት ከአደጋ መጠበቅ ይኖርባቸዋል ይህንን ማስፈጸም ደግሞ የሁሉም ድርሻ ቢሆንም ድርጅቱ ግን ባሉት የወጣቶችና የሴቶች ፕሮግራሙ የተለያዩ ስራዎችን ያከናውናል።
እንደ ወይዘሪት መቅደስ ገለጻ ድርጅቱ በሴቶች ጥቃት ላይ በርካታ ስራዎችን ሰርቷል፤ በዚህም ሴቶችን በማደራጀት ልጃገረዶችን የግንዛቤ ማስጨበጫ ፕሮግራሞችን በመስራት በመንግስት ተቋማት ውስጥ ላሉ የሴት አመራሮችም ጾታዊ ጥቃትን ጨምሮ ሌሎች ራሳቸውን ችለው እንዲቆሙ የሚያስችሉ ፕሮግራሞችን በመስራት ተሳታፊ እንደሆኑ አብራርተዋል።
ይህ ቀይ ካርድ ደግሞ ሴቶች ላይ ለሚመጡ ጥቃቶች አይሆንም ለማለት የሚያስችል ሲሆን ፖሊሲ አውጪዎችን ተርጓሚዎችን ፈጻሚዎች ላይ ተጽዕኖ በመፍጠር ይህንን ነገር ተግባራዊ እንዲያደርጉት ነው፤ ይላሉ።
ቀይ ካርድ ብለን ዘመቻውን ስንቀላቀል በተለይም የጥቃቱ ሰለባዎችን ብቻ ሳይሆን ሊፈጽሙ ይችላሉ ተብለው የሚገመቱ አካላትም በዚህ ዘመቻ ላይ ተሳታፊ በመሆን መከላከሉ ላይ ትኩረት እንዲደረግ ድርጅቱ የራሱን ሚናም ለመጫወት እንደሚያስብ ይናገራሉ።
ይህ የሴቶች ጥቃት ወር በዚህና በሌሎች በርካታ ስራዎች ከመታሰቡ ባሻገር ዝግጅቶቹም ሆኑ ዘመቻዎቹ ምን ለውጥ አመጡ ከየት ተነስተው የት ደረሱ የሚለው ነገር ግን ሁሌም ሊታሰብ የሚገባው ነው።ዓመትን ጠብቆ ብቻ የሴቶች ጥቃት ይቁም ስለተባለ የሚመጣ ለውጥ ስለማይኖርም በዘርፉ የተሰማሩ ድርጅቶችም መንግስት ከልብ ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚያስፈልግም መገንዘቡ መልካም ነው።
በአጠቃላይ በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች ተፅዕኖቻቸውን የሚያሳርፉት በተጠቂ ሴቶች ላይ ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ ማህበረሰቡ ላይ ነው። በዚህም ምክንያት የማህበረሰቡን እኩልነት በመሸርሸር፣ ምርታማነትን በመቀነስ፣ በትምህርት ውጤታቸው ላይ ዝቅተኛ ውጤት እንዲያስመዘግቡ እንዲሁም በሲቪል ሰርቪስ ሥራቸው ውጤታማ ሆነው እንዳይወጡ የሚያደረግ ነው።
በመሆኑም በሴቶች ላይ የሚደርስን ሁሉን ዓይነት ጥቃትም ካልተወገደ ቀጣይነት ያለው ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ብልፅግና ማምጣት አይቻልም። ጤናማ እና የበለፀገ ማኅበረሰብ ለመፍጠር በሴቶች ላይ የሚደርሱ ተፅዕኖዎችን ማስወገድ ይገባል።
በዚህም ሴቶች በእማወራነት ሚናቸው ልጆቻቸውን ለኃላፊነት ስሜት እንዲበቁ እና እንዲጎለብቱ አድርገው ያሳድጋሉ። ሴቶች የማኅበረሰቡ ግማሽ አካሎች ከመሆናቸው አንፃር ድጋፍ፣ እንክብካቤ፣ ማበረታቻና ትብብር ሲደረግላቸው ደግሞ የበለጠ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ይተጋሉ። ቀስ በቀስም በተለያዩ አደረጃጀቶች በመሳተፍና በትምህርት ራሳቸውን በማሳደግ ተቋማትን መምራት ይችላሉ። ኃላፊነታቸውን በሰከነ መንፈስ ስለሚወጡም ውጤታማ ሆነው የበለፀገች ሀገርን ለመገንባት አስተዋፅኦ ያደርጋሉ።