አስናቀ ፀጋዬ
በመምህርነት ሙያ ሀገራቸውን ለዓመታት አገልግለዋል። የሥራ ትንሽ የለውም ብለውም ኑራቸውን መደጎሚያ በጀሪካን ውሃ በመሸጥ ተሰማርተዋል። ወደ ሻይና የፍራፍሬ ጭማቂ ማዘጋጀትም ከፍ ብለው ነጋዴ ተብለዋል። በፖለቲካና ማህበራዊ ተሳትፎም በአካባቢያቸው ይታወቃሉ። ከፖለቲካው ግን የማህበራዊ ተሳትፎአቸው ጎልቶ የወጣ ነበር። በተለይም በስፖርቱ የጎላ ሚና ነበራቸው። የኢትዮጵያ የሴቶች ፕሪሚየር ሊግ አሁን ለደረሰበት ደረጃ ያበረከቱት አስተዋጽኦ ሚናቸውን የጎላ አድርጎታል። በጀሪካን ውሃ መሸጥ የተጀመረው የንግድ ሥራ ዛሬ አድጎ ወደ ኢንቨስትመንት ተሸጋግሯል። ሲዳማ የፈራቻቸው ታታሪው ባለሀብት አቶ ዘርይሁን ቃሚሶ ።
አቶ ዘርይሁን ቃሚሶ ተወለደው ያደጉት በሲዳማ ክልል አለታ ወንዶ ከተማ ልዩ ስሙ ለመላ አሩጂ በሚባል አካባቢ ነው። ስድስት ዓመት ሲሞላቸው ቄስ ትምህርት ቤት ተላኩ። በቄስ ትምህርት ቤት ለአንድ ዓመት ፊደል ከተማሩ በኋላ ከአንደኛ እስከ ስድስተኛ ክፍል በአለታ ወንዶ ከተማ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ትምህርት ቤት፣ ከሰባት እስከ ስምንት በአለታ ወንዶ መለስተኛ ትምህርት ቤት፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ በይርጋለም ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትለዋል።
የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ ሀዋሳ መምህራን ማሰልጠኛ ኮሌጅ ነበር የገቡት። ጊዜው 1975ዓ.ም ነበር። የኮሌጅ ትምህርታቸውን እንደጨረሱም በጊዜው ግዴ አውራጃ ተብሎ በሚጠራውና በዲላ ዙሪያ ተመድበው በመምህርነት ለዓመታት አገልግለዋል። በ1983 ዓ.ም ኢህአዴግ ሀገሪቱን ሲቆጣጠር የመምህርነት ስራቸውን ሙሉ በሙሉ በማቆም ወደ ፖለቲካው ትግል በመቀላቀል በጊዜው የሲዳማ ዲሞክራሲያዊ ድርጅት የአለታ ወንዶ ወረዳ ተጠሪ፣ የሲዳማ የዞን ተጠሪ እንዲሁም የደቡብ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ግንባር የፖለቲካ ኃላፊ ሆነው እስከ 1986 ዓ.ም መጨረሻ ድረስ አገልግለዋል።
ከፖለቲካው መስመር ሲወጡ ገና ወጣት የነበሩት አቶ ዘርይሁን ፖለቲካውን ዳግም ሊመለሱበት ባለመፈለጋቸው ፊታቸውን ወደ ንግዱ ዓለም አዞሩ። ወደ ንግዱ ለመግባት አክስታቸው መነሻ እንደነበሯቸው ያስታውሳሉ። መምህር ሆነው ሲያገለግሉ ዲላ ከተማ ውስጥ የሆቴል ንግድ የነበራቸው አክስታቸው ጋር በመሄድ ሥራ ያግዟቸው ነበር። በወቅቱም ስለንግዱ ግንዛቤ እንዲኖራቸው አስችሏቸዋል። ዕድገታቸው ከተማ ላይ፣ ማህበራዊ ግንኙነታቸውም ጠንካራ መሆኑም ንግዱ ውስጥ ለመግባት እና ለመቆየት ምቹ ሁኔታ ፈጥሮላቸዋል።
ከእግር ኳስ ጨዋታ ጋር በነበራቸው ግንኙነትና አእምሯቸውም አዲስ ሃሳብ ለማፍለቅና ከፖለቲካው ዓለም ከወጡ በኋላም ለውጥ ለመቀበል ፈጣን ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ቀስ በቀስ ወደ ንግዱ ዓለም ተቀላቀሉ። በሀዋሳ ከተማ መናኸሪያ አካባቢ በተከራዩት አነስተኛ ቦታ ላይ ዳስ ጥለው ውሃ በጀሪካን ጋሪ ለሚጎትቱ ፈረሶችና ግንባታ ለሚያከናውኑ ሰዎች መሸጥ ጀመሩ። ጎን ለጎንም ሻይ በማፍላት፣ የፍራፍሬ ጭማቂና ፈጣን ምግቦችን በማዘጋጀት ማቅረብ ቀጠሉ። ደንበኞቻቸውም ከገበያ መልስ መጓጓዣ ፍለጋ ወደ መናኸሪያ የሚሄዱ ነበሩ።
በወቅቱም ንግድ ለመጀመር የሚያስችል ገንዘብ አልነበራቸውም። ንግዱን ለመቀላቀል ምክንያቶች ስለነበሯቸው ብቻ ነው በድፍረት የገቡበት። እርሳቸው እንደሚሉት ቀደም ሲል በነበራቸው የፖለቲካ ህይወት ህሊናቸው ሊቀበላቸው የማይፈልጉ ስራዎችን እንዲሰሩ ይገደዱ ነበር። ነገሮችን ከመሸፋፈን በግልጽ መናገራቸውና ሀቀኛ መሆናቸው አልተወደደላቸውም። ህሊናቸው የማይፈቅደውን ከመሥራት በትንሽ ሥራም ቢሆን ኑሮአቸውን መምራት መረጡ። የአነስተኛ ንግድ መነሻ ታሪክ ህሊና የማይፈቅድን ነገር ከማድረግ ለመሸሽ ነው።
በዚህ ሁኔታ የተጀመረው የሻይ፣ የፍራፍሬ ጭማቂ፣ ፈጣን ምግቦችና የውሃ ንግዳቸው ቀስ በቀስ እየተሟሟቀ መጣ። 200 ካሬ ሜትር ስፋት ባለው ቦታ ላይ በኪራይ ይሰሩበት የነበረውን ቦታም በሂደት የግላቸው ማድረግ ችለዋል። ይህንንም ተከትሎ ወደ ቡና ንግድ ገቡ። ወደ ቡና ንግዱ ለመግባት በጊዜው በቂ ገንዘብ አልነበራቸውም። ሆኖም ግን አብረዋቸው እሽት ቡና መፈልፈያ ተክለው የሚሰሩ አገኙ። የቡና ንግዱ አለታ ወንዶ ላይ ሲሆን፣ ቡና በጋራ አብረው መስራቱን ተያያዙ። በወቅቱም የእርሳቸውና የስራ ባልደረቦቻቸው ቡና መፈልፈያ በአክሲዮን ህብረት ስራ ማህበር የተተከለ የመጀመሪያው ቡና መፈልፈያ ለመሆን በቃ። በዚሁ የቡና ንግድም በመጀመሪያው ዓመት እያንዳንዳቸው 300 ሺ ብር ትርፍ ማግኘት ቻሉ። ቀደም ሲል ሸራ ወጥረው ሻይ፣ የፍራፍሬ ጭማቂ፣ ፈጣን ምግቦችና ውሃ ንግድ ሲያካሂዱበት በነበረበት ቦታ ላይ ስምንት የመኝታ ክፍሎች ያሉትና በጊዜው ትልቅ የተባለ ምግብ ቤት ከፈቱ።
የቡና ንግዱን ለሰባት ዓመታት ያህል ከሰሩ በኋላ አብረዋቸው ሲሰሩ የነበሩ ሰዎች የየራሳቸውን የቡና መፈልፈያ መትከል ሲጀምሩ አቶ ዘርይሁንም የራሳቸውን የቡና መፈልፈያ ተከሉ። ምግብ ቤታቸውም ቀስ በቀስ እያደገ መጥቶ ተጨማሪ ቦታ በመግዛት በጊዜው በሃዋሳ ከተማ ትልቅ የተባለውን ፓራዳይዝ የተባለ ስያሜ ያለውን ሆቴል በ1995 ዓ.ም ከፈቱ። በወቅቱ ሆቴሉ ስራ ሲጀምርም የክልሉ ርእሰ መስተዳደር ሆነው ያገለገሉት አቶ ሃይለማሪያም ደሳለኝ መርቀው መክፈታቸውን ያስታውሳሉ።
የቡና መፈልፈያ ማሽን ከአንድ ወደ ሶስት ከፍ በማድረግ ሥራቸውን ያሰፉት አቶ ዘርይሁን፤ ከዚህ ባሻገር የቡና እርሻ ከፋ ላይ በሶስት መቶ ሄክታር መሬት ማልማት ቀጠሉ። ከሀገር ውስጥ ፍላጎት በዘለለም ቡናን ወደ አሜሪካን፣ ጀርመን፣ ሳውዲ አረቢያና ሌሎችም አረብ ሀገራት ያቀርባሉ። በአካባቢያቸውም ትልቅ የንግድ ኢንቨስትመንት እያካሄዱ ካሉ ግለሰቦች ውስጥ አንዱ ለመሆንም በቁ።
ወደ 64 የመኝታ ክፍሎች ያደገው የፓራዳይዝ ሆቴል ቤታቸውም የስብሰባ አዳራሾችንና የተለያዩ መዝናኛዎችን በማካተቱ በባለ ሁለት ኮኮብ ደረጃ ላይ ደርሷል። በአሁኑ ጊዜም ተጨማሪ በአስር ሺ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ባለአራት ኮኮበ ሆቴል በመገንባት ላይ ይገኛሉ። በመገንባት ላይ ያለው ሆቴል የሲኒማ አገልግሎትን፣ የልጆች መጫወቻዎችን፣ የመዋኛ ገንዳንና ሌሎችንም አገልግሎቶችን ያካትታል። እስካሁን ባለው ሂደትም ግማሽ ያህሉ የሆቴል ግንባታ ተጠናቋል። ሙሉ ስራውን አጠናቆ ለመጨረስም ከባንክ የብድር አገልግሎት በመጠበቅ ላይ ናቸው።
በቡና ንግዱም ሁለት የታጠበ ቡና መፈልፈያና ማዘጋጃ ኢንዱስትሪና አንድ የደረቅ ቡና ማበጠሪያ ያላቸው በመሆኑ ንግዱ ጥሩ እንቅስቃሴ ላይ ይገኛል። ከዚህ በተጨማሪም በሃዋሳ ከተማ ውስጥ ህንጻዎችንና መኖሪያ ቤቶችን ያከራያሉ። ለዜጎች የሥራ ዕድል በመፍጠርም ከፍ ያለ ሚና አላቸው። በቡና ዘርፉ ላይ ብቻ ለአራት ወራት እስከ አምስት መቶ የሚሆኑ ዜጎች በሥራው ላይ ይቆያሉ። በሆቴሉ ደግሞ ከአንድ መቶ በላይ ሰራተኞች ተቀጥረዋል። በአጠቃላይ በዓመት እስከ አንድ ሺ ለሚሆኑ ዜጎች በተለያየ መልኩ የስራ እድል መፍጠር ችለዋል። ባለሀብቱ አጠቃላይ የሚንቀሳቀሰውንና የማይንቀሳቀሰውን ሃብት ጨምሮ 400 ሚሊዮን ብር ካፒታል አላቸው።
በቀጣይም አቶ ዘርይሁን በተለይ የቡና ንግዱን በማጠናከር ቡናን ከማሳው ጀምሮ እሴት ጨምረውና አቀነባብረው ለውጪ ገበያ የማቅረብ እቅድ አላቸው። በሌላ በኩል ደግሞ የሆቴሉን ዘርፍ በማዘመን አገልግሎቱን የማጠናክር ፍላጎት ያላቸው ሲሆን ወደ ውጪ ሀገር የሚልኩትን የቡና ምርት መዳረሻዎች ቁጥር የማስፋት ውጥንም ይዘዋል። በመኖሪያ ቤት ግንባታ(በሪል እስቴት) ገበያ ውስጥም ለመግባት በሃዋሳ ከተማ ቦታ ጠይቀው በመጠባበቅ ላይ ናቸው። ቡናን እሴት ጨምሮና አቀነባሮ ወደ ውጪ ሀገር ለመላክም በይርጋለም አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ ሼድ ገንብተዋል። በነባር ኢንቨስትመንቶች ላይም የቡና እርሻዎችን የማጠናከር ስራዎችን በመስራት ላይ ይገኛሉ። ለዚህ ሁሉ ኢንቨስትመንት ታዲያ ከመንግስት በኩል ተመጣጣኝ የወለድ መጠን ያለው የብድር ድጋፍ ያስፈልጋል ይላሉ። ከውጪ በሚገቡ እቃዎች ላይ የውጪ ምንዛሬ እጥረት እንዳያጋጥም ተመሳሳይ ድጋፍ ከመንግስት ይጠብቃሉ።
አቶ ዘርይሁን ከኢንቨስትመንት እንቅስቃሴያቸው በተጨማሪ ማህበራዊ ግዴታቸውንም በመወጣት አርአያ ናቸው። ለአብነትም ክልላቸውን በመወከል በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ውስጥ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል ሆነው ለስምንት ዓመታት የሰጡት አገልግሎት፣ የሲዳማ ቡናና የሃዋሳ ከነማ እግር ኳስ ክለቦች የቦርድ አመራርና የቦርድ ሰብሳቢ ሆነው የሰሩት፣ በተለይ ሴቶች በፕሮጀክት ታቅፈው እግር ኳስን እንዲጫወቱ በማድረግ የኢትዮጵያ የሴቶች ፕሪሚየር ሊግ እንዲጀመር አስተዋፅኦ ከማበርከት በዘለለ በፕሪሚየር ሊጉ የተጨዋቾች እጥረት እንዳያጋጥመው ሃሳብ ከማፍለቅ ጀምሮ ያበረከቷቸው አስተዋጽኦች ይጠቀሳሉ።
የደቡብ ክልል ቡና አቅራቢዎች ማህበር ፕሬዝዳንት ሆነውም ለረጅም ዓመታት አገልግለዋል። በአሁኑ ወቅት ደግሞ የሲዳማ ክልል ቡና አቅራቢዎች ማህበር ፕሬዝዳንትና የሲዳማ ክልል ንግድና ዘርፍ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሆነው በማገልገል ላይ ይገኛሉ። በሚኖሩበት ክልል አካባቢ ችግሮች በሚያጋጥሙ ጊዜም ቶሎ በመድረስና አረጋውያንን በመርዳት ይሳተፋሉ።
‹‹የቡና ኢንዱስትሪው ዋነኛ ተግዳሮት ከመንግስት በኩል ያለው የፖሊሲ ችግር ነው›› የሚሉት አቶ ዘርይሁን የቡና አምራቾችና ላኪዎች በዚህ ችግር ውስጥ ሲሰሩ ቆይተው ችግሩ እንዳለ በማሳወቅ ነገሮች እየተሻሻሉ ሲመጡ በ2009 ዓ.ም የቡና የፖሊሲ ለውጥ መደረጉን ይጠቁማሉ። ከዚህ የፖሊሲ ለውጥ በኋላም በቡና ላይ ትኩረት ተሰጥቶ በርካታ ስራ መሰራቱንና መሻሻሎች መኖራቸውን ይጠቅሳሉ።
የሆቴል አገልግሎት ዘርፍም ‹‹ትንሽ ኮሽ ባለ ቁጥር በቶሎ የሚጎዳ ዘርፍ ነው›› የሚሉት አቶ ዘርይሁን መንግስት በተለይ በፀጥታና በደህንነት ጉዳይ ላይ ትኩረት ሰጥቶና የለውጡ አካል አድርጎ መስራት እንዳለበት ያመለክታሉ። ለሆቴል ግንባታ የሚያስፈልጉ ግብአቶችንና እቃዎችን ከቀረጥ ነፃ እንዲገቡ በማድረግ ዘርፉን ማበረታታት እንደሚገባም ሀሳብ ሰጥተዋል።
አቶ ዘርይሁን፤ የዚህ ሁሉ ሀብት ባለቤት ከመሆናቸው በፊት ወደ ኋላ መለስ ብለው ሲያስታውሱ። ወር ጠብቀው አነስተኛ ገንዘብ የሚያገኙ ሰው ነበሩ። ዛሬ ከራሳቸው አልፈው ከአንድ ሺ በላይ የሚሆኑ ዜጎችን በማስተዳደር እንዲሁም ጎን ለጎንም ማህበራዊ ግዴታቸውን መወጣት መቻላቸው እጅግ ያስደስታቸዋል። የስኬቱ ቁልፍም ፍላጎትና የስራ ተነሳሽነት ነው ይላሉ። አንድ ስራ ሰርተው በሚያገኙት ገቢ የተሻለ ጥቅምና ትርፍ ለማግኘትና ሌላ ለመስራት የማሰብ ፍላጎትም ለደረሱበት ስኬት የራሱን አስተዋፅኦ እንዳበረከተ ይጠቅሳሉ።
በተመሳሳይ ሌሎችም በዚሁ የቡናና የሆቴል አገልግሎት ዘርፍ ውስጥ ተሳታፊ ሆነው ውጤታማ መሆን ለሚሹ በቅድሚያ ቀና መሆን እንዳለባቸውና ሁሌም ቢሆን በሚያገኙት ገቢ እየተደሰቱ ባለው ላይ ለመጨመር ማሰብ እንደሚያስፈልግ ይመክራሉ። ያገኙትን ገቢ ማድነቅና አምላካቸውን ማመስገን እንደሚገባቸው፣ የሰሩት ስራ ምን ውጤት እንዳመጣ መገምገም እንዳለባቸውና ይህም የበለጠ ስኬትን እንደሚያስገኝም ይጠቁማሉ። ገንዘብ በቶሎ ለማግኘት አቋራጭ መንገዶችን መከተል እንደሌለባቸውና የተገኘውንም ገንዘብ በአግባቡ ስራ ላይ ማዋል እንደሚገባም ያመለክታሉ።
መንግስትም በተለይ የነጋዴውን ማህበረሰብ የንግድና ማህበራት ዘርፎችን የሚመሩ ተቋማትን እንዲጠናከሩ በማድረግና ማህበራቱ የእውቀት አቅማቸውን እንዲጨምሩ በማድረግ የንግዱን ዘርፍ ማሳደግ እንደሚገባውም አቶ ዘርይሁን ይናገራሉ። የአንድ ሀገር ምሶሶ ትምህርትና ንግድ የመሆኑን ያህል መንግስት በእነዚህ ዘርፎች ላይ አተኩሮ መስራትና ተቋማዊ ማድረግ እንደሚገባ ያሳስባሉ።
አዲስ ዘመን ህዳር 26 ቀን 2013 ዓ.ም