(ጌታቸው በለጠ – ዳግላስ ጴጥሮስ)
“እኔም እዚያው ነበርኩ”
ኅዳር 29 ቀን 1999 ዓ.ም። “ሕገ መንግሥታዊ ቃል ኪዳን የአብሮነታችን መገለጫ ነው” በሚል መሪ ቃል የመጀመሪያ የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል በአዲስ አበባ ከተማ፣ ስድስት ኪሎ ይገኝ በነበረው “የኢትዮጵያ ብሔራዊ የባህል ማዕከል አዳራሽ” ውስጥ ሲከበር የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ አንዱ ታዳሚ ነበር።
ብሔረሰቦቻችን በቀለመ ደማቅ ባህላዊ ዝግጅቶቻቸው (አልባሳት፣ ጭፈራ፣ ባህላዊ ምግቦችና ቁሳቁሶች ትዕይንት ወዘተ.) ዕለቱን አድምቀው መዋላቸውን ጸሐፊው በሚገባ ያስታውሳል። ከዝግጅቶቹ መካከል በተለየ ሁኔታ ቀልቡን ስቦ የነበረው አንዱ ኩነት ከሀገራችን ደራስያን መካከል ፍቅረ ማርቆስ ደስታ በሀመር ብሔረሰብ ላይ ተመስርቶ በጻፋቸው የልቦለድ መጻሕፍት ሥራዎቹ ምክንያት በወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስቴር በአቶ መለስ ዜናዊ ተሸላሚ መሆኑ ነበር። ጸሐፊው አንጋፋውን የኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበር በፕሬዚዳንትነት የሚመራበት ወቅት ስለነበር ለደራሲው የተሰጠው ሽልማት ለፍቅረ ማርቆስ ብቻም ሳይሆን ለመላው የኢትዮጵያ ደራስያን እንደተሰጠም ጭምር አምኖ ነበር። ከዚያ በኋላ “ሕያው የጥበብ ጉዞ ወደ ከቡስካ በስተጀርባ” በሚል መሪ ዓላማ አንጋፋው ማኅበር በደራሲ ፍቅረ ማርቆስ ሥራዎች ላይ ተመስርቶ የተወሰኑ አባላቱን ይዞ ወደ ሀገራችን የደቡብ ክፍል አስደናቂ ጉዞ ማዘጋጀቱ ይታወሳል። የደራሲው ሽልማት የበዓሉን አዘጋጆች አንዳች ስሜት አጭሮባቸው ሳይሆን እንደማይቀር በሚገመት ምክንያት በየዓመቱ ለሚደረጉት መሰል በዓላት በተቋቋመው ብሔራዊ ኮሚቴ ውስጥ ይህ ጸሐፊ የሚመራውን አንጋፋ ማኅበር ወክሎ እንዲሳተፍ ደብዳቤ ደረሰው። በራሱ አሳማኝ ምክንያት ከኮሚቴው እስካቋረጠበት ጊዜ ድረስ በተሳተፈባቸው የተወሰኑ ዓመታት ውስጥ ብዙ ተምሯል፤ እጅግ ሲበዛም ያዘንባቸው አጋጣሚዎች ተገዳድረውታል።
በዓሉን በድምቀት ለማክበር የየክልሎቹ የሥራ ኃላፊዎች የቀን ተሌት ትጋትና አዳዲስ ፕሮጀክቶችን በጊዜው ለማጠናቀቅ የነበረውን ሩጫና ትጋት ማስተዋሉ አንዱ በጎ ትምህርት ነበር። “ክልላችንን ሊወክል የሚችል ምን ገላጭ ተምሳሌት እንምረጥ” የሚለው ጥያቄም በክልሉ የተቋቋሙት የበዓል አዘጋጅ ልዩ ልዩ ኮሚቴዎች ዋነኛ ጭንቀት ነበር።
ከበዓሉ በድምቀት መከበር ጋር “ትንሽ ቆሎ ይዘህ ወደ አሻሮ ተጠጋ” እንዲሉ “ፕሮጀክቶቹ በርግጡ ለየክልሎቹ አንገብጋቢ ፍላጎቶች ነበሩ?” የሚለው ጥያቄ ለጊዜው ይቆይና መሠረተ ልማቶቹ ለየክልሎቹ እንደትሩፋት የሚቆጠሩ ነበሩ። ብሔራዊ ኮሚቴው ዝግጅቶቹን ለመገምገም በየክልሉ በተገኘባቸው አጋጣሚዎች ሁሉ ሰፋፊ ጉብኝቶች ይካሄዱ ስለነበር ይህ ጸሐፊ “ኦርጂናሏን” ሀገሩንና የሕዝቡን አኗኗር በጥልቀት እንዲያውቅ ትልቅ ዕድል ፈጥሮለት ነበር። ከትምህርት ቤትም ሆነ ከንባቡ በማያገኘው በዚህን መሰሉ ዕውቀት “መባረኩን” ባይገልጽ ኅሊናው “ንፉግ ነህ” እያለ ይገስጸዋል።
በአንጻሩም እንደ ብሔራዊ ኮሚቴ አባልነታቸው አንዳንድ እሱን መሰል ግለሰቦች በየስብሰባዎቹና በየውይይቶቹ ላይ የሚሰጧቸው ገንቢና ሙያዊ ሃሳቦችና አስተያየቶች ሆን ተብለው ይገፈተሩና ይጣጣሉ ነበር። ጫን ሲልም መንግሥት ካሰመራቸው መስመሮች ፈንገጥ ያሉ ቀና ሃሳቦች ሲሰነዘሩም ግሳጼዎችንና ቁጣዎችን ያስከትሉ ነበር።
አይነኬ የነበረው ሌላው ጉዳይ በበዓሉ ዝግጅት ስም በወጪነት ይያዝ የነበረው በጀት ለታሰበው ዓላማ መዋሉ እርግጠኛ መሆን ያለመቻሉ ነበር። ለበዓሉ የሚዘረጉት መንገዶች እቅድና ክንውን፣ ለግዙፍ ስቴዲዮሞች ግንባታ፣ ለተዋቡ የመሰብሰቢያ አዳራሾችና የእንግዳ መቀበያ ልዩ ቤቶች (VIP Guest Houses) ለመስተንግዶና ለተያያዥ አስተዳደራዊ ጉዳዮች ወዘተ. እንደ ወንዝ የፈሰሱት በጀቶች ወደፊት ታሪክ አበጥሮ ይገልጽ ካልሆነ በስተቀር ዛሬ ይሞከር ቢባል ሰሚ የሚገኝ አይመስልም። “ባለ ከባድ ክብደት” የአንድ ክልል መሪ “ለመሆኑ ለመሠረተ ልማቶቹ ግንባታ የጨረታው አካሄድ እንዴት ተከናወነ? አፈጻጸሙስ ምን ይመስላል?” ተብለው በስብሰባ መካከል ሲጠየቁ የሰጡት መልስ በእጅጉ ግርምትን ቢፈጥርም መልሳቸው የታለፈው በሳቅና በስላቅ ነበር። እንዲህ ነበር ያሉት፤ “ጨረታ ምንትስ የምትሉትን ቢሮክራሲ የምታውቁት እናንተ የፌዴራል ሰዎች ናችሁ። እኛ ሥራውን በተፈለገው ጊዜና ጥራት አቀርባለሁ ላለ ኮንትራክተር እንሰጣለን ስራውን በተባለው ጊዜ እንረከባለን። አላስረክብም ብሎ ካንገራገረም ተገቢውን እርምጃ እንወስዳለን።” መልሳቸው ይህ ነበር። “ሁሉን ቢናገሩት ሆድ ባዶ ይቀራል” እንዲሉ “ዱቢን አቡልቱ -‹ጉዳያችን በይደር ይተላለፍ›” በሚለው የአፋን ኦሮሞ አባባል ማለፉ ሳይሻል አይቀርም።
የበዓሉ ዓላሚ፣ ዒላማና ዓላማው፤
ዓላሚው፤ የኢፌዲሪ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሚያዝያ 21 ቀን 1998 ዓ.ም. ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ ለዜጎችና ለቡድኖች ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች መከበር ዋስትና የሆነው ሕገ መንግሥት የጸደቀበትን ቀን ምክንያት በማድረግ ኅዳር 29 ቀን “የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል” በሚል ስያሜ በፌዴሬሽኑ አስተባባሪነት በየዓመቱ እንዲከበር ውሳኔ አስተላለፈ።
ዓላማውና ዒላማው፤ “በዓሉ ሲከበር በዋነኛነት መታወስ የሚገባው ለ17 ዓመታት ተንሠራፍቶና ሕዝብን አፍኖ የቆየው የደርግ አምባ ገነናዊ ሥርዓት መገርሰሱና በምትኩም የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የእኩልነት፣ የዲሞክራሲና የፍትህ ጥያቄ ተገቢ ምላሽና ዘላቂ ዋስትና ማግኘቱን ጎላ ብሎ እንዲጠቀስም ተወሰነ። በዓሉ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መልካም እሴቶቻቸውን በማጎልበት በሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ በጋራ እንዲሰለፉና ሕገ መንግሥታዊ ዲሞክራሲያዊ እሴቶችን ጠብቀው ከትውልድ ትውልድ እንዲያስተላልፉ ለማስቻል ጭምር መሆኑም ተብራራ።”
በዚሁ ዓላማ መሠረትም በዓሉ ለአስራ ሁለት ዓመታት ያህል “በወርቃማ አርቴፊሻል ቅብ” እየተቆነጃጀ ሲከበር ኖረ። ለምን “በወርቃማ አርቴፊሻል ቅብ” መሰልከው ብሎ የሚከራከር ተቆጭ ካለ፤ “የዘንድሮው የብሔር ብሔረሰቦች ቀን በዓል እንደ እስከ ዛሬው ለይስሙላ ሳይሆን እኩልነትና ኅብረ ብሔራዊ አንድነት በተጠናከረበት መልኩ እንደሚከበር የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ አደም ፋራህ ገለጹ” በማለት የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የዘገበውን ማረጋገጫ ለዋቢነት አቀርባለሁ። ክቡር አፈ ጉባዔው ለማጽናት የሞከሩት የትናንቱ ፍሬ አልባ “አርቴፊሻል ቅብ” ያለመደገሙን ለማረጋገጥ ነበር። አይሆንም እንጂ ከሆነማ በማን ዕድል። “ሽር ጉድ የሚልን ጋባዥ አትተች” ይሉት ይሉኝታ ጠፍሮን እንጂ ብዙ የምንለው ነበር።
የበዓሎቹ አከባበር ዜና መዋዕል፤
በጉዳዩ ላይ ፍላጎት ላላቸው ተመራማሪዎች ያግዝ ከሆነ በእያንዳንዱ ዓመት የተከበረው በዓል በየትኞቹ ክልሎች እንደተካሄደና ለየበዓሉ የተቀረጸውን መሪ ሃሳብና የተወሰኑ መገለጫዎችን በወፍ በረር ቅኝት ለማሳየት እንሞክር። የመጀመሪያው የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓል ቀን ኅዳር 1999 ዓ.ም. ‘’ሕገ መንግሥታዊ ቃል ኪዳን የአብሮነታችን መገለጫ ነው‘’ በሚል መሪ ቃል በአዲስ አበባ ከተማ መከበሩ ቀደም ሲል ተጠቅሷል። በዓሉ የተዘጋጀው የፌዴሬሽን ምክር ቤት ከአዲስ አበባ ከተማ ጊዜያዊ ባለአደራ አስተዳደር ጋር በጋራ በመሆን ነበር።
ሁለተኛው በዓል የተከበረው በሐዋሳ ከተማ ሲሆን በ2000 ዓ.ም. የተከበረው የሚሊኒየም በዓል የሕዝቡን መንፈስ ያነቃቃበት ወቅት ነበር። መሪ ቃሉም፤ “ልዩነታችን ውበታችን፣ ውበታችን አንድነታችንና ጥንካሬያችን።‘’ የሚል ነበር። ሦስተኛው በዓል በ2001 ዓ.ም. በኦሮሚያ ክልል አዘጋጅነት በአዲስ አበባ ከተማ የተከበረ ሲሆን “ዲሞክራሲያዊ አንድነታችንን በማጠናከር ልማታችንን እናፋጥናለን” የሚል መሪ ቃል ነበረው። በ2002 ዓ.ም. የምሥራቅ ኢትዮጵያ ተጎራባች ክልሎች (ኦሮሚያ፣ አፋርና ሐረሪ) ከድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ጋራ በጋራ ያዘጋጁት አራተኛው በዓል መሪ ሃሳቡ “መቻቻል ለዲሞክራሲያዊ አንድነትና ልማት” የሚል ነበር። እነዚህ ክልሎች የሚጋሩትን የታሪክ፣ የባህል፣ የመልክዓ ምድርና የሕዝቦች ትስስር መሰረት በማድረግ መልካም እሴቶቻቸውን አስተባብረው የተመጣጠነ ልማት በማስፈን አስተማማኝ አካባቢያዊ ሰላም ለማረጋገጥ በ2001 ዓ.ም. ኮንግረንስ አካሂደው የመተዳደሪያ ቻርተር ባጸደቁ ማግስት በመከበሩ ልዩ ነበር ተብሎም ተሽሞንሙኖ ነበር።
አምስተኛው በዓል በ2003 ዓ.ም. “የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እጅ ለእጅ ተያይዘን የሀገራችንን ህዳሴ ወደ ማይቀለበስበት ደረጃ እናደርሳለን” በሚል መሪ ቃል በአዲስ አበባ ከተማ ለሦስተኛ ጊዜ ተከብሯል። በዓሉ የተከበረው በአህጉራችን ለመጀመሪያ ጊዜ በመዲናችን ከተካሄደው ዓለም አቀፍ የፌዴራሊዝም ጉባዔ ጋር ተቀናጅቶ ነበር። የመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ተቀርጾ መተግበር የጀመረውም በዚሁ ዓመት ነበር። “ሕገ መንግሥታችን ለብዝሃነታችን፣ ለአንድነታችንና ለሕዳሴያችን” በሚል መሪ ቃል ለስድስተኛ ጊዜ በ2004 ዓ.ም. በመቀሌ የተከበረው በዓል 4.6 ሜትር ቁመት ያለውና 16 ቶን የሚመዝን ግዙፍ የቡና ጀበና በመሥራት እንግዳ ነገር ይዞ ቀርቦ ነበር። አሥራ አንዱ የጀበናው መቅጃ ቧንቧዎችም ዘጠኙን ክልሎችና 2ቱን የከተማ አስተዳደሮች እንዲወክሉ ታስቦ መሰራቱም ተገልጿል። በጊነስ ቡክ ኦፍ ሪከርድስ ይመዘገባል ተብሎ ብዙ የተወራለት የዚያ ጀበና ጉዳይ የት ደርሶ ይሆን? ሆድ ይፍጀው!
ሰባተኛው በዓል “ብዙም አንድም ሆነን በመለስ ራዕይ በሕገ መንግሥታችን ለህዳሴያችን” በሚል መሪ ቃል በ2005 ዓ.ም. በአማራ ብሔራዊ ክልል አዘጋጅነት በባሕር ዳር ከተማ ተከብሯል። በዓሉ የተከበረው ከቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ህልፈት ማግስት ስለነበር ጉባዔው ፍዝነት ቢስተዋልበትም ለዚህ በዓል ሲባል ክልሉ 5 ሜትር ዲያ ሜትር ያለው ግዙፍ መሶብ አሰርቶ ስለነበር ዝግጅቱን አድምቆታል። ተምሳሌትነቱም ለዘመናት ጸንቶ የቆየውን በጋራ የመመገብና የቤተሰብ አብሮነት ባህል የሚያመለክት እንደሆን በአዘጋጆቹ ተገልጾ ነበር። ስምንተኛው በዓል “ሕገ መንግሥታችን ለህዳሴያችን” በሚል መሪ ቃል በ2006 ዓ.ም. በሱማሌ ክልል መከበሩ ይታወሳል። ለበዓሉ ድምቀት እንዲያግዝም 400 ሊትር የግመል ወተት መያዝ የሚችል “ጎረፍ” (ባህላዊ ጮጮ) በማዘጋጀት የዘጠኙ ክልሎች ተወካዮች እንዲጠጡበት ተደርጓል። የሀገሪቱ አርቲስቶች ቀደም ብሎ ክልሉን መጎብኘታቸውን ምክንያት በማድረግ በአዲስ አበባ ሸራተን ሆቴል “የካሊ ምሽት” በሚል ርእስ የኪነ ጥበባት ዝግጅት አቅርበዋል።
ዘጠነኛው በዓል በ2007 ዓ.ም “በሕገ መንግሥታችን የደመቀ ኢትዮጵያዊነታችን ለሕዳሴአችን” በሚል መሪ ቃል በቤንሻንጉል ክልል በአሶሳ ከተማ የተከበረው ሕገ መንግስቱ ከጸደቀበት 20ኛ ዓመት ጋር ተያይዞ ነበር። በዓሉ የታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ በሚካሄድበት ክልል መከበሩን ምክንያት በማድረግም ጉብኝት ተደርጎ ነበር። አሥረኛው በዓል “የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ተሳትፎ ለላቀ እድገትና ትራንስፎርሜሽን” በሚል መሪ ቃል በ2008 ዓ.ም በጋምቤላ ብሔራዊ ክልል አዘጋጅነት በጋምቤላ ከተማ ተከብሯል። ሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ወደ ትግበራ የተገባውም በዚያው ዓመት ነበር። አሥራ አንደኛው በዓል፤ “ሕገ መንግሥታችን ለዲሞክራዊያዊ አንድነታችንና ለሕዳሴያችን” የሚል መሪ ቃል ይዞ በ2009 ዓ.ም. የተከበረው በሐረሪ ክልል ነበር። በዓሉ የተከበረውም ደረጃውን ጠብቆ በተገነባው የአውጠ አባድር እስታዲዮም ውስጥ ነበር።
የአሥራ ሁለተኛው ዓመት በዓል ኅዳር 29 ቀን 2010 ዓ.ም ‘’በሕገ መንግሥታችን የደመቁ ሕብረ ብሔራዊነታችን ለህዳሴያችን‘’ በሚል መሪ ቃል የተከበረው በአፋር ርዕሰ ከተማ በሠመራ ሲሆን ክልሉ አዲስ ባስገነባው ዓለም አቀፍ ስቴዲየም ውስጥ ነበር። በበዓሉ ላይ የጅቡቲ፣ የሱዳን ፣ የሶማሊያ መሪዎች በእንግድነት ተገኝተው አድምቀውታል። የአፋር ክልል የማርሽ ባንድ በአጭር ጊዜ ስልጠና ዝግጅቱን አጠናቆ ትርዒቱን ያቀረበበት በዓል ስለነበር ከፍተኛ አድናቆት ተችሮታል። አሥራ ሦስተኛው በአዲስ አበባ፣ አሥራ አራተኛው ደግሞ በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት አማካይነት የተዘጋጁት “የሀገራዊ ለውጥ አየር ከብዶ ስለነበር” በይድረስ ይድረስና በፈራ ተባ ዓይነት ስሜት ስለነበረ እንዲህ ነው ብሎ ለመመስከር አፍ ይይዛል። ለአስራ አምስተኛ ጊዜ እየተከበረ ያለው በዓል “ኅብረ ብሔራዊ አንድነትና አኩልነት ለጋራ ብልጽግና” በሚል መሪ ሃሳብ ሲሆን የፕሮግራሙን አተገባበሩ ገና “ከምጣድ ላይ ስላልወጣ” እንዲህ ነው ብሎ አስተያየት ለመስጠት ያዳግታል። ካስፈለገ ወደፊት መለስ ብሎ ውሎውን መቃኘት ይቻላል።
እውነታና ተቃርኖ የተስተዋሉባቸው የየበዓላቱ ጉዞዎች፤
የበዓሉ ዓላማ አስፈላጊነት ባልከፋ ነበር፤ አተገባበሩ ከፋ እንጂ። በየዓመቱ በጭፈራ የሚደምቀው በዓል ከብሔራዊ ወጉ ይልቅ ፈረንጆቹ ካርኒቫል እያሉ ከሚጠሩት የአደባባይ ፈንጠዝያ ጋር የመመሳሰል ባህርይ አለው። የሰው ልጅ የፈጠራቸው ቋንቋዎችና ባህሎች ልክ እንደ ፈጣሪያቸው እንደ ሰብዓዊ ፍጡር ይወለዳሉ፣ ያድጋሉ፣ ይፋፋሉ፣ ያበድራሉ ይበደራሉ፣ በኋላም የአገልግሎታቸው ዝናና ክብር እየደበዘዘ ሄዶ ከነጭራሹኑ ታሪክ ሆነው ሊቀሩ ይችላሉ። ባህልና ቋንቋ የቀዳሚው ትውልድ ቅርሶች ብቻ ሳይሆኑ የተቀባዩም የዕለት መስተጋብር መገልገያዎች ናቸው። በጠቀስናቸው ዓመታት ተደጋግመው ለትርዒት ይቀርቡ የነበሩት የየብሔረሰቡ ጭፈራዎችና ተጓዳኝ ትዕይቶች ግን በርግጥም የዛሬው ትውልድ እየተገለገለባቸው ነወይ? ብለን ብንጠይቅ ተገቢውን መልስ ለማግኘት ያዳግት ይመስለኛል። በስመ “ቱባ ባህልነት” የሚስተዋሉ አንዳንድ “ባህሎች” ከዘመን ተኳርፈው እያሳቀቁን ቢሆንም “ባለባህሎቹም” ሆኑ ተመልካቹ ለምን ብሎ ሊወያይባቸው ድፍረት አላገኘም። ምክንያቱም የፖለቲካ ጣጣው በራሱ ጣጠኛ ስለሆነ “እሳት የመጨበጥ ያህል የከፈ ነበር።”
በግሌ ስማቸውና ግብራቸው አልመመጣጠን ብሎ ከብዷቸው እየተንገዳጉ በመከበር ላይ ካሉት የሀገራችን በዓላት መካከል በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሰው የብሔር ብሔረሰቦች በዓል አንዱ ነው። በአዳራሽ ውስጥ ይከናወኑ የነበሩትና የ“ሲምፖዚዬም” ስም ይሸከሙ የነበሩት ስብሰባዎች ለመሠረታዊ የጋራ ሀገራዊ ጉዳዮች መፍትሔ አመላካች ከመሆን ይልቅ በፖለቲካ ድርጅቱ ካድሬዎች የሚሰጡ የአዲዮሎጂ ማንቂያዎች ነበሩ ማለቱ ይቀላል። እንደ ባህል ዘለል የኮሙዩኒኬሽን ተማሪ ብዙ ማለት ቢቻልም የጋዜጣው አምድ ገድቦ አላፈናፍን ስላለኝ ዝርዝሩን “በሆድ ይፍጀው” እና “በነገ ሰው ይበለን ሌላ ቀጠሮ አሲይዤ እሰናበታለሁ። ሰላም ይሁን!
አዲስ ዘመን ህዳር 26 ቀን 2013 ዓ.ም