መልካምስራ አፈወርቅ
የሁለቱ ቅርበት ከወትሮው ለየት ብሏል። በተገናኙ ቁጥር ቁምነገር ማውራት ይዘዋል። ውስጠታቸውን ያዬ ጥቂቶች ሁኔታቸውን የጠረጠሩ ይመስላል። ከሚያደርጉት ተነስተው የራሳቸውን ግምት እየሰጡ ነው። ሰዎቹ ሁሌም ስለሁለቱ ጉዳይ አበክረው ያወራሉ። ምንአልባት የጥንዶቹ ውሎና ሚስጥር ፍቅር ሊሆን ይችላል፡፡
አንዳንዶች ደግሞ በነዚህኞቹ ሀሳብ አይስማሙም። የሁለቱ ወንድና ሴት ግንኙነት ጾታዊ ስለመሆኑ ግምቱ የላቸውም። ስለምን ካሏቸው ደግሞ በቂ ምክንያት ይሰጣሉ። ‹‹ሁለቱ እንደ ጾታቸው ሀይማኖታቸው ይለያያል፣ እስከዛሬም በአንድ የዕምነት ጥላ ስር አልነበሩም›› ይላሉ። ይህን አስታከውም ‹‹ቅርበታቸው ፈጽሞ የፍቅር ሊሆን አይችልም›› ሲሉ ይወስናሉ፡፡
ሲሀም መሀመድ የእስልምና ሀይማኖት ተከታይ ነች። መላ ቤተሰቧም በዕምነቱ ስርአት አመታትን አስቆጥሯል። አቶ ብርሀኑ ረጋሳ የክርስትና ሀይማኖት ተከታይ ነው። እሱም ቢሆን በቤተሰቦቹ ዕምነትና ወግ ለዓመታት ዘልቋል፡፡
ሲሀምና ብርሀኑ አጋጣሚ አቀራርቧቸዋል ።ይህ እውነትም ከውስጣቸው ዘልቆ ቁምነገር ማውጋት ይዘዋል። ሁለቱም የሀይማኖታቸውን ልዩነት አላጡትም። ብዘዎች እንደሚሉትም ግንኙነታቸው የፍቅር ከሆነ ነገሮች መልካም ላይሆኑ ይችላል፡፡
እነሱ ግን ይህ ያስጨነቃቸው አይመስልም። ያሰቡትን ቁምነገር ለመፈጸም ሀይማኖት ብቻውን ‹‹ሰበብ» አይሆንም ሲሉ ወሰነዋል ። ውሳኔያቸውን አጽድቀው ከጫፍ ሲደርሱም በአንድ ጣራ ኖረው በጋብቻ ሊወሰኑ መንገድ ጀምረዋል፡፡
ሶስት ጉልቻ …
ሲሀምና ብርሀኑ ፍቅራቸው ደርቷል። በአንድ አካል አንድ አምሳል ያነጹት ጎጆ ሰምሮም ፍቅራቸው ያስቀና ይዟል። አሁንም በሁለቱ መሀል ሀይማኖት ይሉት ጉዳይ ልዩነት አልሆነም ።ተሳስበው የጀመሩት ኑሮ ስለነገ በጎውን እያሳሰበ ህይወትን ቀጥለዋል፡፡
አሁን የጥንዶቹን ፍቅር ይበልጥ የሚያደምቅ አጋጣሚ ተፈጥሯል። ይህ አጋጣሚ በትዳራቸው ፍቅርና አንድነትን የሚያጠናክር ነውና የሁለቱ ደስታ ለየት ብሏል። ወይዘሮ ሲሀም በሆዷ ያለው ጽንስ መገላበጥ ከጀመረ ወዲህ እርግዝናዋ ዕውን መሆኑን አውቃለች፡፡
ባለቤቷ ብርሀኑም በሚስቱ ነፍሰጡር መሆን ደስታው እጥፍ ሆኗል። ነገ የምታሳቅፈውን ጨቅላ እያሰበም ስለምቾቷ ይጨነቃል ።ከወራት በኋላ ጎጇቸውን የሚቀላቀለው አዲስ እንግዳ ለእነሱ ትዳር ወሳኝ ነው። ፍቅራቸውን አጠንክሮ ህይወታቸውን ለማስመር በጎ ጅምር ይሆናል፡፡
ከዕለታት በአንዱ ቀን ወይዘሮ ሲሀም የአንዲት ትንሽዬ ህጻን ልጅ እናት ሆነች። ባለቤቷ ብርሀኑም የአባትነት ወግ ደረሰው። ባልና ሚስት እናት አባት በመሆናቸው የሚያውቋቸው ሁሉ ደስታቸውን አበሰሩ፡፡
ልጃቸውን በወጉ ለማሳደግ የኃላፊነት መንገድ የጀመሩት ጥንዶች የቤታቸውን በረከት መንከባከብ ይዘዋል። ስሟንም ሪያን ሲሉ ሰይመዋል። ሪያን ለባልና ሚስቱ የጋራ ደስታ መሆን ጀምራለች። ስራ ውሎ የሚገባው አባወራ ልጁን በስስት እያያ የሚያስፈልጋትን ሁሉ ያሟላል፡፡
ክፉ አጋጣሚ…
አሁን ህጻን ሪያን በኮልታፋ አንደበቷ ለመናገር እየሞከረች ነው። ይህን ሙከራዋን ያስተዋሉ ወላጆቿ በድርጊቷ ይረካሉ። የዳዴ ጊዜዋን ጨርሳ ለመቆም ስትፍጨረጨርም አብረዋት ይወድቃሉ፣ ይነሳሉ ።ይህች ህጻን ለእነሱ የትዳራቸው ማገር የአብሮነታቸው ገመድ ናት። ቀሪውን ህይወት በአንድነት እዲዘልቁ ምክንያት ሆናለች፡፡
አንድ ቀን የአቶ ብርሀኑ ባለቤት ወይዘሮ ሲሀም እንደዋዛ የጀመራት ህመም ከአልጋ ጣላት። ከዛሬ ነገ ይሻለኛል ስትል ያደረጋቸው ሙከራ አልተሳካም። እያደር ስር የሰደደው ህመም በድንገት አጣድፎ ለሞት ዳረጋት፡፡
ህልፈቷን የሰሙ ሁሉ ስለ ወይዘሮዋ ክፉኛ አዘኑ ። በተለይ ግማሽ አካሏ ባለቤቷ ሀዘኑ የበረታ ሆነ። ስለነገ ብዙ ማለሙ ከንቱ ሆኖ ታየው። ህጻን ሪያን ገና በወጉ አላደገችም፤ እናቷን ያጣችው በጨቅላነት ዕድሜዋ ነው ። ስለእሷ አብዝቶ የሚጨነቀው አባት ስለሆነው ሁሉ ግራ ገባው፡፡
የሀዘኑ ጊዜ አለፍ እንዳለ አቶ ብርሀኑ ከፍርድ ቤት የተላከ አንድ ደብዳቤ በእጁ ገባ። የደብዳቤውን ጥሪ አክብሮም በተባለው ቀን ከስፍራው ደረሰ። ፍርድ ቤቱ ለአባወራው የተፈለገበትን እውነት አስረዳው። አቶ ብርሀኑ የሟች ባለቤቱ እናት የልጅ ልጃቸውን ተቀብለው ለማሳደግ የሞግዚትነት ጥያቄ አንስተዋል። ፍርድ ቤቱም ሞግዚት ይሆኑ ዘንድ ሀሳባቸውን ተቀብሎ አጽድቋል፡፡
አቤቱታ…
ሰኔ 24 ቀን 2007 ዓ.ም በተጻፈ ማመልከቻ ለኢፌዴሪ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አቤቱታውን ያቀረበው አቶ ብርሀኑ እሱ የክርስትና ዕምነት ተከታይ መሆኑንና እስልምና ሀይማኖት ከነበራት ባለቤቱ ጋር በትዳር መቆየቱን ያብራራል፡፡
በትዳር ቆይታቸው ከሟች ባለቤቱ የተወለደች የአንድ ዓመት ከአራት ወር ህጻን ስለመኖሯ የገለጸው አመልካች ከባለቤቱ ሞት በኋላ ልጁን የባለቤቱ እናት የሞግዚትነት ስልጣን እንዲሰጣቸው በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ሸሪዓ ፍርድቤት ጠይቀው ጥያቄቸው ምላሽ እንዳገኘ ያስረዳል፡፡
ብርሀኑ ለጉባኤው በማመልካቸው አክሎ እንደገለጸው በየደረጃው የሚገኙ ፍርድቤቶች የሞግዚትነት ጥያቄውን ተቀብለው ስለማጽደቃቸው ያትታል። የአፈጻጸም ፋይል ተከፍቶም መጥሪያ እንዲደርሰው ሆኗል፡፡
የልጅቷ አባት ብርሀኑ በወቅቱ ፍርድቤት ተገኝቶ ይሁንታውን አልገለጸም። በፍርድቤቱ ለመዳኘት ፈቃዱን ባልሰጠበትና ለምላሹ ባልተከራከረበት እውነታም የተሰጠውን ብይን አልተቀበለም ።ውሳኔው በህገመንግስቱ አንቀጽ 9/4/አንቀጽ 13፣ 36 /1ሐ/ እና /2/ ጋር የሚቃረን በመሆኑ የህገ መንግስት ትርጉም ሊሰጠኝ ይገባል ሲልም ጥያቄውን አቅርቧል፡፡
የጉባኤው ምልከታ …
ጉባኤው የጉዳዩን አመጣጥ ከስር መመርመር ጀመረ ። የህጻኗ ተጠሪ የሆኑት አያት የሞግዚትነት ጥያቄ አቅርበው ሀላፊነቱ ከተሰጣቸው በኋላ ባስከፈቱት የአፈጻጸም ፋይል አመልካቹ መጥሪያ ደርሶታል። በወቅቱም ወደ ሸሪዓ ፍርድ ቤት በመሄድ መቃወሚያውን አቅርቧል፡፡
አቶ ብርሀኑ ባቀረበው መቃወሚያ የህጻኗ ወላጅ አባት ሆኖ ሳለ እሱ በሌለበትና ባልተስማማበት ሁኔታ አያት ሞግዚት ልሁን ብለው መጠየቃቸውና ፍርድቤቱም ጥያቄያቸውን ተቀብሎ ማጽደቁ ተገቢ አለመሆኑን ያስረዳል። የተሰጣቸው የሞግዚትነት ስልጣን እንዲሻርም ይጠይቃል፡፡
ጉባኤው አሁንም ፍርድቤቱ አስቀድሞ የሰጠውን ውሳኔ መመርመር ያዘ። ፍርድቤቱ ሁለቱን ወገኖች በአንድ ችሎት አቅርቦ አከራክሯል። አቶ ብርሀኑ የልጅ እናቱ ስታርፍ ህጻኗን ሻሸመኔ ለምትኖረው እህቱ /ለህጻኗ አክስት/ አስረክቦ ነበር ።ይህም ድርጊት በአያት ዘንድ ሀላፊነትን ካለመወጣት ተቆጥሮ ለምን የሚል ጥያቄ አስነስቷል። ጥያቄውን ተከትሎም አያት የልጅ ልጃቸው እሳቸው ዘንድ ብታድግ የተሻለ እንደሆነ ለፍርድቤቱ መከራከሪያ አቅርበዋል፡፡
ፍርድቤቱ የሁለቱን ወገኖች ግራቀኝ ካደመጠ በኋላ በሸሪዓ ህግ በክታብ ሙቅኒል ሙህታጂ 3ኛ ክፍል ከገጽ 452 -455 መሰረት የህጻኗ እናት ከሞተች የማሳደግ ስልጣን የሚሰጠው ከአክስት ይልቅ ለአያት እንደሆነ ጠቅሷል። ይህን ውሳኔ ተከትሎም አመልካች ብርሀኑ ያቀረቡት መቃወሚያ ውድቅ ሆኖ የአያት የሞግዚትነት ጥያቄ ተቀባይነት አግኝቷል፡፡
ጉባኤው የአባወራውን ጥያቄና ተያይዘው የቀረቡ የፍርድቤቱ ውሳኔዎችን ከህገመንግስቱ አንቀጽ 36/1/ ሐ እና /2/ ጋር ይቃረን አይቃረን እንደሆነ መመርመር ጀመረ፡፡
በህገመንግስቱ በግልጽ እንደሰፈረው የግልና የቤተሰብ ህግን በተመለከተ በተከራካሪዎች ፈቃድ በሀይማኖት አልያም በባህሎችና ህጎች መሰረት መዳኘትን አይከለክልም። ዝርዝሩ በህግ ይወሰናል በሚል ተደንግጓል። በህገመንግስቱ 78/5/ መሰረትም የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት የሀይማኖትና የባህል ፍርድቤቶችን ሊያቋቋሙ ይችላል በሚል ተደንግጓል።
አዋጁ በሀይማኖታዊ ፍርድቤት ለመዳኘት በፈቃድ መርጦ መቅረብን እንደዋና መስፈርት ያስቀምጣል። የሌላ ዕምነት ተከታይ ለሆኑትም በእስልምና ሀይማኖት ስርአት ለመዳኘት የሚከለክል አሰራር አለመኖሩን ያስቀምጣል፡፡
አመልካች የህጻኗ አባት በአቤቱታው እንዳስቀመጠው ለመዳኘት ይሁንታውን ባልሰጠበት የሸሪዓ ፍርድቤት የተላለፈው ውሳኔ በህገ መንግ ስቱ የተቀመጠውን መብት የሚቃረን ነው። ተጠሪዋ ለህጻኗ የልጅ ልጃቸው ሞግዚት ተብለው ከተሾሙ በኋላ ልጅቷን እንዲያስረክቡ መመሪያ ሲደርሳቸው በቦታው ሳይገኙ የሞግዚትነት ስልጣኑ ለእሳቸው መሰጠቱ አግባብ ያለመሆኑን በማሳየት ተከራክረዋል፡፡
ተጠሪዋ ህጻኗ በወላጅ አባቷ እጅ ማደግ ሲገባት ተላልፋ ለአክስት መሰጠቷ ተገቢ አለመሆኑን በመጥ ቀስ መቃወማቸውን ቀጥለዋል። በዚህ ምክንያትም ተገቢውን ማሳያ አቅርበው የሞግዚትነቱን ሀላፊነት ወስደዋል፡፡
ፍርድቤቱ ባሳለፈው ውሳኔም ማንኛውም ህጻን ወላ ጆቹን ወይም በህግ ለማሳደግ መብቱ ያላቸውን ሰዎች የማወቅና እንክብካቤያቸውን የማግኘት መብት እንዳላቸው አስቀምጧል። በህገመንግስቱ መሰ ረት የህጻኗን መብት ለማስከበር ውሳኔ ከመስጠቱ በፊት መሆን የሚገባቸውና ለአስተዳደጓ የሚበጁ ጉዳዮችን ባለማጣራታቸው ጉባ ኤው ጥያቄ አቅርቧል።
በተሰጠው አቅጣጫ መሰረት ለህጻናት ፕሮጀክት ጽህፈትቤት ደበዳቤ ተጽፎ ፕሮጀክቱ በራሱ አካሄድ ተጉዟል። በዚህም አግባብ ለህጻኗ መልካም አስተዳደግ ሲባል አክስትን ጨምሮ የአያትና አባት መኖሪያዎችን በመጎብኘት ከሚመለከታቸው ጋር መረጃ መለዋወጥ እንደሚችሉ ያትታል። ጽህፈት ቤቱ በጻፈው ደብዳቤም ህጻኗን የማሳደግ መብት ለአባቷ ቢሰጥና አሁን በምትገኝበት ሻመኔ ከተማ ብትቆይ መልካም እንደሚሆን አስታውቋል። የልጅቷ አያትም በሁለት ወር አንዴ የጉብኝት ጊዜ እንዲመቻችላቸውና ይህንንም ሀላፊነት አባት መረከብ ቢችሉ ከሚል ውሳኔ ተደርሷል፡፡
ጉባኤው በመጨረሻ ጉዳዩ በየደረጃው ቀርቦላቸው የተመለከቱትን ፍርድ ቤቶች ውሳኔ መረመረ። በህገመንግስቱ አንቀጽ 36/1/ሐ እና/ 2 /መሰረት የህጻናት ምቹ አስተዳደግን መሰረት አድርገው አለመወሰናቸውን አረጋገጠ። ይህን መሰረት አድርገው ውሳኔ ማሳለፍ ያለመቻላቸውም አመልካቹ አባት ከጠቀሱት የህገመንግስቱ አንቀጽ 36 ጋር የሚቃረን መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡
ምክር ቤቱ የአጣሪ ጉባኤውን የውሳኔ ሀሳብ መሰረት በማድረግ የምክር ቤቱ የህገመንግስት ትርጉምና የማንነት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ያቀረበውን የውሳኔ ሀሳብ መርምሯል። በምክርቤቱ እሳቤ መሰረት ክርክር የተነሳበት የህጻኗ አስተዳደግ ጉዳይ በሸሪዓ ፍርድቤት ውሳኔ ያረፈው ልጅቷ ከወላጅ አባቷ ይልቅ አያቷ ዘንድ እንድታድግ በሚል ነው። ይሁን እንጂ አባት እያለ መብቱን ለአያት ማሳለፍ ተገቢ ያለመሆኑን ማረጋገጥ ተችሏል፡፡
ውሳኔ
አጣሪ ጉባኤው እስካሁን የነበረው የፍርድ አካሄድ ተገቢ እንዳልነበረ ተረድቷል፡፡ የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ የሸሪዓ ፍርድቤትና በየደረጃው የሚገኙ ፍርድቤቶች ያሳለፏቸው ውሳኔዎች እንዲሁም በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድቤት ሰበር ሰሚ ችሎት እንዲጸና የሆነው ውሳኔ ህገመንግስታዊ ድንጋጌዎችን የሚቃረን ነው። በመሆኑም በህገመንግስቱ አንቀጽ 9/1/ ድንጋጌ መሰረት እስከዛሬ የነበሩ ውሳኔዎች ተፈጻሚ አለመሆናቸው በሙሉ ድምጽ ተወስኗል፡፡
አዲስ ዘመን ህዳር 26 ቀን 2013 ዓ.ም