በጋዜጣው ሪፖርተር
በህንዷ ኡታር ፕራዴሽ ግዛት አንድ ሙስሊም ግለሰብ የሂንዱ እምነት ተከታይ የሆነችን ሴት ወደ እስልምና ሊቀይር ሞክሯል በማለት ፖሊስ በቁጥጥር ስር አውሎታል። ግለሰቡ አገሪቷ ባወጣችው ፀረ- እምነት መቀየር ህግ ተጠርጥሮ የታሰረው የመጀመሪያው ግለሰብ ሆኗል።
የኡታር ፕራዴሽ ፖሊስ በትዊተር ገፁ እንዳስታወቀው፤ በህንዷ ኡታር ፕራዴሽ ግዛት አንድ ሙስሊም ግለሰብ የሂንዱ እምነት ተከታይ የሆነችን ሴት ወደ እስልምና ሊቀይር ሞክሯል በማለት ፖሊስ በቁጥጥር ስር አውሎታል፣ ሲል ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
እንደ ዘገባው ከሆነ፤ ህጉ በአክራሪ ሂንዱዎች “የፍቅር ጂሃድ” ተብሎ የሚጠራ ሲሆን፤ ሙስሊም ወንዶች ሂንዱ ሴቶችን በጋብቻ ውስጥ እምነታቸውን እንዲቀይሩ ያደርጓቸዋል የሚለውን ለማመላከት የሚጠቀሙበት ነው። ሆኖም ይህ ህግ በህንድ ውስጥ “ሙስሊም ጠል” ነው በሚል ከፍተኛ ትችትን እያስተናገደ ነው።
ይሁን እንጂ ህጉ በተጨማሪ አራት ግዛቶች ተቀባይነት ያገኘ ሲሆን “የፍቅር ጂሃድ”ን ለመቃወም በሚል ግዛቶቹ እያረቀቁት ነው ተብሏል። ባለፈው ሳምንት የልጅቷ አባት እምነትሽን ካልቀየርሽ በሚል ጫናም እንዲሁም ማስፈራሪያ እያደረሰባት ነው በማለት ሪፖርት አድርገዋል። ግለሰቧ ከሰውየው ጋር በፍቅር ግንኙነት ውስጥ እንደነበረችና ሌላ ሰውም እንዳገባች ተዘግቧል።
እምነት ልትቀይር ሞክረሃል የተባለው ግለሰብም ለአስር ቀናት ያህል ቀጠሮ የተጠየቀበት ሲሆን፤ ከሴትዮዋ ጋር ምንም አይነት ግንኙነት እንደሌለውና ንፁህ እንደሆነም መናገሩ በዘገባው ተመላክቷል። ዋስ የሚከለክለው አዲሱ ህግ ጥፋተኛ ሆኖ ከተገኘ እስከ አስር አመት ያስቀጣል።
ኡታር ፕራዴሽ ግዛት በግድ ወይም በማጭበርበር የሚደረግን የእምነት ቅየራ ለመታገል በሚል አዲሱን ህግ በማፅደቅ የመጀመሪያዋ ሆናለች። ከዚች ግዛት ጋርም ቢያንስ አራት ግዛቶች “የፍቅርን ጂሃድ” እንዋጋለን በሚል ህጉን ለማፅደቅ እቅድ ይዘዋል። ኡታር ፕራዱሽን ጨምሮ አምስቱ ግዛቶችን የሚመራው ባሃራቲያ ጃናታ ፓርቲ ሲሆን ከዚህ ቀደምም በፀረ- እስልምና አመለካከቶቹ ወቀሳ ሲደርስበት ነበር።
ይሁን እንጂ፣ “የፍቅር ጂሃድ”ን የሚተቹ አካላት፣ “የፍቅር ጂሃድ” የቀኝ ክንፍ አክራሪ ሂንዱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም ሲጠቀሙበት የነበረና በህንድ ህገ መንግሥትም እውቅና እንደሌለው በመግለጽ “አስነዋሪ” በማለት ሀሳባቸውን ይገልጻሉ፡፡
አዲስ ዘመን ህዳር 25 ቀን 2013 ዓ.ም